ከሃምሳ ቀናት በላይ በአጋቾች እጅ ያሉት እህቶቻችን ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ሆኖብናል። የአንድ ሃገር ህዝብ ከሁሉ በፊት የሚፈልገው ነገር ዋስትና ነው። ተማሪው፣ ነጋዴው፣ ገበሬው፣ ሰራተኛው ሁሉ ከመንግስት የሚጠብቀው ዋና ነገር ደህንነቱ እንዲረጋገጥለት ነው። የመንግስት ተቀዳሚ ተግባርም ይሄ ነው።
ለውጥ በሃገራችን ጀመረ ካልንበት ማግስት ጀምሮ ከፍተኛ መፈናቀልና አለመረጋጋት ሃገራችንን እየናጣት ነው። ይህንን ችግር የለውጥ ባህርይ ኣድርገን የምናይ ካለን ስህተት ነው። የሰው ደም ሳንገብር ወደ ለውጥ የምናልፍበትን መንገድ ነው የምንሻው እንጂ ከዚህ በፊት በየለውጡ ያየነውን ኣይነት የኢትዮጵያውያን ስቃይ እንዲደገም አንሻም። በመሆኑም የለውጥ መሪዎች ቁጥር አንድ ስራ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ መሆን ኣለበት።
ከሃምሳ ቀናት በላይ በእገታ ላይ የሚገኙት የሃገር ተስፋ የሆኑ እህቶቼና ወንድሞቼ ህይወት በአንድም በሌላም መልኩ ከመንግስት የጸጥታ አመራር ጋር በቀጥታ የተገናኘ ችግር ነው። ስለሆነም መንግስት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እነዚህን ወጣቶች የማዳን ስራ መስራት አለበት። ወታደራዊ ጥበቦችና የአመራር ጥበቦች ሁሉ ወደነዚህ ወገኖች ሊያዘነብሉ ይገባል። እኔ እንደገባኝ አጋቹ ታውቋል። ምክንያቱም የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ሰክሬታሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ሲናገሩ እንደሰማሁት የተለቀቁ ተማሪዎች እንዳሉና ለቀሩት ድርድር እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል። ይህ ማለት መንግስት ኣጋቹን ኣውቋል ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህ እህቶቻችንና ወንድሞቻችንን የማትረፍ ኦፐሬሽን መደረግ ኣለበት። ይህ ኦፐሬሽን በከፍተኛ የሰኪዩሪቲና ወታደራዊ ጥበብ የታገዘ መሆንም አለበት። መረጃዎች ለህብረተሰቡ መገለጽ አለበት።
በተለይ ደግሞ ሴት ልጅ በሽፍታ እጅ ወድቃ የሚተኛ ማህበረሰብ የለንም። ሴት በሽፍታ እጅ ወድቃ እንቅልፍ ኣይኖረንም። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ሆናችሁ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተቀናጀ ትግል እነዚህን ሴቶች መታደግ ያስፈልጋል። ይህንን በማድረግ በሃገራችን ቀድሞ የማናውቀውን ይህንን የማገት ጅማሮ ከስሩ መንቀል ኣለብን። ኢትዮጵያችን የቦኮሃራም ዋሻ ልትሆን በምንም ዓይነት ኣንፈቅድም። በመላ ሃገሪቱ የምትገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የብሄር ልዩነትን ጌጥ አድርጋ ሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ቦኮሃራም ቦታ የለህም ማለት አለባችሁ። ለአጠቃላይ የሃገራችን የደህንነት ዋስትና ቆርጣችሁ መነሳት አለባችሁ። የትም ዓለም ቢሆን ዴሞክራሲና መልካም ኣስተዳደር የመጣው በትግል ነው። መንግስት በገፋነው ልክ የሚሄድ ነገር ነውና ለውጡ በሰዎች መጉላላትና ደም ላይ ሳይሆን በሰላምና በአንድነት እንዲቀጥል ንቅናቄዎች ያስፈልጋሉ።
ሴት ልጁ የተነካበት ማህበረሰብ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ብድግ ብሎ ሊነሳ ይገባል። ለውጥን የሚመራው ህዝብ ነውና በየጊዜው ለውጡን የሚያስቱ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ህዝቡ አቅጣጫ የማሳየትና የመታገል ሃላፊነቱን በንቃት ሊወጣ ይገባል።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ገለታው ዘለቀ (geletawzeleke@gmail.com)
Leave a Reply