አንጀት አርስና አንገት አስደፊ አስተያየት አንጀታቸው ካረረ ሽማግሌ። በመስሪያ ቤታችን የግንቦት 20 በዓልን እያከበርን ነው። ክቡር ሰብሳቢው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ብዙ የበዙና የተባዙ የለውጥ ማሳያዎችን ሲናገሩ ቆይተው በመጨረሻ እንዲህ አሉ፡-
“…ባጭሩ ከግንቦት 20 ድል በኋላ ተቆጥሮ የማያልቅ ብዙ ለውጥ አምጥተናል። በተለይም ኪራይ ሰብሳቢነትን በመታገል ረገድ ሙስና በማኅበረሰቡ ዘንድ ነውር ሆኖ እንዲታይ አድርገናል። ሁላችሁም እንደምታውቁት ድሮ ድሮ… “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል”… እየተባለ በድፍረት ይነገር ነበር። ይህ ማለት ሲሾሙ መብላት ሲሻሩ ላላመቆጨት ወሳኝ መሆኑን ኅብረተሰቡ አምኖበት ነበር። አሁን ግን ይህ አባባል እየቀረና እየተረሳ ነው። ይህም የትግል ውጤት ነው።”
ሰብሳቢው ይህንን በክብር እየተናገሩ እያለ ጋሽ ደፋሩ እጃቸው ላጥ! አድርገው አወጡ። (ጋሽ ደፋሩ የመስሪያ ቤታችን ሽማግሌው ሠራተኛ ናቸው። እንዲያውም በቅርቡ ጡረታ ሊወጡ ነው እየተባለ ይወራል።)
“እዚህ ጋ አስተያየት አለኝ… እዚህ ጋ…” አሉ ጋሽ ደፋሩ የሰብሳቢውን ንግግር በድፍረት አቋርጠው። ሰብሳቢ ንግግሩ በመቋረጡ እየተበሳጨ…
“ለአስተያየት ዕድል እስከሚሰጣችሁ ብትጠብቁ ጥሩ ነው ጓዶች… ለማንኛውም ሽማግሌን ማክበር ስላለብን… ሀሳብዎትን ይናገሩ” ብሎ ፈቀደላቸው።
ጋሽ ደፋሩ “እህህ…እሁሁ..” ብለው ጉሮሯቸውን በመሞረድ ይህንን አሉ። “ስለፈቀድህልኝ በሥልጣን ላይ ሥልጣን ይፈቀድልህ። ስላከበርኸኝም ከጥበቃ እስከ ሚኒስትር ማዕረግ ያለው ሠራተኛ ሁሉ ያክብርህ። ሽማግሌን ማክበር ጥሩ ነው። ቢያንስ ከመረገም ያድናል። … ወደዋናው ጉዳየ ስገባ… እኔ ምለው ልጄ.. የምትናገረውን አታውቅም ልበል?”
“ማ ? እኔ ነኝ የምናገረውን የማላውቅ?” አለ ሰብሳቢው ቆጣ ብሎ።
“አወና ! አንተ ራስህ።” ጋሽ ደፋሩ ንግግራቸውን በድፍረት ቀጠሉ።
“ምን ለማለት ፈልገው ነው?” ሰብሳቢው የበለጠ ተቆጣ።
“ለማለት የፈለግሁትን እስከምል መቼ አስጨረስኸኝ። መናገር እንጅ ማዳመጥ ብሎ ነገር እኮ አልፈጠረብህም።… ባጭሩ ለማለት የፈለግሁት… ይህ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለው አባባል የቀረው በእኛ ትግል ነው ስትል ትንሽም ሀፍረት ያልተሰማህ የምትናገረውን ስለማታውቅ ነው።”
“እስኪ እርስዎ ያወቁት ያስረዱኝ!” አለ ሰብሳቢው አሁንም ንግግራቸውን አቋርጦ። በእጅጉ እንደደነገጠ ፊቱ ያሳብቅበታል።
“አስረዱኝ ማለት ጥሩ። ያልተረዱትን ከተረዱት መጠየቅ የጨዋ ደንብ ነው። አየህ ልጄ…. ይህ አባባል ድሮ ድሮ ተደጋግሞ ይነገር የነበረው ብዙዎቹ ተሹመው ሳይበሉ ከሥልጣን ይወርዱ ስለነበር ነው። አሁን ግን…. ሲጀመር ተሹሞ እንደፈለገው የሚበላ ባለሥልጣን አይሻርም። ቢሻርም እንደተሾመ ይብዛም ይነስም በየአቅሙ በልቶ ስለሚሻርና ማንም በመሻሩ ሲቆጭ ስለማይታይ… አባባሉ እየቀረ ነው። እናም…የአባባሉን መቅረት መናገርህ ሐቅ ሆኖ ሳለ የመቅረቱ ምክንያት “ትግላችን ለውጥ ስላመጣ ነው” ማለትህ ግን ቅጥፈት ነው።”
ተሰብሳቢው በሳ ቅ በታጀበ ጭብጨባ….ጯ..ጯ…ጯ…ቿ..ቿ..ቿ…!!! ሰብሳቢው በሐፍረት ዝምምምም። (መላኩ አላምረው@DireTube)
Leave a Reply