
ትላንት ማክሰኞ መስከረም 26 የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ስብሰባ ሲቀመጥ 2 ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይኸኛው ለ4ኛ ጊዜ (በዝግ እና በክፍት) ነው።
ይኸኛው ስብሰባው ለምን ተጠራ?
– ኢትዮጵያ 7 የተመድ ሰራተኞችን ከሀገር በማስወጣቷ።
– የሰሜን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ሁኔታ ላይ ለመወያየት።
ስብሰባው እንዲካሄድ የጠየቁት፦ አሜሪካ፣ ዩኬ፣ ኖርዌይ፣ ኢስቶኒያ፣ ፈረንሳይ እና አየርላንድ ናቸው።
በስብሰባው ላይ የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የተመድ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ንግግር አድርገዋል። የምክር ቤቱ አባል ሀገራት የተለያዩ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል።
ሙሉ ውይይቱን (ክፍት ውይይት ስለሆነ) በተመድ የዩትዩብ ቻናል መከታተል እንደምትችሉ እየጠቆምን የተነሱ ዋና ሃሳቦችን ግን በአጭሩ እንዳስሳለን።
አንቶኒዮ ጉተሬዝ ምን አሉ?
እየተስፋፋ የመጣውን የሰብዓዊ ጉዳይ ችግር ካለፈው ነሃሴ አንስቶ ሲያሳስቡ መቆየታቸውን ነገር ግን ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል።
7 ሚሊዮን ሰው በትግራይ፣ አማራ እና አፋር የምግብ እና የተለያዩ አፋጣኝ ድጋፎች እንደሚፈልግ ተናግረው 400 ሺህ ሰዎች ረሃብ በሚመስል ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ላለው ችግር በቅርቡ መፍትሄ ካልተፈለገ ሁኔታው ሶማሊያ የዛሬ 10 ዓመት ገጥሟት የነበረውን አይነት 200 ሺህ ሰው ያለቀበትን ረሃብ ሁኔታ ወደሚመስል አደጋ ሊለወጥ ይችላል ሲሉ አበክረው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ተፈላጊነት የሌላቸው ሲል የወሰነባቸው እና ከሀገር ያስወጣቸው 7 የተመድ አባላት በአፋጣኝ ወደስራቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ አሳስበዋል።
ሌሎችም አሉ ያሉትን ችግሮች አንስተው በኢትዮጵያ ያሉ ወገኖች በአፋጣኝ ለሰላም እና ለድርድር እንዲቀመጡ ግጭትም በፍጥነት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ንግግር የሰላም መሰረት መሆኑን ተናግረው ሰላም የብልፅግና እና የመረጋጋት መሰረት ነው ብለዋል፤ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ለአካባቢው ህዝብም ጠንክረን እንስራ ሲሉ ተደምጠዋል።
ከሁለት ቀን በፊት የተመሰረተው እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስት ጠንካራዋን ኢትዮጵያ እንደሚመለስ ተስፋ አደርጋለሁ ያሉ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁሉን አካታች ውይይት ለማድረግ የገቡትን ቃልም አደንቃለሁ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ምን አሉ?
አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በሰጡት ማብራሪያ፥ በዓለም አቀፍ ህግ ሀገራት መብቶቻቸውን መጠቀም ይችላሉ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለውሳኔውም ምንም አይነት ማብራሪያ እና ማረጋገጫ የማቅረብ ግዴታ የለበትም ብለዋል።
ሀገራት የተለያዩ የተመድ ሰራተኞችን እና የሀገራት ዲፕሎማቶችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከሀገራቸው ማስወጣታቸውን እናውቃለን፤ ሆኖም ግን ተመድ በእነሱ ላይ ስብሰባ አድርጎ ያውቅ ይሆን? ሲሉ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃውን ስለመውሰዱ ለማንኛውም አካል ማብራሪያ የመስጠት ግዴታ የለበትም ሲሉ ተናግረዋል።
የተመድ ሰራተኞች የገለልተኝነት መርሆችን በጣሰ መልኩ ለህወሓት የሚወግኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የተመድ ሰራተኞች ያልሞቱ ሰዎችን በረሃብ ሞተዋል በሚል የሀሰት መረጃዎችን ማሰራጨት፤ የመገናኛ መሣሪያዎችን ለህወሓት ወገን ማድረስ፤ ህወሃት መቀሌ ሲገባ ከቡድኑ ጋር ደስታቸውን መግለጽ፤ ከሳዑዲ የትግራይ ተወላጆችን ወደ ሦሥተኛ ሀገር በማምጣት ለቡድኑ እንዲዋጉ ስልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ህወሓትን የሚደግፉ ጹሑፎችን ማዘገጀት ላይ ተጠምደው ነበር ብለዋል።
ማን ይገባል፤ ማን ይወጣል ፣ ማን ይቆያል የሚለውን የሀገር መሰረታዊ ሉዐላዊ መብት ነው ብለዋል።
አንቶኒዮ ጉተሬዝ በተጨማሪ ምን አሉ?
ከኢትዮጵያ ጋር የተዋጣ ግንኙነት እንዲኖር ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አሁንም እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
እንደውም ለኢትዮጵያ መንግስት ታደላለህ በሚል ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲወቅሱኝ ቆይተዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ለአምባሳደር ታዬ ባቀረቡት ጥያቄም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እስካሁን ድረስ ለተመድ የገባ ደብዳቤ የለም፤ ከተባረሩት 7 የተመድ ሰራተኞች በአንዱም ላይ ቢሆን አንድም ደብዳቤ ካለ ያቅርቡልኝ፤ የማውቀው ነገር የለም ስለሚባለው ክስ ብለዋል።
የተመድ ባለስጣናት እና ሰራተኞቹን ኢትዮጵያ የማባረር መብት የላትም ሲሉ ተናግረዋል በግልፅ ፤ ግለሰቦቹን በማባረር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህግ ጥሳለች ብለዋል።
ማንኛውም የተመድ አባል ከስነ ምግባር ውጭ ያደረገው ምንም አድራጎት ካለ እንድናውቅ እንፈልጋለን ብለዋል።
አጀንዳችን አንድ ብቻ ነው እሱም “የኢትዮጵያ ህዝብ መከራ እንዲያበቃ እንፈልጋለን” ይህ ነው አጀንዳችን ሲሉ ተናግረዋል።
አምባሳደር ታዬ የሰጡት ምላሽ
ንግግሮች መደረግ ያለባቸው በኢትዮጵያ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መካከል እንዲሆን ጠይቀው አፋጠነው ማስረጃውን ለማቅረብ እንደሚሰሩ ገልፀዋል። እንዲሁም ልቦናዎች ከኛ ጋር በመሆኑ እናደንቃለን ብለዋል።
** አንቶኒዮ ጉተሬዝ በምክር ቤት ውስጥ ንግግር ሲያደርጉ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የተደረጉት 8 ሰራተኞች ናቸው ያሉ ሲሆን ውጭ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ግን 7 እያሉ ነበር ሲጠሩ የነበረው።
የቻይና ተወካይ ምን አሉ?
ተመድ እና የተመድ ሰራተኞች የተቋሙን መርህ ተከትለው ለኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርሱ ይገባል ብለዋል።
ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አካላት ለመድረስ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለኢትዮጵያ መንግስት ሊያቀርቡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች ድጋፎችን ለማድረስ ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ ላለው ስራ ቻይና እውቅና ትሰጣለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ ቅድሚያ በመስጠት ወደ ሀገር ለሚገቡ ሰራተኞች የቪዛ ሂደቶችን ማቅለሉን፣ የፍተሸ ጣያዎች ቁጥርን መቀነሱን እና የሰብአዊ ድጋፍ ሰራተኞች አስፈላጊውን የተግባቦት መሳሪያ እንዲያስገቡ መፍቀዱንም አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ያለውን ችግር ለመቅረፍ እና ድጋፎች እንዲደርሱ ለማድረግ ያለው ብቸኛ አማራጭ ዲፕሎማሲያው መንገድ ብቻ ነውም ብለዋል።
ቻይና አዲስ ለተመሰረተው መንግስት ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጻ፤ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ይህንን እንዲያድርግ ጠይቃለች።
አንዳንድ ሀገራት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ የተናጠል ማዕቀብ ለመጣል ማሰባቸው ዓለም አቀፍ ህግን መጣስ መሆኑን አስታውቃለች።
በመሆኑም አስመራ እና አዲስ አበባ የተጣሉ ማዕቀብ በአስቸኳይ ሊነሳ ይገባል ብላለች።
የሩሲያ ተወካይ ምን አሉ?
የሩሲያ ተወካይ በተናጠል የሚወሰዱ የማዕቀብ እርምጃዎች ችግሩን እንደሚያባብሱ ገልፀው ተቃውመዋል ።
ሀገራቸው ለኢትዮጵያ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል የገለጹ ሲሆን የግጭቱ መፍትሄ ፓን አፍሪካዊ በሆነ መንገድ ይሆን ዘንድ አቋማችን ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተከሰተውን ችግር መፍታት የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን ሩሲያ ታምናለች ብለዋል። አለማቀፉ ማህቀረሰብም ይህንኑ ከግምት ሊያስገባው አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሰት በሚያደርገው የመፍትሄ ተግባራት ውስጥ የአለማቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ከጎኑ ሊሆን ይገባዋል።
ቀውሱን ለማስወገድ ብቸኛው መንገድ የተቀናጀ ትብብር መሆኑን ገልፀዋል።
የአሜሪካ ተወካይ ምን አሉ?
የአሜሪካ ተወካይ (ሊንዳ ቶማስ) የኢትዮጵያ መንግስት 7 የተመድ ሰራኞችን ከሀገር የማስወጣት እርምጃ አሳሳቢ ነው ብለውታል፤ ኢትዮጵያ ይህንን ላደረገችበት ምንያት ምንም አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ አትችልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔውን ሊቀለብስ ይገባልም ሲሉ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
በጦርነቱ ላይ የተካፈሉ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አጠቃላይ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጠይቀዋል።
ይህ የማይሆን ከሆን ግን የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምር ቤት በአፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
የአሜሪካ ተወካይ በምክር ቤቱ ካሰሙት ንግግር ባለፈም ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው በምክር ቤቱ የተናግሩትን ንግግር አጠናክረዋል።
የአሜሪካ ተዋካይ፤ የፀጥታው ምክር ቤት እሳቸው ኃላፊነት የጎደለው/ግዴለሽ ሲሉ የጠሩት የኢትዮጵያን እርምጃ በበጎ አልተቀበለውም ብለዋል።
ስብሰባው የተባረሩት ሰዎች እንዲመለሱ የሚያሳስብ መልዕክት ያለው ስብሰባ ነበር ሲሉም ተደምጠዋል።
ቃል በቃልም፥ የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃ በምክር ቤቱ ላይ በአባል መንግስታት ላይ እንዲሁም በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች አቅርቦት ላይ የተፈፀመ ድፍረት ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ላይ እያደረሱ ያሉት ጉዳት ነው ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያውያን ነው እየገደሉ ያሉት፤ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያውያን እየደፈሩ ያሉት ብለዋል፤ አምባሳደሯ መሪዎችንም ወንጅለው “ህዝቡን ረስተውታል” ሲሉ ገልፀዋል።
ከ3 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተስፋ ሰጪ ሀገር ትሆናለች ብለን ተስፋ አድርገን ነበር የዛሬ ዓመት አካባቢ ግን ለ2 ሳምንት የተጀመረው የህግ ማስከበር እርምጃ ተራዝሞ አሁን ያለበት ደርሷል በማለት የደረሱትን ጉዳቶችን ዘርዝረው ተናግረዋል።
ተጨማሪ፦
ብሪታኒያ ፣ኢስቶኒያ ፣አየርላንድ ፣ ፈረንሳይ ፣ ኖርዌይ ኢትዮጵያ የተመድ ሰራተኞችን ማባረር አልነበረባትም ብለዋል።
ፈረንሳይ ጠ/ሚ ዐቢይ ሁሉን አካታች ውይይት ለማስጀመር ለወሰዱት ኃላፊነት ድጋፍ አለኝ ብላለች። (ቲክቫህ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply