አንድ ብልጣብልጥ ባለተራ ፤ ከያኔ ነኝ የሚል ጽፎ
በእሱ ቤት የማላውቅበት ፤ መከደሩን ለንብ ቀፎ
በየሔደበት ያወራል ፤ ጸሐፊያንን ነቃቅፎ
ጋዜጣ መጽሔት ድረ ገጽ ፤ ወደዛ! እያለ ተጸይፎ
አታንብቡ አትስሟቸው ፤ ብሎ ያርቃል አንባቢ
የጌቶቹ ጉድ እንዳይወጣ ፤ እንዳይገለጥ ሸባቢ
እንዴት ምን ነካህ? ለሚሉት ፤ ተገርመው በጭፍን ትችቱ
ችግር መኖሩ መች ጠፋን ? ይሄ ሀገር የሚሻው በብርቱ
መፍትሔውን ቢነግሩን ነው ፤ ይላል ልሳኑን አስልቶ
መፍትሔው እንዳልተጻፈ ፤ ከችግሮቹ ጋር ጎልቶ፡፡
ይሄው አይደሉ እነሱ? ማደናቆር መተጣጠፍ
ምን እነግራለሁ ለእናንተ ፤ ታውቋቸው የለ ከወደአፍ?
በዐይን የሚታየው በጉልህ ፤ የሚጨበጠው ተይዞ
ካሳበቃቸው ጭራሽ የለም ፤ በቃ የለማ ማን አዞ?
የማይታየው የሌለው ፤ ምናባዊውን ሕልም እንጀራ
ብሉ ጠጡ ጥገቡ ነው ፤ እንዲሁ በባዶ ጉራ
እንዴ! እንዴት ሆኖ? አትሉም ፤ በቃ ይሄ ነዋ ክደራ፡፡
ግድ የለም ይሁን ወዳጀ ፤ ዐይኔ ዐላየም ካልክ መፍትሔ
ተጽፏል ብለህ ያመንከው ፤ ችግሮች ተብሎ ያ ይሄ
ችግርን ማወቅ መረዳት ፤ ያገር ሀብት ከንቱ የሚያስፈጅ
ግማሽ መፍትሔ ነው እንዲሉ ፤ ምዕራባዊያን ሥልጡን ፈረንጅ
ችግሮችህን መንገሩ ፤ ጸሐፊው ውዱን የሀገር ልጅ
ይገባሀል እንጂ ማመስገን ፤ አደግድገህ በመንሣት እጅ
እኮ በል እንዴት ሆኖ ነው? በአንተ ዝርው አፍ በገፈጅ
የሚነቀፍ የሚኮነነው ፤ መስታውቱ ጉድፍ አስወጋጅ ፡፡
የሌለውን አለ ሳልል ፤ ያለውን ግን አውጥቸ
ከነ መፍትሔ መላውም ፤ ጽፌልሐለው አጥርቸ
እኮ በል ልይህ ስትሔደው ፤ በአልኩህ መንገድ ማምለጫ
መፍትሔም አላልክ መድኃኒት? ከችጋር ግፍ አሳር መውጫ
እኮ በል ልይህ አድርገው? ያው እኮ ነገርኩህ ጩሄ
ግፈኞቹ የተውልህን ፤ የቀረህ ብቸኛ መፍትሔ
ደፋኸውሳ አንገትህን ፤ አሄሄ አሄሄ አሄሄ!
ተነቃቅተናል ወዳጀ ፤ ዝም ብለህ ልቀም ከበርሔ
ቡሌ ፍርፋሪህን ፤ የኩሊነትክን ድርሻ
ምን ማዕረግ አለውና ፤ ከዚህ በላይ የደጅ ውሻ?
ከዚያ ውጭ መፍትሔ ካለህ ፤ የሚሆን ያልተሞከረ
በላ ንገረን እንስማው ? ሳንሔድበት የቀረ፡፡
ግን እባክህን ወዳጀ ፤ የምለምንህ በብዙ
ከያኔ ነኝ አትበለን ፤ ቃናውም የለህ ወዙ
እናት ኪነትን ጠይቄያት ፤ ልጅ እንዳላት ብየ እንዳንተ
ኅሊናውን ለሆድ ሸጦ ፤ ቡሌ የሚለቅም የሳተ
እውነትን የሚረጋግጥ ፤ የግፈኛ አገልጋይ ሎሌ
የሞራል(የቅስም) እሴት የሌለው ፤ የማንም ምናምን ኩሊ
ልጀ አይደለም አላውቀውም ፤ እናቴ አይበለኝ አደራ
አደራ አደራ አደራ ፤ ቁጣየ እጅግ ነው መራራ
የእኔ ልጆቸ የታወቁ ፤ የእውነት ጠበቃ ለሐቅ ያደሩ
ኅሊናቸውን አክባሪ ፤ በሕዝብ በሀገር አይቆምሩ
ከዚህች ፈቀቅ የማይሉ ፤ ሞት እንኳን ቢሆን የማይፈሩ
ግፈኞችን ሳይዋጋ ፤ የሰላ ብዕሩን ወድሮ
መራሩን ዋጋ ሳይከፍል ፤ ለእውነት ሲል ወህኒ ተወርውሮ
ወህኒም ባይወርድ ባይጋዝ ፤ ፊት ሳይነፈግ ተገዳድሮ
የግፉአን ልሳን ሆኖ ፤ ለፍትሕ ለእውነት አብሮ
ይሄን ሳያደርግ ሳይተጋ ፤ መንፈሱን እራሱ ሰብሮ
የጨለማው ዓለም መብራቷ ፤ እንደ ድቅድቅ ጨላማ ጠቁሮ
ህዋሳቱን አደንዝዞ ፤ አእምሮውን አደንቁሮ
የጥፋት ኃይሎች ኃይል ሆኖ ፤ የሕዝብን እውነት ቀብሮ
ድንቄም ከያኔ የእኔም ልጅ ፤ የማን ነው ጭንጋፍ ቀበሮ?
ሕዝብና ሀገርን ከድቶ ፤ የእውነት ቀባሪ መደዴ
ይሄ ከያኔ አይደለም ፤ ነው ለሆዱ ያደረ ነጋዴ
ምንም ነገር እንደማያውቁት ፤ ያለሆዳቸው ምንዳ
ወደ እንስሳነት የተቀየረ ፤ ለምን? እንዴት? አይል ዱዳ
ብላሀለችና እናት ኪነት ፤ ደፍረህ ሳታፍር ሳተፈራ
ገጣሚ ደራሲ ሠዓሊ ፤ ተዋናይ ተጫዋች ዳንኪራ
ኪነት የነፍሴ ጥሪ ፤ ብለህ መስሟ እንዳትጠራ!!!
የፈለገኝ ሊያየኝ የሻ ፤ ምንጊዜን ቢሆን አድራሻየ
ከሕዝብ ከእውነት ጋራ ነው ፤ የእኔ መኖሪያ ቦታየ
የተፈጠርኩበት ዓላማ ፤ ሥራና ተግባር ሞያየ
ቃልኪዳኑን ሲያስርልኝ ፤ የጥበብ አምላክ ጌታየ
ሕይዎትን ቀና ማድረግ ነው ፤ ችግር ግፍ አሳር ታግየ
እንጅ ሕይዎትን ለማምረር ፤ አይደለም ለአውሬ ደልየ
ልብ ያለው ሁሉ ልብ ይበል ፤ ጽኑ ነውና መሐላየ፡፡
ብላለችና ጥበብ ኪነት ፤ መልእክቱ ይድረስ ለሁሉ
የሳተ ቶሎ ይመለስ ፤ ይቅር ይባላል በደሉ፡፡
ነሐሴ 1 2006 ዓ.ም.
መታሰቢያነቷ ለልማታዊ ……በሚሉ
speaker says
I am crying.