በመጀመሪያ ደረጃ “የትግራይ ህዝብ” ስል ከኢትዮጵያ ህዝብ በተዘረፈ ሃብት የቅንጦት ህይወት የሚኖሩትን፣ በስርቆት ሃብት አጉል የሚቀብጡትን የካድሬ ልጆችና ወዳጆች አይመለከትም። “የትግራይ ህዝብ” ስል በህወሓት ድጋፍና ድጎማ የሚኖሩ የድርጅቱን አባላትና ፅንፈኛ ደጋፊዎች አይመለከትም። የእነዚህ ሰዎች ስኬት እና ውድቀት፣ ድህነት እና ሃብት፣… በአጠቃላይ ሁሉ ነገራቸው ከህወሓት ጋር የተቆራኘ ስለሆነ የድርጅቱ አመራሮች የደገፉትን ይደግፋሉ፣ የተቃወሙትን ይቃወማሉ። የእነሱ ዕለት-ከእለት ኑሮ ከህወሓት መኖርና አለመኖር ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ህወሓት የህልውናቸው መሰረት ነው። በእርግጥ እነዚህ ሰዎች የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች “የህወሓት አፈ-ቀላጤዎች” እንጂ “የትግራይ ህዝብ” ሊሆኑ አይችሉም፤ እነሱ የህወሓት ካድሬዎች እንጂ የትግራይ ህዝብ አይደሉም!
ከዚያ ይልቅ “የትግራይ ህዝብ” በፌስቡክ እና ቴሌቪዥን ሲነዛ የሚውለው የፖለቲካ ወሬና አተካራ ለማዳመጥ ግዜና ፍላጎት የሌላችሁ፣ ከዕለት ወሬ ይልቅ የዕለት ጉርስን የሚያስጨንቃችሁ፣ በህወሓት ጭቆና ላይ የኑሮ ዕዳ የተጫናችሁ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የሌላ ፓርቲ አባል ወይም ደጋፊ መሆን የሚያስከትለውን አደጋ በመፍራት፣ በነዋሪነት ብቻ ማግኘት የሚገባችሁን ጥቅምና አገልግሎት የህወሓት አባል ካልሆናችሁ አታገኙም ስለተባላችሁ አሊያም ደግሞ ከህወሓት ካድሬዎች ጥብቅ ክትትል እንዲሁም ዛቻና ግልምጫ ለመገላገል ስትሉ የህወሓት አባል ወይም ደጋፊ የሆናችሁ፤ እኔም በእናንተ ቦታ ብሆን የማደርገውን በማድረጋችሁ እንደ ጥፋት ወይም ስህተት ሊወሰድ አይገባም። ስለዚህ ምርጫና አማራጭ በሌለበት የህወሓት አባል ለመሆን ወይም የድርጅቱ ደጋፊ ለመምሰል የተገደዳችሁ በሙሉ እናንተም “የትግራይ ህዝብ” ናችሁ።
ውድ የትግራይ ህዝብ ሆይ… የህወሓት አመራሮችና አፈ-ቀላጤዎች በነገው ዕለት “መሬት አንቀጥቅጥ” የሆነ የድጋፍ ሰልፍ በመቀሌ ከተማ እንደሚካሄድ እየገለፁ ይገኛል። እነዚህ የህወሓት ካድሬዎች በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለማመን የሚከብድ በደልና ስቃይ ሲፈፅሙ የነበሩ ሌቦችና ጨካኞች አሊያም ለዚህ እኩይ ምግባራቸው ጥብቅና የቆሙ ህሊና-ቢስ የሆኑ ሆድ አደሮች ናቸው። ላለፉት 27 አመታት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ቅጥ-ያጣ ዘረፋና ጭካኔ የተሞላው ተግባር በመፈፀማቸው ለውርደትና ውድቀት የተዳረጉ፤ የተቀረው ዓለም በገዛ ሀገራቸው ላይ በፈፀሙት ግፍና በደል አንቅሮ የተፋቸው፣ ከኢትዮጵያ ውጪ መሸሸጊያ ጥጋት የሌላቸው፣ ከህግና የህሊና ፍርድ ለማምለጥ ወደ ትግራይ በመሸሽ በመካከላችሁ የተደበቁ ጉዶች ናቸው።
ከኤርትራ ህዝብ ጋራ አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ በመግባት የኢትዮጵያን ህዝብ ለጦርነት የማገዱት እነዚህ ጉዶች ናቸው። ለሁለት አስርት አመታት ያህል የኤርትራና የትግራይ ህዝብን የለያዩት እነሱ ናቸው። በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ከተስማሙ በኋላ ውሳኔው ተግባራዊ ሲሆን አምርረው የተቃወሙት እነሱ ናቸው። በአቶ ስዩም መስፍን እና መለስ ዜናዊ የተፈረመውን የአልጄርስ ስምምነት ዶ/ር አብይ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን ሲገልጽ “የኢሮብ ማህብረሰብን ለሁለት ይከፍላል” በሚል ሰበብ በተለያዩ የትግራይ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ የጠሩት እነዚህ የህወሓት አመራሮችና ደጋፊ ልሂቃን ናቸው። የሰላም ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት በአስመራ ከተማ ያልተገኙት እነሱ ናቸው።
ሆኖም ግን የሰላም ስምምነቱ ፀድቆ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላም ሲወርድ፤ ለሁለት አስርት አመታት የተለያዩት የኤርትራና ትግራይ ህዝቦች ዳግም ሲገናኙ በመቀሌ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ የጠሩት እነዚሁ የህወሓት ጉዶች ናቸው። ከኤርትራ ጋር የሚደረገው የሰላም ስምምነት የትግራይ ህዝብን ጥቅምና ተጠቃሚነት ይፃረራል ብለው በማለት የተቃውሞ ሰልፍ የጠሩት ጉዶች ወር ሳይሞላው የድጋፍ ሰልፍ ጠሩ። በዚህ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ያደረገውን ጠ/ሚ አብይ አህመድ እየተቃወሙ፣ ሁለቱን ህዝቦች ጦርነት ውስጥ የማገደውን ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ሲያወድሱ እንደነበር ይታወሳል። ለሁለት አስርት አመታት ሰላም ማውረድ የተሳነውን መሪ እያወደሱ በሁለት ወራት ውስጥ ሰላም ያወረደውን መሪ መቃወም በሽታ እንጂ የጤና ሊሆን አይችልም።
በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል እነሱ በቀሰቀሱት ግጭት ብዛት ያላቸው የአማራና ኦሮሞ ተወላጆች በተገደሉበት ሳምንት “በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የብሔር ጥቃት ይቁም” በሚል ሰላማዊ ሰልፍ መጥራታቸው ይታወሳል። ወጣቶችን የጦር መሳሪያ አስይዘው አደባባይ እንዲወጡ ካደረጉ በኋላ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች “ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ“ የሚል ዲስኩር አሰሙ። አዛውንት እናቶችን በትልቅ ጎራዴ ላይ የትግራይን ባንዲራ እያውለበለቡ እንዲወጡ አድርገው አረንጓዴ፥ ቢጫ፥ ቀይ ባንዲራ አክሱም ጹዮን ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ እንዳይውለበለብ ከልክለዋል። እናቶችን በአደባባይ ጦርነት እንዲቀሰቅሱ የሚያደርጉ፣ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ስለ ሰላም እንዳይፀልዩ የሚያውኩ፣… ፈሪሃ-እግዚያብሔር የሌለባቸው፣ የሰይጣን መንፈስ የተጫናቸው ክፉዎች ናቸው።
የትግራይ ህዝብ ሆይ…. የህወሓት ካድሬዎችና የእነሱ ድቀመዛሙርት፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ የዘረፉት ሃብት መላ ያሳጣቸው፣ የንፁሃን ደምና እምባ ያሰከራቸው፣ ህሊናቸው ታውሮ ማስተዋልና ማመዛዘን የተሳናቸው፤ ጥሩና መጥፎ፣ ትክክልና ስህተት፣ ሥራና ወንጀል፣ ሰላምና ጦርነት የተምታታባቸው ድኩማኖች ናቸው። ባለፉት ወራት በተግባር እንደታዘብነው፤ እነዚህ ሰዎች “የድጋፍ ሰልፍ” የሚጠሩት ሽንፈትና ውርደታቸውን ለመሸፋፈን፣ “የተቃውሞ ሰልፍ” ሲጠሩ ደግሞ ለትግራይ ህዝብ መልካም የሆነን ነገር ለማስተጓጎል እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
ህወሓት ይሄን ሁሉ ሸርና አሻጥር የሚፈፅመው ከተጠያቂነት ለማምለጥ ነው። በመሆኑም የትግራይን ህዝብን ጦርነት ውስጥ በመማገድና ኢትዮጵያን በማፍረስ ዕድሜውን በአንድ ሐሙስ ለማራዘም ጥረት ማድረግ ከጀመረ ሰነባብቷል። በትግራይ ህዝብ ላይ ከእድገትና ልማት ይልቅ ውድቀትና ዕልቂት የሚደግሱ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ደህንነት እነሱን ዕረፍትና ጤንነት የሚነሳቸው ሰዎች ከውድቀት አፋፍ ላይ ናቸው። ሽንፈትና ውድቀታቸው አይቀሬ ነው። የትግራይ ህዝብ ግን ከህወሓቶች መምጣት በፊት እንደነበረ ሁሉ ከእነሱ ውድቀት በኋላም ይኖራል። ኢትዮጵያ በህወሓት አልተገነባችም፣ በህወሓት አትፈርስም።
ፎቶ፡ People of ETHIOPIA Gallery
Tadesse says
That is true,here includes educated people of any kind too.
Gizachew says
ሕወሐት በበርካታ የትግራይ ከተሞች የተካሄዱትን ዓይነት ሰልፎችን በመላ ኢትዮጵያ በኢሕአዴግ ስም በማቀናበር ሕዝብ ደገፈኝ፣ ሕዝብ ተቀበለኝ፣ ሕዝብ ግዛኝ ብሎ ሾመኝ፣ ሕዝብ ድምጹን ሰጠኝ፣ በምርጫ ማሸነፌን ሕዝብ መሰከረልኝ ሲለን የከረመ ቡድን መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። ሕወሐት በጎዳናወችና በአደባባዮች የሰልፍና የፈንጠዝያ ፕሮግራሞችን በማካሄድ ድራማ በመስራትና በማሰራት የታወቀ ቡድን ነው። ሕወሐት በዚህ መሰሉ ዐይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ የሚል የአደባባይና የጎዳና ድራማ በመስራትና በማሰራት ጥርሱን ነቅሎ አድጎ፣ ያረጀ ቡድን መሆኑን መርሳት አይገባም። ሕወሐት በኢሕአዴግ ስም እስከ 2009 ዓም ድረስ በመላ ኢትዮጵያ የብሄረሰቦች ቀን፣ የባንዲራ ቀን፣ የግንቦት 20 በዓል እያለና እያጭበረበረ ተመረጥኩ ብሎ በሚደነፋባቸው ምርጫወች ማግስት አንዴ ተማሪወችን ሌላ ጊዜ ደግሞ ሕዝብን በመላ ኢትዮጵያ ሲያሰልፍ የኖረ ቡድን ነው። ባለፉት ወደ 25 ለሚሆኑ ዓመታት በአማራ፣ በኦሮሞ፣ በጉራጌ፣ በሲዳማ፣ በወላይታና በሌሎችም ምድሮች በተካሄዱት የተለያዩ ሰልፎች የየአካባቢው ሕዝብ አምኖባቸው እንዳልተሰለፈባቸው ሁሉ በትግራይ ከተሞች በተካሄዱ ሰልፎች የወጣው ሕዝብም በጅምላ የደብረጽዮን የመሸፋፈኛ ንግግር አምኖ ተቀብሎ፣ በመወሰድ ላይ ያሉ እርምጃወችንም ተቃውሞ ወደ አደባባይና ወደ ጎዳናወች የወጣ አለመሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል። በትግራይ ከተሞች የተካሄዱ ሰልፎችን ምክንያት በማድረግ የትግራይ ሕዝብ ዘራፊወችንና ግፈኞችን ደግፎ ሰልፍ ወጣ ብለን ሕዝቡን በጅምላ የኢትዮጵያ ጠላት አድርጎ ለመፈረጅ ከመጣደፋችን በፊት በመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይወድ በግድ ይሰለፍ የነበረበትን ጊዜ በማስታወስ አመዛዛኝ ፍርድ መስጠትና ሚዛናዊ አስተሳብ መያዝ ይገባናል። ነገሩን ቀለል አድርጎ ለማየት ከዓመታት በፊት በመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ ባላመነበት ጉዳይ በግዴታ ወይም በውዴታ-ግዴታ ወደ ጎዳናና ወደ አደባባይ ይወጣ እንደነበረው ሁሉ ዛሬ ደግሞ ከወያኔ አገዛዝ ያልተላቀቀው የትግራይ ሕዝብ ገና በመሰለፍ ላይ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።