
በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ሼህ ሀሰን የበሬ ሪፈራል ሆስፒታል ማዕከሉ በ27 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የኩላሊት እጥበት (ዳያሊሲስ) ማዕከል ዛሬ በሶማሊ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፋ ሙሁመድ ተመረቀ::
ከግንባታ ወጪው 40 በመቶ የሚሆነው በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት በሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች፤ ቀሪው 60 በመቶ ደግሞ በክልሉ መንግሥት የተሸፈነ መሆኑ ታውቋል፡፡
ማዕከሉ 10 ማሽኖች እንደተገጠሙለት እና በቀን ለ20 ሕሙማን የኩላሊት እጥበት አገልግሎት እንደሚሰጥ የሶማሊ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ሸርማርኬ ሸሪፍ ገልፀዋል።
የሶማሊ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፋ ሙሁመድ በበኩላቸው ማዕከሉን የማቋቋም ሃሳብ ያፈለቁ ወጣቶችን አመስግነው የክልሉ መንግስት ወደፊትም ለህዝቡ ፋይዳ ያላቸውን ሃሳቦች ለሚያፈልቁ ወጣቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።
በመንግሥትና ህዝብ ትብብር ተገንብቶ ዛሬ የተመረቀው ማዕከል መንግሥት እና ህዝብ በቅንጅት ከሰሩ በአጠረ ጊዜ ልማትን ማረጋገጥ እንደሚችሉ ያሳያል ብለዋል።
ለማዕከሉ አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ፣ የኩላሊት ሕሙማን ለሕክምና ወደ ውጭ ሀገራት የሚያደርጉትን ጉዞ ለማስቀረት ይሰራል ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ።
ማዕከሉ ለኩላሊት ሕሙማን በይፋ የእጥበት አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ ጉብኝትም ተደርጓል።
በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሕክምና ባለሙያዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች መገኘታቸውን ከሶማሊ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply