በሕዝቡ ተሳትፎ እጅግ ከፍተኛ ኩራት ተሰምቶኛል ሞራልም ሰጥቶኛል በማለት አድንቀዋል
ሲነጋ …
በመላ ሀገሪቱ በአንድ ቀን ውስጥ 500 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ዘመቻ ከጥዋት አንስቶ እየተካሄደ ይገኛል። ዘመቻው እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ እንደሚቆይ ነው የተነገረው።
በችግኝ ተከላ ዘመቻው ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ እናቶች ፣ ህፃናት፣ ታዳጊዎች፣ ወጣቶች፣ የተለያዩ ተቋማት ሰራተኞች፣ የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች እና ሌሎችም እየተሳተፉበት ይገኛሉ።
የኢፌዲሪ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፤ ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ስራ የፖለቲካ ጉዳይ ፣ የፓርቲያቸው ፕሮግራም እንዲሁም የመንግሥት ጉዳይ እንዳልሆነ ከዚህ ቀደም ገልጸዋል።
ይህ ጉዳይ ” የኢትዮጵያ ጉዳይ ” እንደሆነና በዚህ የችግኝ ተከላ ዘመቻ አረንጓዴ የምትለብሰው ኢትዮጵያ መሆኗን ፤ ትርፉም ከእኛ አልፎ ለዓለም የሚተርፍ መሆኑን አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፦
– ተራሮች፣
– የወንዝ ግራና ቀኞች፣
– የመንገድ አካፋዮች፣
– የመኖሪያ ቤት ግቢዎች፣
– የሠፈሮች ባዶ ሥፍራዎች፣
– የቤተ እምነቶች ቅጽረ ግቢዎች፣
– የየትምህርት ቤቱ እና የየመሥሪያ ቤቱ ግቢዎች፣
– ለግብርናና ለእንስሳት ግጦሽ የማይውሉ መሬቶች ሁሉ በደን መሸፈን እንዳለባቸው በማስገንዘብ ለዚህ ስራ ሁሉም ያለ ልዩነት ሊሳተፍና ሀገሩን አረንጓዴ ሊያለብስ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በትግራይ ክልል በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው
በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ከጥዋት አንስቶ እየተካሄደ ያለው የችግኝ ተከላ ዘመቻ በትግራይም እየተካሄደ መሆኑ ተነግሯል።
ዛሬ በትግራይ በፅራእ ወንበርታ ወረዳ በተጀመረ የችግኝ ተከላ ዘመቻ የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ እና የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ህብረተሰቡ ተሳትፈዋል።
ከዚህ በፊት በነበሩት ሀገሪቱን በደን የማልበስ መርሀ ግብሮች ላይ ትግራይ በአስከፊው ጦርነት ምክንያት ተካፋይ ሳትሆን ቀርታ ነበር።
የምንተክለው ለቀጣዩ ትውልድ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
በዕለቱ ለ2ኛ ጊዜ ባደረጉት ችግኝ ተከላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በየካ ተራራ የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጋር 500 ሚሊየን ችግኝ በአንድ ጀንበር የመትከል መርሐ ግብር ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር፣ በዕለቱ ለሦስተኛ ጊዜ ከአረጋውያን እናቶችና አባቶች ጋር አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሩ ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል
አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን
ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን ገለጹ።
በአዲስ አበባ በሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል አካል የሆነ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ተካሄዷል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዘላቂ ልማትን የሚያግዝ መሆኑን አምባሳደር ዣኦ ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪን በመቀበል የኤምባሲው ማኅበረሰብ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ሆኖ ታሪክ በመጋራቱ ኩራት እንደሚሰማው ተናግረዋል።
አረንጓዴ አሻራ ትውልድ ተሻጋሪ ዘርፈ-ብዙ ጥቅም እንዳለው ተናግረው፤ በሰውና በተፈጥሮ መካከል ያለውን ቁርኝት ማሳደግ የቻይና የልማት መንገድ አንድ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የምታከናውነው የአረንጓዴ ልማት ቻይና በአድናቆት ትመለከተዋለች ብለዋል።
ቻይና ለተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና አካባቢ ጥበቃ ትኩረት በመስጠት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ተባብሮ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗንም አመልክተዋል።
ማመሻው ላይ …
ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብሯን አሳካች
ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን በላይ ችግኝ የመትከል መርሐ ግብሯን ማሳካቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከችግኝ ተከላ ሁነቶች መከታተያ ክፍል በሰጡት መግለጫ÷ በዛሬው ዕለት እየተካሄደ በሚገኘው የአንድ ጀንበር ከ566 ሚሊየን በላይ ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ዜጎች በንቃት መሳተፋቸውን አንስተዋል፡፡
በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ አካባቢ ከማለዳ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ከ566 ሚሊየን 971,600 ችግኞች መተከላቸውን ነው የተናገሩት፡፡
አቀድን፤ ተባበርን፤ አሳካን፤ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) መርሐ ግብሩ እንዲሳካ ልጆቻቸውን አቅፈው ችግኝ ለተከሉ እናቶች፣ ሕጻናትና ተማሪዎች እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የእንኳን ደስአላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ እንዲሁም ለመላው ዓለም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥና እጅግ የሚያኮራ ተግባር ፈጽመናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የዓየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ ስጋት መሆኑ ታምኖ በጉዳዩ ላይ ንግግር ከተጀመረ መቆየቱን አንስተው÷ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ባከናወነችው ልክ የተጀመሩ ስራዎች ጠንካራ አለመሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ዛሬ በተካሄደው በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብርም 566 ሚሊየን 971 ሺህ 600 ችግኝ በ302 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መተከሉን ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት የተተከሉት ችግኞች የተተከሉበት ቦታ በእርግጠኝነት የታወቁ እንጂ በየጓሮው በየበረንዳው የተተከለውን እንደማይጨምር ተናግረዋል። ይህም ለማንኛውም የዓለምአቀፍ ተቋም ቀርቦ ላገራችን የካርቦን ገቢ የሚያስገኝ ነው የሚሆነው። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘገባ ባለፈው ዓመት ብቻ 52 ሚሊዮን ዶላር ከካርቦን መገኘቱን ገልጸዋል።
ይህ በ302 ሺህ ሄክታር ላይ የተተከለውን ችግኝ በማድነቅ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሥራው ለብዙዎች የሚተርፍ ድንቅ ሥራ ነው፤ በዝናብ በእግራች ሁሉ ተጉዛችሁ የተከላችሁ ላመሰግን እወዳለሁ” ብለዋል። ሲያጠቃልሉም “በሕዝቡ ተሳትፎ እጅግ ከፍተኛ ኩራት ተሰምቶኛል ሞራልም ሰጥቶኛል” በማለት አድንቀዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tassew says
ያው እስቸው መቼም ውሽት ባጠገባችው ስለማያልፍ ተማምናችሁ ነው እንጂ፣ አናንተ ያረጋገጣችሁበት መረጃ የላችሁም።
Tesfa says
ነገርየው እንደ እውሮቹ ሰዎችና እንደ ዝሆኑ ጉዳይ ነው። አይነ ስውሮችን ዝሆን አቅርበው እንዲዳስሱና ምን ዝሆን ምን እንደሚመስል እንዲያስረድ ይጠየቃሉ። ሁሉም በነኩት በኩል ያለውን ብቻ በመናገራቸው ሙሉውን የዝሆን ገጽታ መግለጥ አልቻሉም። የሃበሻው ፓለቲካም እንደዚያ ነው። ሲጀመር ለምን ዛፍ ተተከለ ብሎ የሚያላዝን ፓለቲከኛ ጢምቢራው የዞረ የምድሪቱን መልካምነት ሳይሆን ክፋቷን የሚሻ ነው። ስለሆነም ችግኝ መትከሉ ማለፊያ ነው። ግን ይጸድቃል ወይ? ማን ተንከባክቦ ለቀሪው ትውልድ እንዲደርስ ያደርገዋል? ይህ ድህረ ገጽ መልካም ዜናን በመለጠፍ ይታወቃል። እሱም ወሸኔ ነው። ሌሎቹ ደግሞ በየጊዜው ሞተ፤ ታሰረ፤ ተፈታ፤ ተሰደደ፤ ጦርነት ሆነ ይሉናል። ችግሩ ወሬው ሳይሆን ራሱ ወሬው ሙሉነት አለመያዙ ነው። ጊዜው የውሸት ጡሩንባ ያለ ገደብ የሚነፋበት፤ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያዎች በቀላሉ መጠቀም የሚቻልበት ነው። እውነቱን መዝኖ፤ በሥፍራው ተገኝቶ ያለውን ለማስተላለፍ የሚቻልበት ዘመን ላይ አይደለንም። ሰው ከሞላ ጎደል ሞት፤ እርዛት፤ ግድያና የጦርነት ወሬ ማየት የሚወድ ይመስላል። የሌላው መከራ ምንም አይገባውም። እየየውን የሚለቀው ችግር በሩን አንኳኩቶ ቤቱ ሲገባ ብቻ ነው። በዚህ የተነሳ የሰዎችን መገፋት፤ የፍርድን መዛባት፤ በቋንቋና በዘራቸው መሰቃየትን እያዪ ለዛሬ እኛ ነን በሚል ዘይቤ ግፍን ፈጽመው የሚወላድ ሁሉ የሮም አወዳደቅን ሲወድቁ አይተናል። ከወያኔ የመከራ ዘመን ወደ ኦነግ የግፍ ዘመን የተሸጋገረችው ኢትዮጵያም የሞቱላት ሳይሆኑ የገደሏት የሚኖሩባት ሃገር ሆናለች። መለስ ብሎ የመቶ ዓመት ታሪካችን ብቻ ለተመለከተ ዛሬ ያለው ሁኔታ ትላንት ከነበረው መክፋቱን እንጂ መሻሉን አያሳይም። እውቁ አሜሪካዊ Behaviorist and Psychologist B.F Skinner ከዘመናት በፊት በጻፈው Beyond Freedom and Dignity በተሰኘው መጽሃፉ ላይ እንዲህ ይለናል። What we need is a technology of Behavior. A change in human behavior. የስልጣኔ እምርታ ብቻውን የሰው ባህሪ እካልተለወጠ ድረስ ገመናን እንጂ ደስታን አያመጣም። በሃበሻዋ ምድር የሰው ልጅ ባህሪ ከሰውነት ወደ እንስሳነት ከቀን ወደ ቀን እየተቀየረ ይገኛል። ለመኖር እንገላለን፤ ለመብላት እናታልላለን፤ እናፈናቅላለን። የአንድ እንባ የእኛ ደስታ ይሆናል። እንዲህ ያለ ወገን የአዕምሮ በሽተኛ እንጂ ፓለቲከኛና ለብሄሩ ወይም ለሃገሩ የቆመ ሊሆን አይችልም። ባጭሩ የችግሩ ሁሉ ምንጭ እኛው በእኛው ነን። መፍትሄውም ከእኛው አርቆ ማሰብና መተዛዘን የሚመነጭ እንጂ ከሰማይ አይወርድም።
በመጨረሻም ከፋም ለማም አንድ የሃገር መሪ ኑ ችግኝ እንትከል ማለቱ በጎ ነገር ነው። በሚሊዪን የተተከለው ችግኝም ጸድቆ ለመጭው ትውልድ ጠለላና መከታ ቢሆን እሰየው ያስብላል። ችግሩ ሁሉ በዘርና በቋንቋው ፓለቲካ የተሳከረ በመሆኑ ቆም ብሎ ለማሰብና ይህ ጉዳይ መልካም ነው በማለት መቀበል ሽንፈት ይመስለዋል። ስለሆነም ምንም እንኳን በምድሪቱ የሰላም እጦት፤ የኑሮ ችግርና ሌላም ተደራራቢ ጉዳዪች ቢኖሩም ችግኝ መትከል እሰየው ያሰኛል እንጂ ዘለፋና ስድብን ማስከተል የለበትም። ግን ልክ እንደ አይነስውራኑና እንደ ዝሆኑ የምንዳስሰው ከፊሉን ብቻ በመሆኑ የሃገሪቱን የተሟላ የፓለቲካ ስርግብና የጉስቁልና መልኳን መለየት ተስኖናል። በዚህም የተነሳ የቆምንበት ምድር ሁሉ የዓለም መጨረሻ ጫፍ እየመሰለን የሰፈር ባንዲራ በመስቀል የዘርና የቋንቋ እስክስታ እንወርዳለን። የጠባብነት ክፋቱ እሳቤው ከአፍንጫው አለመራቁ ነው። በቃኝ!