በተለያዩ አካባቢዎች የተሰረቁ ከሁለት መቶ በላይ የሞባይል ስልኮችን በህጋዊ ስም በተከፈቱ የንግድ ሱቆች ውስጥ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖለስ አስታውቋል፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ በህጋዊ የሞባይል ስልክ እና የቴሌቪዥን ጥገና ሱቅ ሽፋን ከግለሰቦች የተሰረቁ ስልኮችን እየገዙ ሲሸጡ ከነበሩ ግለሰቦች ሱቅ ውስጥ 215 ሞባይል ስልኮች መያዛቸው ታውቋል፡፡
የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ እና ባደረገው ክትትል በወረዳ 3 ኤድናሞል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሞባይል ጥገና ስራ በሚሰሩ አራት የንግድ ሱቆች ላይ ትናንት ሃምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም በህግ አግባብ በተከናወነ ብርበራ ነው ከተለያዩ ቦታዎች ተሰርቀው የተከማቹ ሞባይል ስልኮች ሊያዙ የቻሉት፡፡
ከሞባይል ስልኮቹ በተጨማሪ የወንጀል ፍሬ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ እና በጥገና ቤቶቹ ውስጥ የተገኙ የተለያየ መጠን ያላቸው ሰባት ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥኖች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ አራት ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝምፖሊስ አስታውቋል፡፡
ቀደም ሲል በተለያዩ አካባቢዎች በተፈፀመባቸው ወንጀል ሞባይል ስልክ እና ቴሌቪዥን የተወሰደባቸው ግለሰቦች አንበሳ ጋራዥ ጀርባ በሚገኘው የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ እየቀረቡ ማረጋገጥ ይችላሉም ተብሏል፡፡
በወንጀል ምክንያት የተገኙ ንብረቶችን ከወንጀል ፈፃሚዎቹ በሚገዙ ግለሰቦች ላይ ተከታታይነት ያለው እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ፖሊስ የማህበራዊ ትሥሥር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ዘገባዎች መሰራታቸውን ያስታወሰው ፖሊስ ችግሩ በዘላቂነት እስኪቀረፍ ድረስ በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ (ዋልታ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply