“ከኦነግ ሸኔ ጀርባ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) መኖሩን የሚያሳዩ መረጃዎች በፖሊስ ተደርሶባቸዋል” ሲሉ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ገለጹ።
ጀኔራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ ከትላንት በስቲያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው እንዳመለከቱት፤ “በህወሃት ስልጠና ተሰጥቷቸው በኦሮሚያ ክልል ሽብር እንዲፈጽሙ ከተላኩት መካከል የተያዙ ሰዎች እንዳሉ አረጋግጠናል” ብለዋል።
ድምጸ ወያኔ ቲቪ እና ኦኤንኤን ቲቪ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ዘገባዎች በመስራት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ሃይል ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በተለያዩ ቦታዎች የመንግስት ሰራተኞችን፣ አመራሮችን፣ ነጋዴወችን ጨምሮ በንጹ ዜጎች ላይ ግድያ ሲፈጽም መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሁንም በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ የኦነግ ሸኔ ቡድን በህወሃት ታግዞ ጥቃት ማድረሱን ገልጸዋል።
“በዜጎች ላይ ጥቃቱን ያደረሰው አካል ኦነግ ሸኔ መሆኑ ተረጋግጧል” ያሉት ኮሚሽነር ጄኔራሉ፤ ከጥቃቱ ጀርባ ህወሃት መኖሩን የሚያሳዩ መረጃዎች በፖሊስ መገኘታቸውን ገልጸዋል።
የተፈጸመውን ጥቃት የሚያካሂዱ ሰዎች በትግራይ ክልል ውስጥ ስልጠና አግኝተው በህዝብ ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ በህወሃት አቅጣጫ እየተሰጣቸው እንደሆነም ተናግረዋል።
“ፖሊስ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው የጥቃት አድራሾች ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከድርጊቱ ፈጻሚዎች ጀርባ ህወሃት አለ” ብለዋል ኮሚሽነር ጄኔራሉ።
“ህወሃት አሰልጥኖ ለሽብር ድርጊት ወደ ኦሮሚያ ክልል የላካቸው ሰዎች እንዳሉ በፖሊስ ተደርሶበታል” ያሉት ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ፤ ከድርጊቱ ጀርባ ህወሃት ስለመኖሩ የሚነገረው በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርቶ እንደሆነ ተናግረዋል።
በተፈጸመው ጥቃት አንድ ትምህርት ቤትን ጨምሮ ከ50 እስከ 60 የሚደርሱ ቤቶች ተቃጥለዋል።
በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ ሁለት ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን በአጠቃላይ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 34 መድረሱን አመልክተው፤ 12 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አለመታወቁን ገልጸዋል።
በጥቃቱ የተነሳ የተፈናቀሉ ሰዎችን የማረጋጋትና መልሶ የማቋቋም ስራ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።
የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት አስፈላጊውን ርምጃ እንደሚወስድ መገለጹ ይታወቃል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply