
ዛሬ (ማክሰኞ) በተካሄደው 5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሰጡት ማብራሪያ ያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፤
የኢኮኖሚው አጠቃላይ ገጽታ፤
- የፍኖተ ብልጽግና እቅዳችን ያለፉትን 3 አመታት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፤
- የአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም መሰረታዊ አጀንዳዎቻችን
- የብድር ጫና መቀነስ
- ተጀምረው የቀሩ በርካታ ፕሮጀክቶች በፈጠነ መንገድ ማጠናቀቅ
- የወጪ ንግዱን ማሻሻልና ማሳደግ
- ገቢን ማሻሻል
- ገበያን ማረጋጋትና የዕድገት ቀጣይነትን ማረጋገጥ፤
- የህዳሴ ግድብ በነበረበት ችግር ምክንያት የአገር ኢኮኖሚ እግሩ ተፈትቶ መሄድ እንዳይቻል አድርጎ ነበር፤
- የወጪ ንግድም ትልቅ ችግር ውስጥ ነበር፤ ባለፈው አመት ለመጀመሪያ ገፊዜ መሻሻል አሳይቷል፤
- እነዚህን አጀንዳ ስንቀርጽ ኮቪድ አልነበረም፤ አንበጣ ጎርፍና ከሁሉ በላይ ደግሞ ግጭት ማጋጠሙ ተጨማሪ ጋሬጣ ሆኖብናል፤
- በግጭት ምክንያት በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ለልማት ማዋል የምንችለውን ለዛ አውለናል፤
- ኢትዮጵያ የኮቪድ እና ሌሎች ጫናዎችን ተቋቁማ ባለፈው ዓመት 6ነጥብ 1 በመቶ እድገት አረጋግጣላች፤
- ይሄ ዕድገት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተቋማትም አዎንታዊ ዕድገት ካስመዘገቡ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ያምናሉ፤
ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት ገቢዋ ምን ይመስላል?
ከገቢ አንጻር የተመዘገቡ ውጤቶች፤

- በ2010 ዓ.ም 176 ቢሊዮን ብር ገቢ አስገብተናል የሚል ነው፤
- በ2011 ዓ.ም 196 ቢሊዮን ብር ነው ያስገባነው፤
- በ2012 ዓ.ም 228.9 ቢሊዮን ብር ነው ያስገባነው፤
- በስምንት ወራት 191 ቢሊዮን ብር አስገብተናል፤
- ይህ የሚታይ እድገት ነው በቂ ግን አይደለም፤
ገንዘብና ገንዘብ ነክ ስራዎች ባለፉት ሶስት ዓመታት፤
- የገንዘብ ስርጭት በ15 በመቶ አድጓል፤
- ቁጠባ በ25 በመቶ አድጓል፤
- የብድር አቅርቦት 38.4 በመቶ አድጓል፤
- አሁን ላይ አገሪቱ ያለባትን የውጭ እዳ ጫና ባለፉት 3 ዓመታት ከነበረበት 37.6 በመቶ ወደ 26.8 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርግል፤
- የብር ኖትን በመቀየራችን ብቻ 6.2 ሚሊዮን ዜጎች አካውንት ከፍተዋል፤
- ይህ የአንድ አንድ አፍሪካ አገራት ሙሉ ዜጎቻቸው አካውንት ከፍተዋል እንደማለት ነው፤ 98 ቢሊዮን ብር ቆጥበዋል፤
- በ2010 ዓ.ም አጠቃላይ የኢትዮጵያ ባንኮች የሰበሰቡት 730 ቢሊዮን ብር ነው፤
- በ2011 የተሰበሰበው 899 ቢሊዮን ብር ነው፤
- በ2012 ለመጀመሪያ ጊዜ 1 ነጥብ 04 ትሪሊዮን ብር ገባን ብያችሁ ነበር፤
- ዘንድሮ (2013) በስድስት ወር ብቻ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ገብቷል፤
ያልፈታው የዋጋ ግሽበት ጉዳይ፤
- የኢኮኖሚ አንድ ነቀርሳ ነው፤
- የሚያጠቃውም አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ነው፤
- መንግሥት ይህንን ችግር የሚፈታ የተለያየ ግብረ ሃይል አደራጅቷል፤
- በከተማው ውስጥ ያለውን የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈታ ግብረ ሃይል ተቋቁሟል፤
- የዋጋ ግሽበቱ መሰረታዊ ተጽዕኖዎች ሲገለጹም፡-
- ምግብ ነክ ወጪ – ከ54 እስከ 60 በመቶ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ገቢያቸውን ይወስድባቸዋል፤
- የቤት ኪራይ እስከ 20 በመቶ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ገቢያቸውን ይወስድባቸዋል፤
- አልባሳት ከ5 እስከ 6 ያለውን አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ገቢያቸውን ይወስድባቸዋል፤
የባንኮች ብድር
- በ2010 ዓ.ም 170 ቢሊዮን ብር ተመድቦ
- ለግል ሴክተር የሄደው 45 በመቶ ብቻ ነው፤
- 55 በመቶውን ድርሻ የወሰደው መንግሥት ነው፤
- በዓመቱ 2011 ዓ.ም የግሉን ሴክተር ለማነቃቃት በማለም 236 ቢሊዮን አበደርን፤
- ከዚህ ውስጥ ለግሉ ሴክተር የተሰጠው 61 በመቶ ሲሆን መንግሥት 39 በመቶውን ድርሻ ወስዷል፤
- 2012 ዓም 271 ቢሊዮን ብር አበድረናል፤
- የግሉ ሴክተር ድርሻ 70 በመቶ ነበር፤
- በ2013 ዓ.ም በስድስት ወር ብቻ 155 ቢሊዮን ተሰጥቷል፤
- 74 በመቶው ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ ነው፤
በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶችን በተመለከተ፤
- የማይተኙልን ሰዎች ስራዎችን በትኩረት እንዳንስራ በየቦታው የሚፈጠር ግጭት አለ፤
- ይህ ግጭት ጊዜ፣ ጉልበት እና አመራር ይወስዳል፤
- የልማቱንም ስራ ይወስዳል፤
- ነገር ግን ግጭትና ሞት በቀላል በምኞት አይቆምም፤
- ስራ ይፈልጋል፤
- የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዜጎች ወደውና ፈቅደው እንዲሳተፉ ይፈልጋል፣
- እስካሁን ያያነው በፌስቡክ ነው የሚሳተፉት፤
- ፉከራ ብቻ ነው፤ በአካል ሄዶ አንድም ሰው የሚሳተፍ የለም፤
- ይህ ተቋም በሰው ሀብት መገንባትና መጠናከር ይኖርበታል፤
- ሰላም፣ ልማት ዕድገት ይምጣ ሲል ወጣቱ በእነዚህ ተቋማት መሳተፍም ይኖርበታል እና ያልተሳተፈበትን ችግር አልተፈታም ማለት ተገቢ አይደለም፤
የአባይ ግድብ በተመለከተ፤
- የህዳሴን ግድብ አይኑን ገልጦ የማይጠብቅ ዜጋ የለም፤
- ከአንድ ኩባንያ ጋር ብቻ ያለውን ፈተና ከብር አንጻር ብንመለከተው ከባድ ፈተና ሆኖ ነው ያለው፤
- ከለውጡ ወዲህ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ በህዳሴ ግድብ የአንድም ብር ዕዳ የለብንም፤
- ለተሰሩት ስራዎች ሁሉ ከፍያዎች ተፈጽመዋል፣
- ከለውጡ በፊት በነበረው ችግርና በመጓተቱ ምክንያት ሳሊኒ በህዳሴ ግድብ በአንድ ቢሊዮን ዶላር ከሶናል፤
- ከብዙ ድርድርና ውይይት በኋላ ክሱ ቀርቶ ባለፈው ሳምንት በ450 ሚሊየን ዮሮ ነውየተሰማማነው፣
- ይህ ማለት የማናውቀው ከ20 ቢሊየን ብር በላይ ዕዳ ወድቆብናል ማለት ነው፤
ነዳጅን በተመለከተ፤

- ኢትዮጵያ ለነዳጅ በዓመት እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር እናወጣለን፤
- ወገባችንን ከሚቆርጡ ነገሮች መካከል አንዱ ነዳጅ ነው፤
- ከጎረቤት ሀገራት መካከል በአንዷ ሀገር የአንድ ሊትር ነዳጅ ዋጋ 67 ብር ነው፤
- በሌላኛው ሀገር 79 ብር ዝቅተኛ የሚባለው ኬንያ ሲሆን 38 ብር ነው የሚሸጠው እኛ ሀገር ግን 25.6 ብር ነው፤
- የትኛውም ጎረቤት ሀገር እኛ ያለንን የሊትር ዋጋ የለውም፤
- ይህ የሆነው ከተለየ ጉድጓድ ስለምንቀዳ ሳይሆን መንግሥት ስለሚደጉም ነው፤
- መንግሥት ባለፉት ጥቂት ጊዜያት ብቻ የ30 ቢሊዮን ብር ድጎማ አድርጓል፤
- በያዝነው ወር ብቻ 3 ቢሊዮን ብር መንግሥት እዳ ተሸክሟል፤
- ገበታ ለሀገር ተብሎ በዓመት 4 ቢሊዮን በሚሰበሰብባት ሀገር በአንድ ወር ለነዳጅ 3 ቢሊዮን ብር ድጎማ ይደረጋል፤
- ይህ ነዳጅ ብዙ ችግር አሉበት፤ ከምንጩ ተነስቶ ገበያ ላይ እስከሚደርስበት ድረስ ችግር አለበት፤
- በባቡሮች ነዳጅን ማምጣት ብንችል ብዙ ወጪን ይቀንስልን ነበር፤
- ነዳጅ በኮንትሮባንድ በየቦታው ይቸበቸባል፤
- በቂ የሆነ የሽያጭ መሰረተ ልማት የለንም፤
- የዓለም የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ሲሄድ እኛ ደግሞ የነዳጅ ዋጋውን ዝም ብለን ከለቀቅነው የዋጋ ግሽበት ስለሚከሰት መንግሥት ለዋጋ ግሽበቱ በሚል ብዙ ነገሮችን ይሸከማል፤
ስለ ህወሓት ጁንታ፣ ስለኦነግ ሸኔ እና መሰል ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ፤

- የህወሓት አመራሮችን፣ የማዕከላዊ ኮሚቴውን ሁሉ እባካችሁ ብዬ ለምኛለሁ፤ አስለምኛለሁ፤
- ዋና ዋና ባለሃብቶችን ታዋቂ ግለሰቦችን አሰባስቤ በሚስጥር ልኬ እባካችሁ ለምኗቸው ብዬ ሽምግልናም ልኬያለሁ፤
- እብሪት ከፉ ነው፤ አሁንም ያላችሁ አመራሮች ከእብሪት ልትቆጠቡ ይገባል፤
- በህግ ማስከበሩ ከ300 በላይ የኦነግ ሸኔ ሽፍታ አብሮ ሲዋጋ ይዘናል፤
- ኦነግ ሸኔ ለማንም አይበጅም፣ ለሰው ዘር አይበጅም፤ ለኢትዮጵያም ጠላት ነው፤
- ወለጋ ህዝብ ስቃይ ውስጥ በነበረበት አንድም ሰው አልተናገረለትም፤ ከውጭም ከውስጥም፤
- ኦነግ ሸኔ በሰላም ተወዳደር ሲባል እምቢ ብሎ የህወሓት ቡችላ ሆኖ ነው አርሶ አደር ገድሎ ሲፎክር የነበረው፤
- ወለጋ ውስጥ የሞቱት አማራ አርሶ አደሮች አማሮች አይደሉም፤ የኦሮሞ አካል ናቸው፣ እነሱን መግደል ኦሮሞን መግደል ነው፤
- በትግራይ ውስጥ ሰዎችን ማፈን አለ፤ ሌለው ቀርቶ ዕርዳታ የሚሰጡ ሰዎች ይታፈናሉ፣ ይገደላሉ፤
- ዕርዳታ እንዳይሰጡ ተደርጓል፤ በትግራይ ብዙዎች የደረሰውን በደል እያወቁም ሊክዱ ይፈልጋሉ፤
- በአንድ ቀን በ200 ቦታዎች ላይ ነው በተጠና መልኩ በተመሳሳይ ሰዓት ጁንታው ጥቃት የፈጸመው፤
- ኦነግ ሸኔ የኢትዮጵያ ጠላት ነው፤ ለኦሮሞ አይበጅ፤ ለአማራ አይበጅ ለማንም አይበጅም
- ትግራይ ውስጥ አሁን ሰው ይታፈናል፤ ዕርዳታ የሚሰጡ ሰዎች ሳይቀር እየታፈኑ ነው፤ ከዚህ ቀደም ካደረጉት ጥፋት በላይ አሁን የሚያደርጉት ይብሳል፤
- ጁንታው ያኔ 200 ቦታዎች ላይ በተመሳሳይ ሰአት አንድ ላይ ነው ጥቃት የፈጸመው፤
- አማራ ክልል ላይ ጥቃት የፈጸመው ይሄው ሃይል ነው፤ ዓላማውም ጎትቶ ወደ ግጭቱ ማስገባት ነው፤
- ኤርትራ ላይ የተኮሰው ይሄው ሃይል ነው፤ ችገሩን ቀጣናዊ ለማድረግ አስቦ ነው፤
- በትግራይ ከ30 ሺህ በላይ እስረኛ ተለቋል፤ መቀሌ ብቻ 10 ሺህ እስረኛ ተለቆ ዝርፊያ ፈጽሟል፤
- ለትግራይ ህዝብ ጦርነት ግጭት አይገባውም፤
- የእኛ የህግ ማስከበር ሶስት ግልጽ ዓላማዎች አሉት
- በዘሩ ብቻ በማንነቱ ብቻ ለይተው መከላከያ ሠራዊትን የጨፈጨፉትን ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ ነው፤
- ኢትዮጵያን አምነው ለ20 አመት በክልሉ የኖሩ ታግተው የተወሰዱ ከ1000 ሺህ በላይ መኮንኖችን ማስፈታት ነው፤
- መቶ በመቶ አስፈትተናል፤ የገደሏቸውን ቀብረናል፤ የተዘረፍነውን አስመልሰናል፤
- ይህ ክልል ወደ ምርጫ ሄዶ ራሱን እንዲያስተዳድር ነው፤ አሁን ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ በጊዜያዊ አስተዳደር ራሱን እያስተዳደረ ነው፤ ሊታገዝ ይገባዋል፤
- የተበተነው ርዝራዥ ሃይል በየቦታው እየሆነ በመከላከያ ላይ እየተኮሱ ሽንቆጣ ፈጽመዋል፤
- ከዚህ በኋላ ህወሓት ማለት በነፋስ የተበተነ ዱቄት ማለት ነው፤ ከዚህ በኋላ ተሰብስቦ ዱቄት አይሆንም፤
- የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆኖ በትግራይ ክልል ወንጀል የፈጸመ ካለ በህግ ይጠየቃል፤
- በትግራይ ክልል ስለተፈጸመ ችግር የሚያነሱ በሰሜን ዕዝ ላይ ስለተፈጸመው ግፍ አያነሱም፤
- በማይካድራ ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም አካባቢ አልተፈጸመም፤ ግን ተረስቷል፤
- ቤንሻንጉል ላይ ስላለው ጭፈጨፋ ማንም አይናገርም፤ ትኩረት ሁሉ አንድ አካባቢ የሆነው የተንሸዋረረ እይታ ስላለ ነው፤
- በትግራይ ከተካሄደው ኦፕሬሽን በኋላ 4.2 ሚሊዮን ህዝብ መግበናል፤
የአማራ ልዩ ኃይልን በተመለከተ፤
- የህግ ማስከበር ዘመቻው ሲጀመር የአማራ ልዩ ኃይል ተደራጅቶ መሬት ለማስመለስ የገባ በማስመሰል የሚነገረው ስህተት ነው፤
- ተገቢም አይደለም፤
- ሶሮቃና ቅራቅር ላይ ጦርነቱን የጀመረው አማራ ልዩ ኃይል አይደለም፤
- ልዩ ኃይሉ ባህርዳር ተቀምጦ ነው ጦርነት የተከፈተበት፤
- በዚህም ምላሽ አልሰጠም፤
- የአማራ ልዩ ኃይል በህግ ማስከበር ዘመቻው ተጋብዞ ነው የተሳተፈው፤
- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ስለነበርን የአማራ ልዩ ኃይል ኃላፊነት ተሰጥቶት በህግ ማስከበር ዘመቻው ተሰማርቷል፤
- የአማራ ልዩ ኃይል እየሞተ ያለው ሀገር የመጠበቅ መንግሥት የሰጠውን ተልእኮ እየፈፀመ ስላለ ነው፤
- የአማራ ልዩ ኃይልን ከፈለግን ሶማሌ ክልል ላይ ወስደን ተልዕኮ መስጠት እንችላለን፤
- የአማራ ልዩ ኃይል ያጠፋው ጥፋት ካለ ታይቶ በህግ ይዳኛል፤
- ለጊዜው ግን ልክ ከሌላ ሀገር እንደመጣ አጥፊ ማየት ተገቢ አይደለም፤
- መሬትን በሚመለከት በድንበር ኮሚሽንና በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል በሕግ ይፈታል
ከዚህ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሥር ዓመት የልማት ግቦች መካከል የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን አንዱ መሆኑን ገልጸዋል
ትኩረት ከተሰጣቸው የአስር አመት የልማት ግቦች መካከል የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን አንዱ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንደገለፁት፤ እየተከሰተ ያለውን ኑሮ ውድነት ለመግታት የግብርናውን ክፈለ ኢኮኖሚ በማዘመን ምርታማነትን ማሰደግ ያስፈልጋል። ለዚህም በአሰር ዓመቱ የልማት እቅድ ልዩ ትኩረት ከተሰጠው የልማት ዘርፍ አንዱ ግብርናውን እንዲዘምን ማድረግ ነው። የተቀናጀ የመስኖ ልማትና ኩታገጠም ግብርናን በማዘመን መስራት መሆኑንም ገልፀዋል።
ፍኖተ ብልፅግናን ለማረጋገጥ አቅዶና አልሞ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአስር አመቱ ፍኖተ ብልፅግና እቅድ ዓላማ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ‹‹ፕራግማቲክ›› የኢኮኖሚ መር በመከተል የሚመጣ መሆኑን፤ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የኢኮኖሚ ዘርፍንና ተዋናይን ማሳደግ እነደሚገባ፤ ይህን ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚነትን ማሳደግና ድህነትን መቀነስ መቻል የአስሩ ዓመት የልማት ግብ ተደርጎ እተሰራበት እንደሆነም አብራርተዋል።
የግብርነውን ዘርፍ ከሚያዘምኑት መካከል በኩታ ገጠም እርሻ ማልማት መቻል አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህም ከሚሊዮን ሄክታር በላይ እየለማ እንደሆነ ገልጸው ከ50 በመቶ በላይ ማሳደግ ከተቻለ እንደሀገር የሚታዩ የግብርና ምርት እጥረቶችን መቅረፍ ይቻላል ብለዋል።
ጤፍ ሊቀር የማይችል ምርታችን በመሆኑ ጤፍ የሚዘራና የሚያጭድ ማሽን ወደ ሀገር ገብቷል ያሉት ዶ/ር አብይ፤ ይህን ማስፋት ከተቻለና የበጋ እርሻና መስኖን ማሻሻል ከቻልን የሚታየውን የዋጋ ውድነት በምርት አቅርቦት መፍታት አንዱ አማራጭ ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል። (ኢፕድ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
የሃገሬ ሰዎች ምንም እንኳን ፊደላትን ባያውቁ የኑሮን ዘይቤ ለይተው እንዳወቁ ጥለውት ባለፉት ሃሳቦቻቸው እንረዳለን። “ከሰው መርጦ ለሹመት” ይላሉ። ከ 1966 ዓ. ም በህዋላ ሳንጃ ባፈሙዝ ተብሎ ሰው ሁሉ ከመተራመሱ በፊት ነገሮች ከዚያ ወዲያ እንደሆነው አልተካረሩም ነበር። መጤውን የቁስ አካል ፍልስፍና ከተቀበልን ወዲህ ግን ያው ሰውና ግዑዝ ነገር አንድ ሆኑ። አንድ ጊዜ አንድ እስር ቤት ውስጥ ሰውዬው ለምርመራ ውሎ ይመጣና ተሸክመን የታሰርንበት ክፍል ውስጥ አስገብተን ያው በቤቱ ህግ መሰረት (የእስር ቤታችን ህግ) የቤቱ አለቃ ከቤተሰብ የሚመጡልንን ምርጥ ምርጥ ምግብ ለእርሱ እንዲሰጠው ያዛል። ቶሎ እንዲያገግም በማለት። ታዲያ በራሱ እጅ መብላት ስለማይችል እጆቹ ከእስሩና ከዱላው የተነሳ ደንዝዘው የሚያበላው ይመደብለታል። አብይው ለራሱ እየበላ እሱንም ሲያበላ በቁስለኛው ላይ ምንም ለውጥ ስይኖር የሚያጎርሰው ተስማማውና ወፈረ። ሳይታሰብ ሁለቱም (አብይና ቁስለኛ) በአንድ ቀን ተጠርተው በምርመራ ስም ኢፍትሃዊ የሆነ ግፍ ተፈጽሞባቸው ይመለሳሉ። ሃገርህን እወቅ በሚለው የእስረኛው የመዝናኛ ጊዜ የቤቱ አለቃ ቀልድ፤ ተረት፤ ታሪክ፤ ወይም ሌላ ሃሳብ ያላችሁ ለቤቱ አካፍሉ መድረኩ ክፍት ነው ያላል። ያኔ መጀመሪያ ተደብድቦ በሰው እጅ ይመገብ የነበረ (ለነገሩ መመገብ ብቻ ሳይሆን ቂጡም የሚጠረገው በሌላ ሰው ነበር) እኔ አለኝ ሃሳብ ይላል። አፍ አይሞት አይደል። ጎን ለጎን ሆነን ስንደበደብ ለመርማሪው ምን እንዳለው ታውቃላችሁ። ገና አፉ ውስጥ ኳስ አልከተቱም ነበር
ጊዜ ይመጣና ይህ ሁሉ ተሽሮ ገራፊው ሲገረፍ አሳሪው ሲታሰር ያኔ እኔ ባልኖር የሆነውን ባላይ
ባለሁበት ሁኜ እንከተከታለሁ እኖራለን ያሉት በጎኔ ተቀብረው፡
ታዲያ ይህ ሁሉ ከወያኔ የሙቀጫ ልጅ መሆንና ለንፋስ ከተሰጠ ድቄት ጋር ምን አገናኘው ትሉ ይሆናል። እውቁ ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ
ላድነው ስላልቻልኩ እኔ ለመግደሌ
ምሥክር አያሻም ይሄ ነው በደሌ … ጠ/ሚሩ እንዲህ ሲደሰኩሩ ሌሎች ነፍሴ አውጪኝ በማለት ከጥይት በረዶና ከአራጅ መንጋ የሚሮጡበት መጠለያ ጠፍቶ በየቦታው የወደቁበትና የሚወድቁበት ሃገር ናት። ያኔ ድሮ ” አንድ ጥይትና አንድ ሰው እስኪቀር” እያሉ ሰውን ያፋክሩ የነበሩት ሃገርና ወገንን ለጠላት አስረክበው በየስርቻው እንደገቡት ሁሉ አሁንም የቀን ጡሩንበኞች ያደነቁሩናል። በመንደርና በቋንቋ በክልል አስተሳሰብ ብሄርን ተገን አርጎ የሚፈራከተውና ሰውን እንደ እንስሳ አጋድሞ የሚያርደው የኦሮሞ ስብስብ እይታው ምንድን ነው? መጨረሻው ምን ግብ አለው ብሎ በሰከነ መንገድ ላሰበው መልሱ “እብደት” ነው። 70 ዓመት ሙሉ እልፍ ህዝብ ያለፈበት የሩሲያው አብዪት እንኩትኩቱ ሲወጣ ምን አይነት ልብ ያለው ፓለቲከኛ ነው ዛሬ በዘሩ የሚሰለፍ? እህቱን ወንድሙን ሥራ አለ፤ ወደ ውጭ እንላካችሁ እያለ በሰው ህይወት በሚነግድ ጠማማ ትውልድ መካከል እንዴት ነው ሃገራዊ እይታ የሚኖረው? እብዶች በተከመረ ሣር ላይ ነዳጅ ሲያርከፈክፉ ራሳቸውም አብረው የሚጋዪ የፓለቲካ ስብስቦች ያሉባት ምድር ናት። ለእኔ እንጂ ለእኛ የለም። በቅርቡ የእማየን ለአባዬ አይነት አቲካራ በፓርላማ ስንሰማ ህግና ደንብ እንደ ሌለ ተረድተናል። አስለቃሽ ለገንዘቧ እንጂ ስለሞተው ሰው ደንታ የላትም። የሃበሻው ፓለቲካም የአስለቃሾች ፓለቲካ ነው።
አሁን በሃገሪቱ በተለያዪ ክፍሎች የሚለኮሱት እሳቶች ሁሉ ሆን ተብለው የሚቀጣጠሉ፤ በወያኔ ተላላኪዎችና በአኮረፉ የፓለቲካ ውሾች የሚደረጉ ተንኮሎች እንጂ ነሲባዊ አይደሉም። ገናም ብዙ ጉድ ያመጣሉ። ነፋስ የወሰደው ድቄትና የሙቀጫ ልጅ የተባለው ወያኔ እድሜ ለሱዳን ስደተኛውን ልክ እንዳለፈው እያሰለጠኑ በመላክ ሃገራችን ማመሳቸው እየታየ ነው። የሱዳንም ድንበር ዘልቆ መግባት ከአሜሪካና ከግብጽ የተሰጣቸው ተልዕኮ እንጂ በራሳቸው አስበውት አይደለም። ይህንና ሌላውንም በምድሪቱ ላይ የሚተበተበውን የውስጥና የውጭ ሴራ ለመበጣጠስ መጀመሪያ የሃገር ቤቱን ሴራ እርም ማሰኘት ያስፈልጋል። የውስጡ ጭጭ ምጥጥ ሲል የውጭውንም ለይቶ ለመታገል መንገድ ይከፍታል። ከዚህ በተረፈ የዚህም የዚያም የክልል ጡሩንባ የሚነፋው ሁሉ መላ ቢስ ነው። ሰው በሰውነቱ የሚከበርባት ሃገር እንደገና ለማቆም አሁን ያለው ህገ መንግስት መለወጥ አለበት። ያ እስካለሆነ ድረስ ድቄቱም ሆነ ሞቀጫው ስምና ቅርጽን ለውጦ አፍራሽ ሥራውን ከምሰራትና ሃገራችን አንድ ሆና እንዳትኖር መጣሩ አይቀሬ ነው። ትላንትም መከራ፤ ዛሬም መከራ መጪውም ደግሞ የት ላይ እንደሚያደርሰን የሚታወቅ ነገር የለም። በቃኝ!