በማይጠብሪ ግንባር የሚገኘው የወገን ጦር ጠላትን እየደመሰሰ ወደ ፊት እየገሰገሰ ነው።
በጭና ቆርጦ ደባርቅና ዳባትን ሊይዝ የነበረው የትግራይ ወራሪ ቡድን በጭና እና በተለያዩ አካባቢዎች ድባቅ ተመትቶ አብዛኛው ተደምስሷል። የቀረው ወደ ኋላ በመመለስ ወደ መጣበት እየፈረጠጠ ነው። በግንባሩ የተሰማራው የወገን ጦርም እየተከታተለ እየደመሰሰው ነው።
በግንባሩ የክፍለ ጦር አዛዥ እንደነገሩን ሠራዊቱ በቦዛ፣ በጭና፣ በብና እና በተለያዩ አካባቢዎች ከባድ ጦርነት ማድረጉን ነው የተናገሩት። በተደረገው ጦርነትም የጠላት ቡድን ተደምስሷል።
በዛሪማና በድብ ባሕር አድርጎ ወደ ሊማሊሞ ሊወጣ የነበረው አሸባሪ ቡድንም በወገን ጦር ተመትቷል ነው ያሉት። ከድብ ባሕር እስከ ዛሪማ እየተቀጠቀጠ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ መመለሱን ነው የተናገሩት። ጠላት መልሶ እንዳይቋቋም ካደረጉት ምቶች መካከል የዛሪማ ምት አንዱ መሆኑንም ገልፀዋል።
ጠላት የዛሪማን ድልድይ በውስጥ በኩል ቦርቡሮ ፈንጅ ለመደበቅ ጥረት ቢያደርግም የወገን ጦር ባደረገው ፈጣን ማጥቃት ሳያፈርሰው መሮጡንም ገልፀዋል። የወገን ጦር ድልድዩ እንዳይፈርስ ያደረገው ፈጣን ማጥቃትም አስደናቂ እንደነበርም ተገልጿል። ድልድዩ እንዳይፈርስ በፍጥነት የገቡ ሚሊሻዎች ጠላትን ማበራየታቸውን ነው የገለፁት። ጠላት መልሶ ለመቋቋም የሚያደርገው ጥረት በምቱ ጠንካራነት መቋቋም አለመቻሉን ገልፀዋል።
ድልድዩ ቢፈርስ ኖሮ ለማኅበረሰቡም ሆነ ለሠራዊቱ የማጥቃት እንቅስቃሴ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚኖረውም ተናግረዋል። ጠላት ሲሸሽ ማኅበረሰቡን እየመዘበረ፣ እያሰቃየ፣ እየገደለ መሄዱንም ገልፀዋል። የመንግሥት ተቋማትን እያወደመ መሸሹንም ተናግረዋል። የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ ጥቃት በማድረሱ አሸባሪው ቡድን መደምሰሱንና ቶሎ እንዳይቋቋም ማሽመድመዱን ነው የተናገሩት።
የወገን ጦር ቅንጅት አስደናቂ መሆኑንም ተናግረዋል። የኅብረተሰቡ ድጋፍ ለውጊያው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረውም አንስተዋል።
ፋኖው መደበኛ ግዳጅ እየወሰደ የጠላትን ኃይል መምታቱን ነው አዛዡ የተናገሩት።
በዛሪማ የፋኖ መሪ አጋዬ አድማሱ ፋኖው ብዙ ጀብዱ በመፈጸም የጠላትን አንገት አስደፍቶ መመለሱን ገልጸዋል። ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን የሚሰጠውን ግዳጅ በብቃት እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል። ጠላትን እየደመሰስን እስከመቀሌ ለማድረስ ዝግጁ ነንም ብለዋል። (አሚኮ – ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ:-ማይጠብሪ ግንባር – ዛሪማ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply