በፓሪስ ኦሊምፒክ ዋዜማ የተቀሰቀው የእነ ኃይሌና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውዝግብ ወደ ሕግ ማምራቱ ይፋ ሲሆን “ቀድሞም ቢሆን መሆን የነበረበት ጉዳይ ይህ ነበር። አበጃችሁ” ሲሉ ጉዳይን በረጋ መንፈስ የሚከታተሉ አስተያየት ሰጥተው ነበር። በሕግ ሕግን ማስከበርና፣ በሕግ መብትን ማስጠበቅ እንደሚቻል የሚያሳይ፣ ለሌላው ወገን ደግሞ በሕግ ራስን መከላከልና በሕግ መጠየቅ እንዳለ የሚያስተምር አግባብ እንደሆነ አመልክተው ነበር።
ሻለቃ ኃይሌና አትሌት ገዛኸኝ አበራ የሚመሩትና ሁለት ፌዴሬሽኖች የተካተቱበት ወገን ዶክተር አሸብር የሚመሩትን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከስሰው ኮሚቴው የሚያንቀሳቅሳቸውን የባንክ ሂሳቦችና፣ የዕለት ተለት ክንውን ማካሄድ እንዳይችል አስወስነው የነበረው በሕግ በመሆኑ ዜናው ፍሞ ነበር። ጅማሮውን የትግላቸው ውጤት አድርገው ያቀረቡም ጥቂቶች አልነበሩም።
ክሱን ተከትሎ አቤቱታ በማቅረብ እንዲነሳለት ምክንያት ዘርዝሮ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባቅረበው መሠረት ሻለቃ ኃይሌና አትሌት ገዛኸኝ አበራ የፍርድ ቤት መጥሪያው በመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ፣ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቱ ቢሯቸው በር ላይ ተለጥፎላቸዋል። የቴኒስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ደግሞ ፈርመው መቀበላቸውን ጎልጉል አጣርቷል።
እነ ኃይሌ በአካል ሳይቀርቡ በጠበቆቻቸው ቢወከሉም ቀደም ሲል ባቀረቡት ክስ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ጉዳዩ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው አስበው አስተያየት ለመስጠት ጥያቄ ቢያቀርቡም ተቀባይነት እንዳላገኙ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያስረዳል።
የክሱን ጭብጥና የውሳኔውን ስህተት በእኩል ደረጃ ዘርዝሮ፣ የከሳሽ ጠበቆች አስተያየት ባይሰጡም፣ ችሎቱ እንደሚቀጥል ተመልክቷል። በውሳኔው ደብዳቤ እንደተመለከተው ፍርድ ቤቱ የቀደመውን ውሳኔ መርምሮ ለየትኛውም ዓይነት ዕግድ የሚያበቃ “በቂ ምክንያት የለም” ብሏል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ ውሳኔው መቀየሩን ይፋ ያደረገውና ትዕዛዝ የሰጠው ደብዳቤ አግባብ ያላቸው ክፍሎች መርምረው ጉዳዩን እንዲያዩትና ክሱ በመደበኛ ፍርድ ቤት እንዲታይ መርቶ ፋይሉን ሲዘጋ ይግባኝ ክፍት እንደሆነ አመልክቷል። እዚያው ላይ ደጋግሞ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በዓለም ዓቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ቻርተር መሠረት በራሱ ደንብ የሚመራና የሚሠራ ተቋም መሆኑን አስታውሷል።
የሁለቱ አካላት ውዝግብ በፓሪስ የኢትዮጵያን ባንዲራ ተሸክመው ለተሰለፉ አትሌቶች ጭንቀትና የውጤት መበላሸት ምክንያት እንደሆነ መገለጹ ይታወሳል። በወቅቱ አትሌቶቹ ላይ የደረሰውን የስነ ልቦና ቀውስ በቅርብ የተከታተሉ፣ አስቀድሞውንም የሚዲያ ትርምስ ከመፍጠር በሰከነ መልኩ በሕግ አግባብ ሊኬድበት እንደነበር የጠቆሙ የተጀመረው ክስና የክስ መከላከያ እያደር ሊካረር እንደሚችል ምልክት መታየቱን አልሸሸጉም።
ሙሉውን የውሳኔ ዝርዝር ከሥር ያንብቡ
በዚህ አግባብ ዛሬ ያስቻለው ችሎት ቀደም ሲል የሰጠውን ሁለቱም የማገጃ ትዕዛዞች በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 158 መሠረት ማንሳቱን ያስታወቀው በሌላ በኩል ከሳሾችን ወክለው የቀረቡት ጠበቆች ጉዳይ የከሳሾችን መብትና ጥቅም ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የሰፊው ሕዝብ መብት እና ጥቅም ጋር የተያያዘ በመሆኑ 1ኛ ተከሳሽ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ተገቢውን አስተያየት ለመስጠት ጊዜ የሚያስፈልገን በመሆኑ ያለንን አስተያየት በዝርዝር ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠን ሲሉ የጠየቁ ቢሆንም፣ ከሳሾች የፍርድ ቤቱ መጥሪያ ከ3ኛ ከሳሽ ውጪ ለእያንዳንዳቸው የደረሰ መሆኑን የሚስረዳ ማስረጃ ባይቀርብም በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት ይዘው እንዲቀርቡ በአንድም ሆነ በሌላ አግባብ ቀጠሮ መያዙን አውቀው እስከቀረቡ ድረስ ክጉዳይ ውስብስብነት እና አንገብጋቢነት አንፃር የከሳሾች ጠበቆች በአንደኛ ተክከሳሽ በኩል የቀረበው የእግድ ይነሳልኝ አቤቱታ ግልባጭ በችሎት ላይ ከደረሳቸው በኋላ በቀረበው አቤቱታ ላይ ያላቸውን አስተያየት በቃል እንዲሰጡ በችሎት ላይ እድል የተሰጣቸው ቢሆንም፣ ያላቸውን አስተያየት በቃል ለመስጠት ባለመፈለጋቸው ምክንያት ከሳሾች በጉዳዩ ላይ አስተያየት የመስጠት መብታቸው ታልፏል።
ችሎቱም 1ኛ ተከሳሽ በቀን 02/01/2017 ዓ.ም ጽፈው ያቀረቡት የዕግድ ትዕዛዝ ይነሳልኝ አቤቱታ መሠረት በማድረግ እንዲሁም ከሳሾች በተሳሽ ላይ የመሠረቱት የክስ ይዘትና የተጠየቀው ዳኝነት አንጻር የቀረበለትን አቤቱታ በመመርመር ተከታዩን ብይን ሰጥቷል።
ብይን
ለዚህ ብይን መሠረት መነሻው የሆነው ጉዳይ 1ኛ ተከሳሽ ያቀረቡት የእግድ ትዕዛዝ ይነሳልኝ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም በአጭሩ 1ኛ ተከሳሽ በዓለም ዓቀፍ ኦሊምፒክ ቻርተር እና ቻርተሩን ተክትሎ በጸደቀው የተቋሙ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የተቋቋመ በመንግሥት የስፖርት ፖሊሲ መሠረት ስፖርቱን የሚመራና በምንግስት ድጋፍ የሚተዳደር ተቋም ሲሆን የኮሚቴው አባላት ባልሆነ እና ይሄንን አቤቱታ ለማቅረብ መብትና ጥቅም በሌላቸው ሰዎች አማካይነት የቀረበውን አቤቱታ መሰረት በማድረግ ፍርድ ቤቱ ጷግሜ 04 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስም በተለያዩ ባንኮች የተከፈተው የባንክ ሂሳብና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግንቦት 06 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረጋቸው የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባዎች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ እና ያከናወነው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ ታግዶ እንዲቆይ የሰጠው የእግድ ትዕዛዝ የተቋሙን ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም እንቅስቃሴዎች የሚገድብና የተቋሙን ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም ዓቀፋዊ እንቅስቃሴዎችን የሚገድብና የተቋሙ ቢሮ ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ የሚያደርግ በመሆኑ እግዱ እንዲነሳልኝ በማለት አመልክተዋል።
ከሳሽ በ1ኛ ተከሳሽ በኩል የቀረበው የዕግድ ትዕዛዝ ይነሳልኝ አቤቱታ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲያቀርቡ እድል የተሰጣቸው ቢሆንም፣ ቀደም ሲል የተሰጠው የእግድ ትዕዛዝ ሊነሳ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው አጭር ጉዳይ ላይ በቃል ያላቸውን አስተያየት መስጠት እየቻሉ ያለ በቂ ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ መጠየቃቸው ተገቢ አለመሆኑን እንዲሁም ከጉዳዩ አጠቃላይ ሁኔታ እና አንገብጋቢነት አንጻር በጉዳዩ ላይ ተገቢው ትዕዛዝ መሰጠት ያለበት መሆኑን በመረዳት ከሳሾች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት የማቅረብ መብታቸው ታልፎ ጉዳዩ ታይቷል።
በዚሁም መሠረት 1ኛ ተከሳሽ ያቀረቡት የእግድ ይነሳልኝ አቤቱታን መነሻ በማድረግ ኣንዲሁም ከቀረበው የክስ ዓይነት እና ከተጠየቀው የዳኝነት ጥያቄዎች አንፃር በዋናው ጉዳይ ላይ መደበኛ ችሎት ተገቢውን ትዕዛዝ እስከሚስጥ ድረስ ከአሁን ቀደም በዚህ መዝገብ ላይ ተሰጥቶ የነበረው የእግድ ትዕዛዝ ሊነሳ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ከተገቢው የሕግ ድንጋጌዎች አንጻር ጉዳዩ ተመርምሯል።
እንደተመረመረውም መሠረት በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 151፣ 152 እና 154 (1) መሠረት ፍርድ ቤቱ የያዙትን የፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ፍርድ እስከሚሰጥ ድረስ ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ንብረት ወይም ክርክር የቀረበበት ጉዳይ ላይ የሚስጥ ፍርድ የሚፈጸምበት ንብረት እንዳይበላሽ፣ እንዳይጠፋ እና ሌላ አላስፈላጊ ጉዳት እንዳይደርስበት ወይም ከፍርድ በፊት ባለበት ሁኔታ ተከብሮ እንዲቆይ ለማድረግ የሚሰጡት ዋስትና የማቅረቢያ፣ የማስከበሪያ፣ የመያዣ እና የጊዜያዊ ማገጃ ትዕዛዞች በዋናው ጉዳይ የመጨረሻ ፍርድ እስከሚሰጥ ድረስ በተከራከሪ ወገኖች ላይ ወይም በአንደኛው ወገን ላይ የሚደርስን ወይም ሊደረስ የሚችልን ጉዳት እና እንግልት ለመቀነስ እና የፍትሕ አሰጣጥን ሒደቱን ለማቀላጠፍ ዓላማ ያላቸው መሆኑ ግልዕ ነው።
ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ በራሳቸው ምክንያት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ወይም ከላይ በተጠቀሱት የፍትሐ ብሔር ስነ-ስርዓት ሕጉ ድንጋጌዎች መሰረት ከፍርድ በፊት የተሰጡትን የማገጃ ትዕዛዞች ላይ ቅሬታ የተሰማው ወይም ያላግባብ ነው የሚለው ወገን እግዱ እንዲነሳ፣ እንዲሻሻል ወይም እንዲሰረዝ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ለማቅረብ ሕጋዊ መብት ያላቸው ስለመሆኑ እና ፍርድ ቤቱም የቀረበው አቤቱታ በበቂ ምክንያት የተደገፈ መሆኑን በተረዳ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ራሱ አስቀድሞ ሰጥቶ የነበረውን የእግድ ትዕዛዝ እንዲሻሻል፣ እንዲነሳ ወይም ጨርሶ እንዲሰረዝ ለማድረግ ስልጣን ያለው ስለመሆኑ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 158 ስር በግልጽ ተደንግጓል።
በመሆኑም ይህ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል ጳጉሜ 04 ቀን 2016 ዓ/ም በዋለው ችሎት በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቱ ስም በተለያዩ ባንኮች የተከፈተው የባንክ ሂሳብ እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግንቦት 06 ቀን 2016 ዓ.ም እና ሰኔ 04 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረጋቸው የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ እና ያከናወነው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ታግዶ እንዲቆይ የእግድ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም ከሳሾች ካቀረቡት የክስ ዓይነት እና ከተጠየቀው ዳኝነት አንጻር ስናየው ከሳሾች ከተስሳሾች ላይ የሚጠይቁት የገንዘብ ክፍያ በሌለበት ሁኔታ በ1ኛ ተከሳሽ ስም የተከፈተው የባንክ ሂሳብ ታግዶ የሚቆይበት በቂ የሆነ ሕጋዊ ምክንያት አልተገኘም።
ከዚህ በተጨማሪም ከሳሾች ካቀረቡት የዳኝነት ጥያቄ አንጻር የኮሚቴው ጠቅላላ ጉባዔስብሰባ አጠራር ሕጋዊነትና ተቀባይነት፣ የውሳኔ አስተላለፍ ወይም አሰጣጥ ሕጋዊና ተቀባይ እንዲሁም የተደረገው የኮሚቴው ሥራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ ሕጋዊነትና ውጤት በተመለከተ ወደፊት ጉዳዩን የሚመለከተው አካል አይቶ ተገቢውን የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በ1ኛ ተከሳሽ ስም በተለያዩ ባንኮች የተከፍተው የባንክ ሂሳብ ታግዶ እንዲቆይ መደረጉ የተቋሙ ሕልውና መቀጠል እና አለመቀጠል ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ ተቋሙ የአገሪቱን መንግስትና ሕዝብ በመወከል በተለያዮ መድረኮች ላይ በመገኘት የሀገሪቷን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚከለከል በመሆኑ እና እግዱ ተነስቶ በጉዳዩ ላይ የቀረበው ክርክር መታየት የሚከለክለው በቂ የሆነ ሕጋዊ ምክንያት የሌለ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
በአጠቃላይ 1ኛ ተከሳሽ ባቀረበው አቤቱታ ላይ የተጠቀሱትን ምክንያቶች ስናየው ተቋሙ በዓለም ዓቀፍ ኦሊምፒክ ቻርተርና ቻርተሩን ተከትሎ በጸደቀው የተቋሙ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የተቋቋመ እና ሀገራዊ የስፖርት ክንውኖችና እንቅስቃሴዎችን በበላይነት የሚመራ ነፃና ገለልተኛ ተቋም መሆኑን፣ እንዲሁም ተቋሙ በሀገር፤ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ህገሪቷን በመወከል የሀገሪቷን ጥቅምና ጥሩ ስም ከፍ ለማድረግ የተጣለበት ኃላፊነት ለመጠጣትም ሆነ አጠቃላይ የዕለት ዕለት አስተዳደራዊ ስራዎችን እንዳይሰራ የሰራተኞች ደመወዝ፣ የተለያዩ አገልግሎት ክፍያዎች እንዳይፈፀም የሚያደርግ የእግድ ትዕዛዝ መሆኑን በመረዳት በአጠቃላይ በከሳሾች የቀረበው የክስ አቤቱታ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ተቀብሎ የማየት ስልጣን ያለው መሆን አለመሆኑ፣ ከሳሾች ክሱን ለማቅረብ የሚያስችላቸው ሕጋዊ ችሎታ፣ መብት እና ጥቅም ያላቸው ስለመሆነ እና አለመሆን እንዲሁም ጉዳዩ የክስ ምክንያት ያለው መሆን አለመሆኑ ፍርድ ቤቱ መደበኛ ስራው ሲጀምር በመደበኛ ችሎት ታይቶ ተገቢው ትዕዛዝ ወደ ፊት የሚሰጥበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ ቀደም በ1ኛ ተከሳሽ ስም በተለያዩ ባንኮች የተከፈተው የባንክ ሂሳብ ላይ እንዲሁም ተቋሙ ከዚህ በፊት ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም እና ሰኔ 04 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ባስተላለፋቸው ውሳኔዎች እና ባደረጋቸው ምርጫዎች ሕጋዊነት እና ተቀባይነት ጉዳዩ በሚመለከተው እና ስልጣን ባለው አካል ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ተቋሙ እና ተቋሙን የሚመሩ አካላት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ እንዲሁም በተቋሙ ስም የተከፈተውን የባንክ ሂሳቦች እንዳያንቀሳቅሱ የተቀመጠው ክልከላ ከአጠቃላይ የሀገሪቷ እና የሕዝቦቿ ጥቅምና ሙበት አንጻር አሉታዊ ተፅእኖ ያለው ሆኖ ስለተገኘ ይህ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም የተሰጠው የእግድ ትዕዛዝ ቢነሳ በከሳሾች መብትና ጥቅም ወይም በክርክሩ አመራር ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ጉዳት አለመኖሩን መረዳት ተችሏል።
በመሆኑም 1ኛ ተከሳሽ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ የጠቀሷቸው ምክንያቶች በቂ እና ተቀባይነት ያላቸው ከመሆኑም በላይ ከሳሾች ካቀረቧቸው ዳኝነቶች አንጻር ገንዘብ ነክ የሆነ ለከሳሾች ሊክፈል የሚገባ የገንዘብ ጥያቄ በሌለበት ሁኔታ እንዲሁም ተቋሙ ያደረገው ስብሰባ ያስተላለፈው ውሳኔ እና ያከናወነው የስራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ሕጋዊነት፣ ተቀባይነት እና ውጤት አግባብ ባለው አካል ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ እንዲሁም በዋናው የክስ አቤቱታው ላይ በመደበኛ ችሎት ተገቢው ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ ወይም በአጠቃላይ ጉዳዩ ላይ መደበኛ ክርክር ተደርጎ የመጨረሻ ዕልባት አስከሚሰጥበት ድረስ የእግዱ ትዕዛዝ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ውጤት አለመኖሩን በመረዳት ይህ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል ጳጉሜ 04 ቀን በዋለው ችሎት ያስተላለፋቸው ሁለቱም የማገጃ ትዕዛዞች በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 158 መሰረት ሊነሳ ይገባል ሲል ብይን ሰጥቷል።
ትዕዛዝ
በዚህ መዝገብ ላይ ጳጉሜ 04 ቀን 2016 ዓ/ም በዋለው ችሎት በ1ኛ ተከሳሽ ስም በተለያዩ ባንኮች የተከፈቱት የባንክ ሂሳቦች ላይ እንዲሁም የተቋሙ አስተዳደራዊ ተግባራት እና እንቅስቃሴዎች ላይ የተላለፈው የእግድ ትዕዛዝ ሙሉ በሙሉ ተነስቷል። ይህ ትዕዛዝ እግዱ ስለመነሳቱ እንዲያውቁት እና ተገቢውን እንዲፈጽሙ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ይተላለፍ።
በተሰጠው ብይንና ትዕዛዝ ላይ ቅሬታ ያለው ይግባኝ ማለት በሕግ እንደተጠበቀ ነው። ከሳሾች ያቀረቡት ዋናው የክስ አቤቱታ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ መደበኛ ሥራውን ሲጀምር መዝገቡ ለመደበኛ ችሎት ይቅረብ። መዝገቡ ተዘግቷል። ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ። (የማይነበብ የዳኛ ፍርማ አለበት)።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply