![](https://www.goolgule.com/wp-content/uploads/2021/10/1-1.jpg)
በአዲስ አበባ በ2014 በጀት ዓመት ምግብ ነክ የሆኑ ግብቶችን ከባዕድ ጋር በመቀላቀላቸው 23 ተቋማት መታሸጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ የመድሀኒት፣ የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በምግብ እና ጤና ነክ ተቋማት ዙሪያ የቁጥጥር ሥራ እንደሚከናውን ይታወቃል፡፡ በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ በምግብ ክለሳ ላይ ሰፊ ሥራ መስራቱን አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት በ2014 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 146 ተቋማት ላይ በተደረገው የቁጥጥር ሥራ 23 ተቋማት መታሸጋቸውን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ የመድሀኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሙሬሳ ሚደቅሳ ተናግረዋል፡፡
ተቋማቶቹ ቂቤ፣ ማር እና የባልትና ምርቶችን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅለው በመገኘታቸው ነው እርምጃው የተወሰደባቸው።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የማሸግ ሥራ ብቻም ሳይሆን አራት ግለሰቦች በህግ ጥላ ሥር እንደሚገኙ እና በቀጣይም ምርመራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ ባእድ ነገሮችን ይዘው ከታሸጉ ተቋማት ውስጥ መርካቶ፣ አራዳ እና ቦሌ ክፍለ ከተሞች ተጠቃሾች ናቸውም ተብሏል።
በተጨማሪም የፅሁፍ እና የቃል ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ከ30 በላይ ተቋማቶች መኖራቸውን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል ሲል ብስራት ሬዲዮ ዘግቧል፡፡
ህብረተሰቡ ይህን መሰል ድርጊት አልያም ጥርጣሬን በሚመለከትበት ጊዜ በነፃ የስልክ መስመር 8064 ላይ በመደወል ለባለስልጣኑ ማሳወቅ አለበት ሲሉም ሙሬሳ ሚደቅሳ አሳስበዋል። (አዲስ ማለዳ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply