
የዛሬ ሳምንት ረቡዕ ወደ አዲስ አበባ ሊጓዝ ከነበረው መንገደኛ ላይ ዋሽንግተን በሚገኘው ደለስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአሜሪካ ጉምሩክና ድንበር ተቆጣጣሪዎች የተያዘው ገንዘብ 99 ሺህ ዶላር የሚጠጋ እንደሆነ ተነግሯል።
ቢቢሲ እንዳረጋገጠው ከግለሰቡ ላይ የተያዘው የገንዘብ መጠን 98,762 ዶላር ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር ከ3.6 ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል።
የጉምሩክ መስሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ሠራተኛ ስቲቭ ሳፕ ለቢቢሲ በሰጡት የጽሁፍ ምላሽ ላይ እንዳመለከቱት፣ ግለሰቡ ይዞት የነበረው ዶላር የተያዘበት ተጓዦች የያዙትን የገንዘብ መጠን እንዲያሳውቁ የሚጠይቀውን የአገሪቱን ሕግ በመተለላፍ ነው።
በተጨ ማሪም ቢቢሲ ባገኘው መረጃ መሰረት ግለሰቡ በዚሁ ሳቢያ ያልታሰረ ሲሆን የወንጀል ክስ ስላልተመሰረተበትም ማንነቱ እንደማይገለጽ ለማወቅ ተችሏል።
እንዲህ ዓይነት የሕግ ጥሰቶች ሲያጋጥሙ ክስ መመስረትን በተመለከተ የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ ውሳኔ እንደሚሰጥ ያመለከቱት ስቲቭ ሳፕ፤ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዐቃቤ ሕጉ የወንጀል ክስ ላለመመስረት በመወሰኑ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት እንዳልሄደ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን ግለሰቡ የአገሪቱን የገንዘብ ዝውውርና መጠን የማሳወቅ ግዴታን ባለመፈጸሙ 98,762 ዶላር ተይዞበታል።
ስቲቭ ሳፕ እንዳሉት ተጓዦች በተለያየ መንገድና በተደጋጋሚ የያዙትን የገንዘብ መጠን በትክክል እንዲያሳውቁ እንደሚጠየቁና በመጨረሻም ይህን በጽሁፍና በቃል ለጉምሩክ ተቆጣጣሪዎች ማሳውቅ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሳይሆን ከተገኘ የያዙት ገንዘብ እንደሚያዝ ተናግረዋል።
ባለስልጣናት እንዳሉት ኢትዮጵያዊው ግለሰብ በአሜሪካ ሕጋዊ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያለው ሲሆን ወደ አዲስ አበባ በሚያደርገው ጉዞ ላይ ነበር ገንዘቡ ሊያዝ የቻለው።
በወቅቱ ግለሰቡ የያዘውን የጥሬ ገንዘብ መጠን በቃልና በጽሁፍ እንዲያሳውቅ መጠየቁንና 14,000 ሺህ ዶላር እንደያዘ ቢገልፅም ይዞት በነበረው ቦርሳ ውስጥ 19,112 ዶላር ተገኝቷል።
ይህንን ተከትሎ በጉምሩክና በድንበር ተቆጣጣሪዎች ተፈትሾ አልፎ በነበረ ሌላ ሻንጣ ላይ በተደረገ ብርበራ ተጨማሪ 79,650 ዶላር በጫማና በጂንስ ሱሪ ኪሶች ውስጥ አግኝተዋል። በአጠቃላይም የተገኘው የዶላር መጠን 98,762 ሆኗል።
ስቲቭ ሳፕ ጨምረውም ግለሰቡ ይህን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ እንደያዘና ለምን አገልግሎት ሊያውለው እንደነበር ያልገለጸ ሲሆን፤ የገንዘቡ ምንጭ ከየት እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።
በምድር፣ በአየርና በባሕር የአሜሪካ ድንበርን የሚያቋርጡ ሰዎች በሚይዙት የገንዘብ መጠን ላይ በሕግ የተጣለ ገደብ ባይኖርም መንገደኞች ከ10 ሺህ ዶላር በላይ የሆነ ገንዘብ ወይም ሌላ የገንዘብ መገልገያዎችን ወደ አገሪቱ ሲያስገቡም ሆነ ሲያስወጡ ለጉምሩክ ሠራተኞች ማ ሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።
ይህንን ሕግ ተላልፈው የያዙትን ገንዘብ በትክክል ሳያሳውቁ የተገኙ ተጓዦች ከተያዘባቸው ገንዘብ አብዛኛውን ወይም ሁሉም የሚወረስ ሲሆን በተጨማሪም የወንጀል ክስ ሊመሰረትባቸው ይችላል።
ገንዘቡ የተያዘበት ግለሰብ እንዲመለስለት የመጠየቅ መብት ያለው ቢሆንም የተወረሰው ገንዘብ ምንጭና ሊውል የታሰበበት ዓላማ ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።
መንገደኞች ወደ አሜሪካ ሲገቡም ሆነ ሲወጡ በእጃቸው ላይ ያለን የትኛውንም ዓይነት ገንዘብ መጠኑን ማሳወቅ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህንንም የአሜሪካ የጉምሩክና የድንበር ቁጥጥር መስሪያ ቤት ያስፈጽማል።
መስሪያ ቤቱ በተጨማሪም የአገሪቱን የምድር፣ የአየርና የባሕር ድንበሮችን ከመጠበቅ ባሻገር ሕጋዊ የንግድና የጉዞ እንቅስቃሴ እንዲሁም የገንዘብ ልውውጥ እንዲኖር የተለያዩ ሕጎችን ያስፈጽማል። © ቢቢሲ
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply