በአካባቢው ያለውን ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ ለሚመለከታቸው አካላት ቢያሳውቁም እስካሁን መፍትሄ አለማግኘታቸውን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሃይሌ ጋርመንት አካባቢ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ህገ ወጦቹ በአካባቢው የሚገኘውን 20 ሜትር ስፋት ያለው መንገድ 10 ሜትር ገፍተው በማጠር አጥብበውታል ሲሉ ነው ለኢዜአ የገለጹት።
ጉዳዩን ለወረዳው አስተዳደርና ለክፍለ ከተማው መሬት ይዞታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ቢያመለክቱም ወንጀሉን ለማስቆም ያላቸው ዝግጁነት አናሳ እንደሆነ ነው የገለጹት። “ቦታውን ካጠሩት ሰዎች ጋር ተደራደሩ” ከሚል ምላሽ በቀር ሌላ ምላሽ እንዳልሰጧቸውም ኢዜአ ዘግቧል።
የክፍለ ከተማው መሬት ይዞታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ “በፅሁፍ ምላሽ ሰጥተናል” ቢሉም የኢዜአ ሪፖርተር ማስረጃ ጠይቆ ማግኘት አልቻለም። የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ካሣሁን በበኩላቸው የነዋሪዎቹ መፍትሔ ካላገኙ የህግ ይከበር ጥያቄያቸውን ለክፍለ ከተማው ፅህፈት ቤት ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በነዋሪዎቹ የቀረበው ቅሬታ ትክክለኛ መሆኑ ከተረጋገጠ ህግን በተላለፉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድም አረጋግጠዋል። የመሬት ማኔጅመንት ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች፣ የደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ ደላሎችና የፀጥታ አካላት ጭምር ከስራ ማገድን ጀምሮ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑንም ሃላፊው ገልጸዋል። (ኢዜአ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply