ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በሀገሪቱ ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በጥምረት ለመስራት ያስችላል ያሉትን የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።
ትብብሩ በቀጣይ በአገሪቱ እንዲፈጠርና እንዲጎለብት የሚፈለገው የአገራዊ በጎ ሀይሎች ጥምረት መሰረት እንዲሆን ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
በመጪው አገራዊ ምርጫ የመራጮች የጋራ ፍላጎትና ራዕይ ለማሳካት ፓርቲዎቹ በጋራ ለመስራት በማሰብ የተመሰረ የፖለቲካ ትብብር መሆኑንም ነው ፓርቲዎቹ የገለፁት።
በአገሪቱም ሆነ በዜጎች ላይ የተጋረጡ ፈተናዎች እንዳሉ የገለጹት ፓርቲዎቹ፣ ይህንን ከመቼውም ጊዜ በላይ በትብብር ለመታገል በቁርጠኝነት እንደሚሰሩና ትብብሩ ከምርጫው በኋላም እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። (ኢቢሲ)
የባልደራስ መሪና በአሁኑ ጊዜ በእሥር ላይ የሚገኙት አቶ እስክንድር ነጋ ከአማራ ድርጅቶች በተለይ ከአብን ጋር ምሥጢራዊ ግንኙነት አላቸው እየተባ ሲነገር ቆይቷል። እርሳቸው ግን በጎጥ እንደማያምኑ የተናገሩ ቢሆንም በሕብረብሔራዊነት ነው የተደራጀሁት ከሚለው መአህድ ጋር ይሠሩ እንደነበር ራሳቸው መናገራቸው ይታወሳል።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ትብብርን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
የሀገራችን ህዝብ ለዘመናት በተጫኑበት ኢዲሞክራሲያዊና አምባገነን አገዛዞች የተነሳ፣ በነጻነት እጦት፣በስቃይ እና በመከራ ኑሮውን እንዲገፋ ተደርጓል። ጭቆናን አስወግዶ የሚፈልገውን ፍትህ እና እኩልነት እውን ለማድረግ ከፍትኛ ዋጋ መክፈሉም እሙን ነው።
ይሁንና የሃገራችን የለውጥ ፍላጎት እና እንቅስቃሴ ጅማሮው ሳይሳካ፣ ለቀጣዩ ዴሞክራሲያዊ ትግል ተስፋ ሊሆን የሚችል መሰረታዊ የትርክትና የመዋቅር ክለሳ እንኳ ሳይደረግ አምባገነንነትና ዘረኝነት የእጅ ለውጥ ብቻ እያደረጉ የሚፈራረቁባት ሆናለች። በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ያለፈው ህዝባችን አሁንም ዲሞክራሲን፣ እኩልነትንና ዘላቂ ሰላምን በመሻት ለነጻነት የሚያደርገውን ትግል አጠንክሮ እንደቀጠለ ይገኛል።
የዚህ አይነት መልክና ይዘት ተላብሶ የተደራጀው የተፎካካሪ ሀይል ለሰርጎ ገቦች የተጋለጠ፣ በተፈጥሮው ደካማና ተሰባሪ ከመሆኑም በላይ የአምባገነኑን ስርአት ራዕይ አቀንቃኝ እስከመሆን ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። በተጨማሪ የተቃውሞው ጎራ እርስ በርሱ በፍረጃና በሴራ መጠላለፍ ምክንያት በቁርሾ እንዲሞላ በማድረግ የጋራ ሀገራዊ ስምሪት መውሰድ እንዳይችል አድርጎት ቆይቷል።
በዚህ ሂደት ውስጥ አምባገነኖችን በጋራ መታገል ጥረት ከማድረግ ወርደው በመናኛ ፍላጎቶችና በጥቃቅን ልዩነቶች ዙሪያ ታጥረው ሲሻኮቱ በመካከል የባከነው ጊዜ እና የሰው ህይወት የሚያስቆጭ ነው።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሀገራችንን ለድሜ ልክ ዝቅታ የዳረጋት የጥላቻ ትርክት፣ ትርክቱን መሰረት አድርገው የተደነገጉ ህግጋትና የተዘረጉ መዋቅሮች ተከልሰው መላ ኢትዬጵያውያን በእኩልነት፣ በወንድማማችነት፣ በፍትህና በሰላም የሚተዳደሩነት ዘላቂ ስርአት በማስፈን በተለምዶ “መንታ ቅኝት” ያለው የትግል እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። የአብን ስትራቴጂክ ግብ መላውን ኢትዬጵያዊ የፍትሀዊ አማካኝ ተጠቃሚ በማድረግ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የፖለቲካ ማእቀፍ እንዲፈጠር ሲሆን የድርሻውን ለማበርከት አበክሮ እየሰራ ያለ ንቅናቄ ነው።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ/ ደግሞ የኢትዬጵያዊ ህብር አይነተኛ መገለጫ የሆነችውን የአድስ አበባ ከተማ ህዝብ ከከፋፋይና ከጥላቻ ፖለቲካ ነፃ ለማድረግና ህዝቡ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንዲረጋገጥ ለማስቻል በሚል የተደራጀ ስለመሆኑ በሰፊው የሚታወቅ ነው።
አዲስ አበባ ከተማ የኗሪዎቿ መሆኗን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት የጋራ ትግል መነሻ ዴሞክራሲን፣ ነፃነትን፣ ፍትህንና እኩልነትን በማስፈን ላይ የተመሰረተ ሲሆን አንዳች ቅቡልነት ያለው መርህ ወይም ምክንያት ማጣቀስ የማይችሉ ሀይሎች ከተማዋ የአንድ ንጥል ብሄር ንብረት መሆኗን በይፋ በመግለፅ የማታገያ አጀንዳ በማድረግ ህዝቡ በነሱ ፍቃድና ይሁንታ መኖር እንዳለበት አድርገው ያወጁት ያልተገራ ፍላጎት የጋረጠበትን የህልውና ስጋት መቀረፍ እንዳለበት አብንና ባልደራስ የጋራ ፖለቲካዊ አቋም ወሰደዋል።
የሀገራችን ኢትዬጵያ መድናና የመላ ህዝቧ ሰላማዊ መኖሪያ ሆና ዘመናትን የተሻገረችው አዲስ አበባ መደበኛና ነባር ምልከታ ሊቸራት ሲገባ ከልቦለድ የመነጨ የዘረኞች “የልዩ ጥቅም”ቀንበር ጊዜ በረዘመ ቁጥር የህግና የፖለቲካ ቋጠሮው እየጠበቀ መምጣቱና ይዘቱ “በኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና በአዲስ አበባ መስተዳደር ስምምነት” እንደሚወሰን በተሻሻለው ቻርተር መደንገጉ ከተማዋንና ህዝቧን ከአንድ ወገን በተሰባሰበ የፖለቲካ ሀይል ይሁንታ፣ ፍፁም ቁጥጥርና ጥበቃ ስር ለማዋል የተወሰነ መሆኑን ያሳያል። አብንና ባልደራስ ይሄን አምባገነናዊ፣ ፍትህ አልቦ፣ ዘረኛ፣ አግላይና በመጨረሻም የግጭትና የብሄራዊ ደህንነት አደጋ የሆነ አፍራሽ እንቅስቃሴ በጋራ ተሰልፈው ለመታገል ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ትብብሩ በቀጣይ እንዲፈጠርና እንዲጎለብት ለምንፈልገው የሀገራዊ በጎ ሀይሎች ጥምረት እርሾ ሆኖ እንዲያገለግል የታለመ ነው። አስቻይነት የሌለውና በህግ የተደነገገው የጊዜ ገደብ ጉዳይ በነባራዊ ተግዳሮቶች ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን በማረጋገጥ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተመሳሳይ አንድምታ ያላቸውን ጉዳዬች ባስተናገደበት ሁኔታ ትብብሩ ለህጋዊ እውቅና ሲቀርብ በመፍቀድና በመመዝገብ እንዲያፀድቀው የሚቀርብ ይሆናል።
በዚህ መነሻነት ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ትግል በመጪው ሃገራዊ ምርጫ የመራጮችን የጋራ ፍላጎትና ራዕይ ለማሳካት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ/አብን/ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ/ በጋራ የምንሰራበት የፖለቲካ ትብብር ፈጥረን ለመስራት መወሰናችንን ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዬጵያውያን፣ ለመላው አማራ ህዝብና ለአድስ አበባ ህዝብ ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው። ሌሎች ፓርቲዎችን ጨምሮ በሁለቱ ፓርቲ አመራሮች መሃከል ለወራት ሲካሄድ የነበረው ረጂምና አድካሚ ድርድር ፍሬ አፍርቶ መጪውን ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የአብን እና የባልደራስ ትብብር አሸናፊ ሆኖ መውጣት የሚያስችላቸውን የጋራ ስልቶች ቀይሰው በይፋ መንቀሳቀስ ጀምረዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ/አብን/ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ/ባልደራስ/ አጠቃላይ የኢትዬጵያ ህዝብ፣ የአማራ ህዝብ እና የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪ ህዝብ በበደል ውስጥ አምጠው የወለዷቸው የቁርጥ ቀን ልጆቹ እንደመሆናቸው መጠን በተባባረ ክንድ በህዝባችን ላይ የተጫነውን የመከራ ቀንበር እንዲወርድ ከመቸውም ግዜ በላይ በጋራ ትብብር ለመታገል በቁርጠኝነት ተሰልፈዋል፡፡
አብን በጽንፈኞች የተሳሳተ ትርክት መነሻነት በአማራ ህዝብ ላይ በተከታታይ የሚደርሰው ግፍ ድምጽ በመሆን በመጀመሪያው ረድፍ ሆኖ ትግሉን እየመራ ይገኛል። አብን የሀገራችን ኢትዬጵያን ደህንነት ለማረጋገጥና ህልውናዋን ለማስቀጠል አንድ ወሳኝ አምድ የሆነው የአማራ ህዝብ በልዩ ሁኔታ ተፈርጆ የሚጠቃበትን የፅንፈኞች ስሁት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለመግታት የሚያስችል ልዩ ማዕቀፍ ሆኖ የተደራጀ ሲሆን ታሪካዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስሪቱ በኢትዬጵያዊነት፣ ምልከታውም በወንድማማችነት፣ በፍትህና በዴሞክራሲ የተቃኘ ስለመሆኑ ውሎ ያደረ ጉዳይ ነው።
ከላይ በሰፊው እንደተመላከተው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ላይ የተጋረጡ የህልውና አደጋዎችን ለመከላከል፣ የከተማዋ ህዝብም ራሱ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመረጣቸው እንደራሴዎቹ የመተዳደር መብቱን ለማስከበር ባሚያደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ በብቃትና በንቃት በነሳተፍ አያሌ መስዋዕትነቶችን በመክፈል የቀጠለ መሆኑን ራሱ ህዝቡ በተግባር ኖሮ ያረጋገጠው ሀቅ ነው። ከላይ በተጠቀሱት መሰረታዊ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ ግቦች ዙሪያ ሁለቱ ድርጅቶች በፅኑ የሚጋሯቸውን አቋሞች መሰረት በማድረግ ቀጣይ ለሚደረገው ጠንካራና የተቀናጀ የህዝብ ትግል ወሳኝ የማታገያ አጀንዳ እንዲሆኑ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በሃገር አቀፍ ደረጃ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ መላው የሀገራችን ህዝብ፣ በተለይም የአማራ ህዝብና የአዲስ አበባ ህዝብ የተደቀነባቸውን የህልውና አደጋ በትብብር ከመታገል ውጭ ሌላ ተጨባጭ የመፍትሄ አማራጭ እንደሌለ መተማመን ላይ ደርሰዋል።
ከዚህ ቀደም በጋራ አብረውን ለመስራት ንግግር ጀምረው ሳለ በተለያዩ ምክንያቶች በትብብሩ ለመዝለቅ ያልቻሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁንም ጊዜው አለመርፈዱን ተገንዝበው በጎ ፍላጎት ካሳዩን ከግማሽ መንገድ ባላይ ተጉዘን ለመቀበል ዝግጁ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን።
የፈጠርነው ትብብር አርአያ መሆን የሚችልና ከትላንት ለተሻለ አዲስ የፖለቲካ ባህል ማሳያ ፈር ቀዳጅ እንደመሆኑ ከምርጫ በኃላም ትብብሩ ጎልብቶ፤ የሀገራችንን ህዝብ ለዘመናት የቆየ የፍትህ ትግል ዳር ለማድረስ እንዲሁም የመላው ኢትዬጵያዊ የሆነችውን የአዲስ አበባ ከተማን ዓለም አቀፍነት የሚመጥን አመራር ለመስጠት ለመፍጠር ከወዲሁ አብረን መቆም ጀምረናል።
አብንና ባልደራስ የአዲስ አበባ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ዴሞክራሲያዊ መብት አክብረው ከሚቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ትብብር በመፍጠር የከተማዋ ህዝብ በፌደራል መንግስቱ ውስጥ ተወክሎ እንደሁሉም ህዝብ ጥቅሙን ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ትግል የማሳለጥ ሚና እንደሚኖረው ለማሳወቅ እንወዳለን።
አዲስ አበባ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥረት የተገነባች፣የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ ብትሆንም፣ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተነሱ ተረኞች ከተማይቷን በልዩ ጥቅም ስም የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ብቸኛ ንብረት ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ በጋራ አጥብቀን እናወግዛለን። በከተማይቱ እና ነዋሪዎቿ ላይ የተደቀነውን ይህ አደጋ ለመከላከል ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ/ ባልደራስ/ በዋነኛነት እያካሄደ ያለውን ትግል አብን የሚያድንቅ እና በሙሉ ልብ ከጎኑ እንደሚሰለፍ ቃል ይገባል። በአንጻሩም ባልደራስ ፓርቲ በጽንፈኞች ሴራ ኢላማ እንዲሆን በተደረገው የአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍ እና በደል ለማስቀረት በቁርጠኝነት አብን ለሚያደርገው ትግል ክብርና እውቅና እንደሚሰጥ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ስምምነታችን የተበላሸውን የሀገራችንን ፖለቲካ ባሕል በማስተካከል፣ በውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል አብሮ መቆም እንደሚገባ ከማሳየት ባሻገር፣ ሌሎች ለተመሳሳይ አላማ ያነገቡ ፓርቲዎችም ይህን ፈለግ ተከትለው የትብብሩ አካል እንዲሆኑ ፅኑ ፍላጎት አለን።
በመጨረሻም በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ጽንፈኛ ሃይሎች በሚፈጽሟቸው የሽብር ድርጊቶች ምክንያት እየደረሰ ያለውን ሞት፣የአካል ጉዳት፣መፈናቀል እና የንብረት ውድመት ለማስቆም በየእርከኑ ያሉ የፌደራል እና የክልል መንግስታት ሃላፊዎች ተግተው እንዲሰሩ ጥሪ እናቀርባለን።
በተለይ ችግሩ ተባብሶ በሚገኝባቸው የኦሮሚያ፣ የቤንሻንጉል እና አንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች የሚገኙ የመንግስት አስተዳደርና የፀጥታ አካላት ችግሩን የሚመጥን ሀላፊነት በመውሰድ ንፁሀንን ከጥቃት እንዲከላከሉና ወንጀለኞችን ለህግ እንዲያቅርቡ በአፅንኦት እንጠይቃለን።
መሰረተ ቢስ በሆነ ክስ ተወንጅለው ለእስር የተዳረጉትንና የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን የተነፈጉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እናሳስባለን። ትህነግ በለኮሰው ጦርነት በትግራይ ክልል ህግ ለማስከበር እየተካሄደ ባለው ዘመቻ የንጹሃን ዜጎቻችንን ደህንነት እና የሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ልዩ ትኩረት እንዲደረግና የሰብአዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማሳሰብ እንወዳለን።
መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ/ባልደራስ/
አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን
Leave a Reply