
“ጆሊው” ጀቤሳውን በአንድ ወቅት ኢትዮጵያዊነቷና “ኦሮማዊነቷ” ተምታቶባት ከነበረችው ቤተልሔም ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ አዳመጠሁት። ስለ ቤተልሔም ለመናገር ባይሆንም ዋናው ሃሳቤ፤ ቤተልሔም ከለውጡ በፊት ኦሮሞነቷን በአቅራቢያዋ የነበሩ ሰዎች እንኳን አያውቁም ነበር። በኋላ ግን እነ ጃዋር አራት ኪሎን በቅርብ ርቀት ማየት ሲጀምሩ “አኝከህ አኝከህ ወደ ወገንህ ዋጥ” ተብሎ በአማርኛ የተነገረው ብሒል ትዝ አላትና “ልትውጥ” ወደ “ዘመዶቿ” ዞር አለች። “ኢየሱስ ክርስቶስ አሁን በምድር ላይ ቢኖር ኦሮሞ እንደሚሆን እርገጠኛ ነኝ” ብላ አምላክን ኦሮሞ አድርጋውም እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
ወደ ጉዳዬ ስመለስ … ቃለ ምልለሱ ሲጀመር የሚታየው አጅሬው ያሬድ ጥበቡ (ጌታቸው ጀቤሳ) በዚያ አዛውትነቱ ነጭ ሸሚዙን ከደረቱ አጋማሽ ድረስ ከፈት አድርጎ ከውስጡ ካኔተራው እየታየ ዘና ብሎ ሲሆን ቤተልሔም ታፈሰ ደግሞ በዚያ አለባበስ (መጥፎ አልነበረም) ለውይይት መቅረቧን ተመልካቾቿ ይቅርታ በመጠየቅ ነበር። ዩትዩብ ላይ የተለቀቀው የቃለምልልሱ ቪዲዮ ሥር አንዱ ኮማች የሸሚዙን መከፈት በተመለከተ እንዲህ ብሏል፤ “የተከፈተ ሸሚዝ እውዳለሁ ማለትዋን እያስታውሳት ነው?? ነጭ ሸሚዝ ከሽበት ጭገር ጋር ማች (ያደርጋል) ጉድ ነው እኮ!!!”
ሲቀጥል ከገርልፍሬንዱ (ከሴት ጓደኛው እርሱ እንዳለው በዐቢይ ፖለቲከኞች ሤራ) የተለያየው “ጆሊው” ጀቤሳው ቤተልሔምን “አንተ በይኝ” እያለ ሲሞግታት ተስተውሏል። በመጀመሪያ በፈገግታ ዕንግዶቿን ሁሉ “አንቱ” እንደምትል ቤተልሔም ብትገልጽም (ከዚህ በፊት ጃዋርን “አንተ” እያለች ቃለምልልስ አድርጋለች) ያሬድ ግን ቃለምልልሱን ፌስቡክ ገጹ ላይ ሲፖስተው ቤተልሔምን “የኔ ቆንጆ” ባለበት አለላለጽ እየተመለከታት በድጋሚ “አንተ በይኝ ግዴታሽ ነው” እያለ ሲወተውት ተስተውሏል። እሷም ፈገግታዋን ወደ ጽልመት በመቀየር ኮስተር ብላ በአንቱታው ርቀት ቀጠለች።
ለነገሩ ቤተልሔምን አንድ ሁለቴ በስልክ አነጋግሬአታለሁ። ኩራቷ ገደብ የለሽ ነው፤ ቃለምልልስ እሷ የምትፈልገው ካልሆነ ቦታው፣ ጊዜው፣ ሰዓቱ፣ ቀኑ ሁሉ እርሷ ባለችው ሁኔታ ነው የሚካሄደው። እርሷ የምትፈልገው ከሆነ ደግሞ ዕንግዳው ቤት፣ ቢሮ ድረስ ሄዳ ታነጋግራለች። በነፍስ ማጥፋት እና ሌሎች ወንጀሎች ተከስሶ እስር ቤት የሚገኘው ጃዋር መሐመድን ቢያንስ ሁለት (ምናልባትም 3) ጊዜ ያነጋገረችው ቤቱ ድረስ ሄዳ ነው። ወደ ያሬድ ስንመለስ ቃለምልልሱ የተካሄደው የያሬድ ባልሆነ ቤት፤ ራሱ ያሬድን “ና” ብላ በጠራችው ቦታና ጊዜ የተካሄደ ነው። ይህ በራሱ ቃለምልልሱን ከጠያቂዋ ይልቅ ተጠያቂው በጣም እንደፈለገው ያመላክታል።
ቃለምልልሱ ተጀመረ፤ እያንዳንዱን ጉዳይ በዝርዝር አልሄድበትም። ነገርግን በ“ያ ትውልድ” ዙሪያ የገጽታ ግንባታ በሠፊው ተካሄደ። ቤተልሄም ራሷ የዚያ አውዳሚ ትውልድ ደጋፊና አድናቂ መሆኗን በተደጋጋሚ “አፖሌጂቲክ” በመሆን ነበር ስትናገር የተደመጠችው። ያሬድም የተሰጠውን ዕድል በመጠቀም፤ መቦጥረቅ በሚችለው ልክ ተቦጠረቀ። ሲቀጥልም የዚህን ዘመን ወጣት በእጅጉ ነቀፈው። ያልገባው ግን የዚህ ዘመን ወጣት ወያኔን እና የ“ያ ትውልድ” ሰዎችን ከሥራቸው መንግሎ የነቀለ መሆኑን ነው። ተነቅለው መዳረሻው ጠፍቶባቸው እየዋጀጁ ያሉት የነ ያሬድ ያ ትውልዶች ናቸው።
እዚህ ላይ ሳልጠቅስ የማላልፈው፤ ቤተልሄም ብቃት አልባ ስለሆነች ነው እንጂ ያሬድ በዚህ ልክ ስለ ያ ትውልድ ሲቦጠረቅ እሷም የዚያ ትውልድ ደጋፊ በመሆኗ ዝም ልትለው አይገባትም ነበር። በቅርቡ ስለዚያ ትውልድ ያልተሰሙ ክፋቶችና በደሎች፤ የኢህአፓው ቺፍ የነበረው ብርሃነመስቀል ረዳ ባለቤት ታደለች ኃይለሚካኤል የጻፈችውን “ዳኛው ማነው?” የሚለውንና የአንዳርጋቸው ጽጌን “ትውልድ አይደናገር፣ እኛም እንናገር” መጽሐፍት ላይ የተነገረውን አስደንጋጭ እውነታዎች በመጥቀስ ልትሞግተው ይገባት ነበር። ግን እሷ ለዐቅመ ትችት ስላልደረሰች ልተዋትና ወደ ጀቤሣው ልመለስ።
ለውጡ የመጣ ሰሞን ያሬድ የዐቢይ ደጋፊ ከመሆን አልፎ ያለልክ ሲተረተር ነበር። ለነገሩ ዶ/ር ዐቢይን ብዙ ርቀት ሄደው ያመሰገኑ (ያሽቋለጡ) ናቸው በብርሃን ፍጥነት ስድብ የጀመሩት። የ360ው ኤርሚያስ ለገሠ ዱሮ ለኢህአዴግ እንዳለቀሰ ለዐቢይም ማልቀስ ነበር የቀረው – በፍቅሩ ተነድፎ። ያሬድ ደግሞ “ዐቢይን አንመጥነውም” ብሎ ራሱን እና መላውን ሕዝብ የእግር መረገጫ ምንጣፍ ለማድረግ የሞከረ ነው። ሁለቱም የቋመጡለት ሥልጣን የጠዋት ጤዛ ሲሆንባቸው “ሰይጣን” የሚለውን መጠሪያ “ዐቢይ” በሚል የመተካት ያህል ጠቅላዩን ጠሉት።
ያሬድ ሞቶ ተሟሙቶ የጫራትን መጽሃፍ ከዋሽንግተን ዲሲ እስከ “ዋልድባ” ድረስ እንዲነበብለት ሲወተውት ቆይቶ የለውጡ ሰሞን ይህንኑ መጽሃፉ ይዞ ወደ ጦቢያ ወርዶ ነበር። ዓላማው ድርብ ነው። መጽሃፍ ለመሸጥ ብቻ ሳይሆን የጠቅላዩ አማካሪ ለመሆንም ነበር። ታዲያ ያኔ እንዲህ ተብሎ ሲወራ በሙሉ ልቤ አላመንሁም ነበር። ዛሬ ግን ከቤተልሔም ጋር ባደረገው ውይይት “ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማማከር ተመኝቼ ነበር” በማለት አፉን ሞልቶ ተናግሯል።
እናም መጽሃፉን ይዞ ወደ አገር ቤት ከገባ በኋላ በተለይ በአማራ ክልል ለበርካታ ቀናት ከተቀመጠበት ሆቴል ሲለቅ ሒሳብ ይጠየቃል። “የምን ሒሳብ?” ይላል ጀቤሳው። “እንዴ ይህንን ሁሉ ቀናት የተቀመጡበት ነዋ ጌታው?” ይባላል። የክፈል አልከፍልም እሰጥ አገባው ወደ መካረር ሲሄድ ሁኔታው ያላማራቸው ወደ ክልሉ ጽ/ቤት በመደወል ጉዳዩን ያስረዳሉ። ጉዳዩ በቶሎ እንዲዳፈንና የአደባባይ መሳቂያ ከመሆን ለመዳን የክልሉ ጽ/ቤት ሹም ለሆቴሉ ሰውየውን ልቀቁት፤ ሒሳቡን እኛ እንዘጋለን አሉና ተዘጋ። በጀቤሣው ቅሌት የተሸማቀቁት የክልል ሰዎች “ይሄ ነው እንዴ ሰውየው?” በማለት የትዝብት ማኅደር ውስጥ ከተቡት።
ወደ ቃለመጠይቁ ስመለስ … ሃፍረተቢሱ ያሬድ፤ ለቤተልሔም እጅግ በሚያስደነግጥ መልኩ “ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ ለማሻገር ትክክለኛው ሰው እኔ ነኝ” በማለት መጃጀቱን በይፋ አውጇል። ያሬድ በዚህ ደረጃ የወደቀበትን ነገር ወደኋላ መለስ ብለን ስንቃኘው በተደጋጋሚ ለማግኘት የተመኘውን ነገር ያጣ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ግልጽ ነው። ለውጥ ሲመጣ ከማንም በላይ ደጋፊ ሆነ፤ በድርብ ተደመረ፤ ሥልጣን ተመኘ፤ ያውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ፤ አቶ ደመቀ መኮንንን ሁለት ጊዜ አነጋገራቸው፤ በተደጋጋሚ ዶ/ር ዐቢይን ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልሳካ አለው፤ ወደ አሜሪካ ተመልሶ መጣ፤ ጠበቀ … ጠበቀ … ጠበቀ … በመጨረሻም “በቃኝ” አለና ከዚህ በፊት “ከበረከት ጋር በረሃ ድንጋይ ላይ ቁጭ ብለን ስናወራ የነበረው ናፈቀኝ … የአዲሱ ለገሠ ሳቅ ናፈቀኝ …” በማለት ሲናገር እንደተደመጠው፤ ሁሉ ነገር ዙሪያው ገደል ሲሆንበት ህወሃት ማሪኝ ብሎ ዐቢይን መሳደብ ጀመረ።
ቃለ ምልልሱ ላይ የሚሰማው ነገር በሙሉ ከላይ የጠቀስኳቸውን ጨምሮ ሌሎች ጆሮ የሚያደሙ ንግግሮች ተደምጠዋል። ያሬድ ዶ/ር ዐቢይን ለኢትዮጵያ ፖለቲካ “ክስረት” ብቻ ሳይሆን ከሴት ጓደኛው ጋር ለመጣላትም ምክንያት አድርጎታል። ሁኔታው ያስደነቃቸው ኮማቾችም ምላሽ ሰጥተውታል፤ “በወጉ ያላገባሀትን መንግስት አፋታኝ ስትል አታፍርም። ዛሬም ተመልሰህ ወያኔ ቂጥ ስር ለመሸጎጥና ያንን ያለፈውን አረመኔያዊ አገዛዝ መልሳችሁ ልትጭኑብን መሞከርህ አሳፋሪ ነው። አንተና ያ የስኳር ሌባ ተመልሳችሁ አፈር ልሳችሁ ወደስልጣን ከወያኔ ጋር ፈጽሞ እንደማትመለሱ የኢትዮጵያ ህዝብ በደሙ የጀመረውን ለውጥ እያፀና ነው።”
ሌላው ደግሞ “(የበፊቱ ባሏ) ሰለሞን ማነው? ያጥ (ያሬድ ጥበቡ) ከችክዎ በመባረርዎ ያልተሰማኝን ሀዘን እገልፃለሁ! እስካሁን ግን ሶስት ጉልቻ ሳይመሰርቱ ተጎልተው መቆየትዎ ትንሽ አያሳፍርም? መንግስት ነው ያፋታኝ አሉ ጨክነው? እዚህ ፍሎሪዳ ሰሞኑን ያጠቃንና ቤታችንን ያፈረሰው ሀሪኬንም የኢትዮጵያ መንግስት ነዋ? ገባኝ” ባልስማማበትም አንዱ ክፉ ኮማች ግን ይህንን ብሎታል፤ “ያሬድ ጥበቡ ምንአልባት ሰትዬዋ ጥላህ የሄደችው ከታችም ከላይም ትንሽ ሆነህባት ነው” ብሎታል።
በዚህ ቃለምልልስ ያሬድ ከዋንኞቹ ወንበዴዎች በላይ ትህነግን ሲያሞካሽ መስማት አሉላ ሰለሞን ወይም ስታሊን ገ/ሥላሴ ምን እየሠሩ ነው ያሰኛል። ሠራዊታችንን የካደውና በግፍ የገደለውን ትህነግ በእስረኛ አጠባበቁና እንክብካቤው ወደር የለውም በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል። እኔ በረሃ የነበርኩ ጊዜ ህወሃትን በደንብ አውቀዋለሁ፤ እስረኛ በሥነሥርዓት አስተናግዶና ተንከባክቦ ነው የሚይዘው ፤ አሁንም በቅርቡ እንዳየነው የያዛቸውን እስረኞች በክብር ተንከባከቦ አስረክቧል በማለት ነበር ያሬድ ሠራዊታችንን ዳግም የገደለው። ለዚህ ንግግሩ ምንም ምላሽ አልሰጥም፤ ምላሽ መስጠት በራሱ ያቆሽሻል፤ ያረክሳል። ይልቅ ቶሎ ልጨርስ …
“እኔ እንዲያውም በልቅነት ነው ራሴን የማየው” በማለት ወግአጥባቂ እንዳልሆነ እና ለመብቶች እንደሚቆም የተናገረው ያሬድ ከተናገረው ቀልቤን የሳበው “እኔ ዳፍንታም ነኝ (ነበርኩ)” ያለው ነው። በዘመነ ኢህአፓ ዳፍንታም ስለነበረ ሁልጊዜ የምትመራው አንዲት ሴት እንደነበረች ይተርካል። ከቃለ ምልልሱ ሁሉ በጣም ሊጠቀስ የሚገባው ጥሩ ንግግሩ ይህ ነበር። በእርግጥም ዳፍንታም ነው፤ የአካል ብቻ ሳይሆን የአመለካከትም፣ የፖለቲካም፣ የአስተሳሰብም ዳፍንታም ነው!
ለገሠ ነኝ ከሲልቨር ስፕሪንግ፤ ሜሪላንድ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣበ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
የትኛው መቀመጫውና ማሰቢያው የተምታታበት ነው ያን ትውልድ “አውዳሚ ትውልድ” በሚል የሚዘልፈው?