ኢትዮጵያን መምራት ከጀመሩ ሶስት ወር ያስቆጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ በአሸባሪዎች የተከበበች አገር መሆኗን አመለከቱ። ኦብነግ በመገንጠል ስም የፖለቲካ ንግድ የሚያካሂድ ድርጅት እንደሆነ ገለጹ። መንግስታቸው ለሚታማበት ጉዳይ ማስተባበያ አቀረቡ።
ከአልጃዚራ ቴሌቪዥን እንግሊዝኛው ክፍለጊዜ ጋር ቃለ ምልልስ ያካሄዱት አቶ ሃ/ማርያም ስለ አሸባሪዎች የተናገሩት በአገሪቱ የተነሳው የእስልምና ሃይማኖት ጥያቄና ተቃውሞ ስለቀረበበት የአህባሽን አስተምሮ ተከትሎ ከአያያዝ ጉድለት ጉዳዩ ወደ ቀጠናው እንዳይሸጋገር ስጋት ስለመኖሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ ነው።
“ጥያቄው የጥቂቶች ነው” በሚል አቃለው በማቅረብ ማብራሪያቸውን ጀመሩ። መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ በማመልከት አብዛኞቹ ሙስሊሞች ጥያቄያቸው የአስተዳደርና የሲስተም መሆኑንን አመላክተው ማንም ያልደፈረውን ጉዳይ አነሱ።ኢትዮጵያ የበርካታ ሃይማኖቶች አገር መሆኗን በመጥቀስም የአኻዝ መረጃ ሰጡ።
በአገሪቱ የክርስቲያኖች ቁጥር ከአጠቃላይ ህዝብ 43 በመቶ፣ ሙስሊሞች 35 በመቶ የተቀሩት ሃይማኖቶች ቀሪውን ቁጥር እንደሚይዙ በተዛዋሪ ተናግረው በሁሉም ሃይማኖቶች ጽንፈኞች መኖራቸውን አስታወቁ። አያይዘውም አገሪቱ በቃጣናው በአሸባሪዎች የተከበበች አገር እንደሆነች አመለከቱ። ይህ አኻዝ አወዛጋቢ ነው ቢባልም The World Factbook የሚባለውና በመላው ዓለም በዋቢነት የሚጠቀሰው የአሜሪካ የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ድረገጽ በኢትዮጵያ ያሉትን ሃይማኖቶች ቁጥር 43.5በመቶ ኦርቶዶክስ፣ ሙስሊም 33.9በመቶ፣ ፕሮቴስታንት 18.6በመቶ፣ ባህላዊ 2.6በመቶ፣ ካቶሊክ 0.7በመቶ እና ሌሎች 0.7በመቶ በማለት በዝርዝር ያሰፍራል፡፡
ጠያቂዋ እንደ ቢቢሲው የሃርድ ቶክ ጋዜጠኛ ትንታግ ሆና ከማፋጠጥ ይልቅ አቶ ሃይለማርያም መንግስታቸው የሚታማበትን ጉዳይ እንዲያስተባብሉ እድል የሰጠቻቸው በሚመስለው ቃለ ምልልስ አቶ ሃይለማርያም “አሸባሪዎቹ አገር ቤት ድር አላቸው” ሲሉ ማንም አገር እንደሚያደርገው ሁሉ እርሳቸው የሚመሩት መንግስት ከነዚህ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ህግ ፊት እንዳቀረበ ተናግረዋል። በዚህም በሙስሊም ኢትዮጵያውያን የተነሳውን “የመንግስት ጣልቃገብነት” ይቁምና የ“ድምጻችን ይሰማ” ጥያቄ ወደ አሸባሪነት አጠጋግተውታል።
“ማንም ፖለቲከኛም ሆነ የመንግስት ሰው ከህግ በታች ነው” ያሉት አቶ ሃይለማርያም “በህዝብ የተመረጥን እንደመሆናችን የህዝባችንን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት አለብን” በማለት ራሳቸው ፈገግ ብለው ጠያቂዋንም አስደምመዋታል። ስለ ኢኮኖሚ እድገት ሲያነሱ በተከታታይ የእጥፍ አኻዝ እድገት መኖሩን አቶ ሃይለማርያም ሲናገሩ “እሱ እውነት ነው” በማለት የምስክር ወረቀት ሰጥታ ወደ ቀጣዩ ጥያቄ የገባችው ጋዜጠኛ የተለያዩ የኢኮኖሚ ተቋማት የኢኮኖሚ ዕድገቱ ከዚህ በታች እንደሆነ የዘገቡትን በንጽጽር በመጥቀስ መስቀለኛ ጥያቄ ሳታቀርብ የቀጠለችው አቶ ሃይለማርያም ነካ ወዳደረጉት የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ጉዳይ ነበር።
የተጀመረው የእርቅ ድርድር የቆመው ህገመንግስቱን ለመቀበል ኦብነግ ፈቃደኛ ሊሆን ባለመቻሉ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሃይለማርያም፣ ህግመንግስት ቅድመ ሁኔታ ባለመሆኑ፣ ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ሁሉ ህገመንግስትን ማክበር ግዳጅ በመሆኑ ኦብነግ ይህንን ሊቀበል ባለመፈለጉ ድርድሩ መቋረጡን አመልክተዋል። ኦብነግ የተከፋፈለ እንደሆነ፣ ከተካፋፈሉት መካከል አገር ቤት ገብቶ ህገ መንግስቱን አክብሮ ለመስራት የጠየቀ መኖሩንና መጨረሻው ወደፊት እንደሚታይ ገልጸዋል። ኦብነግ በተመሳሳይ በመጀመሪያ ድርድር የተደረሰበት ስምምነት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር እንደነበር አስታውቆ የመከላከያ ሚኒስትሩ የመሩት ልዑክ በሁለተኛው ድርድር በቅድሚያ ህገመንግስቱን መቀበል የሚል ቅድመ ሁኔታ በመነሳቱ ድርድሩ መቋረጡን በድርጅቱ ድረገጽ የገለጸውን ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ማተሙ ይታወሳል።
ኦብነግን የሚያነሳው የመገንጠል ጥያቄ በህገመንግስቱ የተረጋገጠ መሆኑን ያወሱት አቶ ሃይለማርያም “በመሬት ላይ ያለው እውነት ሌላ ነው። የፖለቲካ ንግድ ነው የተያዘው” በማለት ተዛልፈዋል። ኦጋዴን ውስጥ መንግስት አደረገ የተባለውን ኢሰብአዊና አስከፊ የማሰቃየት ተግባር አቶ ሃይለማርያም “የአንድ ወገን መረጃ” በማለት ሊቀበሉት አልቻሉም። የቢቢሲ የምርመራ ጋዜጠኛና ሂውማን ራይትስ ዎች ኦጋዴን ውስጥ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት መጣሱን ተበዳዮችን በማነጋገር፣ በቪዲዮ የተደገፈ መረጃ በማስደገፍ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው። በወቅቱ በህወሃት/ኢህአዴግ የሚመራው የአቶ መለስ አገዛዝ ጉዳዩን በተመሳሳይ አስተባብሎ ነበር።
ስለ መሬት ነጠቃና የመሬት ነጠቃው ለምግብ እጥረት ችግር መንስዔ ስለመሆኑ በማንሳት መልስ እንዲሰጡ እድል ያገኙት አቶ ሃይለማርያም “የመሬት ነጠቃ የለም።ይህ ስህተት ነው” በማለት ነበር ጀመሩት። ከአርሶ አደሮችም ሆነ ከአርብቶ አደሮች ላይ መሬት እንዳልተቀማ፣ ለውጪ ባለሃብቶች የተሰጠው መሬት ሰው የሌለበት ትርፍ የግጦሽ /ሳቫና ላንድ/ እንደሆነ በመግለጽ የጋምቤላና የኦሞ ሸለቆ የቀዬው ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ሸምጥጠው ክደዋል። የምትልመጠመጠዋ ጠያቂ ተጨማሪ ማስረጃ አቅርባ መከራከር ባለመቻሏ ስለድህነት ጥያቄ አንስታ አቶ ሃያለማርያም “በሁሉም አገር ያለ እውነት ነው” የሚል መልስ በመስጠት ተገላግለዋል።
ሁለቱም ምስሎች በጋምቤላ አካባቢ ከሳተላይት የተወሰዱ ናቸው፡፡ ቀያዮቹ ነጥቦችና በቀይ የተከበቡት ቦታዎች በሙሉ በመሬት ነጠቃ ከቀያቸው የተፈናቀሉና ቤታቸው የፈረሰ አባወራዎችን ሲሆን ቢጫዎቹ ደግሞ ተፈናቃዮቹ በግዳጅ የሰፈሩበትን ነው፡፡
አምስት ሚሊዮን ረሃብተኛና በድርቅ የተጎዱ ተመጽዋቾች ስለመኖራቸውና እድገትና በርካቶች ስራ ፍለጋ ወደ የመን ይጎርፋሉ ስለሚባለው አቶ ሃይለማርያም የሚያዝናና መልስ ነው የሰጡት። መልሳቸው አቶ መለስ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚሰጡትና ትተውት ከሄዱት “መጽሐፍ” የተቀዳ ይመስላል፡፡ “ከ25 ሚሊዮን አሁን 90 ሚሊዮን ደርሰናል።” በሚል አምስት ሚሊዮን ርዳታ ፈላጊዎች መኖራቸው ሊገርም የሚችል አለመሆኑን፤ አገር ለቆ ስራ ለመፈለግ ወደ ሌላ አገር መሄድ የፖለቲካ ሳይሆን የኢኮኖሚ ችግር መሆኑን አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስን አስመራ ሄደው ለማነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ቀደም ሲል ስምምነት አውርዶ አገር ቤት ከገባው አንድ የኦጋዴን ክንፍ በተጨማሪ ሌሎችም በተመሳሳይ ወደ አገራቸው ለመግባት ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል። ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ በድርጅት ሳይሆን በግል ከድርጅት መሪዎች ጋር የውስጥ ለውስጥ ንግግር ከተለያዩ ክፍሎች ጋር በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።
የእስልምናን እምነት ተከታዮችን አስመልክቶ ዜናውን ለማመጣጠን አስተያየት የሚሰጠን አካል ማግኘት አልቻልንም። ሆኖም በዚህና በተመሳሳይ ቀጣይ ስራዎቻችን ላይ የተመጣጠነ ዜና ለማቅረብ ይቻለን ዘንድ፣ በዚህ ዜና ላይ መልስ ወይም መቃወሚያ ካለ፣ በሚታወቅ አድራሻና ማህበር፣ ድርጅት ወይም መልስ ለመስጠት አግባብነት ካላቸው አካላት ቢቀርብልን ለማስተናገድ ፈቃደኛ መሆናችንን ለመግለጽ እንወዳለን።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
በለው ! says
ልጅ እናትህ የት ሄደች ? ቢሉት ያላዩባትን ልታውራ አለ መቼም ኃለይለመልስ በሄዱበት ሁሉ ነገሮች ያመልጣቸዋል አቶ መልስ እና ኢሳያስ አፈወርቂ በድብቅ ይሰሩ ነበር?አቶ ኢሳያስ የምስራቅ አፍሪካ የቀጠናው አተራማሽ የሽብርተኞች መደበቂያና መሰልጠኛ ተብለው ተፈርጀው መየኢኮኖሚ ማዕቀብ ተጥሎባቸው አልነበረም? ኃይሌ ስለምን ሊነጋገሩ ነው የሚሄዱት? ኤርትራን ወደ እናት ሀገሯ ለመመለስ ወይስ ቶሎ እንዳይፈነግሏቸው ሊማፀኑ? አይ አቶ ሃይለማርያም ጥርሰ ፍንጭት ነዎት እና ሲናገሩ እያሰቡ አላልኩም!!? በፓርላማ ያን ያህል ኮሶ እንደጠጣ ተኮሳትረው የእጅዎ ሰዓት እሰኪፈናጠር ሲወራጩ ሲጮሁ ለኤርትራ ጊዜ ባልጀዚራ ቲቪ እንዲህ ክብሯን ጠብቃ ኖራ ሠርጓ እንዳማረላት ኮረዳ ፍንድቅድቅ አሉ። ታዘብኩዎት!!
፩) “በአገራችን የአሸባሪዎች ድር አለ”
-እሰይ ታዲያ ዋናው ባለራዕይ ሸማኔ አለቃዎ አቶ መልስ ዜናዊ አልነበሩም?
ዛሬስ ወንበሩ ራዕዩ መንፈሱ በኃይለመልስ አደለምን?
፪) ጥጡ ከየት መጣ?
ከደደቢት
፫) ለመሆኑ ማጉ ምንድንው?
-ዘረኝነና ጉጠኝነት!
፬) አስመጪና ላኪው?
– ወያኔ (ህወአት)
፭) ማን አደወረው?
-ካድሬ ሆድ አደር ደደብ ምሁር
፮) ድውሩ ምንድነው?
-እርስ በርስ ማባላት፣ ማሠር ፣ማፈን፣ መግረፍ ፣
፯)ልቃቂቱሰ?
-እንግዲህ ቀስ እያለ የመጣው የሕዝብ ብሶት
፰) ኩታ ነው? ነጠላ ነው? ጋቢ? የአንገት ልብስ?
-እንግዲህ ማየት ነው ብቻ ትልቅ ነው ማጣፊያው እንዳያጥር !!
፱) ለመሆኑ ባለቤቱና ገንዘቡስ
-በኢፈርት ኢፈርት በኋላም “ሃፍረት” ይሆናል!።
፲) የግብይይቱ ዓይነት?
-ቢቻል በስምምነት በመተሳሰብና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ
፲፩) ሰነድ አለው ?
እንዴታ! አለ ግን የማይነበብ የማይተረጎም ህገ -ወያኔ
(በራሳችሁ ድር ትተበተባላችሁ በለው!!)