ከትህነግ ጎን ተሰልፈው የነበሩ 120 የአፋር ነፃ አውጪ ታጣቂዎች ሀገርን እንዲያፈርሱ በጥፋት ሀይሉ የታቀደላቸውን ጥፋት ተግባራዊ ሳያደርጉ ወደ አፋር ክልል በሰላም እንዲገቡ መደረጉን የሀገር መከላከያ ሠራዊት አስታውቋል።
ለውጡን ተከትሎ ከኤርትራ በርሀ ወደ ሀገር የገቡት “የኡጉጉሙ” ታጣቂዎች ለአንድ ዓመት ያህል በትህነግ ስልጠና ተሰጥቷቸው ለጥፋት ቢዘጋጁም በመከላከያ እና በአፋር ክልል መንግስት የጋራ ጥረት እንዲመለሱ ተደርገው የሰላም ውይይት መጀመራቸው ነው የተገለፀው።
ታጣቂዎቹ ሲገቡ የተቀበላቸው፣ ያኔ ለመሰደዳቸው ምክንያት የነበረው ትህነግ እድሉን በመጠቀም ለሌላ ጥፋት እንዳሰማራቸው ከሀገር መከላያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የኡጉጉሙ 120 ታጣቂዎች ለአንድ ዓመት ያህል በትህነግ ስልጠና ተሰጥቷቸው ለጥፋት ቢዘጋጁም፤ በመከላከያ እና በአፋር ክልል መንግሥት የጋራ ጥረት በሰላማዊ መንገድ ከእነ ትጥቃቸው ከትግራይ ክልል ወደ አፋር ክልል እንዲገቡ መደረጉ ነው የተገለፀው።
ትህነግ በሀገር ላይ ጥቃት ሲፈፅም የኡጉጉሙ ታጣቂዎች “የአፋር ህዝብ ኢትዮጵያን የመክዳት ታሪክ እንዳላወረሳቸው” በመግለፅ የሰለም ጥሪውን እንደተቀበሉ የታጣቂዎቹ አስተባሪዎች ተናግረዋል።
የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ የሰብዓዊ መረጃ ሀላፊ ብረጋዲር ጄነራል ደምስ አመኑ ትህነግ የኡጉጉሙ ታጣቂዎችን በመጠቀም ዋናውን የጁቡቲ መንገድ የመቆጣጠር እቅድ ነበረው ብለዋል።
የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ የሰብዓዊ መረጃ ስምሪት አባል ኮሎኔል ጤናው ዳምጠው እንደሚሉት ደግሞ ታጣቂዎቹ ስልጠና ሲሰጣቸው የአፋር ክልል ሰላማዊ እንቅስቃሴን ችግር ውስጥ እንዲያስገቡ ጭምር ታስቦ ነበር።
ከሁለት ዓመት ወዲህ መቀሌ የጥፋተኞች ምሽግ ሆና እንደቆየች የሚጠቅሱት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ትህነግ ታጣቂዎችን በመጠቀም አፋርን የማበጣበጥ እቅድ እንደነበረው ተናግረዋል።
መከላከያ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የአፋር መንግስት ታጣቂዎች ወደ ጥፋት እንዳይገቡ ለማድረግ የሰሩት ስራ ውጤት ማስመዝገቡን ያነሱት ርዕሠ መስተዳደሩ ትህነግ ፍላጎቱ አልተሳካለትም ብለዋል።
የኡጉጉሙ ታጣቂዎች በቀጣይ ትጥቃቸውን ፈትተው በፈለጉት ዘርፍ ገብተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ተገልጿል። (ምንጭ:- EBC)
ጎልጉል የድገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply