በቅርቡ አሜሪካ የሚኖሩት ወገኖቻችን በተባበረ ጥረታቸው ለብዙ ጊዜ ሲዋጉለት የነበረውንና የኢትዮጵያን መንግሥት ቢያንስ ቢያንስ ወደ ተከላካይነት ሊያወርደው ይችላል ተብሎ የታመነበት የአሜሪካ ኮንግረስ ውሳኔ በአደባባይ ለመላው ዓለም ሲታወጅ የተሰማን ደስታ ወሰን አልነበረውም። እኛ የአንጋፋው ትውልድ፣ ከሩቅ ሆነን ሲመቸን ብቻ “በርቱ” እያልን “ድጋፍ” ስንሰጣቸው የነበርነውን ይህን ያህል ያስደስተን፣ በቦታው ሆነው ሌት ተቀን ሳይታክቱ ከስቴት ወደ ስቴት እየተደዋወሉ በተወካዮቻቸው የኮንግረስ አባላት ዘንድ በመደወልና በመጻፍ ተጽዕኖ እያሳደሩ በመጨረሻ ላይ የለፉለት ግቡን ሲመታ ምንኛ እንደተደሰቱ ገምቼ እኔም በጣም ተደሰትኩላቸው። ብዙዎቹ እንደነገሩኝ ከሆነ፣ ያን ቀን በጥዋት ተነስተው ወደ ካፒቶል በማምራት፣ አሰልቺውን የጸጥታ ምርመራ በትዕግሥት አልፈው ወደ ኮንግሬስ ተወካዮቻቸው ቢሮ ድረስ በመዝለቅ “ኤች አር 128 እኮ ዛሬ ነው ለምርጫ የሚቀርበው፣ እባክዎትን ድጋፍዎን አይንፈጉን” እያሉ የወተወቷቸው መሆኑን ነግረውኛል። የተጠበቀውም ሆነ። ወሳኔው ያላንዳች ተቃውሞ አለፈ። የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም በዲያስፖራ ያለውና በውሳኔው ረቂቅ በኮንግሬስ ተደግፎ እንዲያልፍ ከልባቸው ይለፉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ከልባቸው ተደሰቱ። ታላቅ ድል!
ውሳኔው ባያልፍ ኖሮ ሁለት ነገሮች የሚከሰቱ ይመስለኛል፣ የመጀመርያው፣ ኢህአዴግ በሚሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ገንዘብ እየከፈለ በአሜሪካ ባለሥልጣናት ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር የቀጠረው የዋሺንግተን ዲሲ የደላላ ኩባኒያ ሥራውን በደንብ ሰርቶአል በማለት የልብ ልብ ይሰማው ነበር። “ከአሜሪካ መንግሥትም ጋር ያለኝ ወዳጅነት አስተማማኝ ደረጃ ላይ በመሆኑ የዲያስፖራው ሁካታ ሊያደፈርሰው አይችልም” በማለት ለሳምንታት በሞኖፖሊ በሚቆጣጠረው ቲቪ ጥሩ አርዕስተ ዜና አድርጎም ያቀርብ ነበረ። ግን ያላሰበው ሆነ። ሁለተኛው፣ ውሳኔው ባያልፍ ኖሮ፣ ረዘም ላለ ጊዜ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ሰውተው ይቀሰቅሱ ለነበሩት አክቲቪስቶቻችን ተስፋ አስቆራጭ ይሆን ነበር። እንደዚያ ተለፍቶበት ጥሩ ውጤት የማያመጣ የፖሊቲካ እንቅስቃሴ ደግሞ ጥልቅ የሆነ የሞራል ውድቀት እንደሚያስከትል መገመት አያዳግትም።
ጥሩው ነገር ውሳኔው አለፈ፣ እኛም ለዘመናት ከውጭ ብቻ እያየነውና እንፈራው የነበረውን ካፒቶልን ከውስጥ ሆነን ለማየት በቃን። የመረጥናቸው የኮንግሬስ አባላትንም ቢሮና ወንበር ገብተን አየን፣ በግል አነጋገርናቸው፣ አወቅናቸው። ካሁን በኋላ የኛን ጣልቃ መግባት የሚያስፈልግ የትውልድ አገራችን ጉዳይ ከተነሳ፣ ምን ማድረግና የት መሄድ እንዳለብን በደንብ አውቀነዋል። እንደ ዜጎች፣ መራጮችና ግብር ከፋዮች፣ ህገ መንግሥታዊ መብታችንን ተጠቅመን ተወካዮቻችን ስለ ትውልድ አገራችን ሁኔታ በትክክል እንዲገነዘቡና፣ የህዝቦቿ መብት ተጥሷል ስንላቸው አምነውን በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቅያሜያቸውን እንዲገልጹ ለማድረግ መቻላችን ትልቅ ድል ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከድንጋይና ዱላ ሌላ አንዳችም ኢህአዴግን የሚያስፈራራበት “ትጥቅ” ለሌለው ተበዳይ ትውልድ፣ እኛ እዚህ በሰላም ከምንኖርበትና ያላንዳች ፍርሃት መንገድ ላይ ወጥተን ብሶታችንን ከማሰማት በተጨማሪ፣ ካፒቶል ድረስ ሄደን ተወካዮቻችን ላይ ተገቢውን ጫና ለማድረግ የመቻል መብታችንን ተጠቅመንበት፣ የኢህአዴግ መንግሥት የህዝባችንን መብት መጣሱን የማያቆም ከሆነ ከዚህኛው ውሳኔ የተሻለ “ጥርስ ያለውን” ህግ እንዲያሳልፉ ለማድረግ፣ በዚህኛው እንቅስቃሴያችን ሂደት የታዘብናቸውን ክፍተቶች በሚገባ ሸፍነን ለሚቀጥለው ዙር ራሳችንን እናዘጋጅ እላለሁ።
ኤች አር 128 እና ይዘቱ፣
ይህ በሰፊው የተወራለትና ግብ እንዲመታም ከልብ የታገልንለት የውሳኔ ረቂቅ፣ በኮንግሬስ አባላት ሙሉ ድምጽ ድጋፍ የጸደቀው ኤች አር 128ን ይዘት ስንመረምር ግን፣ ምናልባትም የጠበቅነውን ያህል ጠንካራ ያልሆነና ለስለስ ካለ “ማስጠንቀቂያ” ባሻገር ኢህአዴግን “በህዝቡ ላይ እንዲህ ዓይነት በደል ስለፈጸምክ ይህንን እርምጃ ልንወስድ ወስነናል” የሚል ዓረፍተ ነገርን ያላዘለ፣ የተለመደውና ማንኛውንም ወገን ላለማስቀየም መንግሥታት የሚያሳልፉት “ጥርስ የሌለው ውሳኔ ነው” ቢባል ከእውነት የራቀ አይመስለኝም። አዎ! ብዙዎቻችን ይዘቱን በደንብ ሳንመረምር ወይም ሳንረዳ፣ ውሳኔው በመጽደቁ ብቻ ኢህአዴግ ላይ አንዳች ዓይነት እርምጃ የሚወሰድ መስሎን ተደስተን ነበር። ተስፋ ጥሩ ነገር ነው። ዕውኔታው ግን ሌላ ነው። ኤች አር 128ን ሳነበው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ከ1967 ዓ/ም ጀምሮ ያለማቋረጥ የሚያሳልፋቸውን እሥራኤልን የሚያወግዙ ውሳኔዎችን ያስታውሰኛል። በውሳኔዎቹ ማለፍ መጀመርያ መጀመርያ ላይ ይደሰቱ የነበሩ ፍልሥጤሞች ዛሬ ግን ውሳኔው ጸደቀም አልጸደቀ የሚያመጣው ውጤት ባላመኖሩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ ያላቸውን ተስፋ እርግፍ አድርገው ትተው በራሳቸው “ቄሮ” ላይ በመተማመን ኢንቲፋዳውን አፋፍመው ወራሪውን የእሥራኤል መንግሥትን በድንጋይ “እያርበደበዱት” ነው። አዎ! የፖሊቲካ ሂደት ደግሞ እንዴትና መቼ አቅጣጫውን እንደሚቀየር ስለማይታወቅ፣ እንደው አንድ ቀን ሁኔታዎች ይቀየሩ ይሆናል በሚል ተስፋ፣ የፍልሥጤም ዲፕሎማቶች በየቦታው አገራቸውን ከወረራ ነጻ ለማውጣት ለሚያደርጉት ትግል ፖሊቲካዊና ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲሰጡ ኃያላን አገራትን ለማሳመን ተግተው እየሰሩ ነው።
ኤች አር 128 “ጥርስ የሌለው ውሳኔ ነው”። የአሜሪካ መንግሥት በሌሎች አገሮች ላይ ለምሳሌ በሩሲያ፣ በቬኔዙዌላ ወይም በሰሜን ኮርያ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ የሚያስተላልፈው ውሳኔ፣ “በደል ፈጽመዋል” በተባሉት ግለሰቦች ላይ በነጻነት ካገራቸው ውጭ እንዳይንቀሳቀሱና በውጭ አገር ባንኮች ያስቀመጧቸው ሃብቶቻቸውና የንግድ እንቅስቃሴያቸው ላይ ያሳለፏቸው ዕገዳዎች “ጥርስ ያላቸው” ናቸው። በኤች አር 128 ውስጥ ግን፣ ኢህአዴግ በውሳኔው ውስጥ የተካተቱትን ክፍተቶች ካላሟላ ወደ ፊት “ዓለም አቀፍ የማግኒትስኪን ህግ” ሥራ ላይ እናውለዋለን ከማለትና “ሰላምና ዲሞክራሲን ለማምጣት ከጎንህ ነንና ትንሽ መሻሻል አድርግበት” ከሚሉ ምክር አዘል አባባሎችን ብቻ ነው ያቀፈው። ሆኖም ግን ጥሩ ጅምር ነው። የውሳኔውን መጽደቅ አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥት የተገኙ አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ የተለመደውን የተቃውሞ ድምጹን አሰማ። እንደ ማንኛውም መንግሥት ማድረግ ያለበት የሥራውን ድርሻ ስለፈጸመ ማንንም አላስደነቀም። የሚያስደንቀው የተቃውሞ ድምጹን ሳያሰማ ቢቀር ነበር። ያሰማው የተቃውሞ ድምጽም ልክ እንደ ውሳኔው ጥንካሬ ያለው የውግዘት ቃል ሳይሆን የተለመደው በመንግሥታት መካከል የሚለዋወጡት የርስ በርስ “ጉንተላ” ዓይነት ነበር።
ዓለም አቀፍ ግንኙነት
ለምንድነው ግን እነዚህ ያደጉ “ዲሞክራሲያዊ” አገሮች መንግሥታት እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ሃገራት ዜጎች ከመንግሥት የተለየ አስተሳሰቦችን በማስተናገዳቸው ብቻ እንደ ጠላት ተቆጥረው በየወህኒ ቤቱ ሲወረወሩና ሲሰቃዩ ወይም በጠራራ ፀሃይ በመንግሥቱ ወታደሮች ሲረሸኑ እያዩ ጥርስ ያለው ውሳኔ የማያስተላልፉት ወይም ማዕቀብ የማያደርጉባቸው? “ማህበረሰባችን የሰውን ልጆች በእኩልነት የሚያይና በደልን በማይፈቅድ በአይሁዳዊ-ክርስቲያን እሴቶች ላይ የተመሰረተ ነው” እያሉ እየለፈፉ ይህ ሁሉ በደል በሰው ልጆች ላይ ሲፈጸም እያዩ ግን አንዳችም እርምጃ ለመውሰድ የማይደፍሩት ለምንድነው? ለምንድነው ለምሳሌ በየመን ሕዝብ ላይ የጅምላ ግድያና የዘር ማጥፋት ጦርነት የምታካሄደውን ሳዑዲ ዓረብያን እንደማውገዝ፣ ሆን ብለው ከሷ ጋር ወዳጅነታቸውን የሚያጠናክሩትና ህዝቡን የምትጨፈጭፍበትን የጦር መሳርያ በገፍ የሚያቀብሏት? ለምንድነው የቬኔዚዌላ መንግሥት የራሱን አገር አብዛኛው ዜጎቿ በመረጡት የፖሊቲካ ሥርዓት አስተዳድራለሁ በማለቱ ብቻ እንደ ጠላት ተቆጥሮ “ጥርስ ያለው” ማዕቀብ የተደረገበት? ለምንድነው ሳዳም ሁሴን፣ ምንም ዓይነት የጅምላ ጨራሽ መሳርያ የለኝም እያለ እውነቱን እየነገራቸው በውሸት ላይ ተመስርተው እነዚህ “ፍታሃዊ በሆነው በአይሁዳዊ-ክርስቲያን መሪህ ነው የምንተዳደረው” ብለው የሚኩራሩት ኃያላን “ዲሞክራቲክ አገሮች” ኢራቅን ወርረው፣ ሳዳምን አስሰቅለው፣ የቻሉትን ያህል ገድለው ኤኮኖሚዋን አዳሽቀውና ህዝቡን ለርስ በርስ ጦርነት የዳረጓት?
አዎ! መንግሥታት የየራሳቸው ብሄራዊ ጥቅም (national interest) አላቸው። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚከሰቱትንም የሰው ልጆች መብት ጥሰቶችን የሚያዩት በዚህ ብሄራዊ ጥቅም በተባለው መነጽራቸው ነው። ለመደገፍም ሆነ ለመኮነን መለኪያቸው ከዚህ ብሄራዊ ጥቅም በመነሳት እንጂ በሰው ልጆች መብት ጥሰት ወርድና ጥልቀት ተመዝኖ አይደለም። የብሄራዊ ጥቅም መመዘኛ ደግሞ አገሪቷ ለምሳሌ አመርቂ የሆነ የከርሰ ምድር ሃብት ያላት፣ ለምርቶቻቸው ማራገፍያ ገበያ አቅራቢ ወይም የጠላታቸው ጠላት መሆን ነው። ያደጉ አገራት የራሳቸውን ጥቅም እስካስጠበቀላቸው ድረስ ከአምባገነን መንግሥታትም ጋር ወዳጅነትን ከመመስረት ወደ ኋላ አይሉም። በአንጻሩም ብሄራዊ ጥቅማቸውን ከተቀናቀነ በህዝብ የተደገፈን መንግሥት እንኳ ቢሆን ከማፍረስ አይመለሱም። ይህ መሰረታዊ የሆነና የመንግሥታትን የርስ በርስ ወዳጅነትንና ጠላትነትን የሚቆጣጠር ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት መሪህ ነው። ባጭሩ፣ ያደጉ መንግሥታት በታዳጊ አገራት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የሚገቡት ብሄራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ብቻ እንጂ የሰው ልጆችን ከጥቃት ለማዳን ተብሎ አይደለም። ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ጉዳይ ደግሞ፣ እነዚህ ያደጉ አገራት፣ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ከማውገዛቸው በፊት፣ ሌላ እንደ አማራጭ ሥልጣን ለመውሰድ ያኮበኮበው ድርጅት፣ አሁን ያለው መንግሥት ከሚሰጣቸው የተሻለ ሊሰጣቸው የሚችል አንዳች ዓይነት ጥቅም አለ ብለው ካመኑበት ብቻ ነው። ለምሳሌ ዛሬ ሥልጣን ላይ ያለው የቬኔዙዌላ መንግሥት የነፈጋቸውን ያገሪቷን የነዳጅ ሃብት ቁጥጥር ተቃዋሚው ፓርቲ ሥልጣን ከያዘ ያን የተነፈጉትን “ቁጥጥር” መልሰው የሚያገኙ ከሆነ፣ በተቻላቸው መጠን ተቃዋሚውን ደግፈው በየፓርላማቸው ወይም ኮንግሬስ “ጥርስ ያለውን” ውሳኔ ያስተላልፋሉ ማለት ነው። የድህረ ኢህአዴግ መንግሥት ደግሞ ዛሬ ኢህአዴግ ከሚሰጣቸው የተሻለ ጥቅም ሊሰጥ ስለማይችል፣ የአሜሪካ መንግሥት፣ ኢህአዴግን አስመልክቶ የሰው ልጆች መብት በመጣሱ ብቻ “ጥርስ ያለው” ውሳኔ ያስተላልፍ ይሆናል ብለን ባንጠብቅ ይሻላል ለማለት ያህል ነው።
ሌላው የዚህ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መሪህ አካል ደግሞ፣ በመንግሥታት መካከል ዘላቂ ወዳጅነትንና ጠላትነት አለመኖሩ ነው። ባንድ ወቅት ታማኝ ጓደኛ አድርገው የተወዳጁትን መንግሥት፣ ብሄራዊ ጥቅማቸውን የነካባቸው መስሎ ከታያቸው፣ ከመቅጽበት ወደ ጠላትነት የመቀየር ባህሪ መደበኛ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ነው። ለሰሩለት አገርና በሥራቸውም ጠባይ ምክንያት ለተዋወቁት ህዝብ ታማኝ ሆነው የሚቀሩት ወንጌላውያንና አንዳንድ ቱሪስቶች ወይም በህብረተሰብ የምርምር ሥራ የተሰማሩ ምሁራን ብቻ ናቸው። ትናንት የኢትዮጵያ መንግሥትን ያማክሩ የነበሩ የነዚህ የምዕራብ አገር “ባለሙያዎችና ዲፕሎማቶች” ዛሬ ደግሞ ለኤርትራ መንግሥት አማካሪ መሆን ቅንጣት ታህል አይከብዳቸውም። ነገ ደግሞ ሁኔታዎች ከተቀየሩ ተመልሰው ለኢትዮጵያ መንግሥት አማካሪ መሆን ያንኑ ያህል ይቀልላቸዋል።
በተለያዩ ታዳጊ አገራት በመከሰት ያለውን የሰው ልጆች መብት ጥሰት በተለምዶ ራሳቸውን የበላይ ጠባቂ አድርገው የሾሙት እነዚህ የምዕራብ አገራት፣ ራሳቸው ከታዳጊ አገሮች እኩል ወይም በከፋ መልኩ የሰው ልጆችን መብት ጣሽ ሆነው በመገኘታቸው፣ ዛሬ ስለ ሰው ልጆች መብት ጥሰት አፋቸውን ሞልተው መናገር የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ከተናገሩም በጥሞና የሚሰማቸው ጆሮ የለም። በተባበሩት መንግሥታት የሰው ልጆች መብት ኮሚሽንም ቢሆን ምክር ቤቱ በግልጽ የሚያራምደውና ቅድሚያ የሚሰጠው ለአባላቱ ብሄራዊ ጥቅም እንጂ ለሰው ልጅ መብት አለመሆኑን ከምን ጊዜም በላይ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ለዚህም ነው ለምሳሌ በተባበሩት መንግሥታት የሰው ልጆች መብት ኮሚሽነር ምክር ቤት በአሜሪካ ግፊት ሩሲያን ከአባልነት አስወጥተው የሰው ልጆችን መብት መጣስ በታወቀችው በሳዑዲ ዓረቢያ የሚተኳት።
ብዙዎቻችን ለምሳሌ በቅርቡ የተላለፈው የኮንግሬስ ውሳኔ “ጥርስ ቢኖረውና” ሌላው ቢቀር የኢህአዴግን የምጣኔ ሃብት ቀዳዳ ይሸፍናል ተብሎ የሚታመንበትን የአሜሪካ መንግሥት የሚሰጠውን እርዳታ ቢያቆም ደስ ይለን ነበር። ግን አልሆነም፣ ያደጉ አገራት ዕርዳታ ባብዛኛው ለይስሙላና “ረድተናል” ብለው ዓለም አቀፋዊ “ጉራን” ለመቀዳጀት እንጂ ለግሰናል ከሚሉት ገንዘብ አብዛኛው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እዚያው ሰጭው አገር ነው የሚቀረው። ከተለገሰው ገንዘብ አብዛኛው የሚውለው ከ“ስጦታው” ጋር አብረው “የሚለገሱ” የራሳቸውን ሥራ አጦች “ጠቢባን” (experts) ተብዬዎች ደሞዝና ኢንሹራንስ መክፈያ ነው። ብዙዎች “ጠቢባንም” ባማረ የሥጦታ ጨርቅ የተጠቀለሉ ሰላዮች መሆናቸው የዓደባባይ ምሥጢር ነውና፣ ዕርዳታ ማለት የለጋሿን አገር ብሄራዊ ጥቅም “በሰብዓዊ ዕርዳታ” አሳብቦ “የሚሰጥ” ባዶ ቅርጫት ነው ማለት ይቻላል።
ውጤቱ፣
ዛሬ ላይ ቆም ብዬ ስመለከተው አብዛኛውን የአፍላ ዕድሜያችንን ጉልበት ያፈሰስነው፣ ማፍሰስ ባልነበረብን ቦታ ላይ ይመስለኛል። ያኔ ጥገኝነት ወይም ዜግነት ተሰጥቶን እንኖርባቸው በነበሩት አገራት በየቀኑ በየሻይ ቤቱ ተገናኝተን እርስ በርስን በማሳመን ላይ ጊዜ ከማጥፋት፣ በምንኖርባቸው አገራት የፖሊቲካ ህይወት ተካፋይ በመሆንና የፓርላማው ወይም የኮንግሬስ አባል ሆኖ ከውስጥ ደጋፊዎችን በማፍራት ላይ ብናተኩር ኖሮ ዛሬ የኢትዮጵያ መንግሥት በወገኖቻችን ላይ ስለሚፈጸመው ግፍና በደል የምንኖርባቸው አገራት ተወካዮቻችን የሚሰሙት፣ ውጭ ቆመን ከምንጮኸው ከኛ ሳይሆን፣ ውስጥ ካሉት የፓርላማ ወይም የኮንግሬስ አባላት ትውልደ-ኢትዮጵያውያን አፍ ይሆን ነበር። ይህንን ጉድለት በጊዜው እርማት አድርገንበት ከማስተካከል ይልቅ፣ ያገራችንን ቀውስ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅና እርዳታ ለመጠየቅ፣ ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት ተጠራርተን፣ በተገኘው ዘዴ ጊዜያችንን ሃብታችንና ጉልበታችንን ሰውተን የአውሮፓ መንግሥታት ተወካዮች መናኸርያ ወደ ሆነችው ብራሴልስ አምርተን፣ በሰላማዊ ሰልፍ ከተማዋን ድብልቅልቁን አውጥተን የምንወዳቸውን ባንዲራዎቻችንን አውለብልበንና ላንቃችን እስኪሰነጠቅ መፈክር አሰምተን፣ መጨረሻ ላይ፣ በብርቱ ጥንቃቄ ያረቀቅነውን የአቤቱታ ደብዳቤ “ለሚመለከተው” ክፍል እንዲያደርስልን ለዘበኛው ሰጥተንና “ዓላማችንን ከግቡ አድርሰን” ወደየመጣንበት እንመለሳለን።
በሰሜን አሜሪካ ያሉት ወገኖቻችንም፣ ከተቀነባበረ የስልክና ደብዳቤ ወደ ተወካዮቻቸው ከመላክ ተልዕኮ ባሻገር፣ ከየቦታው ተጠራርተው ወደ መዲናው ዲሲ በመሄድ “በነጩ ቤት” ወይም ካፒቶል ፊት ለፊት ተሰልፎ መፈክር አሰምቶ ከመለያየታቸው በፊት፣ የአቤቱታ ደብዳቤያችንን ለሚመለከተው ክፍል እንዲያደርስላቸው ለዘበኛው አስረክቦ መሄድን ልምድ አደረግነው።ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ ዛሬም፣ በምንኖርባቸው አገራት የውስጥ ፖሊቲካ ህይወት አካል አለመሆን ብቻ ሳይሆን እነዚህ አገራት የሚመሩበትን፣ ለምሳሌ የሃሳብ ልዩነትን አቻችሎ ባንድ ላይ መራመድ የመቻልን ዲሞክራሲያዊ ባህል እንኳ ለመቅሰም አለመቻላችን ነው።
ለኔ እንደሚመስለኝ ለሁለት መቶ ዓመታት የተዘፈቅንበት የፊውዳሉ ሥርዓት አንዳች ዓይነት ተጽዕኖ ቢያሳድርብን ነው እንጂ፣ አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ሥር ሆነው ለነጻነታቸው ይታገሉ በነበረበት ዘመን እኛ እንደ ነጻ ህዝብ ሆነን በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የታወቅን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንኳ ሲመሰረት ብቸኛ ጥቁር አገር ተካፋይ ብቻ ሳይሆን የድርጅቱ ቻርተር ሲረቅቅ፣ የህግ ክፍሉን ያረቁ የነበሩትን ምርጥ የዓለም የህግ ባለሙያዎችን ይመራ የነበረውን አክሊሉ ሃብተወልድን ያፈራች አገር፣ እንዴት ዛሬ ከሰባ ዓመት በኋላ ከዚያ “መውደድን እንጂ መተማመንን” ከማይፈቅደው የፊውዳሉ ሥርዓት የአስተሳሰብ ዘይቤ ለመላቀቅ አልቻልንም ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ።
የኛ ሚና (ማድረግ ያለብን)
ባገራችን በመካሄድ ላይ ባለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እዚህ ውጭ አገር ያለን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ሊኖረን የሚገባንን ሚና በትክክል ለመገንዘብ አንዳንድ ዕውኔታዎችን በግልጽ ማስቀመጡ ለአፈጻፀም ይረዳናል ብዬ አስባለሁ። በኔ ግምት፣ እነዚህን ዕውኔታዎች በትክክል አለመረዳትና ወቅታዊ ክስተቶችን ከነባራዊው ሁኔታ ጋር ለማገናዘብ አለመቻላችን፣ ምኞትና ተግባርን ያማታብን ይመስለኛል። ለማንኛውም ከብዙዎቹ ዕውኔታዎች ጥቂቶቹ እነሆ፣
ሀ) ባገራችን በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ዓመጽ የራሱን ቦይ ተከትሎ በመሄድ የራሱን መሪዎች ከራሱ መሃል እየፈጠረ ነው። በሂደቱ የተፈጠሩት መሪዎች ትግሉን ከግብ ያድርሱ አያድርሱ በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ትግሉን ለመምራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ግን ጥያቄ ውስጥ ማስገባት አይቻልም። ከማንኛችንም በላይ የአግዓዚን ጦር በባዶ እጃቸው የተጋፈጡ፣ ለቆሙለት ዓላማ የታሰሩበትና ፍዳቸውን ያዩበት ስለሆኑ ከማናችንም ውጭ አገር ካለነው የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎችና አባላት በላይ የሞራል የበላይነት አላቸው ብዬ አምናለሁ። በዲያስፖራ ለዓመታት የኖርነው አንጋፋው ትውልድ ጊዜያችንን ያሳለፍነው አገሪቷ ውስጥ የሚካሄደውን ማንኛውንም የለውጥ እንቅስቃሴ “እንመራዋለን” ወይም “አመራር እንሰጣለን” በሚል ራስን በራስ የመሾም የህልም ዓለም ውስጥ ነበር ብል የተጋነነ አይመስለኝም። ለዘመናት ባገራችን ሰፍኖ የነበረው ፊውዳላዊው ሥርዓት ለፖሊቲካ ፓርቲዎች መፈጠር አመቺ ባለመሆኑ፣ ባገሪቷ ሰፍኖ የነበረውን አስተዳደራዊ ቀውስንና የመደብና የብሄሮችን ጭቆና ለመፍታት የሚደረገው ትግል ይመራ የነበረው ባብዛኛው በውጭ አገር ይኖሩ በነበሩ የተማሪው ማህበር አባላት በመሆኑ፣ ዛሬም በዚያው መንፈስ እዚህ ውጭ አገር ያለነው የተለያዩ ድርጅቶች አባላትና መሪዎች፣ ባገር ቤት በመካሄድ ላይ ያለውን ትግል የምንመራ መስሎ ቢታየን አይፈረድብንም ለማለት ያህል ነው። ግን ዘመኑ ተቀይሮአል።
ለ) ካገራችን ውጭ በምንኖርባቸው አገራት የፖሊቲካና ማህበረሰባዊ እንቅስቃሴ አካል ሳንሆን ለዘመናት ራሳችንን አግልለን ኖረናል። ከብዙ ዓመታት በፊት ወደ ምዕራብ አውሮፓ በተሰደደኩበት አገር፣ ከኔ ቀደም ብለው ለብዙ ዓመታት ይኖሩ የነበሩ የትግል ጓደኞቼ፣ ባገሩ በየሶስት ወይም አራት ዓመት እየሄዱ የፓርላማ አባላትንና መሪዎቻቸውን ከመምረጥ ባሻገር ባገሪቷ የፖሊቲካ ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳልነበራቸው ተገነዘብኩ። በህዝቡ መካከል እየኖሩ፣ ቋንቋውን እየተናገሩና ባህሉን በደንብ እየተረዱ የማህበረሰቡ አካል ሆኖ “ያላመኑትን ከማሳመን” ይልቅ፣ በሻይና ቢራ ቤት እየተገናኙ ስለ ኢትዮጵያ ፖሊቲካ ለርስ በርስ ማስረዳት ቀዳሚ ተግባራቸው ነበር። ከጥቂት ጊዜ ባኋላ እኔም የነሱን ፈለግ ተከትዬ ከሥራ በኋላ ወደ ሻይ ቤታችን (ፓርላማችን) እያመራሁ ስለ ኢትዮጵያ ፖሊቲካ “መወያየትን” መደበኛ ሥራዬ አደረግሁ። ከዚህ ሻይ ቤት ውጭ፣ በያመቱ በሜይ ዴይ ቀን ለዓመታዊ የድጋፍ ሰልፍ ካልሆነ በስተቀር የትም ቦታና በምንም መልኩ ከምንኖርበት አገር የፖሊቲካ ህይወት ጋር በሚያገናኘን መድረክ ላይ ተገኝተን አናውቅም። አጋጣሚ በተገኘ ቁጥር ከያለንበት ተጠራርተን ወደ “ፓርላማችን” ጎራ እያልንና “የተጠመቅነው እርስ በራሳችን ተሰባብከን” ማታ ወደየቤታችን ከመመለስ ባሻገር ይህ ነው የማይባል ተጽዕኖ ለማሳደር አልቻልንም። የሚገርመው ደግሞ ወቅቱ ያገሪቷ ገዢ ፓርቲ፣ ከሌላ አገር የመጡትን ዜጎች በፓርቲው ውስጥ በአባልነት ለማካተት ሙከራ ያደርግ የነበረበት ጊዜ ነበር።
ሐ) ኢትዮጵያዊ ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊ ልጆቻችን በሚኖሩባቸው “አዳዲስ አገራት” የፖሊቲካና ማህበረሰባዊ እንቅስቃሴ ንቁ ተሳታፊ እንዳይሆኑ አናበረታታቸውም። በምንኖርባቸው ዲሞክራሲያዊ አገራት የሚወለዱት ልጆቻችን እንኳ ሳይቀር፥ “የኛን ባህልና ቅርስ እንዲወርሱ” በማለት፣ እንደ ጓደኛቻቸው በነጻነት እንዲያድጉ ከመገፋፋት ይልቅ “ባህላችን አይፈቅድም፣ እንዲህ አታድርግ እያልን” “በጨዋ ደንብ” እንዲያድጉልን በማሰብ አስተሳሰባቸውን በነጻ እንዳይገልጹ አድርገን አሳደግናቸው። እንደ ጓደኞቻቸው፣ ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ የስደቱን ዓለም እንደተቀላቀሉት የሶማሌ ስደተኞች ልጆች፣ ከኬንያ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በተባበሩት መንግሥታት እርዳታ ወደ ሰሜን አሜሪካ ተልከው ዛሬ የፓርላማ አባልና ሚኒስቴር መሆን መቻላቸውን እያየን፣ እኛ ግን በሚኖሩባቸው ማህበረሰባት ውስጥ የሚካሄዱትን የመረዳጃ ወይም የፖሊቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት እንዳይካፈሉና በትምህርታቸው ብቻ “ጎብዘው” ኤንጂኔር፣ ሃኪም ወይም በሌላ የተፈጥሮ ሳይንስ ሙያ ልቀው ዶክተር እንዲሆኑልን ነበር የምንገፋፋቸው። ከሁለት ወይም ሶስት የስደት ትውልድ በኋላ ባፈራናቸው የተፈጥሮ ሳይንስ ሊቃውንት ልክ፣ አንድ እንኳ ታዋቂ የቢቢሲ የሲኤንኤን ወይም የአልጄዚራ ጋዜጤኛ ለማፍራት አልቻልንም። የኢትዮጵያ ሁኔታ ተቀይሮ ዲሞክራሲ ሰፍኖ ጓዛችንን ጠቅልለን ከነልጆቻችን በቅርቡ የምንመለስ እየመሰለን፣ የኢትዮጵያም ሁኔታ ሳይሻሻል፣ እኛም እያረጀን፣ ልጆቻችንም በያሉበት አገራት የፖሊቲካ ህይወት ሳይቀላቀሉ በመቅረታቸው፣ ብሶታችንን ከውስጥ ሆኖ የሚያሰማልንን ሳናፈራ፣ ከሁሉም ያጣን ተከታታይ ትውልድ ሆነን ቀረን ብሎ መደምደሙ ትክክል ይመስለኛል።
በኔ ግምት፣ የውጭ አገራትን መንግሥት አስተማማኝ ድጋፍ ለማግኘት የምንችለው፣ የራሳችን ልጆች በያገራቱ የፖሊቲካ ሂደት ውስጥ ከተሳተፉና ብሎም በሂደት የፓርላማ ወይም ኮንግረስ አባል ከሆኑ ብቻ ነው። በርግጥ ረጅም ጉዞ ነው፥ ግን ደግሞ ዛሬ ካልጀመርነው መቼም አንደርስበትም። እንደሚመስለኝ ከሆነ የብዙዎቻችን ችግር፣ የኢትዮጵያ ሁኔታ በኛ ዕድሜ የሚቀየር እየመስለንና እኛም ከነልጆቻችን ከዛሬ ነገ እንመለሳለን የሚል ተስፋ ሰንቀን ስለምንዞር፣ ልጆቻችንን በሚኖሩባቸው ህብረተሰብ የፖሊቲካ ህይወት ውስጥ ገብተው በንቃት እንዲሳተፉ ጥረት አናደርግም። ግን ትልቅ ስህተት ነው። ከኛ በፊት የነበሩ አንጋፋ ትውልድ የምንላቸውም እንደዚህ እያሉ፣ የኔም ትውልድ እንደዚሁ በቅርቡ እንመለሳለን እያልን “ከውስጥ ሆነው ላገራችን ህዝቦች መብት እንዲታገሉ” ልጆቻችንን ሳናዘጋጅ መቅረታችን የትውልድ ስህተት መሆኑን አምነንበት ከዛሬው ብናስብበት ጥሩ ይመስለኛል። የኢትዮጵጵያ ሁኔታ በቅርቡ ተቀይሮ ዲሞክራሲ ሰፍኖ እናያለን የሚለውን ማማ በሰማይ አይነት wishful thinking ወደ ጎን ትተን ምናልባት አንድ ቀን ልጆቻችን በሚኖሩባቸው ዲሞክራቲክ አገራት ተወዳድረው አሸናፊ ሆነው ባገኙት የፓርላማ ወይም የኮንግረስ መቀመጫቸው ላይ ሆነው፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ “ጥርስ ያለው” ውሳኔ ለማስተላለፍ የሚችሉ የህዝብ ተወካይ እንዲሆኑ ለማብቃት መጣር አለብን ባይ ነኝ።
መ) ከውጭ “ዲሞክራቲክ” መንግሥታት የምናገኘው የቁሳቁስም ሆነ የሰብዓዊ እርዳታ፣ ህዝባችን ለሚያደርገው የሰላምና ዲሞክራሲ ትግል ድጋፍ እንጂ ወሳኝ ሊሆን አይችልም። በውጭ መንግሥታት የቀጥታም ሆነ ተዘዋዋሪ “እርዳታ” ፍትህና ዲሞክራሲ የትም አገር ሰፍኖ አያውቅም። ስለሆነም በየቦታው ተደራጅተን የግብር ከፋይነትና የመራጭ መብታችንን ተጠቅመን በተወካዮቻችን ላይ ጫና ማሳደሩ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ያህል በህዝባችን ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማሳወቁና የራሳችንን ዕድል የምንወስነው እኛ ብቻ መሆናችንን መገንዝበን ያለብን ይመስለኛል። የሰላም የፍትህና የዲሞክራሲ ምሰሶ ከራሱ ከህዝባችን የተቀነባበረ ትግል ውጤት የሚመነጭ ብቻ ነው። ስለዚህ፣ በምንኖርባቸው አገራት በፓርላማና ኮንግረስ ያሉት ተወካዮቻችን፣ በትውልድ አገራችን በመከሰት ላይ ያለውን የሰው ልጆች መብት ጥሰት ጉዳይ “እንዳሳሰባቸው” ድጋፋቸውን እንዲሰጡን የምንጠይቀውን ያህል፣ ከነሱ የዲሞክራሲ ባህል ምሰሶ የሆነውን “ተቻችሎ የመኖርን” ልምድ ደግሞ ቀስመንና በመካከላችን ያለውን መሰረተ-ቢስ መከፋፈል አቁመን በጋራ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን መሰረት ለመጣል መረባረብ ተያያዥ ሚናችን ይመስለኛል።
ሠ) ባገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ ጥገናዊ በመሆኑ፣ መሰረታዊ ለውጥ በአፋጣኝ መጥቶ በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ዲሞክራሲ በኛ ዕድሜ ይሰፍናል ብሎ በትክክለኝነት መናገር አይቻልም። ለዘመናት ተጭኖብን ከነበረው የፊውዳሉ ሥርዓት የወረስነውን ጎጂ አሰራር ባንድ ሁለት ትውልድ ዕድሜ በትግል አፍርሰነው በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንተካዋለን ብሎ ማሰብ ግመልን በመርፌ ቀዳዳ ለማሳለፍ የመሞከር ያህል ይመስለኛል። የተጀመረው ተፈጥሮያዊ የጥገና ለውጥ ግቡን ይመታል እንኳ ብንል፣ ልናገኝ የምንችለው፣ ዜጎች ከገዥው ፓርቲ የተለየ የፖሊቲካ አስተሳሰብ በማስተናገዳቸው ብቻ ሽብርተኛ ተብለው መታሰራቸውና መሰቃየታቸው ይቀንስ እንደሁ እንጂ፣ የምንመኘውና በተለይም በምዕራብ አገራት የተላበስነውን የሰው ልጆች መብት መከበር ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ውሎ እናያለን ብዬ አልገምትም። ኢህአዴግም፣ ራሱ ከውስጥ በስብሶም ሆነ በህዝብ ግፊት ቢፈርስና የዛሬዎቹ ተፎካካሪ ድርጅቶችና ግለሰብ ፖሊቲከኞች ሥልጣን ላይ ቢወጡ እንኳ፣ ዲሞክራቲክ ሆነው ሰላምና መረጋጋትን አስፍነው ዜጎቿ በእኩልነት የሚኖሩባትን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ይገነባሉ ብዬ አፌን ሞልቼ ለመናገርም ይከብደኛል። ለማለት የፈለግሁት ባገራችን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማስፈን አይቻልም ሳይሆን፣ ካሰብነው በላይ የተወሳሰበና አስቸጋሪ በመሆኑ ረጅም ጊዜ ሊፈጅ ይችላልና አቋራጭ መንገድ አንፈልግ ነው። Turra malee hinuurra jette boombiin goes the Oromo saying. “ይዘገያል እንጂ እንበሳዋለን” አለች አሉ ጥንዚዛ።
ለመደምደም ያህል፣
ባገር ቤት ላሉት ወገኖቼ የማስተላልፈው ብዙም ምክር የለኝም። የኤች አር 128 ውሳኔ በማለፉ ከትግላችሁ የማያዘናጋችሁን ያህል ባያልፍም ኖሮ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይሆንም ነበር። በመሰረቱ ተመሳሳይ “የዲሞክራቲክ አገሮች” ፓርላማዎች የሚያሳልፉት የፖሊቲካ ውሳኔ ትግላችሁን ትንሽም ቢሆን ሊደጉም ይችላል። ግን ራሳችሁን በራሳችሁ አደራጅታችሁ ትግሉን መምራት ብቻ ሳይሆን፣ በመደራጀት ውስጥ የመንግሥትን ጠንካራ መሰረት ሊያናጋ የሚችል ትልቅ ኃይል እንዳላችሁ ተረድታችሁ በየአደባባዩ በመውጣት ለሰላም ለዕኩልነትና ለዲሞክራሲ ያላችሁን ፍላጎትና ቁርጠኝነት በተግባር እያሳያችሁ ስለሆነ ከዚህ ራቅ ካለ ቦታ ሆኖ ይህን አድርጉ ያንን አታድርጉ ብሎ ለመምከር መሞከሩ ጊዜው ያለፈበት አሰራር ይመስለኛል። በሙያችንና በልምዳችን ግን፣ አቅማችን እንደፈቀደ ትግላችሁን ለመደጎም የተቻለንን ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማንል ቃል እንገባላችኋለን።
በውጭ አገር ላለነውና ያገራችን ጉዳይ ያገባናል ብለን ደፋ ቀና ለምንል ወንድሞቼና እህቶቼ ግን የሚከተለውን ለማለት እሻለሁ። ያገራችን ኤኮኖሚያዊና ፖሊቲካዊ ቀውስ በቅርቡ መፍትሄ ያገኛል የሚል ግምት ስለሌለኝ፣ ዛሬም ሆነ የዛሬ ሃምሳ ዓመት ወደ ትውልድ አገራችን ብንመለስ፣ እናት አገራችንን አምላክ እንደፈጠራት እንደዚያው እንደ ጥንቷ የምናገኛት ይመስለኛል።
በመሆኑም፣ አንድ ቀን የምንመኘው ዲሞክራሲ ባገራችን ሰፍኖ ልጆቻችን እንዲያዩ ከፈለግን፣ ዛሬ ህዝባችን ለሰላምና ዲሞክራሲ የሚያደርገውን ትግል ከያለንበት በገንዘብና በሃሳብ እንዲሁም ባካበትናቸው ልምዶች መርዳቱ ታሪካዊ ግዴታችን ይመስለኛል። እንደ ዓፄው ዘመን እዚህ ባህር ማዶ ተደራጅተን ትግሉን እንመራለን ማለት ወይም አመራር ለመስጠት መሞከር ግን ራስን ማታለል ሆኖ ይታየኛል። የኛ ትውልድ ሳናውቅ በስህተት ራሳችንን ከምንኖርባቸው አገራት የፖሊቲካ ህይወት ማግለላችን ያስከተለውን ድክመት ግንዛቤ ውስጥ በመክተትና፣ ልጆቻችንም በሄድንባቸው የስህተት ጎዳና እንዳይሄዱና ካሁን በኋላ ዛሬ በሚኖሩባቸው አገራት እንጂ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ባገራችን የፖሊቲካ ህይወት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንደማይሆኑ ተረድተን፣ እዚሁ በሚኖሩባቸው አገራት የፖሊቲካ ህይወት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ሆነው የፓርላማ ወይም የኮንግረስ አባል እንዲሆኑ ማበረታታት አለብን እላለሁ። መልካም ጊዜ ለሁላችሁም እመኛለሁ።
*****
ጄኔቫ 20 April 2018
ባይሳ ዋቅ-ወያ፣ wakwoya2016@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply