በቅርቡ “የትምህርት ሚኒስቴር” 400 ተማሪዎች በፈተና ቅጾች ላይ ኢትዮጵያውያን አይደለንም ብለው ሞሉ የሚል መረጃ አወጣ ሲባል ሰምቼ ቆሽቴ አርሮ ነበር። የተናደድኩበት ምክንያት የመንግስት የ26 አመት የጸረ-ኢትዮጵያዊነት ፖሊሲ አፈጻጸም ይህን የመሰለ ውጤት እንዴት ሊያመጣ ቻለ በሚል ሳይሆን እንዴት ዛሬ ስርአቱ በሞት አፋፍ ላይ ቆሞ እንኳን የሩብ አመት ድካሙ ከንቱ መሆኑን አይገባውም ብዬ ነበር። እንጂ ኢትዮጵያን የማትመስል ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሌት ተቀን ያለመታከት ሲዘራ የኖረው የጎሳ መርዝ 400 የተበላሹ እጽዋትን አበቀለ ቢሉኝ እንኳን ጉዳታችን ከዚህ በላይ አልሆነ ብዬ በእፎይታ እተነፍስ ይሆናል እንጂ ብዙም አላዝንም። መንግስት ግን ላመታት ስራው ከንቱነት ዋቢ የሆነውን መረጃ ዛሬም ሳያፍር እንደመልካም ዜና ማወጁ ያስገረመኝ መሆኑን ግን መሸሸግ አልችልም።
የዛሬ ርእሴ ግን ይህ አይደለም። የጎሳ ፖለቲካ ቀባሪ አጥቶ እንጂ በህዝብ ህሊና ውስጥ ከሞተ ቆይቷል። አሁን የኢሀዲግ ኢትዮጵያ ቅዠት ሆና የህዝቡ ኢትዮጵያ እውን ልትሆን የተስፋ ቾራ ብቅ ማለት ጀምሯል። ህዝብ ላመታት በጎሰኝነት ፖለቲካ ስትጎሳቆል የኖረቺውን አንዲት ኢትዮጵያ ሊያድስ ሲታጠቅ እየታየ ነው። የሰሞኑ የባለራእይ የዖሮሞ ወጣቶች አስገራሚና አስደማሚ የሰሜንኢትዮጵያ ጉብኝት የዚህ የሀገር መልሶ ግንባታ ጥረት ግሩም ጥንስስ ነው። ኢትዮጵያን ለማፍረስ የታቹት የኢትዮጵያ ዖሮሞ ወጣቶች ኢትዮጵያን ዳግም ለመገንባት አስደናቂ ታሪክ ሰሩ። በጣና አረም ተምሳሌነት የኢትዮጵያን የተበላሸ ታሪክ አረሙት። የደበዘዘውን የህዝብ አንድነት እንደገና በፍቅር አደመቁት። “ኢትዮጵያ ኬኛ” ሲሉ። የአንድነት ታሪክን ስርዝ ድልዝ በብሩህ የወጣት አእምሯቸው በቀረጹት አዲስ የፍቅር ብእር አድምቀው ጻፉና በሁላችንም ልብ ነገሱ።
ይህ ያልተጠበቀና ኢምንት የሚመስል ግን ደግሞ የኢትዮጵያን የታሪክ አቅጣጫ ከመሰረቱ የሚለውጥ ድንቅ እርምጃ አድማሱ መስፋት ይኖርበታል። በዚህ የፍቅር መርከብ ሁሉም መሳፈር ይኖርበታል። የአማራና ዖሮሞ ህዝብ አንድነት ለኢትዮጵያ አንድነት ያለው ፋይዳ ግዙፍ ነው። ሆኖም ኢትዮጵያ ከዚህም በላይ ናት። የትግራይ፣ የደቡብ፣ የቤኒሻንጉል፣ የጋምቤላና የሶማሌ ህዝብ ከኢትዮጵያ ሌላ እናት የለውም። እናም የዖሮሞ ወጣቶች ያሳዩን የፍቅር አበባ በሁሉም አቅጣጫ ሲበተን ማየት እንሻለን። በተለይ የትግራይ ህዝብ የሚነቃበት ጊዜ አሁን መሆን አለበት። በእኔ እምነት የትግራይ ህዝብ ወንድምና እህቶቹን የሚጠላ ህዝብ አይደለም። እንዲያውም የፍቅር ህዝብ ነው። ባልጠበቀው መንገድ የቅሬታ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ ተደረገ እንጂ ህዝቡ በባህሪው ፀረአንድነት አይደለም። ስለዚህ ያለፍላጎቱ የተፈጠረበትን የአንድነት ክፍተት የሚሞላበትን ስልት ለመፈለግ ከዚህ በላይ አጋጣሚ ሊኖር አይችልም። የኢትዮጵያ የፍቅር ልብ ለሁሉም ክፍት ነው። አማራና ዖሮሞ ዜጎች የከፈቱት የፍቅር አዳራሽ ለማንም አይጠብም። ኢትዮጵያውያን አስተዋይ የዖሮሞ ወጣቶች ባቀጣጠሉት የፍቅር ሻማ መብራት እየተመሩ የደበዘዘ ያንድነት ታሪካቸውን ዳግመኛ ሊያደምቁት ይገባል። የዖሮሞ ወጣቶች የጀመሩት የታሪክ እርማት ስርዝ ድልዝ ባለበት ገፅ ሁሉ ሊቀጥል ይገባል። እናንት አስተዋይ የኢትዮጵያ ወጣቶች፣ ባስተዋይ ምግባራችሁ ሁላችንም ኮርተናል፤ ኢትዮጵያም ለዘላለም ትኮራባችhኋለች።
ህሩይ ደምሴ (zobar2006@gmail.com)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply