ከኤርትራ ሰሞኑን የሚወጡ መረጃዎች ከጉዳዩ ባለቤቶች ማረጋገጫ ወይም ማስተባበያ ባይቀርብበትም ከኤርትራ ጋር በተያያዘ የተለያዩ አቋምና ተስፋ ባላቸው ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኗል። አንዳንድ በብሎግ ሂሳብ የሚጫወቱ የኤርትራ መንግሥት አገልጋዮች ለጉዳዩ ጆሮ ዳባ ቢሉም በዋና በተቃዋሚነት የሚታወቁት የኢሳያስ ባላንጣዎች ለወሬዎቹ ሽፋን በመስጠት ግንባር ቀደም ሆነዋል።
የ1997 ምርጫን ተከትሎ በተፈጠረው አለመረጋጋት “ህወሃት ሰራዊቴን በመያዝ ጓዜን ጠቅልዬ ወደ ትግራይ ምድር እገባለሁ” ማለቱን አስነብቦ የነበረው ኢንዲያን ኦሽን ኒውስ ሌተር ሰሞኑን የህወሃት ሊቀመንበርን ጠቅሶ ኤርትራ ላይ ጦርነት የማወጅ ፍላጎት እንዳለ ይፋ አድርጓል። ኢንዲያን ኦሽን ከውስጥ አዋቂዎች አገኘሁ በማለት ሌላ ያሰነበበው ዜና የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዶ ካናዳ ጥገኝነት መጠየቃቸውን ነው። ይህ ብቻ አይደለም ኢትዮጵያን ሪቪው ኢሳያስ ከስልጣናቸው በፍቃዳቸው ለመውረድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን በተመሳሳይ “ታማኝ” ያላቸው ምንጮቹ እንደነገሩት ጠቅሶ ከነምክንያቱ ዜና አሰራጭቷል።
ትግራይ ኦን ላይንን ጨምሮ የተለያዩ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች ይህንኑ ዜና በታላቅ ብስራት “የአሊ አብዶ መክዳት የኢሳያስ የመጨረሻ ውድቀት መጀመሪያ” ሲሉ ዜናውን አሙቀውታል። ለአንድ ሳምንት የሞቀውን ጉዳይ አስመልክቶ ይህ ሪፖርት እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ከጉዳዩ ባለቤት ማረጋገጫም ሆነ ማስተባባያ አልቀረበም።
የፕሬዚዳንት ኢሳያስ “ልጅ” ይሉዋቸዋል። ከበረሃ ጀምሮ የኢሳያስ የራዲዮ ኦፕሬተር ነበሩ። ከሌሎች በተለየ ሁኔታ መኖሪያ ቤታቸውን በኢሳያስ ምስል ዙሪያውን በማሸብረቅ ይታወቃሉ። ከፕሬዚዳንቱ ጋር ያላቸው ግንኙነት እጅግ የጠበቀ በመሆኑ ቁልፍ የሻዕቢያ መረጃ እጃቸው ላይ እንደሆነ ይነገራል። እኚህ ሰው አቶ አሊ አብዶ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር ናቸው።
ከኖቬምበር 17/2012 ጀምሮ በስፋት ስለሚወራው የአቶ አሊ አገራቸውን፣ በተለይም “ያሳደጓቸውን” ኢሳያስን መክዳት በስደት አገራቸውን ለቀው ለሚኖሩ የኤርትራ ተወላጆች አስገራሚ ሆኗል። ስለ ጉዳዩ ሲጠየቁ “አናምንም” የሚል የመገረም አስተያየት ነው የሚሰነዝሩት። በፖለቲካ ውሳኔ ውስጥ ስለሚኖረው የኃይል ሚዛን አይቶ መገልበጥ ወይም በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ፊትን ማዞርና ከዳተኛ የመሆን አማራጭ ሰፊ ቢሆንም ለኤርትራ ተወላጆች ግን ይህ የፖለቲካ ቁማር ከቶውንም ሊዋጥላቸው አልቻለም።
ምንም ተባለ ምን አቶ አሊ ከዱ ማለት የኢሳያስ የምስጢር ውሳኔዎችና ትዕዛዞች፣ የተወሰዱ ርምጃዎች፣ የስለላ ሚስጥሮች፣ ከዘይት ባለሃብቶች ጋር በምስጢር ስለተደረጉ ድርድሮች፣ ኤርትራ ስለምትታማበት የሶማሊያና የኢራን ጉዳይ፣ በተለይም በህይወት ይኑሩ ይገደሉ ተለይቶ ስለማይታወቁት እስረኞችና ስለራሳቸው ስለ አቶ ኢሳያስ ህይወት በርካታ ምስጢሮች ይፋ ይወጣሉ የሚል ስጋት እንደሚኖር አብዛኞች ይስማማሉ። ይህ ሊሆን እንደሚችል ቢስማሙም ግን የሚወራውንና ኢሳያስም ሆኑ አቶ አሊ ጆሮ ዳባ ስላሉት ዜና እውነትነት አምነው ለመቀበል ይቸገራሉ።
በስዊድን የሚኖሩት የኤርትራ ስደተኞች “አሊ … የኢሳያስ ልጅ! አይከዳም፤ አናምንም” በማለት መገረማቸውን ከጥርጣሬ ጋር ይገልጻሉ። ሲሉ ይደመድማሉ። ላለማመናቸው የተለየ ምክንያት በማቅረብ ግን አይከራከሩም። በስዊትዘርላንድና በስዊድን የጎልጉል ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኤርትራ ተወላጆች በጉዳዩ ላይ ሰፊ መከራከሪያ ባያቀርቡም አንድ አዲስ መረጃ ግን ያመላክታሉ።
የከረን ተወላጅ የሆኑት አቶ አብዶ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል በሚል የታሰሩት አስራ አምስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲፈቱ ሽምግልና ሞክረው ነበር። የኢሳያስ ቀኝ እጅ የሆኑትን ልጃቸውን በማግባባት ሽምግልና የሞከሩት አቶ አብዶ ብዙም ሳይቆይ “አክራሪ” በሚል ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ መታሰራቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ይናገራሉ። አስገራሚው ጉዳይ አቶ አሊ አባታቸው ሲታሰሩ ሄደው እንኳ አልጠየቋቸውም። በዚህ ተግባራቸው ቅጠል ተበጥሶባቸዋል። ከንፈር ተመጦባቸዋል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ለስርዓቱ ታማኝ በመሆናቸው እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም። የአቶ አሊ አባት ይፈቱ፣ ይታሰሩ አለያም ስለሚገኙበት ሁኔታ ምንም እንደማያውቁ በስደት ያሉት አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ በዚሁ መነሻ አባቱ አስር ቤት ሲጣል ዝም ያለ ሰው ኢሳያስን ሊከዳ የሚችልበት፣ ወይም የኢሳያስን አስተዳደርና ኢሳያስን በግላቸው ሊከዱ የሚችሉበት ምንም ምክንያት የለም ባይ ናቸው።
በህወሃት በኩል ከኤርትራ ጋር ያለው ችግር መቋጨት አለበት የሚል ክርክር በተነሳበት፣ አቶ መለስ ህይወታቸው ካለፈ በኋላ በማንኛውም ሰዓት ውጊያ ሊከፈትብኝ ይችላል በሚል ስጋት የገባው ሻዕቢያ አዛውንት የቀድሞ ታጋዮችን “ብረት አንሱ” ሲል ትዕዛዝ ባስተላፈበት ወቅት፣ ላይ አቶ አሊ ኮበለሉ መባላቸው ከሚኒስትሩ አቅም በላይ ዜናውን “ወቅታዊ ዜና” እንዳደረገው የሚናገሩ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በሌላ ጉዳይ አቶ አሊ በቅርቡ የኤርትራን ህዝብና መንግስት ይቅርታ መጠየቃቸውን ይጠቅሳሉ።
ከጥቂት ወራት በፊት ከአሜሪካ ሬዲዮ የአማርኛው ክፍል ጋዜጠኛ ሄኖክ ሰማእግዜር ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት አቶ አሊ አብዶ አሰብ ወደብን አስመልክቶ “የአሰብ ወደብ ለጥቅማችን ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ጎረቤት፣ እንደ ወንድም ህዝብ፣ ወደቡን የመጠቀም መብቱ የማይፋቅ መብቱ ነው። ምክንያቱም ሞራላዊ ግዴታችን ነው። ተባብረን ነው የኃይለሥላሴንና የመንግሥቱን ስርዓት ያስወገድነው። ከሁሉም ህዝቦች በላይ አሰብን መጠቀም የሚችለው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው” ብለው መናገራቸው ከመንግሥታቸውና ከህዝባቸው ቅሬታ አስነስቶባቸው ነበር። ዳንስ ቤት በምትመስለዋ የኤርትራ ቲቪ ERI-TV ስቱዲዮ ውስጥ ሆነው በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ “የኢትዮጵያ ህዝብ ለመጠቀም መብቱ ነው ያልኩት በነጻ ሳይሆን በገንዘብ ለማለት ነው። የአገላለጽ ችግር ነው” ሲሉ ንግግራቸውን ለወገኖቻቸው በሚመች መልኩ እንዳቃኑት ዘወትር የኤርትራን ጉዳይ በማንሳት በፓልቶክ የሚወያዩት የኢሳያስ ተቃዋሚዎች አመልክተዋል። ይህን ጉዳይ ያነሱት አስተያየት ሰጪዎች ከዚህ መግለጫ በኋላ አቶ አሊ “በአፍ ወለምታ” መከሰሳቸው ቅሬታ ፈጥሮባቸው ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አቶ አሊ የታዩበትን ገጽታ የሚያነሱ አሉ። በየሳምንቱ ማክሰኞ ኢሳያስ የሚሰበስቡት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውይይት አካል እንደሆነ በተነገረለት መድረክ ላይ ከሌሎች በተለየ መልኩ ጸጉራቸውን አንፈርፍረው /ፍሪዝ አድርገው/፣ ፕሮቶኮሉን ያልጠበቀ ልብስ ለብሰው የታዩት አቶ አሊ ለህዝብ እይታ የበቁበት አግባብ “ፍንዳታው” ሚኒስትር በሚል አስወርፏቸዋል። አሁን ከመክዳታቸው ወሬ ጋርም ያያዙታል።
“ነገ ወይም ከነገ ወዲያ ሻዕቢያ ወሬውን ሁሉ ውሃ ይደፋበታል” በማለት ለጎልጉል አስተያየቱን የሰጠ እንዳለው “እኔ ካናዳ ነዋሪ ነኝ። አገሬን የሚመለከት መረጃ አያመልጠኝም። አቶ አሊ ካናዳ ቢኖር እሰማ ነበር” በማለት ሚኒስትሩ አገራቸው ስለመኖራቸው ይከራከራል። ለማጣራት ባደረገው ሙከራ አቶ አሊ አስመራ እንደሆኑ በርግጠኛነት ይናገራል። አያይዞም ኢሳያስ ሞቱ ሲባል ቆይቶ እንደተደረገው ሁሉ ወሬውን ሁሉ በዜሮ የሚያጣፋ ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት እንዳለ አስታውቋል።
ERENA/ኢሬና ራዲዮ ጁላይ 15/2009 ከኤርትራ በተሰደዱ ጋዜጠኞች የተቋቋመና በድንበር የለሽ ዘጋቢዎች (Reporters without Borders) የሚታገዝ፣ በኤርትራ ያለውን የፕሬስ ነፃነት ለማመጣጠን የሚሰራ ሚዲያ ነው። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ህይወታቸው ማለፉንና የኤርትራ ጀኔራሎች አስቸኳይ ስብሰባ በማካሄድ ስልጣን መከፋፈላቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ሲኤንኤን ጨምሮ ኢሳያስ ሞተዋል፣ በጠና ታመዋል፣ ደክመዋል፣ የጉበት ለውጥ አድርገው ማገገም አልቻሉም፣ … በሚል በስፋት ላሰራጩት ዜና ኢሳያስ መታመማቸውን በሚያሳብቀው ገጽታቸው “የባርካን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ለአስራ አራት ሰዓት ያለ እርፍት በተሽከርካሪ ስጎበኝ ቆይቼ ስመለስ በጣም ደክሞኝ ስለ ነበር ረጅም እንቅልፍ ተኛሁ፤ ስነቃ ሰማሁ” በማለት ነበር ነገሩን አመናምነው ለማሳየት የሞከሩት። “አልዘገዩም” ተብለው ለተጠየቁት አስቂኝ መልስ ሰንዝረው ነበር።
እንቅልፉ ሳይለቃቸው የፕሬስ ፀሃፊያቸው ከሰጠቻቸው ወረቀቶች ላይ ስለሳቸው ሲወራ የነበረውን መመልከት እንደቻሉ ተናገሩ። “ሞባይል (ስልክ) የለኝም፤ ኢንተርኔትም አልጠቀምም” የሚሉት አቶ ኢሳያስ የተወራውን ሁሉ እንደንፋስ እንደሚቆጥሩት አስምረውበት ነበር። ውሸት በተወራ ቁጥር ቴሌቪዥን ላይ በመውጣት ማስተባበያ መስጠት እንደማይቻል በመጠቆም የተወራባቸውን ክፉ ወሬ ያመከኑት ፕሬዚዳንቱ “እኛ ተመስገን ብለን አስራ ሁለት ሰዓት ስንተኛ፣ ውሸታሞቹ ሃያ ሶስት ሰዓት ከሃምሳ ዘጠኝ ደቂቃ እንቅልፍ የላቸውም” ሲሉ በተወራባቸው ወሬ ለማላገጥ ሞክረው ነበር።
“አሁን” አሉ አቶ ኢሳያስ “አሁን ውሸቱ ሁሉ አርጅቷል። አልቋል” የኤርትራ ህዝብም ሆነ በውጪ አገር ያሉት ተረጋግተውና የሚሰሙትን ሁሉ እንደማስታወቂያ ባለመቀበል ህይወታቸውን እንዲመሩ ጥሪ አቀረቡ። እስካሁን ለምን ዘገዩ በሚል ለተጠየቁት ምላሽ ሲሰጡ ውሸታሞች የሚሉዋቸው ራሳቸውን ውሸታቸውን እንዲያስተካክሉ እድል ለመስጠት በማሰብ መሆኑን አመላክተዋል። ከወሬው ጋር በተያያዘ ሲአይኤን ወንጅለውም ነበር።
ኢሳያስ ይህን ይበሉ እንጂ የጤናቸው ሁኔታ አጅግም እንደሆነ ይሰማል። ለዚሁም ይመስላል ኢሳያስ ከዓመት በፊት በስታዲየም ባደረጉት ንግግር ከሁለት ዓመት በኋላ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንደሚካሄድና ህዝብ በመረጠው እንደሚተዳደር እርሳቸውም ተራ አስተማሪ ሆነው መኖር እንደሚችሉ ይፋ አደርገው ነበር። የዚሁ ውሳኔ አካል ይሁን የሌላ ባይታወቅም ኢትዮጵያን ሪቪው ታማኝ ምንጮቹን በመጠቀስ ኢሳያስ ራሳቸውን ከስልጣን ለማግለል መወሰናቸውን አስነብቧል። በዘገባው ኢሳያስ ስልጣን ለተተኪ በማስተላላፍ በኤርትራ ልክ እንደ ማንዴላና ጆርጅ ዋሺንግተን ስማቸው የሚወደስ ግንባር ሰው የመሆን እቅድ እንዳላቸው አውስቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ህወሃት ከኤርትራ ጋር ያለውን መቋጫ ያጣ ውዝግብ “ሊቋጭ ይገባል” የሚል አቋም መያዙ እየተሰማ ነው። ቀደም ሲል አቶ መለስ የሚሟገቱለት ሻዕቢያ መደምሰስና መተንፈስ አለበት የሚል አቋም የያዙት እንደሚበዙም ታውቋል። በተለይም “ትግራይን የኢንዱስትሪ ማዕከል እናደርጋለን” የሚለው መፈክር ሻዕቢያ በህይወት እያለ ተግባራዊ እንደማይሆን የሚስማሙት የህወሃት አመራሮች በስራ አስፈጻሚ ደረጃ ይህንን ጉዳይ አንስተው መነጋገራቸውን ኢንዲያን ኦሽን ኒውስሌተር ይፋ አድርጓል።
ኢህአዴግ በሥራ አስፈጻሚና በምክር ቤት ደረጃ ቀደም ሲል ባካሄደው ግምገማም ሆነ አሁን ድረስ እንደሚያምነው የኢትዮጵያ ህዝብ ሻዕቢያን ለመምታት ምንጊዜም ለሚቀርብለት ጥሪ ምላሹ በአዎንታ የሚደመደም ነው። ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ በኩል ለሰላም ድርድር የተቀመጠውን ባለ አምስት ነጥብ የመደራደሪያ ሃሳብ በመቀበል ለመሸማገል ፍላጎት መኖሩ ነው በይፋ በየመድረኩ የሚነገረው። ከዚህም በተጨማሪ ደቡብ ሱዳን ሁለቱን አገሮች ለማስማማት ተስፋ ማግኘቷን ማስታወቋ አይዘነጋም።
ስለ ሰላም የሚዘምረው የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ኤርትራ፣ አንዳቸው የሌላውን ተቃዋሚዎች በመርዳትና በማደራጀት ሥራ መጠመዳቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።ሰሞኑን ኢሳት ያነጋገራቸው የትህዴን ሊቀመንበር አቶ ሞላ አስገዶም ከኤርትራ በተሰጣቸው ነጻ ምድር ላይ በመንደርደር ተደጋጋሚ ጥቃት ማድረሳቸውን ይፋ አድርገዋል። የኢትዮጵያዊ አብዮታዊ አስተሳሰብ (Ethiopian Revolutionary Minds) የተሰኘው የንቅናቄ አውታር አሰራጭቶታል በተባለው ቪዲዮ በምስራቅ ኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ሃይሎችን በመሰብሰብ ንግግር ያደረጉት ባለስልጣን ሻዕቢያ የሚያደራጃቸው ሃይሎች ጥቃት እየሰነዘሩ መሆኑንን ይፋ አድርገዋል። የሰራዊት መክዳት እንዳሳሰባቸው ያስታወቁት ስማቸውና ሃላፊነታቸው ያልተጠቀሰ የህወሃት ሰው በተሰባበረ አማርኛ ኤርትራን ሲያወግዙና የተሰበሰቡትን የፌደራል አባላት ሲቀሰቅሱ “በሁመራ በኩል ያለው አደገኛ ነው” ሲሉ ተደምጧል።
እንደ አገር መተዳደር ከጀመረች አንስቶ ምርጫና ህገመንግስት የማያውቃት ኤርትራ በቅርቡ የተበላሸባትን ዲፕሎማሲ ለማስተካከል ደፋ ቀና እያለች ባለበትና አዲስ ህገ መንግስት እያረቀቀች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የወታደሩ ደመወዝ ጥያቄ፣ ለዳግም ዘመቻ የተጠሩ ነበር አዛውንት ታጋዮች፣ የሥራ አጥነት፣ ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ አፈናና ጭቆና የሰለቻቸው ዜጎቿ በየቀኑ በስደት የሚለዩዋት አገር ሆናለች። የስደት ማመልከቻቸውም ይህንኑ በማገናዘብ አፋጣኝ መልስ በማግኘት ግንባር ቀደም ባለሪከርድ ሆነዋል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
yrga negash says
በአጭሩ
ሠላም ይሻላል