ወሳኔው የተላለፈው በዚያን ጊዜው ህወሓት እንደፈለገ በሚዘውረው ፓርላማ ነበር።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ “የኢህአዴግ ከፍተኛ ሹሞችን ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅም የሚያስከብር አዋጅ ጸደቀ” በሚል ርዕስ (February 13, 2017) ባተመው ዜና መረጃውን ሲዘግብ ይህንን ብለን ነበር፤
ከሁለት ዓመት በፊት በጭምጭምታ ደረጃ ወሬዉ ወደ አደባባይ የወጣዉ ባለሥልጣናት “ጡረታ” ሲወጡ የሚከበርላቸዉ ጥቅማጥቅም አሁን “ህጋዊ ዕዉቅና” አግኝቷል።
ሐሙስ ዕለት በዋለዉ የኢህአዴግ “ፓርላማ” የህወሃት/ኢህአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከኃለፊነታቸዉ ሲነሱ ጥቅማጥቅማቸዉን የሚያስከብር አዋጅ ተሸሽሎ እንዲጸድቅ ተደርጓል።
የተሻሻለዉ አዋጅ ከኃላፊነታቸዉ የሚነሱ የመንግስት ባለሥልጣናት እንደ የኃላፊነት ደረጃቸዉ የመቋቋሚያ አበል፣ የሥራ ስንብት ክፍያ፣መኖሪያ ቤት፣የቤት ሰራተኞች፣ የምግብ አብሳዮች፣ የቀንና የማታ ቤት ጠባቂዎች፣ የተሸከርካሪ አገልግሎት ከነአሽከርካሪዉና ጠባቂ (body guard) እንዲሟላላቸዉ አዋጁ ያብራራል።
ቀደም ሲል ለኢህአዴግ ነባር ታጋይ ባለሥልጣናት መኖሪያ ቤት በሚል ከመንግስት ካዝና ያለ ፓርላማዉ ይሁንታ (ምንም እንኳን ልዩነት ባይኖረዉም) በአዲስ አበባ ወረገኑ አካባቢ አርሶ አደሮችን በማፈናቀል “ጡረታ ለሚወጡ ስድስት ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በመቶ ሃምሳ አራት ሚሊዮን ብር (እያንዳንዳቸው ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ በድምሩ 154 ሚሊዮን ብር) መጦሪያ ቤቶች ተገንብተው እየተጠናቀቁ” መሆናቸውን ጉዳዩን በኃላፊነት የሚመራው ተክለጻዲቅ ተክለአረጋይ (አቡነአረጋይ) ታህሳስ 1፤2008ዓም/November 12, 2015 ለሸገር ሬድዮ መናገሩ በዕለቱ ተዘግቦ ነበር። ተክለጻዲቅ ሲቀጥልም “አገራችን እነዚህን ቤቶች ለባለስልጣኖች መገንባቷ ከአፍሪካ አንደኛ ያደርጋታል” ከማለቱ በተጨማሪ “የመዋኛ ገንዳ (ስዊሚንግ ፑል) ያላቸው እነዚህ ቅንጡ ቤቶች የሚገነባላቸው ባለስልጣኖች ተለይተው መታወቃቸውን” ማስረዳቱ የህወሃት/ኢህአዴግን ዓይነደረቅነት ያሳየ ተግባር ሆኖ ነበር።
ዜናውን አያይዞ “ከጠቅላላ ሕዝቧ ውስጥ ከ2 ፐርሰንት በታች ለሆኑ አዛውንት ዜጎቿ የጡረታና የማህበራዊ ዋስትና የሌላት አገር ብትሆንም በስልጣን ዘመናቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ለዘረፉ ሌባ ባለስልጣኖቿ ግን ቅንጡ መጦሪያ ቤት የምትገነባ አገር ሆናለች” በማለት በወቅቱ በተጨማሪ መዘገቡ የሚታወስ ነው።
ሰኞ ዕለት የገንዘብ ሚኒስቴር ባታወቀው መረጃ መሠረት እነዚህ ቅንጡ ቤቶች ሊሸጡ መወሰኑን ገልጾዋል። እንዲህ ይነበባል፤
አገልግሎታቸውን አጠናቅቀው በጡረታ ለሚወጡት የቀድሞ የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት የተገነቡት ቅንጡ መኖርያ ቤቶች ሊሸጡ ነው ተብሏል።
ዘመናዊ የመኖርያ ሕንፃዎቹ ለታለመለት ዓላማ ስላልዋሉ ገንዘብ ሚኒስቴር ቤቶቹ ተሽጠው ለግንባታ ያወጣሁት ወጪ ይመለስልኝ ማለቱን ሸገር ኤፍኤም 102.1 ዘግቧል።
በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ ለከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተብለው የተገነቡት ቄንጠኛ መኖርያ ቤቶች 6 ናቸው።
CMC አካባቢ ከተገነቡት 6 እጅግ ዘመናዊ ቤቶች መካከል ትልቁ 2,441 ካሬ ሜትር ላይ አርፏል። ለአንዱ መኖርያ ቤት ብቻ በጨረታ የመሸጫ ዋጋ መነሻ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ተጠይቋል። በአጠቃላይ እስከ 1.2 ቢሊዮን ብር ከቤቶቹ ለማግኘት ታስቧል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply