በድሬደዋ የፀጥታ አካላት በጋራ ባካሄዱት የክትትልና ቁጥጥር ስራ በህገ -ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የሀገርን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች መያዛቸው ተገለፀ።
ገንዘቡ በቁጥጥር ስር የዋለው ትላንት መስከረም 6/2013 ዓ/ም ሲሆን ከህበረተሰቡ በተሰጠ ጥቆማ መሰረት ባደረገ ክትልል መሆኑን ድሬ ፖሊስ አስታውቋል።
ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 4 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ መታየት መጀመሩም ተገልፃል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የብር ኖቶች ውስጥ በዋነኝነት፦
- ዘጠኝ መቶ አርባ አርት ሺ አንድ መቶ አስር (944,110) የኢትዮጽያ ብር
- አንድ ሺ ሁለት መቶ ሀምሳ (1250) የአሜሪካን ዶላር
- አንድ መቶ ስልሳ አምስት (165) የሳውዲ ሪያል
- ሰባት መቶ አርባ አምስት (745) ዩሮ
ሲሆኑ ከእነዚህ ጋር አብሮም ከዘጠኝ በላይ የሚሆኑ ሀገራት የተለያየ መጠን ያላቸው የብር ኖቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በሌላ በኩል ደቡብ ኦሞና ጌዴኦ ዞኖች ሀሰተኛ የብር ኖቶችና አዘዋዋሪዎች መያዛቸው ተገልጿል።
የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኢንስፔክተር እታገኘሁ ዜና እንዳሉት በደቡብ ኦሞና ጌዴኦ ዞኖች 35 ሺህ ባለአንድ መቶ ሃሰተኛ የብር ኖቶችና አራት ተጠርጣሪ አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።፡
በቁጥጥር ስር ማዋል የተቻለው ህብረተሰቡ ባደረሰው ጥቆማ መነሻ ላለፉት ሶስት ቀናት ፖሊስ ባደረገው ክትትል ነው ብለዋል፡፡
ከሀሰተኛ የብር ኖቶች ውስጥ 27 ሺህ 900 በደቡብ ኦሞ ጂንካ ከተማ፣ ደቡብ አሪና ኛንጋቶም ወረዳዎች ቀሪው 7 ሺህ 200 በጌዴኦ ዞን ገዴብ ወረዳ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የሀሰተኛ የብር ኖቶች አዘዋዋሪዎቹ ገበያዎችና ሱቆች አከባቢ በመንቀሳቀስ በያዟቸው በሀሰተኛ የብር ኖቶች ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ አልባሳትና መሰል ዕቃዎች ግብይት እያካሄዱ ባሉበት ወቅት እንደተደረሰባቸው ኢንስፔክተሯ አስረድተዋል።
ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ከሚያዘዋዉሩ መካከል ሶስቱ ከደቡብ ኦሞ ቀሪው ከጌዴኦ ዞን እንደተያዙ አመልክተው በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እይተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ነባሩ የብር ኖት በአዲስ እየተቀየረ በመሆኑ በዚህ አጋጣሚ ህገ ወጥ ተግባር ለመፈጸም የሚጥሩ አካላትን ለመከላከል ፖሊስ እየተቆጣጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply