• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የጃዋር፣ የበቀለና የእስክንድር የፍርድ ቤት ውሎ

August 10, 2020 03:52 am by Editor Leave a Comment

“የመናገር መብት ከሌለን ለምን እንመጣለን?” ተጠርጣሪ በቀለ ገርባ

“በጠበቆቻችሁ አማካይነት በቂ ጊዜ ተሰጥቷችሁ ተናግራችኋል” ፍርድ ቤት

በተጠረጠሩበት የእርስ በርስ ግጭት በማነሳሳትና በሌሎች የወንጀል ድርጊቶች ከሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 14 ተጠርጣሪዎች፣ የጊዜ ቀጠሮ ምርመራ መዝገባቸው ተዘግቶ በአንድ የምርመራ መዝገብ ተጠቃለው በተከፈተባቸው የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ላይ ያቀረቡት ተቃውሞ ውድቅ ተደረገ።

ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን ተቃውሞ ውድቅ ያደረገው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ልደታ ማስቻያ አንደኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ከፌዴራል ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ ምርመራ ቡድን የምርመራ መዝገቡን ተረክቦ፣ ቀዳሚ ምርመራ በተመሳሳይ ፍርድ ቤት መክፈቱንና ምስክሮችን ለማሰማት ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበውን ጥያቄ ተጠርጣሪዎቹ ተቃውመው ነበር።

ተቃውሞውን ያቀረቡት አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሐምዛ አዳነ፣ ያለምወርቅ አሰፋ፣ አቶ ጌቱ ተረፈ፣ አቶ ታምራት ሁሴን፣ አቶ ሰቦቃ ሳፎ፣ አቶ ኬኔ ኡመታ፣ አቶ ጋሪ አብደላ፣ አቶ ቦጋለ ድሪብሳ፣ አቶ ሸምሰዲን ጣፋ፣ አቶ ቦናና አቶ መለስ ድርቢሳ (ጋዜጠኛ) ሲሆኑ፣ መቃወሚያ ክርክራቸውን በጠበቆቻቸው አማካይነት አቅርበዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቢያነ ሕግ አቶ ፈቃዱ ፀጋ (የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክተር) እና አቶ ኤፍሬም ኃይሉ (ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ) በተጠርጣሪዎቹ ላይ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 215585 ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀዳሚ ምርመራ መክፈታቸውን፣ ማለትም የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በምስክርነት ቃል የተቀበላቸውን የሰዎች ማስረጃዎች በፍርድ ቤት አቅርበው መረጃውን የማረጋገጥና የማስጠበቅ ሥራ ለማከናወን መዝገቡን መክፈታቸውን ገልጸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ባቀረቡት አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ዓቃቤ ሕግ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 38(ለ) ድንጋጌ መሠረት ቀዳሚ ምርመራ ለማድረግ ወስኗል። በመሆኑም ቀዳሚ ምርመራው በሰፊ የማስቻያ አዳራሽ ሆኖ በርካታ ታዳሚዎች መግባት በሚችሉበት ግልጽ ችሎት እንዲካሄድ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል። በተጨማሪም ዓቃቤ ሕግ በቀዳሚ ምርመራ የሚያቀርባቸው ምስክሮች የሚመሰክሩበትን የክስ ጭብጥና የምስክሮቹን ስም ዝርዝር እንዲሰጣቸው እንዲታዘዝላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ ለፍርድ ቤቱ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ከአንቀጽ 80 እስከ 93 ባሉት ድንጋጌዎች ቀዳሚ ምርመራ ማቅረብ እንደሚችል ከመደንገጉ ባለፈ፣ ለተጠርጣሪ የክስ ጭብጥ እንዲደርሰው ያለው ነገር ባለመኖሩ ለፍርድ ቤቱ ከማስረዳት ባለፈ የሚያስገድደው የሕግ ድንጋጌ እንደሌለ ገልጿል። ሊገደድ የሚችለው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ሲመሠርት ብቻ መሆኑን ጠቁሞ፣ ቅድመ ምርመራ ላይ የቀረበው የተጠርጣሪዎች ጥያቄ ተገቢ ባለመሆኑ ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል። የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ጥያቄ ባልቀረበበት ሁኔታ ቅድመ ምርመራው በግልጽ ችሎት ይታይ የሚል አቤቱታ ማቅረባቸውም ተገቢ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በድጋሚ ባቀረቡት ክርክር ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹ የሚያረጋግጡትን የምስክርነት ጭብጥ የመስጠት ግዴታ አለበት ብለዋል። ዓቃቤ ሕግ በጠቀሰው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 85 ድንጋጌ የሚያስረዳው ተጠርጣሪው (ተከሳሹ) ቃሉን ያለመስጠት መብት እንዳለው ስለሚገልጽ፣ ይህ ማለት ደግሞ የሚከሰስበትን አንቀጽ ካወቀ በኋላ መስጠት እንዳለበት የሚያመለክት መሆኑን በማውሳት ተከራክረዋል።

በሌላ በኩል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 ላይ ተጠርጣሪው የተጠረጠበት የወንጀል ዓይነት በዝርዝር ሊነገረው እንደሚገባ ጠቁመው፣ ዓቃቤ ሕግ “ጭብጥ አልሰጥም” ሲል ሕገ መንግሥቱን ዋጋ ማሳጣት በመሆኑና አግባብ ስላልሆነ የዓቃቤ ሕግ አቤቱታ ውድቅ ተደርጎ የጠየቁት እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

ዓቃቤ ሕግ ሌላው ያቀረበው ክርክር የምስክሮች ስም ዝርዝር እንዲሰጣቸው የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ሲሆን፣ ይህንንም የምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ (4) ድንጋጌን በመጥቀስ ከሚያቀርባቸው 15 ምስክሮች ውስጥ አምስቱን አዋጁ በሚፈቅደውና የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎትም ውሳኔ ስለሰጠበት በመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ እንዲታዘዝለትና የተጠርጣሪዎቹን ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።

ጠበቆች ለሦስተኛ ጊዜ በተሰጣቸው ዕድል ባቀረቡት መከራከሪያ ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ ጥበቃ ካላገኙ ምስክሮቹ ውጪ ያሉትን ምስክሮች ጭብጥና ስም ዝርዝር እንዲሰጠው መጠየቁን፣ የተጠርጣሪዎችን የመስማት መብት የሚያጣሩ መሆኑንም ማከሉን፣ ዓቃቤ ሕግ ጭብጡን ሰጥቷቸው ዓይተውትና ተወያይተውበት “ቀዳሚ ምርመራው አስፈላጊ ነው ወይም አይደለም የሚለውን ዕድል ሊሰጠን ስለሚችል ሊሰጠን ይገባል፤” በማለት ተከራክረዋል።

ፍትሐዊ ውሳኔ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ሊጠቅም እንደሚችልም አክለዋል። የሚያነሱት ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ የመሰማት መብት መሆኑን ጠቁመው፣ ጭብጡ የሚሰሙትን ምስክሮች በሚመለከት፣ “መቼ ነው የሚያስፈልገው? ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም?” የሚለውን ዓይተው ለፍርድ ቤቱ ምላሽ ለመስጠት እንደሚረዳቸውም ደጋግመው አስረድተዋል። ለወንጀል ፍትሕ አስተዳደር መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑንም አክለዋል። በደንበኞቻቸው ላይ ሲቀርብ የነበረው ምርመራ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት ለማነሳሳትና አስከሬን ከመንገድ ላይ ማስመለስ የመሳሰሉት እንደነበር ጠቁመው፣ በቀዳሚ ምርመራ ላይ ግን ምን ምን ጥያቄ እንደሚያቀርብ እንዳልተገለጸላቸውም ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል። ምስክሮች እንዳይታወቁ መከልከል ኢሕገ መንግሥታዊ መሆኑን ተናግረው፣ የሚያዩት ምስክር ድርጊቱ ሲፈጸም ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረ ይሁን ወይም ያልነበረ ስለመሆኑ እንዴት ሊያውቁት እንደሚችሉም እንደሚቸገሩ ገልጸዋል።

ዓቃቤ ሕግ በአጭሩ በሰጠው ምላሽ የተጠርጣሪዎች ጠበቆች የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 85 ጠቅሰው ቢናገሩም አንቀጹ በራሱ የሚያስረዳ እንጂ፣ ዓቃቤ ሕግ ጭብጥና የምስክሮች ስም ዝርዝር እንዲሰጥ የሚያስገድድ አለመሆኑን ተናግሯል። ቀዳሚ ምርመራ የነበረን ማስረጃ የማቆያ እንጂ ክርክር እንዲደረግ የሚያደርግ አለመሆኑንም ጠቁሟል። የሚያስገድድ የሕግ ድንጋጌ ባለመኖሩ ሊገደድ እንደማይችል ዓቃቤ ሕግ አስረድቷል።

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት ከግማሽ ሰዓት በላይ ዕረፍት ወስዶ እንደተመለሰ ብይን ሊነግር ሲል አቶ በቀለ እጅ በማውጣት ተጨማሪ አስተያየት እንዳላቸውና ሊናገሩ እንደሚፈልጉ ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱም ከሥነ ሥርዓት ውጪ መሆኑን በማስታወቅ እንደማይፈቅድላቸው ሲነግራቸው፣ “የመናገር መብት ከሌለን ለምን እንመጣለን?” ብለዋል። ፍርድ ቤቱም፣ “በጠበቆቻችሁ አማካይነት ከበቂ በላይ ጊዜ ተሰጥቷችሁ ተናግራችኋል፤” በማለት ብይኑን አስታውቋል።

ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር ከ80 እስከ አንቀጽ 93 ድረስ ሲጠቅስ ያቀረበው፣ የቅድመ ምርመራ ጥያቄ ማስረጃ የመጠበቅና የወንጀል ምርመራ አካል መሆኑን ማረጋገጥ እንደሆነ ገልጿል። የምስክሮችን ስም ዝርዝር በሚመለከት ድንጋጌው የሚለው ነገር እንደሌለና ወደፊት ክሱ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲቀርብ በራሱ የሚመረምረው መሆኑንም ጠቁሟል። በመሆኑም ጠበቆች የምስክሮች ስም ዝርዝርና ጭብጥ እንዲደርሳቸው የሚል የሕግ ድንጋጌ ባለመኖሩ ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉን አስታውቋል። ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ጥያቄ በሥነ ሥርዓቱ አንቀጽ 80 እስከ አንቀጽ 93 ያለውን ስለሚያሟላ፣ ምስክሮቹን ማሰማት እንደሚችል ገልጿል። የምስክሮቹ ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ (4) ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ጋር እንደማይጋጭ በመግለጽ፣ ዓቃቤ ሕግ አምስቱን ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ እንዲያስመሰክርና ቀሪዎቹ በግልጽ ችሎት እንዲመሰክሩ ትዕዛዝ በመስጠት ምስክሮቹን ለማሰማት ለነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሌላ የምርመራ መዝገብ ጊዜ ቀጠሮ ሲጠየቅበት የከረመው የእውነተኛ ዴሞክራሲ ለፍትሕ (ባልደራስ) ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ ላይም የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ምርመራውን ማጠናቀቁን ገልጾ፣ የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ መክፈቱን ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በማቅረብ ምስክሮቹን እንዲያሰማ ትዕዛዝ እንደሰጥለት ጠይቋል። ፍርድ ቤቱም በመፍቀድ ለነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።

ታምሩ ጽጌ፤ ሪፖርተር

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Law, Right Column Tagged With: bekele gerba, chilot, eskinder, jawar massacre, ችሎት

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ባልደራስ የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ በመጣል ሊጠየቅ ይገባዋል ተባለ July 1, 2022 09:23 am
  • “ሚካኤል ችግኝ ነው። … ችግኝ ይተክላል” ቴዲ አፍሮ June 29, 2022 03:30 am
  • “የእኔን ልጆችና የልጅ ልጆች (22ቱንም) የቀበርኩት እኔ ነኝ” አቶ መሀመድ የሱፍ ከምዕራብ ወለጋ June 28, 2022 01:07 pm
  • የገዳ ሥርዓት እና የኦሮሞ ገዢ መደብ June 20, 2022 11:34 pm
  • “የወልቃይትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበው ቀይ መስመራችን ነው” ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል June 12, 2022 07:09 pm
  • የሰሜን ምዕራብ ዕዝና የአማራ ልዩ ኃይል ተከዜ ክፍለ ጦር ዕውቅናና ሽልማት ተሰጣቸው June 12, 2022 06:21 pm
  • ሀገር በቀል ባህላዊ የግጭት አፈታቶችን በተገቢው በመጠቀም ዘላቂ እርቅና ሰላምን ማምጣት ይቻላል June 12, 2022 05:40 pm
  • የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በገረጂና በቀበና ያስገነባቸውን የመኖሪያ አፓርትመንቶች አስመረቀ June 12, 2022 05:35 pm
  • በኦነግ ሸኔ ፈርሶ የነበረውና ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለው ድልድይ ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት ጀመረ June 10, 2022 09:13 am
  • ጃዋር በዳውድ ኢብሣ ቀይ መስመር ተሰመረለት June 8, 2022 12:59 pm
  • ወልቃይት: ቢመረንም ለመዋጥና ራሳችንን ለመመልከት እንሞክር June 8, 2022 11:53 am
  • እብድ ይሻለዋል እንጂ አይድንም፤ ሐጂ ጃዋር አሁን ለምን ብቅ አለ? June 8, 2022 05:59 am
  • ሕዝብ ድምፅ የነፈጋቸው “ፓርቲዎች” የሽግግር መንግሥት ይቋቋም አሉ June 7, 2022 01:11 am
  • “አድጌ እንደናንተ መሆን እፈልጋለሁ” June 5, 2022 06:58 pm
  • በሳምንት ለ100 ያህል ሕሙማን አገልግሎት የሚሰጥ የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል ሥራ ጀመረ May 30, 2022 02:20 am
  • የጥቁር አንበሳ ዕጩ መኮንኖች (ካዴቶች) ተመረቁ May 29, 2022 04:01 pm
  • “ኢትዮጵያን መንካት አይቻልም!!” በሚል ቁጭት ነው እየሠራን ያለነው May 29, 2022 01:04 pm
  • “ከሞፈርና ቀንበር ወደ ትራክተር” በሚል መርህ ለአማራ ገበሬዎች የግብርና ሜካናይዜሽን ተሰጠ May 29, 2022 02:02 am
  • ኢትዮ 360 “የወያኔ፣ የጁንታ ሚዲያ ነው” – ባለከዘራው ጄኔራል May 27, 2022 02:51 am
  • “እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤ የሚያጣሉን ፖለቲከኞች ናቸው” የአማራ ወዳጃቸውን አደራ ቤት የመለሱ የቅማንት ተወላጅ May 27, 2022 01:40 am
  • ትግራይን አገር እናደርጋለን፤ “በውይይት እና በጦርነት” ሁሉንም ጉዳይ እንቋጫለን – የወንበዴው መሪ ደብረጽዮን May 26, 2022 09:18 am
  • “ሁለቱ የምዕራብ ዕዝ ተዋጊ ዶክተሮች” May 26, 2022 08:19 am
  • ወደ ትህነግ ሊተላለፍ የነበረ አምስት ሚሊዮን ብር ከ20 ተጠርጣሪዎች ጋር ተያዘ May 25, 2022 01:57 am
  • የጦርነቱ ስትራቴጂያዊ እውነታዎች May 19, 2022 09:37 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2022 · Goolgule