የፖሊስ ምርመራ ቡድን ፍርድ ቤቱ በሰጠው የምርመራ ጊዜ ያገኘውን የምርመራ ሥራ ለፍርድ ቤቱ አብራርቶ ለቀሪ የምርመራ ሥራዎችም የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።
በምርመራ ቡድኑ አፈፃፀም እና ቀጣይ ጥያቄ ዙሪያ የተጠርጣሪ ጠበቆች እና የምርመራ ቡድኑ ያደረጉትን ክርክር የመረመረው ችሎቱ፣ የፖሊስን የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ጥያቄ አልተቀልኩም ብሏል።
ጠበቆችም አቶ እስክንድር ነጋ የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅ የጠየቁ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል።
ምክንያቱ ደግሞ መርማሪ ቡድኑ አቶ እስክንድር የጠረጠረበት ወንጀል ሞት ያስከተለ በመሆኑ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ከ15 ዓመት በላይ ሊያስቀጣቸው ስለሚችል ነው ብሏል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአቶ እስክንድር ላይ የቀዳሚ ምርመራ ፋይል እንዲከፈት የወሰንኩ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ይስጠኝ በማለት አመልክቷል።
በዚህም ችሎቱ በሰጠው ትዕዛዝ ዐቃቤ ሕግ ለቀዳሚ ምርመራ ችሎት የሚያቀርበው አቤቱታ እስከነምስክሮች ዝርዝር እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ለነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም ዐቃቤ ሕግ በሚያቀርበው አቤቱታ የጠበቆች መቃወሚያ ካለም እሰማለሁ ብሏል።
ይህ እስከሚሆን ድረስ ግን ተጠርጣሪው አቶ እስክንድር ነጋ በፖሊስ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ አዝዟል።
ከዐቃቤ ሕግ ባገኘነው መረጃ መሠረት ከአቶ እስክንድር ጋር ስንታየሁ ቸኮል እና ቀለብ ስዩም የተባሉ ተጠርጣሪዎች በዚሁ የቀዳሚ ምርመራ ፋይል ውስጥ የሚካተቱ ይሆናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁከት እና ግጭት በማስነሳት ወንጀል የተጠረጠሩ የአስራት ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች እና በጥቁር አንበሳ የህክምና ቤተ ሙከራ ህይወቷ አልፎ የተገኘችው ሃይማኖት በዳዳ ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 7 የጥበቃ አባላት ፍርድ ቤት ቀረቡ።
መርመራ ፖሊስ በአስራት ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ላይ ከህገ መንግስት እና ከሙያ ስነ ምግባር ውጭ ያፈነገጠ የሃይማኖትና የብሄር ግጭት የሚያስነሳ ፕሮግራም ሰርተዋል ሲል ይህንን አስመልክቶ የሰራውን ስራ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።
በፕሮግራሙ ላይም የሰነድ ማስረጃ ማሰባሰቡን ገልፆ እጃቸው ላይ ያገኘውን የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ በመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) እንዲመረምር እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
መርማሪ ፖሊስም ተጨማሪ 14 ቀን ለምርመራ ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩሉ 4 ኪሎ የሚገኘው የአስራት ቴሌቪዥን በቂ ምርመራ ተደርጎበታል ተጨማሪ ምርመራ አደርጋለሁ መባሉም አግባብ አይደለም ሲል ተከራክሯል።
አየር ላይ የዋሉ ፕሮግራሞች ከዩ ቲዩብ እና ሌሎች ድረ ገፆች ላይ ማግኘት ይችላሉ፤ የተጠርጣሪዎች የተናጠል ድርሻ ሊቀርብ ይገባል ያለ ሲሆን የዋስትና መብታቸው ሊከበር እንደሚገባም ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዳልተደረገላቸው ገልፀው ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ሶስተኛ ተጠርጣሪ የጤና ሁኔታውን ገልፆ አያያዛቸው እንዲስተካከል የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ሁሉም ተጠርጣሪዎች ጤንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን አዟል።
ከቤተሰብ ጋርም በጥንቃቄ እንዲገናኙ ትዕዛዝ አስተላልፎ ለተጨማሪ ምርመራ 12 ቀን ፈቅዷል።
በተያያዘ ዜና በጥቁር አንበሳ የህክምና ክፍል ቤተ ሙከራ ውስጥ ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ህይወቷ አልፎ የተገኘችው ሃይማኖት በዳዳ ግድያ ጋር በተያዘ የተጠረጠሩ 7 የጥበቃ አባላት ፍርድ ቤት ቀረቡ።
በእነ ሃብቴ ጓቤ መዝገብ የቀረቡት እነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ መርማሪ ፖሊስ እየሰራ ያለውን ስራ አስመልክቶ ተጨማሪ ጊዜ የጠየቀ ሲሆን ግድያ ፈጽሜያለሁ በሚል የእምነት ክህደት ቃሉን ከሰጠው ደግነት ወርቁ በተጨማሪም እነዚህ ተጠርጣሪዎች ከግድያው ጀርባ ያላቸው ግንኙነት እየለየ መሆኑን ፖሊስ አስረድቷል።
ሟች ተማሪ በአማካሪዋ ተደውሎላት ወደ ጥቁር አንበሳ የሄደች ሲሆን የስልክ ልውውጡን ፖሊስ እየመረመረ መሆኑን አስረድቷል።
ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ሁለተኛ ተጠርጣሪ በወቅቱ የኤጀንሲ ጠባቂዎች መሆናቸውን በመጥቀስ ተማሪ ሃይማኖት ህይወቷ አልፎ የተገኘበት ህንፃ በበጀት ጉድለት ምክንያት ጠባቂ እንደሌለው ተናግረዋል።
የዋስትና መብታችን ይጠበቅ ያሉ ጠይቀዋል ፍርድ ቤት በበኩሉ መርማሪ ፖሊስ የተናጠል ተሳትፏቸውን እንዲያቀርብ በማዘዝ የ7 ቀን ጊዜ ፈቅዷል። ምንጭ፤ ©ፋና
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply