የ63 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ እና የ5 ልጆች አባት የሆነው አቶ ገብረ ተንሳኢ ተክላይ ከወይዘሮ ዘነበች በርሄ ጋር ለ14 አመታት በትዳር ተጣምረው በአሶሳ ከተማ የንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው 4 ልጆችን አፍርተዋል።
በትዳር ህይወታቸው ውስጥ ምንም አይነት እንከን እንደሌለ የሚገልፀው አቶ ገብረተንሳኢ ተክላይ ወይዘሮ ዘነበችን ከማግባቱ በፊት አንዲት ሴት ልጅ እንዳለችውና እሷም ለብቻዋ አዲስ አበባ እንደምትኖር በመግለፅ ይህንን እኩይ ተግባር ለመፈፀም የተነሳሳውም የግል ልጁን ለመርዳት እንደሆነ ተናግሯል።
ከሚኖርበት አሶሳ ከተማ ወደ ነቀምት ከተማ በመጓዝ “ኦጌቲ” በሚባል ሆቴል ውስጥ ለሁለት ቀናት አልጋ ይዞ በመተኛት ከሆቴሉ አስተናጋጆች የ21 ዓመት ልጅ የሆነውን ወጣት ገመቹ ዮናስን በመግባባት የአጋችና ታጋች ድራማውን አብሮት እንዲሰራና ለዚህም ታግቻለሁ ብሎ ከሚላክለት ብር ላይ 25,000 ብር እንደሚሰጠው በመንገር ያሳምነዋል።
በዚህም መሰረት ባል አቶ ገብረተንሳኢ ተክላይ በሸኔ ታግቻለሁ ብሎ ለባለቤቱ ደውሎ በመንገር ስልኩን ይዘጋል። ሚስት ወይዘሮ ዘነበች የምትይዘው የምትጨብጠው ይጨንቃታል። ከ24 ሰዓታት በኋላ ወጣት ገመቹ ዮናስ ደውሎ ኦነግ ሸኔ ነን አግተነዋል 800,000 ብር ካላስገባሽ ባልሽን አታገኝውም ይላታል። ሚስት እባካችሁ የልጆቼ አባት ነው እንዳትገሉብኝ ለምኘም ቢሆን ያገኘሁትን ብር እልክላችኋለሁ ስትል መልስ ሰጠች።
በወቅቱ ይህ የሃሰት የወንጀል ድራማ ከምዕራብ ዕዝ የመረጃ ሞያተኞች ጆሮ በመድረሱ በከፍተኛ ጥንቃቄ የጉዳዩን መነሻና መድረሻ በመከታተል የተሟላ መረጃና ማስረጃ ለመያዝ መንቀሳቀሳቸውን የዕዙ መረጃ መኮነን ተናግረዋል።
ወይዘሮ ዘነበችም በዙሪያዋ ያሉ ዘመድ ወዳጆቿን አስተባብራና ያላትን ሁሉ ጨምራ የልጆቿን አባት ለማስፈታት 500,000 ብር ለመላክ አዘጋጅታለች። በሁለተኛው ቀን አጋች ነኝ ያለው ወጣት ገመቹ ዮናስ ደውሎ ባልሽን አትፈልጊውም ? ይላታል ። በፈጠራችሁ አምላክ 4 ልጆች ያለ አባት ማሳደግ አልችልም እያለች በመማፀን ያለኝ 500,000 ብር ነው ልላክላችሁ እና ልቀቁልኝ ትላለች።
ሃሰተኛ አጋችና ታጋች አገኘሁ ባለችው ብር ተስማምተው ገንዘቡን የምትልክበት አካውንት በመላክ ሌላ ነገር ብታስቢ ግን እንገለዋለን ብሎ ያስፈራራታል። ብሩም በወጣት ገመቹ ዮናስ አካውንት ተላከ።
አቶ ገብረተንሳኢ ተክላይ ለገመቹ የገባውን ቃል 25,000 ብር በመስጠት ቀሪውን አውጥቶ የግል ልጁ በሆነችው አካውንት አስገብቶ እንዲቀመጥ ይነግራታል።
ከዚህ ሁሉ በኋላ በንቃትና በትኩረት ጉዳዩ ሲከታተል መረጃና ማስረጃዎችንም ሲያሰባስቡ መቆየታቸውን የገለፁት የምዕራብ ዕዝ የመረጃ ቡድን የሃሰት አጋችና ታጋችን በቁጥጥር ስር በማዋል ገንዘቡንም በፍጥነት ከገባበት አካውንት ተመላሽ እንዲሆን በማድረግ ዋና ወንጀል አድራጊና የወንጀሉ ተባባሪን ለነቀምት ከተማ ፖሊስ አስረክበዋል።
ወይዘሮ ዘነበች በርሄን ከአሶሳ ከተማ በስልክ አናግረን በጉዳዩ ላይ በሰጠችን ቃለ- ምልልስ 14 አመታትን አብሮኝ ከኖረውና ከልጆቼ አባት ይህንን ፍፁም አልጠበቅም። ማመንም ተስኖኛል። በተግባሩ አፍሬአለሁ አንገት የሚያስደፋ ነው። የያዘው ህግ ነው ህግ የሚወስነውን ይወስን። እውነታን አፈላልገው ለዚህ ሃቅ ላበቁኝ የህግ አካላት ግን ምስጋናዬ ከፍተኛ ነው ስትል ሃሳቧን ሰጥታለች። (የመከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም ገጽ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply