ኢህአዴግ ከወትሮው በበለጠ አስመራ ላይና አስመራን ተገን ያደረጉ ተቃዋሚዎች አስመልክቶ የተንጠለጠሉ ጉዳዮችን አንድም በሰላማዊ መንገድ፣ አለያም በሃይል ለመቋጨት ፍላጎት እንዳለው ከተለያዩ ምንጮች ይሰማል። ይህንኑ መረጃ የሚያጠናክሩ መግለጫዎችና ዜናዎችም በቀጥታና በተዘዋሪ እየተደመጡ ነው። ድርድሩ የሚካሄደው ኦነግን ጨምሮ ከተለያዩ ድርጅት አመራሮች ጋር በተናጠል ስለመሆኑ ለስርዓቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ጠቁመዋል።
ኦነግንና ኢህአዴግን ለማስማማት ከላይ ታች የሚሉት የአገር ሽማግሌዎች የሚባለውን ቁጥሩ በውል የማይታወቅ ኮሚቴ የሚመሩት ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅን ጨምሮ የቀድሞው የኦነግ አመራር አባቢያ አባጆቢር፣ የኢትዮጵያ መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ፕሬዚዳንት የነበሩት ቄስ ኢተፋ ጎበናና ከሳቸው ጋር የሚሰሩት ኮሚቴዎች፣ በአሜሪካ የወንጌላዊት ሉትራን ቤ/ክ የአፍሪካ ብሔራዊ አገልግሎቶች ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ገመቺስ ቡባ ደስታ ከፊት ለፊት ረድፍ የተቀመጡ አሸናጋዮች መሆናቸው ብዙም የተሰወረ አይደለም።
ቄስ ኢተፋ ጎበናና ዶ/ር ገመቺስ “እርቅ ከፍትህ ጋር” የሚል የጸና እምነት ያላቸው ሲሆን “ትግል በቃኝ” በማለት አገር ቤት በመግባት ግጭትን በማስወገድ ላይ መሰረት አድርጎ የሚሰራ ተቋም ከዶ/ር ያዕቆብ ሃይለማርያም ጋር የመሰረቱት አባቢያ አባጆቢርና ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ የሚመሩት የአገር ሽማግሌዎች ቡድን እርቅ ላይ ስለሚከተለው መሰረታዊ እምነቱ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም። የቅንጅት አመራሮች እንዲፈቱ በማድረግ ረገድ “ወርቃማ ገድል ፈጽሜያለሁ” የሚሉት ፕሮፌሰር ኤፍሬም በተለያዩ አካላት ተቃውሞ የደረሰባቸውና የ“ኢህአዴግ አፈ ቀላጤ” በሚል የሚያወግዟቸው ጥቂት አይደሉም።
መንግሥት ሲፈልግ “የለም” ሲያሻው “አሸባሪ” በማለት ከሚከሰው ኦነግ ጋር በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉት ድርድሮች ውጤት ሊያመጡ ያልቻሉበት ምክንያት አንዱ ሌላውን እምቢተኛ በማድረግ ከመወቃቀስ በዘለለ እርቁ ስለተበላሸበት ምክንያት ሁለቱም ወገኖች የሚስማሙበት እርግጠኛ ምክንያት አልተደመጠም።
አንዳንዴ ሶስት፣ ሲልም አራት ቦታ መሰነጣጠቁ የሚነገርለትን ኦነግ ከኢህአዴግ ጋር ለማስማማት በተለያዩ ወቅቶች የተደረጉ ድርድሮች ለመሰናከላቸው ትክክለኛው ምክንያት ባይቀርብም ዋናውና ትልቁ ችግር ግን የኦህዴድ ጉዳይ እንደሆነ ይነገራል። በኦህዴድ ውስጥ ድርድሩን የሚደግፉ ያሉትን ያህል የሚቃወሙትም አሉ። ስማቸው እንዳይጠቀስ የሚፈልጉ የኦህዴድ ሰዎች “ኦነግ ቢስማማና ህገ መንግስቱን አከብራለሁ ብሎ አገር ቤት ቢገባ የኦህዴድ እድል ምን ሊሆን ነው?” የሚል ጥያቄ ከሚያነሱት መካከል ይመደባሉ።
በተለያዩ መንገዶች ዋናውን ኦነግ አስማምቶ አገር ቤት የማስገባት ስራ እንደሚሰራ ማወቃቸውን የሚገልጹት ክፍሎች ጡረታ የወጡ የኦነግ ሰዎችን ፕሮፌሰር ኤፍሬም በማነጋገር ላይ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። አባቢያም በተመሳሳይ ጀርመንና አሜሪካ ያሉ ወዳጆቻቸውን እያግባቡ እንደሆነ ይናገራሉ። የድርድሩ ደረጃ ምን ያህል እንደተጓዘ ባያብራሩም ድርድሩ ከሰመረ የተወሰኑ ሰዎች አገር ቤት ሊገቡ እንደሚችሉ ነው ያስታወቁት። መረጃው ምንጩ እንዳይታወቅ በመጠንቀቅ ዝርዝር ጉዳዮችን ያላብራሩት የኦህዴድ አባላት አሜሪካ ያሉ የኢህዴግ ዲፕሎማቶችና ወዳጆች በጉዳዩ ዙሪያ እየሰሩ እንደሆነ አመልክተዋል። ድርድሩ ከኦነግ ጋር ብቻም እንዳልሆነ ጠቁመዋል። እነዚህ ክፍሎች ቄስ ኢተፋ ጎበናና ዶ/ር ገመቺስ ስለሚመሩት እርቅ ግን ያሉት ነገር የለም።
ከፊሎቹ ደግሞ “ኦነግ ተደራድሮ በሰላም በምርጫ ለመወዳደር አገር ቤት ይገባል የሚለው ጉዳይ ላም አለኝ በሰማይ አይነት ነው” በማለት ከቶውንም ኢህአዴግ እንዲህ ያለ እብደት ውስጥ እንደማይገባ ይከራከራሉ። ምናልባትም በሰላም እንደሚያምን፣ ለእርቅ የተዘጋጀ እንደሆነ ለውጪው ዓለም ለማሳመን ካልሆነ በቀር።
እነዚህ ክፍሎች የማይሸሽጉት አንድ እውነት ግን አለ። ኢህአዴግ ቁልፍ የኦነግ ሰዎችን መማረክ ይፈልጋል። እነዚህ ቁልፍ ሰዎች በድርድር ተማርከው ወይም ተስማምተው አገር ቤት ከገቡ ኦነግ በተደጋጋሚ ከደረሰበት የውስጥ ችግር ጋር ተዳምሮ ከደጋፊዎቹ ጋር ይለያያል ይላሉ። ለዚህ ጠንካራ ነገር ግን ቅዠት የሚመስል ትንታኔያቸው የሚያቀርቡት ማስረጃ አስደንጋጭ ይመስላል።
ለጎልጉል እንደወትሮው ስማቸው እንዳይጠቀስ በማስጠንቀቅ ማብራሪያቸውን የሚያቀርቡት ክፍሎች፣ ታዋቂ የሆኑትን የኦነግ ሰዎች ለማጥመድ ኢሳያስ አፈወርቂ አንደኛው አማራጭ ናቸው። ሰሞኑን በግምገማ ተወጥሮ የከረመው ህወሃት በሃይል ኢሳያስን የማስወገድ አቋም እንዳለው ጠቅሶ ኢንዲያን ኦሽን ኒውስ ሌተር የጻፈውን እንደሚስማሙበት የሚጠቅሱት ክፍሎች በየትኛውም መመዘኛ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ወገን የሃይል እርምጃ ቢያጣድፋት የመመከት አቅም አይኖራትም። ይልቁኑም ኦፕሬሽኑ አጭር፣ የማያዳግም፣ ኢሳያስንና አብረዋቸው ያሉትን በሙሉ ሊጠራርግ የሚችል ይሆናል። በዚህ መነሻነት ኢሳያስ ከመለስ ሞት በኋላ ያለውን ህወሃትን እንደፈሩት አስረግጠው ይከራከራሉ።
ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩ፣ ከወራት በፊት ከኢትዮጵያ በኩል በተደጋጋሚ ድብደባ የተፈጸመባቸው ኢሳያስ የደረሰባቸውን ቁሳዊና ሰብዓዊ ጥፋት ለተባበሩት መንግስታት በክስ መልክ ከማቅረብ የዘለለ የወሰዱት ርምጃ የለም። የወትሮው ኢሳያስ እንኳን ተነክተው እንዲያውም ጸብ የሚሸታቸው እንደነበሩ የሚጠቁሙት ክፍሎች አስመራ ከተማ ጡረታ የወጡ የቀድሞ አዛውንት ታጋዮችን ከማስታጠቅ የዘለለ እርምጃ አለመውሰዳቸው የፍርሃታቸውን መጠን አመላካች መሆኑን ያሳያሉ። ተጨማሪ የማጠናከሪያ ማስረጃም ያቀርባሉ።
“ስለሆነም” ይላሉ የሚያውቁትን የግምገማ ማጠቃለያ ሲያቀርቡ “ኢሳያስ ከኢትዮጵያ ወገን የሚቀርብላቸውን የሰላም ድርድር አልቀበልም የሚሉበት ምክንያት የላቸውም። ሊሉም አይችሉም። ለድርድር ሲቀርቡም በቀድሞው ኃይል፣ ምንጩና መነሻው ኢትዮጵያ ላይ ማንጸባረቅ በሚፈልጉት ግራ የሚያጋባ የበላይነት ስሜት ሊሆን አይችልም” በማለት ኢሳያስ ወደ ድርድር የሚመጡበትን አስገዳጅ ሁኔታዎች ያስቀምጣሉ።
ኢሳያስ ለድርድር ከተቀመጡ የመጀመሪያው ጥያቄ ተቃዋሚዎችን ወደ ሰላም እንዲመጡ ማስገደድ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስትም በተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳል። ቀጣዩ የባድመ ጉዳይ አቶ በረከት ስምዖን እንዳሉት “የኢትዮጵያ አይደለም” ይባልና በድንበር ማካለሉ መጠነኛ የሞራል መጠበቂያ ሽግሽግ ተደርጎ ይጠናቀቃል የሚል መደምደሚያ ይሰጣሉ።
“በየቀኑ በርካታ ወታደሮች የሚኮበልሉባቸው ኢሳያስ የሚቀርቧቸውን የተቃዋሚ ቁልፍ ሰዎች በማደራደር ስም ኢህአዴግ እጅ እንዲወድቁ ያደርጓቸዋል። ይህ የማይቀር እውነት ነው። የውጪ አገራትም ድጋፍ አለበት” የሚሉት ክፍሎች “ከዚህ የተለየ ጉዳይና ድርድር ካለ ኦህዴድ እንዲፈርስ ማድረግ ነው። ይህንን ማድረግ ደግሞ እብደት ነው። ይደረግ ከተባለም ስርዓቱ ያከትምለታል” ባይ ናቸው። እነዚሁ ክፍሎች አቶ በረከት በቅርቡ ስለኤርትራ የተናገሩትንና ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ አስመራ ድረስ ለድርደር እንደሚሄዱ መናገራቸውን የቅርቡ ጊዜ ማጣቀሻ አድርገው ያሳያሉ።
ኢህአዴግ ከወትሮው በተለየ የእርቅና የሰላም ድርድር ላይ እየሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር አስመራ ሄደውም ቢሆን ለመደራደር ቢጠየቁ ፈቃደኛነታቸውን ያለ አንዳች ማቅማማት እንደሚያሳዩ መግለጻቸው ኢሳያስን ወደ ድርደር ለመጋበዝና ለማማለል እንደሆነ ተደርጎ ተወስዷል።
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከአልጃዚራ እንግሊዝኛ ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሲናገሩ “አስመራ ሄደህ ከኢሳያስ ጋር ተቀምጠህ ትደራደራለህ? ብለሽ ብትጠይቂኝ” አሉና ራሳቸውን ጠየቁ። “አዎ! ነው መልሴ” በማለት ለራሳቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጡ። አስከትለውም “በርግጥም አደርገዋለሁ” በማለት ማረጋገጫ ሰጡ።
ጠያቂዋ የቀድሞው መሪ አቶ መለስ ሊያደርጉት እንደማይችሉ ስትጠቁም፣ አቶ መለስ ከሃምሳ ጊዜ በላይ አስመራ ሄደው ለመደራደር ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጥያቄ ማቅረባቸውን በማስታወስ ምላሽ የሰነዘሩት አቶ ሃይለማርያም፣ ድህነትን መዋጋት ትልቁ ጉዳይ እንደሆነ በመግለጽ “ሁለታችን ብንስማማ እጅግ ታላቅ ውጤት ይኖረው ነበር” ያሉት።
የጎልጉል ምንጮች እንደሚሉት ደቡብ ሱዳን በውጤት አጠናቅቀዋለሁ የምትለው የሁለቱ ድርጅቶች (ህወሓትና ሻዕቢያ) የሰላም ድርድር ተግባራዊ ይሁንም አይሁን፣ በሌላ አሁን ይፋ ሊያደርጉት በማይፈልጉት አካል አማካይነት የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይሆናል።
የኦህዴድ ሰዎች ያቀረቡትን ማብራሪያ የሚያጣጥሉ ክፍሎች በበኩላቸው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከቀድሞው በተሻለ ዲፕሎማሲያቸውን አስተካክለዋል። ይህም ባይሆን ህወሃት ኢሳያስን ተጭኖና ተከራክሮ ያሸነፈበት አንድም ጊዜ ስለሌለ ወደፊትም የተለየ ነገር አይመጣም ይላሉ።
በስልጣን ተዋጽኦና በሃላፊዎች ስብጠር ችግር ገብቶታል የሚባለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የመዋጋት ፍላጎቱ እንደቀድሞው እንዳልሆነ የሚያመለክቱት እነዚህ ክፍሎች “ጦሩ አስመራ ለመግባት እየተንደረደረ በነበረበት ሰዓት በተፈጸመበት ክህደት አዝኗል። እንደ ዘመቻ ጸሃይ ግባት በወኔና በእልህ የመዋጋት ፍላጎት የለም። ኢህአዴግም ይህንን ስለሚረዳ ጦርነትን በፍጹም አይሞክርም። ችግር ከተፈጠረ ቀዳሚው ተጎጂ ህወሃት ነው። ህወሃት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ደግሞ ህልውናን አስከማጣት ያደርሰዋል። በዚሁ ፍርሃቻ የሰላም ስምምነት ቢኖር እንኳ ኢህአዴግ እንደለመደው ብዙ በመስጠት ጥቂት ተቀብሎ ሊስማማ ይችል እንደሆነ እንጂ አያተርፍም” የሚል መከራከሪያ አላቸው።
ኢሳያስ በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን እንዲሁም በቅርቡ ካናዳ ጥገኝነት ጠየቁ ሲባሉ በቅርብ የሚያውቋቸው “የኢሳያስ ልጅ አይከዱም” በማለት የተከራከሩላቸው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አሊ አብዶ አሰብን አስመልከቶ “የኢትዮጵያ ህዝብ በአሰብ ወደብ የመጠቀም ሙሉ መብት አለው” ማለታቸው ውስጥ ውስጡን ለሚካሄደው ስምምነት አመላካች እንደሆነ ገለልተኛ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
ሌላው የሚያነሱት መከራከሪያ አቶ መለስ ያደረጁዋቸውና ኢትዮጵያ ውስጥ የስደት መንግስት አቋቁመው የኢሳያስን ውድቀት የሚጠባበቁት የኤርትራ ተቃዋሚዎችን አደረጃጀት ነው።ተቃዋሚዎቹ በውስጣቸው ያቀፏቸው ብሄርን መሰረት ያደረጉ ፓርቲዎች ወደ ስልጣን ከመጡ በኤርትራ ሊከሰት የሚችለው አደጋ ለሁሉም አገር ወዳድ የኤርትራ ዜጎች ስውር አይደለም።በዚህም ሳቢያ ኢሳያስ ከለቀቁ ቀጣይዋ ኤርትራ የብሄርና የጎሳ ፖለቲካ የሚፈለፈልባት ልትሆን ትችላለች የሚለው ስጋት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ኤርትራውያን አገራቸውን መስዋዕትነት ከፍለው ለመከላከል ዋናው ምክንያታቸው ነው። በዚህም ምክንያት ግጭት ከተነሳ በአጭር ጊዜ የሚፈጸም አድርጎ መታየቱን ይቃወማሉ። ኢህአዴግም ይህንን እንደሚረዳ ያስገነዝባሉ።
ህወሓት/ኢህአዴግ የሚፈልገውና የሚያሳስበው ነገር ካለ በሱዳን እንዳደረገው መሬት በመስጠት ጭምር እንደሚደራደር ያመለከቱት አስተያየት ሰጪዎች “በሰላማዊ መንገድ የኤርትራና የኢትዮጵያ ጉዳይ በዘንድሮው ዓመት አንድ ደረጃ ላይ የሚደርስ ይመስለናል” በማለት ቅድመ ግምታቸውን ያኖራሉ። ኤርትራ ላይ የከተሙ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎች ድርድርም ሆነ ማግባባት ካለ ከወዲሁ በመጠንቀቅ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ይመክራሉ።
የሃይለማርያም ደሳለኝን የዕርቅ ጅማሮ ጥቅምና ጉዳት ከሌላ አንጻር የሚያብራሩ ደግሞ አቶ መለስ በአገር መክዳት ከተወነጀሉበት የባድመ ጦርነት በኋላ ሌላ የትግራይ ባለሥልጣን ወደ ኤርትራ ሄዶ ከኢሳያስ ጋር እጅ ቢጨባበጥ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ የሚፈጥረው ስሜት ጀምሮ በህወሓት ውስጥ ሌላ ህንፍሽፍሽ (ክፍፍል) ከማስነሳቱና ከሻዕቢያም በኩል የኤርትራን ስነልቦና ከመጠበቅ አኳያ አቶ ሃይለማርያም ጥሩ ፊት ሊኖራቸው ስለሚችል የጠ/ሚ/ሩ ሥልጣን በህወሓት ከመወሰዱ በፊት ወቅቱ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል ይላሉ፡፡
ከሰባ ሺህ በላይ ወገኖችን ሕይወት የቀጠፈው የባድመ ጦርነት መንስዔ የሆነው የድንበር ውዝግብ እስካሁን እልባት አላገኘም። የተባበሩት መንግስታት የድንበር ኮሚሽን ባድመን ለኤርትራ እንድትሆን አድርጎ ተቀብሏል፤ ሄግ ያስቻለውን ችሎት የፈረደውን ውሳኔ ኢትዮጵያ ተግባራዊ በማድረግ ባድመን ለቃ እንድትወጣ ብትታዘዘም አሁን ድረስ መሬቱን የምትቆጣጠረዋ ኢትዮጵያ መሆኗ ይታወሳል። ከዚህ ዘግናኝና ታላቅ ሰብዓዊ ቀውስ ካስከተለ ጦርነት በኋላ ከኢሳያስ ጋር ለመነጋገር ሃይለማርያም ኤርትራ ከሄዱ ከጦርነቱ በኋላ ኤርትራን የሚረግጡ የመጀመሪያ መሪ ይሆናሉ።
በሌላ ተመሳሳይ ዜና ኦነግን ለማስማማትና ወደ ድርድር ለማቅረብ ፕ/ር ኤፍሬም ኖርዌይ መታየታቸውን ተከትሎ ኢህአፓ ለኖርዌይ መንግስት የተቃውሞ ደብዳቤ መላኩን አስታውቋል። ድርጅቱ በደብዳቤው የኖርዌይ መንግስት እንዲህ ካለው ተቃዋሚዎችን የሚጎዳ እንቅስቃሴ ከመፈጸም እንዲትቆጠብ በላከው የተማጽኖና የማሳሰቢያ ደብዳቤ አምባገነኖችን በመርዳት የሚደረገው ድጋፍ ሊቆምና ለዴሞክራሲ መበልጸግ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አመልክቷል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
በለው ! says
ገብረማርያም ኃይለማርያምን አጠመቀው…ኃይለማርያም ገብረማርያምን አጠለቀው…ገብረሚካኤል ኃይለማርያምን አስፈራራው! እንዲህም አለው በመልስ ‘ራዕይ’ ምዕራፍ ሁለት ላይ…” ሽሽታችሁ ሁሉ ወደ ሰሜን ይሁን የተጣላችሁትን ታረቁ የሠረቃችሁትን እንድታሸሹ…እውነት እውነት እላችኋለሁ እኔስ ዘር ግንዴ ከዚያው አደለምን? እነሱስ ባይኖሩ እኔ እና እናንተ በሥልጣን እንተካካ ነበርን? ትግራይስ ነፃ ትሆን ነበር?
ኃይለመለስም አለ …”ክቡር አባቴ ሆይ ላለፉት ሃያ(፳) ዓመት ሃምሳ(፶) ጊዜ በሚስጥር ፕሬዜዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እግር ላይ እየወደቁ ለእርቅ አልቅሰው መለመንዎን ነግረውኛል አይቻለሁም፡ በዚሁ ራዕይዎ እና በነደፉልን ዕቅድ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን ፈጥረውናል ለጋሲነትዎም በዓለም ገኗል። እኔም ይህንኑ ለጋሲ ለማስቀጠል ምንም እንኳ ከንባታ ብለው እንደማያሳፍሩኝ በማመን ለሃምሳ(፶፩)ኛ ጊዜ የቸርች አባላትን አስከትዬ እቤታቸው ድረስ ሄጄ እግራቸው ላይ ተደፍቼ እንደምለምናቸው በአልጀዚራ ቴሌቪዥን ላይ ለዓለም ሁሉ ቃል ገብቻለሁ።” እርስዎም ያለውን ሁኔታ ተከታተሉ ምሩን እረስዎ ከተሰወሩ ጅምሮ አምርረው ላለቀሱ ሁሉ የሰጡኝን ሥልጣን በመተሳሰብ እና በመፈቃቀድ ላይ በተመሠረተ የሥልጣን መጋራት ለሁሉም ሰጥቻለሁ ብቻዬን እነደእረስዎ አልጠቀለልኩም ምነው ዛሬ ቀና ባሉና አድናቆትዎን በሰማሁ ሁሌም በመኝታ ቤቴ ከባለቤቴ ጎን ያድራሉ ለእርስዎ መቶ ብር ፎቶዎ መታተም አደለም ካገኘሁት ጋር ሁሉ እላተማለሁ አክባሪ ታዛዥ አገልጋይ የራዕይዎ መሰኪያ ሃይለመለስ ነኝ።
አለበለዚያ ከፍተኛውን ቁጥርና ሥልጣን ያለው ፎጋሪው አማራ በብአድን እና በወያኔ ውስጥ ሠርጎ የገባው የሻቢያ ዲቃላ የባሪያ ፈንጋይ ልምድ ያለው በመሆኑ ለኀይለመለስም ሆነ ለሀገሪቱም አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሷል። በለው!
dawit says
አቶ ታደለ ይመር የሚባሉት ሰው አማራውን በመወከል ኢሳያስ ደጅ ወድቀው “አማራው ላጠፋው ጥፋት ይቅርታ ይደረግልን”በማለት ኢሳያስ ደጅ ካፖርት ለብሰው መንከባለላቸውን የሰማሁት ትዝ አለኝ።የአሰሪዎች ፌዴሬሽን ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ታደለ በማህበር ደረጃ ያላገለገሉት በሴቶች ማህበር ብቻ ነው።እሱንም መሆን ያልቻሉት ከስራ ብዛት እንጂ ቀሚስ አጥልቀውም ቢሆን የሴቶችን ማህበር ለመምራት ሞራላቸው ትልቅ ነው።ታሪክን ለማስታወስ አህል ነው።