ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ዛምቢያ ካቴቴ አውራጃ ውስጥ በበሀገሬው ቺቦላያ ነዋሪዎች በተፈጸመ ጥቃት መገደሉን ዛምቢያ ሪፖርትስ ትናንት በድረ-ገጹ ዘግቧል። አምሳዎቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዛምቢያ የገቡት ምዋሚ በተሰኘው ድንበር በኩል ሲኾን፤ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ከማቅናታቸው አስቀድሞ ካቴቴ ውስጥ በሕገወጥ ቆይተዋል ሲል የአካባቢው ፖሊስ ተናግሯል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ባረፉበት ቦታ በሌሊት በድንገት ባደረሱት ጥቃት ከግድያው ባሻገር ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን መጠነኛ የመቊሰል አደጋ እንደደረሰባቸው የአካባቢው ፖሊስ ኮሚሽነር ሉክሰን ሳካላ ገልጠዋል። ከኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ መካከል 38ቱ በፖሊስ ሲያዙ ማንነታቸው ያልተገለጡ ኹለት ስደተኞች ግን ማምለጣቸውን የፖሊስ ኃላፊው አክለው ተናግረዋል።
የፖሊስ አዛዡ፦ የአካባቢው ነዋሪ በሰፈራቸው ስለመጡ ሰዎች ጥርጣሬ ቢያድርበትም ጥቃት መፈጸሙ ግን ስህተት ነው፤ ማድረግ የነበረባቸው ለፖሊስ ማሳወቅ ነው ብለዋል። ግድያ እና ጥቃት ፈጻሚ ዛምቢያውያን ላይ ፖሊስ የወሰደው ርምጃ ስለመኖሩ ግን ዘገባው አይጠቅስም።
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተደጋጋሚ ወደ ደቡብ አፍሪቃ በሚያደርጉት ሐገወጥ ስደት ዛምቢያ እና ማላዊን እንደመሸጋገሪያ ሲጠቀሙ ይታያል። በኹለቱም ሃገራት ስደተኞቹ ላይ ተደጋጋሚ አደጋ መድረሱ ቢዘገብም ስደቱ ግን አልተቋረጠም። (@ጀርመን ድምፅ)
Leave a Reply