በትግራይ ክልል የተካሄደውን ሕግ የማስከበር ተግባር ተከትሎ በሴቶች ላይ ጥቃት ስለመፈጸሙ የሚያጣራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ መቀሌ መግባቱን የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ግብረ ኃይሉ በክልሉ ያሉ የሴቶችና ህጻናት ቢሮዎችን የማደራጀትና አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን የመለየት ተጨማሪ ኃላፊነቶች እንዳሉትም ተገለጸ፡፡
የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አድነው አበራ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ከጤና ሚኒስቴር፣ ከሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከመከላከያና ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተውጣጣ ነው፡፡
ግብረ ኃይሉ በዋናነት በትግራይ ክልል የተካሄደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በመቀሌና በሌሎችም የትግራይ አካባቢዎች ተፈፅሟል እየተባለ በውጭ አካላትና በማህበራዊ ሚዲያ የሚወራው ጾታዊ ጥቃት ስለመፈፀሙ ለማረጋገጥ፣ ችግሩ ተፈጥሮ ከሆነም ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በመሆን እገዛ የሚደረግበትን ሁኔታ የማመቻቸት ተልእኮ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም ዘመቻው በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያሉ ሴቶችና ህጻናት ከአልባሳት፣ ከምግብ እጥረት፣ ከሕጻናት አልሚ ምግብ፣ ኮቪድን ከመከላከል አንጻር የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን እንደሚለይና እገዛም እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
እንደ አቶ አድነው ገለጻ፤ ግብረ ኃይሉ በትናንትናው ዕለት መቀሌ መግባቱንና ቦታው ላይ በመገኘት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች መኖር አለመኖራቸውን የማረጋገጥ ስራ ጀምሯል፡፡ (ኢ ፕ ድ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply