በቅርቡ የተደረገውን የዶላር ጭማሪ ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 77 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መዉሰዱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮዉ ሃምሌ 23 እና 24 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገዉ የክትትል ሥራ በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ 11 እንዲሁም በየካ ክ/ከ 2 በድምሩ 13 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ያስተወቀ ሲሆን ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በሁሉም ክፍለ ከተማ በተደረገ የአሰሳ ስራ 77 ንግድ ሱቆች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሰውነት አየለ ተናግረዋል።
ኃላፊው ጨምረውም አብዛኛው የተወሰዱ እርምጃዎች በማኅበረሰቡ ጠቆማ እንደሆነ ገልጸው የከተማው ነዋሪዎች አሁንም የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ የንግድ ድርጅቶችና ሱቆች በአቅራቢያቸው በሚገኝ ወረዳ መጠቆም እንዳለባቸዉ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በሁሉም ክፍለ ከተማ ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ ግብረ ኃይል በማቋቋም የክትትል ሥራውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል፡፡
ንግድ ቢሮዉ በከተማዉ በሚገኙ የንግድ ድርጅቶች ላይ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን እና ኅብረተሰቡ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ድርጅቶችን ሲመለከት በ8588 የነፃ መስመር ለቢሮው ጥቆማ እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡ (መናኸሪያ ሬዲዮ 99.1)
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በስግብግብ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ ተቀምጧል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጡን በቁንጽል ሳይሆን በምልዐት መመልከት ይገባል” ሲሉም ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ዛሬ ለአመራሮቻቸው ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ዓላማችን የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ነው። አካኼዳችን ድኻ ተኮር ነው።
ትኩረታችን ለችግር በመጠቃት ተጋላጭ የሆኑ ደካሞችን መደገፍ ነው ያሉ ሰሆን የሕግ አስፈጻሚ አካላት የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጥ ስራውን ባልተገባ ሕገ ወጥ መንገድ ለመጠቀም በሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ እንዲወስዱ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል”ብለዋል። (esat)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply