እሑድ ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ባካሄደው የውይይት መድረክ “ፖለቲካ ማለት” በሚል ርዕስ ሰፊ ጥናት ያቀረቡት የፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ “እንኳን ተለያይተንና እርስ በርስ ተባልተን፣ በአንድነት ቆመንም ወጀቡን መቋቋም አቅቶናል” አሉ። ፕሮፌሰሩ አክለውም “ያኔ በእኛ ዘመን ዕድገት በኅብረት እንደሚባለው፣ ዛሬ ላይ ደግሞ እብደት በኅብረት የታወጀ ይመስላል” በማለት አሁን ላይ እየታየ ስላለው አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሁኔታ ተናግረዋል። አሁን የሚታየው ውዝግብ የበዛበት የዓለም ሁኔታ የሥልጣኔ ቀውስ መሆኑንና ኢትዮጵያን ጭምር ሰለባ ማድረጉን አስረድተዋል።
“የዓለም ሁኔታ ምን እየሆነ ነው? የሰው ልጅስ ወዴት እየገባ ነው?” በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጥልቀት ሲያሰላስሉ መቆየታቸውን የተናገሩት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ ከዚህ በመነሳት አሁን ያለውን የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታም ሥልታዊ ፍቺ ለመስጠት መሞከራቸውን በመግለጽ ነበር ወደ ጥናታቸው የተንደረደሩት።
ፖለቲካ ለእሳቸው ምን ማለት እንደሆነ ሲናገሩ “ለእኔ ፖለቲካ በጋራ ውሳኔ የመስጠት ሒደት ነው። የፖለቲካ ሥርዓት ደግሞ ይህን በጋራ (በቡድን) ውሳኔ የመስጠት ሒደት ሕግና ተቋም አበጅተው ሲያካሂዱት የሚመጣ ነው፤” በማለት ፍቺ ሰጥተዋል።
“ፖለቲካ ለእኔ ማኅበረሰብን ወደ ተሻለ ደረጃ ለመውሰድ ጥረት ማድረግ ነው፤” የሚል ፍቺ የሰጡት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ አሁን ባለው የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ እርግጠኝነት የጠፋበትና በውዝግብ የተሞላ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል። የሰው ልጅ ሕይወቱን ለማሻሻልና መተባበሩን ለማጠናከር ብሎ በፈጠራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች እየተዋጠ መምጣቱን አመልክተዋል። “ሰዎች በተፈጥሮ የማይጠረቁ መሆናቸው ገንዘብና ቁስ አምላኪነትን ፈጥሯል፤” ብለዋል።
መጠላላትና መገፋፋት የሞላበት የዓለም ሁኔታ መፈጠሩን የተናገሩት ፕሮፌሰሩ፣ “አላዋቂዎች የአደባባይ ተናጋሪ ሆነውና መድረኩን ሞልተው አዋቂዎች ግን ተሸማቀው ዝም ያሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤” ብለው፣ ቴክኖሎጂ በተለይም ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዓለምን የሁካታ ገበያ እንዳደረጓትም አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የሰው ልጆች ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ሁኔታ ዓለምን ለመቆጣጠር ስለቻሉበት መነሻ ጠለቅ ያለ ሐሳብ የሰነዘሩት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ “መተባበር” ሰዎችን ታላቅ ፍጡር ማድረጉን ጠቁመዋል።
“ሰው ከሌሎች ፍጡራን በልጦና ገኖ መውጣት የቻለው ከራሱና በአካባቢው ካሉ ሰዎች ውጪ ሰፊ ትብብር መመሥረት በመቻሉ ነው፤” ሲሉ ገልጸውታል። “የለበስነው ልብስ፣ የእጅ ስልክ፣ የምንነዳው መኪና ወይም በየዕለቱ የምንገለገልበት ቁስአካል ተመርቶ ተጠቃሚው ጋር እስኪደርስ እጅግ የበዙ የማይተዋወቁ ሰዎችን መተባበር ይጠይቃል፤” ሲሉም አክለዋል።
“ሰዎች በትብብር ለመኖር የሚያስችሏቸው ብዙ ዓይነት ትርክት ፈጥረዋል። እነዚህ ትርከቶች ደግሞ ለትብብሩ መሠረት ሆነዋል። ገንዘብ አንዱ ትርክት ነው። ሃይማኖት፣ ኮርፖሬሽንና ሌላም ፈጥረዋል። የሰው ልጅ እነዚህን ትርክቶች ከመፍጠር አልፎ ተፈጥሯዊ ናቸው ብሎ እስኪያምናቸውና መልሰው ራሱን እስኪቆጣጠሩት ድረስ ይሄዳል፤” በማለት ነበር ወደ ዋና ጉዳያቸው የገቡት።
የሰው ልጆች መተባበር በመካከላቸው ከሌለ እንደሚጠፉ በምሳሌ ያብራሩት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ ከረዥም ዘመናት ጦርነት በኋላ በአውሮፓ እ.ኤ.አ. በ1641 የዌስትፋሊያ ስምምነት ላይ መደረሱን አውስተዋል። ይህም የአገሮችን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መፍጠሩን አስረድተዋል። የኔሽን፣ የስቴት፣ እንዲሁም የኔሽን ስቴት ዕሳቤዎችንና ልዩነት ከዚያ በተጨማሪም በየጊዜው የመጡ ርዕዮተ ዓለሞች መውጣትና መውረድን አለፍ ገደም እያሉ ጠቃቅሰዋል።
“አሁን ያለው የዓለም ሁኔታ በርዕዮተ ዓለም ከመመራት ይልቅ፣ በጩኸትና ሁከት የተሞላ ነው። በአጠቃላይ ዓለማችን የሥልጣኔ ቀውስ ገጥሟታል፤” ሲሉ በይነውታል። በሌላ በኩል ነባራዊው የዓለም ሥርዓት መቀየር አለበት የሚል የጂኦ ፖለቲካ ፍጭት ተደራቢ ችግር መሆኑን አመላክተዋል። ብሪክስ የተባለ ማኅበር መፍጠርና ማጠናከር የመጣው የዓለም ሥርዓትን ለመፎካከር መሆኑን አስታውሰዋል።
“እኛ ያለነው የት ጋ ነው?” የሚል ጥያቄ ያነሱት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ በለውጡ ማግሥት ተፈጠረ ያሉትን ቀውስ ገልጸዋል። “በለውጥ ማግሥት በብሔር የሚያስቡ ሰዎች ተራው የእኛ ነው አሉ። አንዳንዶች እኛ በታገልነው የቀደሙት ኃይሎች ሊገቡ አይገባም አሉ። የተበድለናል ትርክት የሚያነሳውም በርካታ ሆነ፤” በማለት በለውጡ ማግሥት ድብልቅልቅ ያለ ጎራ መፈጠሩን አስረድተዋል።
አሁን አሁን ምክንያታዊ ውይይት እየቀረ በየአቅጣጫው መጮህ እየበዛ መሄዱን የተናገሩት የኢዜማ መሪ፣ በተቻለ መጠን ጥሞናና መረጋጋት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ኢዜማ ቢያንስ የችግሩ አካል ላለመሆን ይህንኑ መንገድ መምረጡን አመልክተዋል።
ዓለምን የመምራት ሚና ሊኖራቸው የሚገባ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሉ ተቋማት ሚናቸውን እንዲወጡ እየተደረገ አለመሆኑን፣ እንደ ፍራንሲስ ፋኩያማ ያሉ ምዕራባዊያን ምሁራን “የሥልጣኔ መጨረሻ” (The End of Civilization) ብለው የፎከሩለት ሊበራሊዝም ዛሬ ዓለምን የተረጋጋች አድርጎ ለመቀጠል ጥያቄ እየተነሳበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
አሁን በርዕዮተ ዓለም የመሠለፍ ጉዳይም ሳይሆን “የገደል ማሚቱ” (Eco Chamber) መሆን ባህል እየሆነ መምጣቱን፣ መደማመጥ በሌለበት የመጮህ አባዜ በዓለም ላይ መግነኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ነባራዊ ቀውስ ራሱን የቻለ ጠባይ ቢኖረውም፣ ከዚሀ የዓለም ሁኔታ ፍፁም የተለየ ግን አለመሆኑን ሞግተዋል። (ሪፖርተር)
ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የኢዜማ መሪ
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Miherete Tibebe says
OK!!!