ባለፈው “ምን ይባላል?” በሚል ርዕስ ላቀረብነው የብሌን ከበደ ግጥም በመሳተፍ ጨዋታውን በግጥም ላደመቃችሁት Yaredo Enkubi እና በለው ምስጋናችን የላቀ ነው:: ሌሎችም በፌስቡክ ገጻችን በኩል አስተያየት የሰጣችሁንን ከልብ እናመሰግናለን:: ለዛሬ ደግሞ የዘወትር ተሳታፊያችን የካናዳው ከበደ ይህንን ግጥም ለከውንናል – “የኔ” የምለው በማለት ለላኩልን ግጥም እናንተስ ምን ትላላችሁ? “የኔ” የምትሉትን በማለት ጨዋታውን እናድምቀው – ሃሳባችንን እንንወጣው – የልባችንን እንግለጽ::
“የኔ” የምለውን፤
ታሪኬን ኩራቴን
መብቴን ነፃነቴን
…ኢትዮጵያዊነቴን
ከውስጤ አውጥታችሁ
መሬቴን ወስዳችሁ፤ ቤቴን አፍርሳችሁ
መንገድ ብትሠሩ
ፎቅ ብትደረድሩ
ቢትረፈረፍ እንኳን
መብራቱ ባቡሩ
እኔ “የኔ” ብየ እስካልተቀበልኩት፤
እስካልያዝኩት ድረስ
ምንም አይመስለኝም
ቢነድ፤ ቢቃጠል፤ ቢናድና ቢፈርስ
ትዕግሥቱ ሲሟጠጥ
ሰው ሲቆርጥ ተስፋ
ተመልከት ሲሪያን፤
አገር በልጆቿ እንደምትጠፋ
(የካናዳው ከበደ)
በለው ! says
***************
ታሪከ! ነፃነት! ክብር! ዜግነትማ! ተገፎ ተዋርዶ
ሕዝብ እየተናቀ ገንዘብና ጉልበት ህብሪትን ወልዶ
ለመኖር ለመሄድ መናገር ለቀብር ለምኖ አስፈቅዶ
ተገዛም ተሰጠ ፍቅረ-ንዋይማ ስብዕናን ወስዶ
በቋንቋ በዘር በአሳላጭ ተጫጭቶ በጥቅም ተሞዳምዶ
በሙስና ፍቅር በመሬት ተጣልቶ በሕንፃው ላይ ተዋዶ
ከሰው የበለጠው የድንጋይ ክምር ዋሻ ነው ወይ ነዶ !
___—-___——___አዎን!
ሲዘርፉ ሲግድሉ ሲበሉ ለእናንተ ነው ሲሉን
የእናንተ የእኛ በእኛ ለእኛ ብቻ ይሆናል ያሉን
በጥቅም ሲጣሉ ሲሻሙ ሲቃሙ እሪ በሉ የሚሉን
የጠገበ እርስ በርሱ ይባላል የተራበ ይበላል መሪውን
የማን ነው ብለን ነው ዘራፍ በሉ ያሉን!?
ከቶ ለማን ብለን? አባሉን እንጂ መች አበሉን?አስበሉን?
አውቀነዋል ለምን ባልበላ አንጀታችን ሙት እያሉ የሚምሉልን ።
በለው! ከሀገረ ካናዳ
Mohammed Seid Ali says
ደግ ተንፍሰሃል የካናዳው ከቤ፤
ይህ የኔም ሃሳብ ነው የነፍሴ የልቤ፣
ግንኮ ወዳጄ እኔ የኔ ምለው አለኝ ብዙ ሀብት፤
አንበሽብሾኝ የለ ፀሃዩ መንግስት፤
ቢፈርስንኳ ቤቴ መልሶ እንዲለማ፤
ሰጥቶኛል ቅሊንጦን አሲዮ ቤሌማ፤
አባይም ይገደብ ዛሬ እኔ ታርዤ፤
ነገ እቀዳዋለሁ ጀሪካኔን ይዤ፤
ስደትም የኔ ነው ስቃይ እንግልት፤
አስፓልቱም ይደልደል ነገ ባደባባይ እንድሞትበት፤
ኢቲቪም የኔ ነው ፋናየም የኔው ናት፤
የተኸለቁልኝ ስሜን ለማጠልሸት፤
አጋዚው ልዩ ሃይል ፌዴራል ፖሊሱ፤
በየኮሌጆቼ ፈጥነው የሚደርሱ፤
አሉኝኮ አስጠኚ ሂሳብ ኬሚስትሪ፤
እያገላበጡ በጥቁር ጉማሬ፤
ከፈለኩኝ ደግሞ ለነፍሴ ማደር፤
በየመስጊዶቹ ገዳማት ደብር፤
ቁርአን የሚያቀራ ወንጌልን የሚሰብክ፤
ልማታዊ ካድሬ ፂሙን አንዠርግጎ ቆቡን አርጎ ልክክ፤
አለኝ ቄስ ቃልቻ የሽፈራው ምሩቅ፤
የሚያቃርብ ሳይሆን ከጌታ የሚያርቅ፤
እና ወዳጄ ሆይ እኔ የኔምለው፤
የወያኔ መንግስት ዘርቶ ያበቀለው፤
አለኝ አለኝ አለኝ እልፍ ወአእላፍ፤
አንዷን ካጎደልኩኝ ቶርች የሚያስገርፍ።
Bombu says
የካናዳው ከቤ ያቀረብከው ግጥም
ካርስቱ ጀምሮ በቁምነገር ፍርጥም
ያለ ስለሆነ እኔም ወድጃልሁ
ይልመድብህ ብዬ ወደኔ መጣልሁ
እንደኔ ከሆነ እንደተራ ዜጋ
ሰማይ መሬት ወርዶ ባግድም ቢዘረጋ
ኣይደለም ሥርዓት የሕዝብ ድጋፍ ያጣ
እምቢ ለዜግነት እረ ማንም ይምጣ
የሥልጣኔማ መነሻው ከድሮ
ሓገር መንግሥት ዜጋ ባንድነት ተሳስሮ
ነበረ ዕውቀቱ ከውነት መዳረሻ
ይባስ በኢትዮጵያ በስው ዘር መነሻ»
አሥራደው (ከፈረንሳይ) says
“የኛ” ነው! “የኛ” ነው! – “የኛ”ነው የ’ኔ ቃል፤
“የኔ” እምለው የለም – “የ’ኛ” ይበልጥብኛል::
ያንቺ የሷ ይሁን – የነሱ ለነዚያ፤
አብሮነት አንድነት – ይሁነን መመሪያ፤
ያንተ የኔ ሆኖ – የኔ ያንተ ይሁን፤
ኢትዮጵያ የኛ ናት – እኛም ያገራችን::
ወዳጅ እንዲያከብረን – ጠላት እንዲፈራን፤
በጋራ አብሮ መኖር – “እኛ” ነው እሚበጀን::
የ’ኔ የ’ኔ ቀርቶ – የ’ኛ ስንባባል፤
ፍቅራችን ያብባል – አገርም ይለማል::