
ከለውጡ ሾፌሮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ የሽግግሩ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ጃዋር መሐመድ አጥብቆ ሲከራረከር ነበር። አቶ ለማ የፌዴራል ፓርላማ ተወካይ ባለመሆናቸው እርሳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳይሆኑ የሚከለክላቸው መሆኑ የታወቀ ቢሆንም በወቅቱ ግን ጃዋር ከጓደኞቹ እነ ሕዝቅኤል ገቢሣ ጋር በመሆን “ኢህአዴግ አዲስ መመሪያ/ሕግ አውጥቶም ቢሆ አቶ ለማ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊያደርጋቸው ይገባል” በማለት ሃሳብና መመሪያ ቢጤም ሲሰጥ ነበር።
ጃዋር ያለውና ያሰበው ሳይሆን አቶ ለማ በለውጡ ሙቀት ውስጥ ባሉበት ወቅት “እኔና ዐቢይን ሞት ብቻ ነው የሚለየን” በማለት የድርጅት ሊቀመንበርነታቸውን ለዶ/ር አብይ አሳልፈው በመስጠት ዐቢይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን የበኩላቸውንና ድርጅታዊ ኃላፊነታቸውን ከባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው እውን አደረጉ።
የሆሮ ጉድሩ ተወላጅ የሆኑት አቶ ለማ በዚህ ተግባራቸውና ከለውጡ መፈንዳት ጀምሮ ለህዝብ ባቀረቡት ዲስኩር የተወደዱትን ያህል ከህወሃት አፍቃሪዎችና ጭፍራዎች ዘንድ ግን ተቃውሞ በስፋት ይሰነዘርባቸው የጀመረው ወዲያው ነበር። በተለይም በኦሮሚያ የደኅንነት ቢሮ ሥልጣናቸው ወቅት የሰሩትን በመጥቀስ።
ስለ አዲስ አበባ የሕዝብ አሠፋፈር (ዴሞግራፊ) የተናገሩት ቅጂ አደባባይ ከወጣ በኋላ ተቃውሞ እየከበባቸው የመጣው አቶ ለማ በዛው ቅጽበት ከጃዋር መሀመድ ጋር በየዕለቱ እንደሚገናኙና አብረው እንደሚሰሩ ከየአቅጣጫው መረጃዎች ይሰራጩ ጀመር። በዚያው መጠን ከዶ/ር ዐቢይ ጋር ልዩነት እንደፈጠሩ በተደጋጋሚ በተለያዩ የሚዲያ ማሰራጫዎችና ማህበራዊ ገጾች ተዘገበ። በዳያስፖራ የሚገኙትና ራሳቸውን ተንታኝ አድርገው የሰየሙ ዜናውን ዞሩበት።
ከኦሮሚያ ርዕስመስተዳድርነታቸው ተነስተው ወደ መከላከያ ሚኒስትርነት የመዛወራቸው ሚስጢርም ይኸው የልዩነቱ ነጸብራቅ እንደሆነ ትርጉምና ትንታኔ እየቀረበበት ከሚዲያ ወደ ሚዲያ ተራባ። በመጨረሻም ራሳቸው አቶ ለማ በቪኦኤ ቀርበው ልዩነት እንዳላቸውና “እንደመር” እያሉ ሲፈክሩበት ከነበረው ሃሳብ ጋር መጣላታቸውን ይፋ አደረጉ።
በተለይም የብልጽግናን መመሥረት፣ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች ውህደት እንደማይቀበሉ ሲናገሩ ተቃውሟቸውን በሚያሳምን መንገድ ባለማስረዳታቸው ሕዝብ ደነገጠ። መሠረታዊ ምክንያታቸው ምን ይሆን ሲል በማኅበራዊ ሚዲያ ክርክርና መላምት ማስቀመጥ ተጀመረ።
የለውጡ ተጻራሪዎችና ጭፍን ነቃፊዎች፣ በተለይም የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር በፓርቲ ደረጃ፣ እንዲሁም ደጋፊ የማኅበራዊ ገጽ ጭፍሮቹ የአቶ ለማን ቃለ ምልልስ አጯጯሁት። “ብለን ነበር” ሲሉ የለውጡ ሃዲድ እንደተሰበረ፤ ባቡሩ አቅጣጫውን እንደሳተ አወጁ።
የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ከዘወትር ታማኝ ምንጮቹ ባገኘው መረጃ አቶ ለማ እዚህ ችግር ውስጥ የወደቁት ፈልገውና ወደው እንዲሁም የለውጡ የትግል አጋሮቻቸውን ለማስቀየም አስበው ሳይሆን ከፌደራሉ የመረጃና የደህንነት አጄንሲ (ደኅንነት) ጋር በጥምረት በሚሠራው የኦሮሚያ የስለላ መዋቅር ውስጥ በከፋ ሁኔታ ተነክረው ስለነበር ነው።
“ማበስበስ” በሚባለው በህወሃት ስልት ውስጥ በኦሮሞ ተወላጅ የኦነግ ታጋዮች፣ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ላይ ሲያከናውኑት የነበረው የስለላ ሪፖርት ሪኮርዶች ህወሃት እጅ አሉ። ህወሃት በክልሉ መሪ ሳይቀር “ሚስጢር እናወጣለን” በሚል የሚሰነዝሩት ዛቻ በአብዛኛው በአቶ ለማ ላይ ያነጣጠረ መሆኑንን የጎልጉል ዘጋቢ ለህወሃት ቅርብ የሆኑ ክፍሎችን ጠቅሶ ዘግቧል። ይህ የህወሃት ዛቻ በዶ/ር ዐቢይ ላይ ቢሆን ኖሮ መዛትም አያስፈልጋቸውም ነበር፤ ውሸት ፈጥሮ በሚያናፍሰው የዲጂታል ወያኔ መስተጋብራቸው ያለገደብ ያራግቡት ነበር።
ከወራት በፊት “አቶ ለማ የኦሮሞ ተወላጆችን ሲያሳድድ የነበረ ዋናው ወንጀለኛ ነው” ሲል የህወሃት ደጋፊና ፕሮፓጋንዲስት የሆነው ዳንኤል ብርሃኔ፤ ጌታቸው አሰፋ ላይ የሚቀርበውን የነፍሰ በላነት ውንጀላ ለመከላከል ባቀረበው ጽሁፍ ላይ መጥቀሱ አይዘነጋም። ከዚያም በኋላ የብልጽግና ፓርቲ መቋቋሙን ተከትሎ ይኸው ሚስጢር ይፋ እናደርጋለን የሚለው ጉዳይ በስፋት ሲናፈስ የከረመውም ያለምክንያት አልነበረም።
በዚሁ ምክንያት አቶ ለማ ከኦሮሞ ህዝብ ሊነጥላቸው የሚችለው ይህ ሚስጢር እንዳይወጣ ኦዲፒን ወይም ብልጽግና ፓርቲን እንዲለዩና ህወሃት ጠፍጥፎ እየሠራቸው ካሉት የፌዴራል ኃይሎች ጋር እንዲዋሃዱ አማራጭ እንደቀረበላቸው ነው ለህወሃት ቅርብ የሆኑት ለጎልጉል መረጃ የሰጡት።
ህወሃት ከፌዴራል ኃይሎች ጋር በማበር ዳግም መንግሥት ለመሆን እንደሚሰራ በግልጽ ማሳወቁና አቶ ለማም ፓርቲያቸውን ጥለው ወደ ፌዴራል ኃይሎች የመንደርደራቸው ዜና ሌላ ምክንያት እንደሌለው የጎልጉል ዘጋቢ ካሰባሰበው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
አቶ ለማ መገርሳ ብልጽግና መቃወምና መደመርን በማጣጣል የተናገሩትን ቃለ ምልልስ “አንዱ የመጫወቻ ካርዴ ነው” ሲል ገልጾት የነበረው ጃዋር ረቡዕ ዕለት ለኤልቲቪ ባልደረባ ጋር ባደረገው ጭውውት መሳይ ቃለ መጠይቅ፣ በመጪው ምርጫ አቶ ለማን አካትተው ወደ ውድድር እንደሚገቡ በገደማዳሜና በሳቅ አረጋግጧል። ጃዋር ለጊዜው መናገር ያልፈለገው የፓርቲዎች ጥምረት እንደሚኖርም ጠቁሟል። ህወሃትም በጌታቸው ረዳ አማካይነት ጃዋር ከተቀላቀለው ኦፌኮ ጋር ህወሃት ግንባር የመፍጠር ሥራ እየሠራ መሆኑንን የበቀለ ገርባን ስም በመጥራት አረጋግጧል። ይህ ሁሉ ትሥሥርና ቅንነት የጎደለው፣ በሤራ የተሸበበ “ሥልጣን ወይም ሞት” በማለት በጭፍን የሚመራው ፖለቲካ አምስት ሺህ ሰው የተገበረበት ህወሃትን የማስወገድ ትግል ወዴት ይወስደዋል? ወይም ወዴት ይመልሰዋል? የሚለው ጥያቄ በስፋት እንዲነሳ ያደርገዋል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
አብይና ለማ በሕወሐት ጊዜ በአገዛዙ የስለላ መዋቅር ይሰሩ እንደነበር የሚታወቅ ነው። ሕዝቡም ይሕን እያወቀ ነበር እኮ ለውጡን በይቅርታ መንፈስ ሙሉ ለሙሉ የደገፈው። በእርግጥ የለማ አስተዋጽኦ የከፋ ቢሆንም። ነገር ግን አሁን ላይ ቆመን አቶ ለማን ሕወሐት የበፊት ታሪክ መዛ ስላስፈራራች ነው፣ አቋም የለወጡት-የሚለው ክርክር ውሐ አይቋጥርም። ቢያንስ፣ቢያንስ በቃኝ ብለው ስልጣናቸውን በመልቀቅ ሕዝብ የሰጣቸውን ክብር መጠበቅ ይችሉ ነበር።የአሁኑ እርምጃቸው በጥፋት ላይ ሌላ ጥፋት ከመደራረብ ያለፈ ፋይዳ የለውም!
You hateful idiot!! You will lose.
Lose what? If I may ask the smart Nahom