
መጪዎቹን የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ ለማድረግ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅቶች ማድረጋቸው ተገለፀ።
ይህን የገለጸው ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፀጥታና ደህንነት አካላት በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ ተግባራዊ የፀረ-ሽብር ሥልጠና ሰጥቷል።
ሥልጠናው ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ ከሪፐብሊካን ጋርድና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ኃይል ለተውጣጡ ከ330 በላይ አመራሮችና አባላት ነው የተሰጠው።
የንድፈ ሃሳብና የተግባር ሥልጠናው ሽብርተኝነትን መከላከልና ማክሸፍ፤ የሽብር ተልዕኮዎችንም አስቀድሞ ማወቅ የሚቻልበትን የመረጃ ሥራ ያካተተ ነው።
በዚሁ መሰረት ሰልጣኞቹ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊ /ቪ.አይ.ፒ/ እገታን በተቀናጀና ዘመናዊ መሳሪያ በመጠቀም ማስለቀቅ የሚያስችል ኦፕሬሽን በተግባር ስልጠናው አካሂደዋል።
ኦፕሬሽኑ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ፣ ፈንጂ አምካኝ ሮቦትና ሌሎች የጸረ ሽብር ተግባራትን በማሟላት የተካሄደ ነው።
ሠልጣኞቹ ተለዋዋጩ የዓለም ሽብርተኝነት በሚያስከትለው ጉዳት የሕዝብ ሠላምና ደህንነት እንዳይደፈርስ ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም ከስልጠናው ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የሽብር ጥቃቶች በኢትዮጵያ ቢቃጡ ቴክኖሎጂ በመጠቀም አስቀድሞ ለመከላከልና ለማክሸፍ ስልጠና አቅም እንደሆናቸውም አክለዋል።
ረዳት ኢንስፔክተር ተስፋዬ ብርሃኑ እና ኮማንደር ሰለሞን ፋንታሁን እንዳሉት በተግባር ልምምዱ በሽብርተኞች የሚጠመዱ ፈንጂዎችን ዘመናዊ ሮቦት በመጠቀም ማክሸፍ እንደሚቻል አሳይተዋል።
የፈንጂ አምካኝ ምህንድስና ባለሙያው መስፍን እንዳለ መሳሪያው ከሰው ሃይል አቅም በላይ የሆኑ የተጠመዱ ፈንጂዎችን በጥንቃቄ ማክሸፍ እንደሚችል ገልጸዋል።
ሥልጠናው ማንኛውንም አይነት የሽብር ወንጀል በቅንጅት ለመከላከልና ለማክሸፍ እንደሚያስችላቸው የተናገሩት ደግሞ የልዩ ኮማንዶ አስተባባሪ አቶ ለማ ባቱ ናቸው።
በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ ላይ የሚቃጡትን ጉዳት ለመከላከልም ያግዛል ብለዋል።
ሥልጠናው አል ቃይዳ፣ አይ.ኤስ እና አልሸባብ የሽብር ቡድኖች የኢትዮጵያና የአካባቢውን አገራት የሠላም፣ የትብብርና የልማት ማዕቀፍ ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመግታትና ለማክሸፍ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ሽብርተኝነት የደቀነውን ስጋት ለመመከት ስልጠናው በአገሪቷ የተለያዩ የክልል ከተሞችም ቀጣይነት እንዳለው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኢዜአ ገልጿል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply