• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ህወሓት በክህደት አከርካሪው ተመታ

February 6, 2019 10:20 am by Editor 1 Comment

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) በማለት ራሱን የሚጠራው የበረሓ ወንበዴዎች ስብስብ አባል የነበረው ዛዲግ አብርሃ ከድርጅቱ አባልነት ለቋል። በህወሓት ታሪክ ዓይነተኛ ቦታ የሚሰጠው ይህ ክህደት ድርጅቱን ክፉና ጎድቶታል። ዛዲግን የሚከተሉ ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል።

በጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ ግንቦት 2፤ 2010 በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል ኃላፊ ሆኖ የተሾመው ዛዲግ አብርሃ የካቲት 5፤2011ዓም ከድርጅቱ መልቀቁን በጻፈው አምስት ገጽ ደብዳቤ ገልጾዋል።

ከዚህኛው ሹመቱ በፊት ዛዲግ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጦር እንዲዘምት ትዕዛዝ በሰጠው የጦር ወንጀለኛ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ዘመን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ የነበረው ነገሪ ሌንጮ ምክትል በመሆን ሠርቷል። ከዚያም በፊት “የሕዳሴ ግድብ” አስተባባሪ ኃላፊ ሆኖ መሥራቱ ይታወቃል።

በአምልኮተ መለስ የሚታወቀውና መለስን ከምንም በላይ እንደሚያደንቀው ይናገር የነበረው ዛዲግ ሜይ 3፣ 2016 ከፎርቹን ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ የሚከተለውን ማለቱ ይታወሳል፤ “መለስ መንፈሴን ይቀሰቅሳል (ኢንስፓየር ያደርገኛል)፤ … ለዓላማው 17 ዓመት ታገለ፤ ከዚያም ደግሞ ለአገሪቷ የተሻለ ነገር ለማድረግ የሚገባውን ድርሻ በመወጣት ተሰዋ፣ ጽናቱ፣ አይበገሬነቱ፣ ማቆሚያ የሌለው ድፍረቱ ሁልጊዜ ይመስጠኛል፣ መንፈሴን ይቀሰቅሳል፤ እንደሱ ማድረግ እችል ይሆን ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፤ እሱና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ባልደረቦቹ ያለማቋረጥ ለሦስት ዐስርተ ዓመታት ያደረጉትን ማድረግ እችል ይሆን ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ” ነበር ያለው።

ማክሰኞ ከህወሓት አባልነቱ ሲለቅ ደግሞ ይህንን በማለት ነበር ባለ አምስት ገጽ ደብዳቤውን የደመደመው፤ “ፀረ-ለውጥና ፀረ-ዲሞክራሲ ከሆነው ድርጅት (ህወሓት) ጋር ለመቀጠል ህሊናዬ ባለመፍቀዱ በገዛ ፈቃዴ ከድርጅቱ አባልነት የለቀኩ መሆኑን እያሳወቅሁ በቅርቡ ያታግለኛል ከምለው ድርጅት ጋር ተደራጅቼ የራያና የመላ የአገሬ ህዝብ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝና ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ እየተደረገ ባለው ርብርብ ለማገዝና ለመታገል እንደምሰራ ከወዲሁ ለማሳወቅ እወዳለሁ” ብሏል። አውቆም ሆነ ሳያውቅ ለበደላቸው ይቅርታም ጠይቋል።

ዛዲግ አብርሃ ከህወሓት ለመልቀቅ ያስገደደውን ሁለት አንኳር ምክንያቶች በዚህ መልኩ ነው ያስቀመጠው፤ የመጀመሪያው ህወሓት በአገሪቱ የተጀመረውን ዴሞክራሲያዊ ለውጥ በሚገባ ያልመራውና አንዳንዴ ሲቃወመው ይስተዋላል፤ ሌላው ደግሞ ህወሓት ከወንድሙ የአማራ ህዝብ ጋር አንድ ላይ ለመሆን ጥረት እያደረገ ያለውን የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ምላሹ አፈሙዝ መሆኑ ከህወሓት ለመልቀቁ ያነሳቸው ምክንያቶች መሆኑን ገልጾዋል።

በኢትዮጵያ እጅግ አስከፊ የሚባልና ትውልድን ያወደመ ርዕዮት በመከተል አገር ያፈረሰው የወንበዴው ህወሓት ቡድን በዓለምአቀፍ የአሸባሪዎች የመረጃ ቋት በአሸባሪነት እስካሁን ተመዝግቦ ቢኖርም አሁንም በርካታ አባላትን ይዞ ይህንኑ የሽብር ተግባሩን በአገር ደረጃ ሲፈጽም ይታያል። ህወሓትን በመርህ ደረጃ ተቃውሞ በዚህ ዓይነት መልኩ በቅርቡ ከአባልነት በይፋ የለቀቀ አለመኖሩ የዛዲግን ውሳኔ ትልቅ ሥፍራ የሚያሰጠው ነው። ከዚህ በፊት ከአቶ ገብረመድኅን አርአያ በስተቀር አብዛኛዎቹ ከህወሓት ሲለቁ ዋንኛ ምክንያታቸው የመርህ ጉዳይ ሳይሆን በዚያ የተሸፈነ የሥልጣን ሸኩቻ እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አራማጁ ዛዲግ ቁልጭ ባለ የመርህ ችግር ድርጅቱን መልቀቁ ኪሣራውን የከፋ ያደርገዋል።

ከዚህ አኳያ የዛዲግ በይፋ መልቀቅ በተለይም የለቀቀበት ምክንያት አንዱ የራያ ማንነትና የህወሓት ምላሽ መሆኑ ህወሓት አከርካሪው የተመታ ያህል እንደሚቆጠር ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ ገልጸዋል። ዛዲግ እንደሚከዳ ከተሰማ በኋላ (ይፋ ከመውጣቱ በፊት) ህወሓት አንዳንድ እርምጃዎችን ለመውሰድ አስቦ የነበረ ቢሆንም አልተሳካለትም። ህወሃትን ለዚህ ያነሳሳው ጉዳይ የዛዲግ መክዳት ከራያ ጋር የተገናኘ በመሆኑና ይህም የሚያመጣው የፖለቲካ ኪሣራ በከፍተኛ ሁኔታ የህወሓትን አከርካሪ የሚሰብር በመሆኑ ነው ብለዋል አስተያየት ሰጪው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የዛዲግን መክዳት ተከትሎ ሌሎችም ይህንኑ ፈለግ እንደሚከተሉ ጎልጉል የደረሰው መረጃ ይጠቁማል። በተለይ በመንግሥት በኩል ዋስትና የሚሰጣቸው መሆኑ በማያሻማ መልኩ ከተረጋገጠ በዚህ መንገድ የሚሄዱና የወንበዴውን ቡድን ደጋፊ አልባ አድርገው የሚያስቀሩ እየታዩ እንደሚሄዱ ይጠበቃል።

ዛዲግ አብርሃ የህወሓት ያስገባው ደብዳቤ ሙሉ ቃል እንዲህ ይነበባል፤    

የካቲት 5, 2019

ለ – ህወሐት ልዩ ዞን ጽ/ቤት
አዲስ አበባ

ላለፉት አመታት በህወሓት ድርጅት ስር ተደራጅቼ እንቅስቃሴ ሳደርግ እንደቆየሁ ይታወቃል። ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም በፖለቲካው መስክ የመሳተፍ ፍላጎቱ ያልነበረኝ ቢሆንም በታሪክ አጋጣሚ የአገራችንን ፖለቲካ የመቀላቀል ዕድሉን አግኝቻለሁ። በተፈጠረው አጋጣሚም ስለሃገሬ የፖለቲካ ምንነት እና በፖለቲካ ገበያው ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችንና ተቋማትን በቅርበት የማወቅና የመሳተፍ እድሉ ገጥሞኛል። በዛው ልክ ደግሞ በህወሀት ውስጥ አደርግ በነበረው ትሳትፎ በር የመዝጋት የመጠራጠርና እንደ ባዳ የመታየት ስሜት ከላይ እስከ ታች ድረስ አጋጥሞኛል። ገና ከጅምሩ ትግሉ ድርብ ድርብርብ ነበር። በአንድ በኩል የመጣሁበት አካባቢ በክልሉ ፖለቲካ ውስጥ በዳርነት የሚመደብ ነውና አጠቃላይ ጉዞው እጅግ አቸጋሪ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ ወጣቶችን የመጠራጠርና ያለማመን ከፍተኛ ችግር የተንሰራፋበት ነውና እኔም እንደማንኛውም ወጣት ጉዞየ በሳንካ የተሞላ እንዲሆን አድርጎብኛል። ነገር ግን ሁሉንም በአንድ ሙቀጫ መውቀጥ ጥሩ አይደለምና በህይወቴ ነገሮችን በተለየ መልኩ እንዳይ ያደረጉኝ እንዲሁም ትምህርት የሰጡኝ ጥቂት ሰዎች ነበሩና በነሱ ድጋፍና ምክር በችግርም ውስጥ ቢሆን እስካሁን ድረስ ለመዝለቅ ችያለሁ።

በእርግጥም! በሃገሬ ፖለቲካ ረጅም ርቀት ተጉዤ አስተዋጽኦ ላደርግበት የምችልና የሚገባ መሆኑን የማታ ማታ ለመረዳት ችያለሁ። ይሁንና ገና ከማለዳው ጀምሮ በህወሓት ውስጥ የነበረኝ የፖለቲካ ተሳትፎ አልጋ በአልጋ አልነበረም። በአጭሩ በሴራና በአሜኬላ የተሞላ ነበር ብሎ መናገር ማጋነን አይሆንም። ሆኖም ችግር ሲመጣ መሸሽና ማፈግፈግ ሳይሆን ፊት ለፊት ተጋፍጦና ተፋልሞ ማሸነፍ እንደሚገባ ላስተማረኝ ለውድ አያቴ ለሃዋደ ሻረው አቢቱ አበራ እና በአጠቃላይ ለራያ ማኅበረሰብ ምስጋና ይግባውና ምርጫዬ “እግሬ አውጭኝ” ብሎ መሸሽ ሳይሆን አሜኬላውን መንቀልና ሴራውን ደግሞ ማፈራረስ ነበር።

በአንፃራዊነት ከእድሜየና ከቆይታየ እንፃር ሲታይ በእርግጥ እድገቴ ፈጣን ነበር ብሎ መናገር ይቻላል። ነገር ግን እድገቱ የመጣው በእኔ የስራ ፍላጎት እምነት ያላቸው የሌሎች ደርጅቶች የግንባሩ አመራሮች እየገፉና እየጠየቁ እንጅ በህወሓት በኩል እንደዛ አይነት ፍላጎት ስለነበረ አይደለም። እንዲያውም ቅናት ያደረባቸው አንዳንድ የህወሓት አመራሮች እድሉን ለማሰናከል ሲተጉ ተስተውለዋል ። አንዳንድ ግብዝ የዚሁ ድርጅት አመራሮች ተመልሰው የማይገኙ በትላልቅ የአሜሪካ ትምህርት ቤቶች የመማር የነፃ የትምህርት እድልን ሳይቀር ትቼ አገሬን ለማገልገል በመወሰኔ በስልጣን ፍላጎት ከሰውኛል። በየቢሮው እየዞሩ የስልጣን ያለህ እያሉ የሚውሉት እነዚህ ግለሰቦች ከስልጣን ሲነሱ ደግሞ እንደ ልጅ እያለቀሱ የሚማፀኑ ናቸው። ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው ነገር ደግሞ እያንዳንዱን እንጥፍጣፊ ስልጣን ለግል ጥቅምና ዝና ያላንዳች ርህራሄ የሚያውሉትና ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የስንቱን ምስኪን ህይወት የቀጠፉት እነዚህ ጨካኞች በግሌ ያገኘሁትን የነፃ የትምህርት እድልን መሰዋእት ያደረኩትን እኔን በስልጣን ፍላጎት ይከሳሉ።

ይህን የመልቀቂያ ደብዳቤ እንዳዘጋጅና ከህወሓት ራሴን በፈቃዴ እንዳሰናብት በርካታ ገፊ ምክንያቶቼን እንደሚከተለው በዝርዝር የገለጽኩ ሲሆን የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ሊረዱት የሚገባ ትልቅ ቁም ነገር ቢኖር ድርጅቱን በይፋ ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት እንዲስተካከል የምችለውን ሁሉ ጥረት ማድረጌን ነው።

እስካሁን መልቀቂያ ሳላቀርብ የቆየሁበት ዋና ምክንያት ከዛሬ ነገ ወደ ማስተዋልና ካለፈው ተምረው በስህተታቸውም ተጸጽተው ነገሮችን ያስተካክሉ ይሆናል በማለት ለዚህም ጊዜ መስጠቱ መልካም ነው ብዬ በማሰብ ነበር። ነገር ግን ይህንን እንደማያደርጉና ምንም የሚለወጥ ስብዕና እንደሌላቸው የስካሁኑ አካሄዳቸው ግልጽ ስላደረገልኝ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ።

በነዚህ ዓመታት በግሌ የምከተለውን አቋም እና የነበረኝን የትግል አካሄድ ትክክለኛነት እና ፍትሃዊነትን ተረድተው “አይዞህ” ብለው የሞራል ብርታት የሰጡኝ ከፍ ሲልም ከጎኔ ቆመው የታገሉ ጥቂቶች አልነበሩም። ነገር ግን ወደ ላይ በወጣሁ ቁጥር የተበጀልኝ ሴራ ይበልጥ እየተወሳበሰበ መጣ። በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዴሊቨሪ ሚኒስትር ሆኜ በተሾምኩ ማግስት ጀምሮ ጥቃቱ ተቋማዊ መልክ እየያዘና ትልልቅ ቱባ የህወሃት ባለስልጣናትም ጭምር የሚሳተፉበት ወደመሆን ተሸጋገረ። የፖለቲካ እስረኞችን ሙሉ በሙሉ ለመፍታትና የሰቆቃ ማእከል ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ማእከላዊ ተዘግቶ ወደ ሙዝየምነት እንዲቀየር ተወሰኖ ለመላው ህዝባችን ይፋ እንዲሆን ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በግለሰብ ደረጃ ይህ ነው የማይባል ጥቃትና ዛቻ እንዲሁም ማስፈራሪያ ደርሶብኛል።

የአገሪቱ ቁንጮ የህወሓት ባለስልጣናት የተሳተፉበት ይኸው ጥቃት “ለምን የፖለቲካ እስረኛ አለ ብለህ ይፋ አወጣህ፤ ውሳኔው በቀጥታ twitter እና Facebook ለአለም በማሰራጨት የጠቅላይ ሚንስትሩን ውሳኔ የማስቀየር እድላችንን ዝግ እንዲሆን አድርጋሀል ፤ በአጠቃላይ ከጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም፤ ከምክትል ጠቅላይ ምንስትር ከአቶ ደመቀ መኮንን፤ ከኦህዴድ አመራሮችና ከፈረንጆች ጋር ወግነህ የስርአት ለውጥ ለማምጣት የምትንቀሳቀስ የቀለም አብዮተኛ ነህ፤ ከዚህ በኋላ ከአንተ ጋር የምንነጋገረው በጥይት ነው!” በማለት ውሳኔው ከተላለፈባት ከዚያች ምሽት ጀምሮ ከፍተኛ ዛቻና የስነ-ልቦና ጫና ከትላልቅ የህወሓት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ በተለያዩ ወቅቶች ደርሶብኛል።

እዚህ ላይ ግልፅ የሆነልኝ ነገር የድርጅቱ አመራሮች ምን ያክል እንደተበላሹና በታሰሩ ዜጎች መፈታት ምን ያክል እንደሚያማቸው ነው። ጫናው ሲያይልና ይፋ የተደረገበት ምክንያት ግቡን ሲመታ በፌስቡክ ገፅ የተፃፈንውን ነገር ትንሽ ቆየት ብለንና በነጋታው ደግሞ በተለይም የውጭ ሚዲያ ወኪሎች የቀድሞውን ዘገባ እንዲያስተካክሉ አድርገናል። ነገር ግን መረጃው አስቀድሞ በበቂ መጠን ስለተሰራጨ ግቡን ሊመታ ችሏል።

ከዛ በኋላም ቢሆን በነበሩት ተደጋጋሚ የህወሓት ስብሰባዎች ተመሳሳይ ስሞታና ዛቻ ደርሶብኛል። በእርግጥ አገራችንን ወደ ትልቅ እስር ቤት እየቀየራት የነበረው የጥቂት አምባገነኖች እርምጃ መቆም እንዳለበትና የነሱ ሰለባ የሆኑት የህሊና እስረኞች ከገቡባቸው ነጻ መውጣት እንዳለባቸው ካመንኩኝ ውየ አድሬያለሁ።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የታገልኩት የሰብአዊ መብት ለማክበር ነው፤ እስረኞች በህግ ጥላ ስር ሊመቱ አይገባም እያለ በአደባባይ ላይ ያለአንዳች ሃፍረት የሚለፍፍ ስርአት ራሱን ፉርሽ በሚያደርግ ሁኔታ ደብዳቢ እና ተጋራፊ ሆኖ መገኘቱ አንድ በቅርብ በማውቀው ወዳጄ ላይ ተከስቶ ካገኘሁት ጊዜ ጀምሮ የህሊና እረፍት ሊሰጠኝ ባለመቻሉ ይህ ሁኔታ መለወጥ እንዳለበት ካመንኩኝ ሰናባብቻለሁ።

እናም መልካም እድልና ምቹ ሁኔታ ሲፈጠር መጠቀም ይገባ የነበረ በመሆኑ የህሊና እስረኞችን ለመታደግና ማዕከላዊን ወደ ሙዝየም ለመቀየር በተደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሚና ከተጫወቱ መሪዎች ጋር ሆኜ የድርሻዬን ተወጥቻለሁ። በዚህ ውሳኔ ሂደት ውስጥ የበኩሌን የጠብታ ታክል ድርሻ ተወጥቼ ከሆነ በህይወቴ የምኮራበት ትልቅ ተግባር እንጂ በምንም መልኩ አላፍርበትም። ሆኖም የአምባገነንነት እርካቡ እየተናደበት እንደነበር የገባው ህወሓት ውስጥ የመሸገው ቡድን በርግጎና በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ተነሳስቶ ለዚህ ውሳኔ ድርሻ ነበራቸው በሚላቸው ሃይሎች ያነጣጠረ እርምጃ መውሰድ መቼ ይቀርና!!

በተለይም ደግሞ አክራሪው ቡድን በህወሓት ውስጥ መሽጎ እንደሚገኝ የውስጥ አርበኛ ወስዶኝ ነበረና አንገቴን እንድደፋና ሸሽቼ እንድጠፋ ለማድረግ የተቀነባበረ የስም ማጥፋትና የጥቃት ውርጅብኝ ተካሂዶብኛል። ይህ ሁሉ ሁኔታ እየተካሄደ በነበረበት ሁኔታ እንኳን ምርጫየ ትግል እንጅ መፈርጠጥ አልነበረም።

“ሳይደግስ አይጣላም!” እንዲሉ አበው . . . ከዛ በኋላ በፍጥነት በተቀያየረው ሃገራዊ ሁኔታ ትኩረታቸውን ስቦት እና አዛብቶት እንጅ የታሰበልኝን እና የተደገሰልኝማ ነገር አሳምሬ አውቃለሁ። ይህ ሁሉ እየሆነም ቢሆን ምርጫዬ መሸሽና አንገት መድፋት ሳይሆን አንገትን ቀና አድርጎ መታገል ነበር። ምክንያቱም ጥቃቱ በእኔ በግለሰብ ደረጃ ላይ ያነጣጠረ የነበረ በመሆኑ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የራያ ህዝብ ያለ ምርጫውና ያለውዴታው ገና ከማለዳው “ሆ. . .!” ብሎ የተቃመው አከላለል ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ መግደልና ማሳደድን መቀጠላቸው ህዝቡም በተደራጀ መልኩም ባይሆን ትግሉ አላቆመም ነበር። የራያ ህዝብ ትግል ፍሬ እንዳያፈራ ካደረጉት መሰረታዊ ምክንያቶች/ጉዳዮች አንዱ ትግሉ በተደራጀ መንገድ አለመከናወኑ መሆኑን አውቆ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተደራጀ መንገድ ወደ ትግል ገብቷል። ወንድሜ ከሆነውና በጠንካራ ማህበረሰባዊና ስነልቦናዊ ገመድ ከተሳሰርኩት የአማራ ህዝብ ጋር አብሬ ልኑር ብሎም እየተዋደቀ ይገኛል።

ይህ ሲሆን ታዲያ የኢትዮጵያ የናሽናል ጥያቄ (የብሄረሰቦች ጥያቄ) ብዝሃነትን የማስተናገድ ችሎታ እጦት ነውና “ኢትዮጵያ ብዝሃነትን ልታከብር ይገባታል!” ብሎ በፕሮግራሙ ላይ በነጭና በጥቁር በደማቁ የጻፈው እንዲሁም በዛ ላይ ተመስርቶም ላለፉት 45 አመታት የፖለቲካ ሞብላይዜሽን ያደረገው ህወሓት ምላሽ ጥይት፤ ግድያ፤ ማፈናቀልና እንግልት ሆኗል።

ነገሩ “ሆድ ሲያውቅ ደሮ ማታ ነው!” እና ድርጅቱ ለፕሮግራሙና ለዚያም ሲባል መስዋእት ለሆኑት ታጋዮቹ ክብር እንደሌለው በአደባባይ አስመስክሯል። የማንነት ጥያቄን ያነሱ እምቦቃቅላ ህጻናትን እስከ አፍንጫው በታጠቀው የክልሉ ልዩ ሃይል አናት አናታቸው እየተመቱ በእንጭጩ ተቀጭተዋል።

በአጠቃላይ የራያ ህዝብ የተደራጀ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የስንቱ ህይወት እንደተቀጠፈ፤ ለእስር እንደተዳረገና እንደተፈናቀለ ቤቱ ይቁጠረው። አካባቢው በዚህ ምክንያት ለከፋ ማህበራዊ መስቅልቅልና ቀውስ እንዲሁም ለጸጥታ ቀውስና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ተዳርጓል። በራያ ህዝብ ላይ ይህን የመሰለ ግፍና መከራ እየፈጸመ ካለ ድርጅት ጋር አብሬ እንድቀጥል ህሊናዬ አልፈቀደልኝም።

በእርግጥ ገና ከገባሁ በጥቂት አመታት ውስጥ ልቤ ሸፍቶ በመንፈስ የራቅኩት ድርጅት ዛሬ ቀኑ ደርሶ በወጉ የአባልነት ግንኙነታችን ያበቃ ዘንድ የራያው ጉዳይ አንዱ ምክንያት ሆኗል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እና በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ የለውጥ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል። በእርግጥ የአገራችን ችግር መሰረታዊ ለውጥ የሚሻና ውስብስብ ቢሆንም ችግሩን የሚመጥን መሰረታዊ የለውጥ ፕሮግራም ተነድፎ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሆነ መናገር ይቻላል።

ህወሓት በጥቂት ጠባብ ጸረ ለውጥ ቡድን ተጠልፎ ከሃገራዊ ለውጥ ጎን መቆም ሳይሆን ፀረ- አቋምን ምርጫው አድርጎ ለውጡ የትግራይን ህዝብ ጨምሮ መላው የአገሪቱ ህዝብ የሚጠቅም ቢሆንም ቅሉ፤ የውስን ሰዎች ጥቅም የሚያስቀር ሆኖ በመገኘቱ ብቻ ድርጅቱ ሊታገልለት የሚገባውን የትግራይ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ሳይሆን የጥቂት የህወሐት ባለስልጣናት ጥቅም ለማስከበር ሲል ለውጡን ተቃርኖ ብቻ ሳይሆን አፍራሽ በሆነ የሰላ ጥግ ላይ ቆሟል።

በመሰረቱ ዲሞክራሲም ሆነ እኩልነት የትግራይ ህዝብ ለዘመናት የታገለላቸው እና ውድ ልጆቹን የገበረላቸው የህልውና ጥያቄዎች እንጂ ባለጋራዎቹ አይደሉም። አዲሱ የለውጥ ፕሮግራምም ተንጋዶ የበቀለውንና የማቃናትና አሜኬላውን የመንቀል እንጅ ከትግራይ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተቃርኖ የመጣ አይደለም። ህወሓት በዚህ ታሪካዊ ወቅት እየተወሰደ ያለውን ትክክለኛ እርምጃ የመቃወም ግዙፍ ስህተት ከድርጅቱ ጋር አብሬ እንዳልቀጥል ካደረጉኝ መሰረታዊ ምክንያቶች ሁለተኛው ነው።

ከዛሬ ነገ ችግሮች ተቀርፈውና ተሻሽለው ከመስመር የወጡ አካሄዶችም ፈር ይዘው ይራመዳሉ በሚል ትዕግስትና ተስፋ፤ ብዙ ነገሮችን በራሴ ይዤ እየታገልኩ ቆይቻለሁ። በግሌም ሆነ በተገኘሁበት ማህበረሰብ ላይ እጅግ መራር ውርጅብኝ እየወረደ፤ ይባስ ብሎም በአገር ደረጃ ነገሮች እየተበለሻሹ እየሄዱ እንኳ ነገሮችን ለማቃናትና ለማሻሻል የበኩሌን እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ አካሂጃለሁ። የሆነ ሆኖ ከግትር አቋማቸው ፈቀቅ የማይሉ ተቸካዮች በህዝብና በአገር ላይ የሚያደርሱት ግፍ አልበቃ ብሏቸው፤ በተገኘችው ጭላንጭል ዕድል ይህን መከራ ለማስቆም የሞከርኩትን ግለሰብ ስም ለማጥፋት በየመንደሩ ሲባዝኑ ይውላሉ።

ከጥንት ጀምሮ ለነፃነት ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር አብሮ የተዋደቀውን የትግራይ ህዝብ፤ ዛሬ እንደሰብዓዊ ምሽግ ተጠቅመው ሊለያዩት ቢሞክሩም፤ ይህ የአክራሪ ወንጀለኞች የቀን ቅዠት እንደጉም መብነኑ እና መክሸፉም የማይቀር ነው! ኢትዮጵያዊነትን ከትግራይ ህዝብ ልብ ላይ መፋቅ ከቶም የማይቻልና ዛሬም ቢሆን እላዩ ላይ ተጋድመው የተጫኑትን የቀንበር እንጨቶች ሰብሮ ዳግም ለእኩልነትና ነፃነት እንደሚበቃ ቅንጣት ጥርጥር የለኝም!

በመጨረሻም ፀረ-ለውጥ እና ፀረ-ዴሞክራሲ ከሆነው ድርጅት ጋር ለመቀጠል ህሊናዬ ባለመፍቀዱ በገዛ ፍቃዴ ከድርጅት አባልነት የለቀቅኩኝ መሆኑን እያሳወቅኩ በቅርቡ ያታግለኛል ከምለው ድርጅት ጋር ተደራጅቼ የራያና መላ የአገራችን ህዝብ ጥያቄ ይበልጥ መልስ እንዲያገኝና ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተደረገ ያለውን ርብርብ አቅም በፈቀደው ሁሉ ለማገዝና ለመታገል እንደምሰራ ከወዲሁ ለማሳወቅ እወዳለሁ። የራያ ህዝብ በተድላና በፍቅር ከወሎ አማራና ከመላው የአማራ ህዝብ ጋር ለዘላለሙ ይኖራል። ምክንያቶቹ በትንሹ እነዚህ ሲሆኑ በማወቅም ይሁን ባለማቅ በእስካሁኑ የፖለቲካ ህይወቴ ያስቀየምኳችሁ ካላችሁ ከልብ የመነጨ ይቅርታን እጠይቃችኋለው።

ዛዲግ አብርሀ
ድልና ነፃነት ለራያ ህዝብ!
ዴሞክራሲና ሰላም ለመላ የአገራችን ህዝብ!


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: News Tagged With: Full Width Top, Middle Column, zadig

Reader Interactions

Comments

  1. holdig migroinn says

    February 6, 2019 11:14 pm at 11:14 pm

    The chicken came home to roast

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • “ዐቢይ ይውረድ፣ እኛ እንውጣ፣ በተራችን እንግዛ” ስልቴዎች (ስብሃት፣ ልደቱ፤ ቴዎድሮስ) June 11, 2025 01:56 am
  • ኤሊያስ መሠረት የሚሠራው ለማነው? ለብጽልግና? ወይስ …? June 3, 2025 01:27 am
  • በግንቦት 20 – የሁለት መሪዎች ወግ May 28, 2025 02:01 am
  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am
  • ከትግራይ ሾልኮ የወጣው ምሥጢራዊው ሰነድ ምንድነው? May 20, 2025 09:18 am
  • በደቡብ ጎንደር በጸዳሉ ደሴ የተመሩት 72 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ May 19, 2025 02:24 pm
  • የተመሠረተው የፋኖ አደረጃጀት ዋነኛ ዓላማው ድርድር መሆኑ ተነገረ May 14, 2025 11:07 pm
  • ከፍተኛ የፋኖ አመራሮች መገደላቸው ተነገረ May 6, 2025 10:40 pm
  • ሃይማኖትን ለተራ የፖለቲካ ሸቀጥ ማዋል ውርደት ነው April 24, 2025 12:43 am
  •  የኬሪያ ኢብራሒም ኑዛዜ “ብትንትናችን ወጥቷል” April 22, 2025 12:08 am
  • ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አመራሮች ወታደራዊ ሥልጠና ተሰጠ April 16, 2025 11:44 pm
  • ዓቅም እንደሌለው የገመገመው ሻዕቢያ ፊቱን ከጦርነት ወደ ዲፕሎማሲ እያዞረ ነው   April 15, 2025 12:32 am
  • “አንድ የፋኖ ተቋም (የእስክንድር) ተመሥርቷል፤ ሌሎቹ ደግሞ እንዲሁ አንድ ተቋም መሥርተው ወደዚህ ይመጡ” አበበ ጢሞ April 11, 2025 12:07 am
  • መለስ (ለገሰ) ዜናዊ – ተዋርዶ ያዋረደን! April 9, 2025 10:28 pm
  • የተከዜ ዘብ: የሉዓላዊነት መጠበቂያ April 8, 2025 11:49 pm
  • አዲስ አበባ አስተዳደር የሪፖርተርን የተዛባ መረጃ ኮነነ፤ ሕጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ አለ April 8, 2025 10:06 pm
  • ሀሰተኛውን የሪፖርተር ዘገባ ንግድ ባንክ በጽኑ ተቃወመ፤ እርማትም ጠየቀ April 8, 2025 09:48 pm
  • “ኦሮሚያ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ስታደርገው ከነበረ ትግራይ ወስጥም የማታደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርህም” ነው ጌታቸው ረዳ April 7, 2025 10:22 pm
  • “TPLF’s belief in a strong federal government was always tied to its own dominance in Addis Ababa” April 7, 2025 10:15 pm
  • Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation March 31, 2025 02:36 am
  • የኤሊያስ መሠረትን ፌክ መረጃ ማን ያጋልጥ? February 19, 2025 06:00 pm
  • አዘርባጃን፡ የሻዕቢያን ሸምቀቆ ማጥበቂያ?! February 19, 2025 12:29 am
  • የአሜሪካ ድምፅ/ቪኦኤ ይዘጋ ተባለ  February 12, 2025 03:37 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2025 · Goolgule