ኢህአዴግ መሽቶበታል። አቅሙ ክዶታል። ባልሞት ባይ ተጋዳይነት አለሁ ቢልም ዘላለማዊ ዕንቅልፉ ግን የሚቀርለት አይመስልም።
የሜክሲኮውን ፒ አር አይ ፓርቲ አርአያው አድርጎ ሰባ አመታትን እጓዛለሁ ብሎ የተነሳው ድርጅት ግማሽ መንገድ እንኳን ሳይጓዝ ሊፈርስ ከጫፍ ደርሷል። ገዥው ፓርቲ ውስጥ ያለው የርዕዮተዓለም ልዩነት በማይታረቅ መንገድ የአደባባይ ሙግት ጀምሯል።
ኦዲፒ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መማል ካቆመ ቆይቷል። ሊቀመንበሩ ዓብይ አህምድም (ዶ/ር) ከትናንት ጋር የተኳረፉት ለዚህ ይመስላል። ብአዴን የምመራበትን ርዕዮተ ዓለም ዳግም አጤነዋለሁ ብሎ ዛሬ መወያየቱን ጀምሯል (ይህ ዘገባ ከተጻፈ በኋላ ብአዴን አዴፓ በሚል ህወሓት የሰጠውን ቀይሮታል)። ከዚህ በአንጻሩ ህወሓት አብዮታዊ ዲሞክራሲን ብረሳ ቀኜ ትርሳኝ ብሎ ሙጥኝ ማለትን ወዷል። ደኢህዴን ሁለት ጎራ ይዞ የለየለት ፍልሚውን ቀጥሏል።
የኢህአዴግ እህት ድርጅቶችን የተካረረ አቋም ለተመለከተ ሰው ኢህአዴግ በመፍረስ ጫፍ ላይ መሆኑን በውሉ ይረዳል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር አንድ የፖለቲካ ፕሮግራም ያስተሳሰረው ድርጅት መሆኑ ይታወቃል። ይህ ፕሮግራም ሁሉንም እህት ድርጅቶች ለአንድ ዓላማ ያሰለፈ የህልውና መገለጫ ተደርጎ የሚቆጠር ነው።
አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚል የዳቦ ስም ያለው ይህ የግንባሩ መሰሶ ከተናጋ ቤቱ መናዱ እንደማይቀር ዕሙን ነው። ለዚህ ደግሞ የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ትልቅ ምስክር ነው።
ኢህአዴግ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ “ኢህአዴግ የሚመራባቸው አጠቃላይ የአደረጃጀት መርሆዎች” በሚል ንዑስ ርዕስ ስር “ኢህአዴግ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አላማ ተግባራዊነት የሚንቀሳቀስ ድርጅት ስለሆነ በአባልነት ሊቀበልና ሊያሰባስብ የሚችለው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አላማን በግልፅ በፕሮግራማቸው ላይ የቀረፁ ድርጅቶችን ብቻ ነው”ይላል። የገዥው ፓርቲ የአባልነት መሰፈርት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፕሮግራምን ዓላማ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በውሉ ለተግባራዊነቱ መረባረብን ይጠይቃል። ይህ የፓርቲው ምሰሶ ዛሬ እንደ ደመራ በአንድ አቅጣጫ ዘሟል። የሚጠበቀውም መቼና በየት በኩል ይወድቃል የሚለው ብቻ ነው።
በየት በኩል ይወድቃል?
ኢህአዴግ በወረቅት ላይ ለጋስ ፓርቲ ከሚባሉት ተርታ የሚሰለፍ ነው። በዚህ ምክንያትም ማንም እህት ድርጅት ከኢህአዴግ አባልነት በፈለገው ጊዜ መውጣት እንደሚችል በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ አስፍሯል። በድርጅቱ ህግ አንቀጽ 13/2 ሀ. “ማንኛውም የግንባሩ አባል የሆነ ድርጅት ለግንባሩ ምክር ቤት አሳውቆ በፈለገው ጊዜ ድርጅቱን መልቀቅ ይችላል” ይላል። ዛሬ ኢህአዴግ ቤት ያለው መፈራራት ማን ቀድሞ እንዲህ ያለውን ኃላፊነት ይወስዳል የሚለው ነው። ነገርየው ደመራው በየት በኩል ይወድቃል የሚልን ጉጉት ያጭራል። ከዚህ ከፍ ሲልም ከኢህአዴግ ቤት የወጣ ድርጅት ከማን ጋር ተጣምሮ መንግስት ሊመሰርትስ ይችላል የሚል ጥያቄም ያስከትላል።
ብዙዎች ኢህአዴግ ከወደቀ የሚወደቀው በኦዴፓ አልያም በብአዴን (በአሁኑ አዴፓ) በኩል ነው የሚል ሀሳብ ይሰነዝራሉ። ኢህአዴግ ከፈረሰ በኋላም በጥምረት መንግስት የመመስረት ያላቸው ክልል ተሻጋሪ አጀንዳ ያላቸው ፓርቲዎች እነሱ ናቸው ይላሉ። ይህ ግን ከፖለቲካ ካፒታል ጽንሰ ሀሳብ አንጻር ከተመለከትነው ትልቅ ስህተት የሚሆን ይመስለኛል። ሁለቱ ድርጅቶች የየአካባቢያቸውን ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት የሚሄዱበት መንገድ ለየቅል ነው። የሁለቱ ክልል ፖለቲካ ልሂቃን የብሄርተኝነት አረዳዳም በሁለት ጫፍ ላይ የቆመ ነው።
ሊበራሊዝም ርዕዮተ ዓለም ጥላ ሁኖ ያስተሳስራቸዋል የሚለው ግምትም ከብሄር ወደ መደብ ላልተሸጋገረ ህዝብ ፖለቲከኛ የሚያዋጣ አይደለም። ከዚህ አንጻር ሁለቱ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ቤት ከመውጣት በላይ አንድ ሊያደርጋቸው የሚችል የፖለቲካ ርዕዮትን የመንደፍ ከባድ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።
በእኔ ግምት የኢህአዴግን የዘንድሮውን ጉባዔ ለየት የሚያደርገው በዚህ አጣብቂኝ መኃል መገኘቱ ነው። ዛሬ ላይ ቢያንስ አንድ ነገርን በእርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ኢህአዴግ በ2013 ዓ.ም የሚያደርገው ጉባዔ እንደቀደመው ጊዜው አራት እህት ድርጅቶቹን ይዞ የሚካሄድ አይሆንም።
ይህ ከዛሬ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የሚደረግ የፖለቲካ እንድምታ ነው። ይህ የእንድምታ ፍካሬ ግን ብቸኛ አይደለም። የገዥው ፓርቲ አፈለኛ አመራር ከርዕዮተ-ዓለም በላይ የስልጣን ጥቅም ያስተሳሰረው ከሆነ ኢህአዴግ የጣር ድምጽ እያስማም ቢሆን ሊጓዝ ይችላል። እንዲህ ያለው መንገድ ግን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን በኢህአዴግ ውስጥ ባለ አለመግባባትም ወደለየለት ምስቅልቅል ይወስደዋል። የሀገር ህልፈትንም ሊያስከትል ይችላል። (ማዕረግ ጌታቸው በድሬቲዩብ)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply