የደመራ ዋና ዓላማ፤ “ሲቃወምና ሲጻረር የነበረውን የዕዳ ጽህፈት ክርስቶስ ከነ ሕግጋቱ በመደምሰስ በመሰቀል ላይ ቸንክሮ ከመንገድ አስወገደው” (ቆላ ፪፡፲፬)። ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው፤ የተደበቀውን እውነት ለመግለጥ፤ በሰው ላይ ተጭኖ የነበረውን ዕዳ ለመደምሰስ፤ ለሰባዊ ክብርና ልዕልና ተጻራሪ የሆነቱን ነገሮች ለማስወገድ ነው። [በሰፊው መረዳት ከፈለጉ ይህን ሰንሰለት ይጫኑ። ደመራ]
ሙሴ አራቱን የኦሪት መጻሕፍት ከጻፈ በኋላ፤ በአራቱም መጻሕት የገለጻቸውን ጠቅለል አድርጎ በድጋሚ ያቀረበበት አምስተኛው መጽሐፍ ዘዳግም ይባላል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሰባዊ ክብርና ልዕልና ተጻራሪ የሆነውን ለማስወገድ የገለጸባቸውን ኃይለ ቃላት ለማስጨበት “አማን አማን እብለክሙ” እያለ በመደጋጋም ተናግሯል። በጸሎተ ቅዳሴያችንም “ተንስኡ ለጸሎት” የሚለውን እንደጋግማለን። ቃጭልም በመደጋገም እናቃጭላለን። የሚደጋገሙበት ምክንያት፤ የሰው ቀልብ ባዘነጊ ነገር በፍጥነት ይሰረቃል። ለዘላቂ ህይወቱ ተጻራሪና ከንቱ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ ተንሸራቶ ስለሚገባ፤ ቀልቡንና ትኩረቱን ለመጠበቅ ነው። እንደዚሁ ሁሉ፤ እኔም አባቶቻችን የገጠማቸውን ችግር መፍቻ አድርገው የደመራውን በዓል እንዴት እንደተጠቀሙበት በመደጋገም ለማሳየት፤ ይህችን ጦማር ዘዳግም በሚል ርእስ ሰየምኳት።
የደመራም ሆነ የቀሩት ሁሉ በዓለት በየአመቱ በተደጋጋሚ የሚከበሩት፤ እውነትንና ፍትህን ለማስጠበቅ፤ ሰባዊ ክብርንና ልዕልና ለማስከበር፤ ለሰው ልጅ ደህንነት ተጻራሪና እንቅፋት የሆኑትን ለማስወገድ ነው። እኛም በጻድቃን፤ በሰማእታትና በአርበኞች የተከፈሉትን የመስዋዕትነት ዓይነቶች እያስታወስን፤ ምሳሌነታቸውን ተከትለን ችግራችንን ለመፍታት እንድንጠቀምባቸው ነው። እየተደጋገሙ የሚከበሩትን በዓላት ስርወ ነገራቸውን ሳንረሳ፤ ቀልባችንንና ትኩረታችንን በግርግሩ በመብሉና በመጠጡ ሳናሰርቅ፤ ህሊናችንንም በሸፍጠኞች ስብከትና ሽር ጉድ ሳናስረግጥ የምናከብራቸው ከሆነ፤ ለክብራችንና ለልዕልናችን ዘብ ከመቆም አንዘናጋም። የእግዚአብሔር ረድኤትም አይለየንም።
ዘመናት ሲወራረሱ፤ አጿዋማትና በዓላት የሚውሉባቸውን ወራትና እለታት ሊቃናት አበው ሲያውጁ፤ “ዘመኑን እግዚአብሔር ይባርክልን። በዚህ አመት የሚታወሱትንም ዓበይት በዓለት የሰላም፤ የደስታ፤ የፍስሀ፤ የጤና፤ የብልጽግና ያድርግልን” ይቀበለው እግዚአብሄር፤ እንበል አቡነ ዘበሰማያት” ብለው በጸሎት የሚያስተላልፉትን፤ በደመራው በዓል ከአየኋቸው፤ ከሰማኌቸውና ከታዘብኳቸው ክንውኖች ጋራ ሳነጻጽራቸው፤ የተጋጨ ስለመሰለኝ የደመራውን በዓል በማክበር ለተሳተፈው ሁሉ የተሰማኝን ለማካፈል ፈለኩ።
አባቶቻችን ባዲሱ አመት የሚታወሱትን ዓበይት በዓለት “የሰላም፤ የደስታ፤ የፍስሀ፤ የጤና፤ የብልጽግና ያድርግልን” ከአባር ከቸነፍር፤ ከእርዛት፤ ከርሀብና ከስደት ይሰውረን” ብለው ሲያውጁ፤ በዚህ ዓለም መከራና ደስታ መፈራረቃቸው የማይቀር ተወራራሾች እንደሆኑና እንዴት እንደምናስተናግዳቸው ገልጸውታል። በዓላቱ በሚታወሱባቸው ወቅቶች ሰላም፤ ደስታ፤ ጤናና መረጋጋት የሰፈነባቸው ከሆኑ፤ በትኩረትና በአንክሮ ያሉ አዛውንትና እቤራት “ንሴብሆ” እያሉ በደስታ አምላካቸውን እያመሰገኑ አብረው ይበላሉ ይጠጣሉ። ይደሰታሉ። ወጣቶቻቸውን ይዳራሉ። ይኩላሉ። አዕሩግና እቤራት በተረጋጋ መንፈስ ይጦራሉ። ጎረምሶች ኮበሌዎችና ቀነጃጅት (ደናግል ልጃገረዶች)ና ድኅረ ገቦች ሰባዊ ውበትን ከተፈጥሮ ውበት ጋራ በማነጻጸር ይዘፍናሉ። ሁሉም በእድሜውና በጾታው መስመር ተሰልፎ እንደየ አቅሙ እንደየ ስሜቱ በዘመነ ፍስሀ የሚውሉትን በዓላት በፍስሀ በደስታና በሀሴት ያከብሯቸዋል።
ዘመኑ፤ ዘመነ መንሱት ሲሆን፤ “የእግዚአብሔር ዐይኖች፤ የህብረተ ሰብ ቀንዶች” የሚባሉት ሊቃውንት ካህናት “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” በሚለው መመሪያቸው የምህላና የተጠንቀቅ መልእክት ለጠቅላላ ምእመናን ያስተላልፋሉ። አዛውንቶች የተጋረጠውን መከራ መመከት፤ መከላከል፤ መቋቋምና ማስወገድ የሚችሉትን ጎልማሶችን በእምነት በጥበብና በማስተዋል ያዘጋጃሉ። ባዛውንቶች የተዘጋጁ ጎልማሶችም፦
“አማን ነውይ፡ አገር አማን ነወይ?
ይህ ሰርቶ መብላት ጤና ላይሆን ነወይ? እያሉ በየጎራው፤ በየሸንተረሩና በየዱሩ ማቅራራትና መሸለል ይጀምራሉ። ኮበሌዎችም የጎልማሶችን ሽለላና ቅራርቶ በየመንደሩና በየመስኩ “እምቢ በል” በሚል ፉከራቸው ያጠናክራሉ። ድኅረ ገቦች፤ ቆነጃጅት (ልጃገረዶች)ም
“ዓባይ ሽቅብ እንጅ አይወርድም ቁልቁለት፤
ለእምነት መሰዋትን በላይ አስተምሮት” እያሉ ያዛውንቶችን የተጠንቀቅ መልእክት፤ የጎልማሶችን ሽለላና ቅራርቶ፤ የኮበሌዎችን እምቢ ባይነት ያጅባሉ። ሁሉም በእድሜውና በጾታው መስመር ተሰልፎ እንደየ አቅሙ እንደየ ስሜቱ በዘመነ መንሱት የሚውሉትን በዓላት ለችግር መፍቻ በማድረግ ያከብሯቸዋል።
ከኛ በፊት የነበሩት ኢትዮጵያውያን የከበቧቸውን ሁኔታወች ከግራ ከቀኝ፤ ከፊት ከኋላ እየቃኙ እንደየ ሁኔታዎች በዓላትን ስለሚያከብሩ በዓላትን ለችግራቸው መፍቻ አድርገዋቸዋል። ከበዓላቱ መሰረታውያን ነገሮች አፈንግጠው፤ ትኩረታቸውን በከንቱ ነገሮች ማለትም በመብል፤ በመጠጥ፤ ባዳዲስ ልብሶች በማጌጥና ተግባር በተለየው መዝሙርና ሽብሸባ ብቻ በዓላቱን የሚያከብሩ ከሆነ ግን፤ በዓላቱን ለችግራቸው ማጠናከሪያና ማረዘሚያ እንደሚያደርጓቸው የተገነዘቡ ነበሩ።
ዛሬ ወያኔዎች በዝሙተኞች፤ በዘራፊዎች፤ ሰባቂዎቻቸው፤ ቆሞሶቻቸውና ጳጳሶቻቸው አማካይነት ኢትዮጵያዊ ግንዛቤ የነበራቸውን የቤተ ክርስቲያናችንን ሊቃውንት ላንዳንዶች የማርያም ጠላትነትን ለሌሎች ፖለቲከኛነትን እየሰጡ፤ ከህዝብ በመለየት፤ ያዛውንቱን መንፈስ በሚያዳክምና የጎልማሶችን ወኔ በሚመታ እኩይ መርኋቸው፤ ኢትዮጵያን ወና፤ ቤተ ክርስቲያናችን ባዶ አድርገዋቸዋል። ባጫጭር ኮርሶች እየሞራረዱ በሰገሰጓቸው በቆመሱና ባልቆመሱ ጎረምሶች ግራ ቀኝ ወደፊትና ወደ ኋላ እንዳያይ በሚያዘናጋ አባዜ (አዚም) ህዝቡን አስረውና ቀይደው ይዘውታል።
የነጠረው የተዋህዶው ክርስትና ትምህርት ብቅ ሲል፤ ህዝቡን እኛን ከመሳሰለ ብቁአን ካህናት መምህራን ሊለዩዋችሁ ነውና አትስሟቸው። የሚጽፉትን አታንቡ፤ እኛ የምንነግራችሁን ብቻ በመስማት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተመላለሱ። ገንዘብ ስንጠይቃችሁ ያላንዳች ማቅማማት ለገሱ” እያሉ በግልም በቡድንም ይናገራሉ። በይፋ ባደባባይ ከተከሰሱበት፤ ከተወቀሱበትና በቅዱሳት መጻህፍት ተመዝኖ ከተወገዙበት መስመር ወጥተው ህዝብን ይቅርታ ሳይጠይቁ፤ ንስሀ ሳይገቡ ገንዘብ ላለማጣት ሲሉ በድፍረት ገብተው በመቀደስ ያቆርባሉ። ምእመናኑን “ቤተ ክርስቲያን ተከፍቶልን ከተሳለምን፤ የነሱን ስብቀት ከሰማን፤ ለብሰን አጊጠን በዓላትን ካከበርን፤ ጳጳሱ ቢዘርፍ ቢዘሙት ወንደ ላጤው ሁሉ ቢቆምስ፤ የሰው ትዳር ቢያፈርስ እኛ ምናገባን” እያለ ለኃጢአታቸው ደጋፊ እንዲሆን አድርገውታል። “ለኃጥአን የወረደ መቅሰፍት፡ ለጻድቃን ይተርፋል” እንዲሉ፦ በበደላቸው ከቀጠሉት ጳጳሳትና ቆሞሳት ይልቅ፤ እኛ ምናገባን በሚሉት ሰዎች ላይ የሚከሰተው መለኮታዊ ቁጣ እጅግ ያየለ ይሆናል። ከነዚህ መሳይ መምህራን የሚፈልቀው ርካሽ ስብቀት፤ ለነሱ ጊዜአዊ ርካት ይጠቅማቸው እንደሁ እንጅ፤ ለሚከተላቸው ህዝብ ለነፍሱም ለሥጋውም ፈጽሞ የሚጠቅም አይደለም።
ካስመሳይ ጳጳሳትና ቆሞሳት ጋራ አብረው በዓል እያከበሩ፤ በቡራኬ ስም መርገም እየተቀበሉ ሞራልን ሀላፊነትን የሚጠይቅ ጉዳይ ሲመጣ ምን አገባኝ ማለት፤ “ደመረ ሥጋሁ ምስለ መለኮቶ” ክርስቶስ ሰውነትን ከመለኮት ጋራ በመደመር ከፈጸመው የማዳን ተግባር፤ ቅድስት ዕሌኒ መስቀሉን ከተደበቀበት ካገኘችበት ደመራ እና፤ አባቶቻችን ችግራቸውን ከፈቱበት ደመራ ጋር የተጋጨ ያረመኔ ባህርይ ነው። አገራችንና ቤተ ክርስቲያናችን ከችግር ላይ የሚወድቁት ከደመራው አላማና መልእክት ጋራ የተጋጨ ዓላማ ያሏቸው ሰዎች የመሪነቱን ቦታ ሲወስዱና፤ በነሱም የሚመሩ ሞራለ ቢሶች የሆነ ሰዎች የሚሰጡት ሽፋን ነው።
ከደመራው መከበር በፊት፤ የተደረገውን ዝግጅት፤ በተከበረበት ሰሞንና ከተከበረባት ቀን በኋላ በተለያዩ ቦታዎችና በኢምባሲው ግቢ የተከናወኑትን ነገሮች፤ ከደመራው መሰረታዊ ዓላማ ጋር ሳነጻጽራቸው፤ በበዓሉ ዙሪያ የታዩት ትርፍና ከንቱ ነገሮች፤ የብዙሀኑን ትኩራት የሰረቁት ስለመሰለኝ፤ የተሰማኝን ስሜት በ፭ አናቅጽ ይህችን ጦማር አዘጋጀሁ።
፩ኛ፦ “ኢትዮጵያውያን እራሳቸው የሰሯቸውንም ሆኑ፤ ከውጭ የተቀበሏቸውን ክስተቶች፤ ከራሳቸው ባህልና ታሪክ ጋራ በማስተሳሰር ለክፉም ለደጉም ይጠቀሙባቸዋል”
፪ኛ፦ ክርስቶስ ደመራን ለችግር መፍቻ ተጠቀመበት
፫ኛ፦ እሌኒ ደመራን ለችግር መፍቻ ተጠቀመችበት
፬ኛ፦ አባቶቻችን ደመራን ለችግር መፍቻ ተጠቀሙበት
፭ኛ፦ በዲሲ የሚኖሩ ወገኖችም የዘንድሮውን ደመራ ለችግር መፍቻ ተጠቀሙበት።
፩ኛ፦ “ኢትዮጵያውያን እራሳቸው የሰሯቸውንም ሆኑ፤ ከውጭ የተቀበሏቸውን ክስተቶች፤ ከራሳቸው ባህልና ታሪክ ጋራ በማስተሳሰር ለክፉም ለደጉም ይጠቀሙባቸዋል”
ብለው የተናገሩት ኬንያ በነበርኩበት ኮሌጅ፤ የአንትሮፖሎጅና የሚሲዮሎጅ ፕሮፌሰር ዶ ክተር ስሚዝ የሚባሉ እንግሊዛዊ ናቸው።
በኮሌጁ ሁል ጊዜ ከእራት በኋላ Epilogue የሚባል መርሀ ግብር ነበረ። ትርጉሙ ከዘዳግም የራቀ አይደለም። በዚህ መርሀ ግብር በክፍል ከሚሰጡ ትምህርቶች ውጭ ባካባቢው፤ በአፍሪቃና በዓለም ዙሪያ አዳዲስ ነገሮችን ሲከሰቱ ወደ ክፍል በማምጣት ተማሪውን በማኳሸት ያስተቻሉ። በተማሪዎች መካከል ብዙ ፍጭት ከተካሄደ በኋላ፤ ፕሮፌሰሩ ባካበቱት እውቀታቸው፤ ዝርው የሆነውን የተማሪዎችን ሀሳብ ሰብስበው፤ አንጓለውና አበጥረው ይደመድሙታል። የውይይቱ ቋንቋ እንግሊዘኛ ከመሆኑ በቀር፤ በግእዙ ቋንቋ የምንፋጭበት ቅኔ ቤት የነበርኩ ስለሚመስለኝ በጣም ደስ ይለኝ ነበር።
ከዕለታት አንድ ቀን ከጆሞ ኬንያታ ጋራ እንግሊዞችን ታግለው ኬንያን ለነጻነት ያበቁ ባለውለታ ተብለው የሚከበሩ ትልቅ ሰው ሞቱ። እኒህ የተከበሩ ሰው፤ ኮሌጁ እንዲሰራበት ቦታቸውን የለገሱ ሰው ነበሩ። የሚሲዮሎጅ እና ያንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰር እያንዳንዳንዳችን ተማሪዎች ማስታዋሻ ይዘን የቀብራቸውን ስርአት ተመልክተን፤ ከየአገሮቻችን የቀብር ሥርአት ጋራ በማነጻጸር አንዳንድ ገጽ እንድንጽፍ አዘዙንና ተዘጋጅተን ቀብሩ ወደ ሚፈጸምበት ቦታ ሄድን። ከኔና ዮሐንስ ሁንቄ ከሚባል ኢትዮጵያዊ በቀር፤ ተማሪዎች እንግሊዞች በቅኝ ግዛት ይገዟቸው ከነበሩት፤ አሁን common-wealth በሚል መርሆ ከተሳሰሩ አገሮች የመጡ ነበሩ።
በሀዘን የጠወለገ፤ ሀዘንን የሚያሳይ ልብስ የለበሰ፤ ወደጃ፤ ዘመድ፤ ወንድሜ፤ ጓዴ፤ አባቴ እያለ የሚያለቅስ ሰው ጠብቄ ነበር። ነገር ግን በሬሳው ዙሪያ ያሉት ሰዎች ከመሳሳቅ በቀር የሚያለቅስ ሰው አላየሁም። የሰውየው ባለቤትና ልጆቹ ነጫጭ ልብስ ለብሰዋል። በየተወሰኑ ደቂቃወች ውሀ የሚያቀርቡላቸው ሰዎች ነበሩ። ቀብሩ ተፈጽሞ የማጽናኛ ትምህርት ከተሰጠ በኋል፤ ህዝቡ “till we meet” እያለ በመዘመር ተበተ። “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እየተባለ በደስታና በሀሴት የምናከብረውን የጥምቀት በዓል መሰለብኝ።
ከስርአቱ ፍጻሜ በኋላ እንደየግንዛቤያችን የጻፍነውን ለፕሮፌሰሩ አስረከብን። የኔ ጽሁፍ ከጠቅላላው ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን፤ አብሮኝ ኮርሱን ይሳተፍ ከነበረው ኢትዮጵያዊ ዮሐንስ ሁንቄ ካቀረበው ጽሑፍም የተለየ ሆነ። ለካ እሱ የጻፈው፤ “ለሞተ ሰው ማልቀስ ተስፋ እንደሌላቸው አረመኔነት ነው” (፩ኛ ተሰ ፬፡፲፫) ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ትንሳኤ ያስተማረውን ትምህርት ላልተረዱ ለተሰሎንቄ ሰዎች በተናገረው ላይ መስርቶ፤ የቀብሩን ስርአት “ተገቢ ክርስቲያናዊ ስርአት ነው” በማለት አድንቆ ጽፏል። የተለያዩ ትናንሽ ነገሮች ቢንጸባረቁም፤ የሱም የብዙዎች ሀሳብም የተቀራረቡ ሆኑ።
እኔ የጻፍኩት በወቅቱ ያየሁትን ሳልጨምርበት ሳልቀንስለት፤ ከመጣሁበት ባህል ጋራ አወዳድሬ፤ አንጻጽሬና ለክቼ ነበር። በአገሬ እንኳን ሰው እንስሳት ከወገናቸው አንዱ ታርዶ ወይም በአደጋ ሞቶ፤ ፈርሱ ሳይጠረግ ደሙ ሳይታጠብ ካካባቢው ከደረሱ። በፈርሱ ዙሪያ እየዞሩ ይጓጉራሉ። ወደ ሰባዊነት ስናመጣውም፤ አብርሃም ለሳራ አለቀሰ። ክርስቶስም እንኴን ለአላዛር አለቀሰ። ለሞተ ወገን ማልቀስ በእንስሳትና በሰው ከተፈጸመ፤ መደረገ ያለበት የተፈጥሮ ህግ መሆኑ ነው። ልቅሶን በሞት ለተለየ፤ ዘፈንን ለሙሽራ ካልተጠቀምንበት “ለሁሉም ጊዜ አለው” ከሚለው ጋራ ይጋጫል። ስለዚህ ያየሁትን የቀብር ስርአት ኢትዮጵያዊነቴ አልተቀበለውም” የሚል ነበር። ለካ ያቀረብኩት ተማሪው ሁሉ ካቀረበው ጽሑፍ አፈንግጧል።
ፕሮፌሰሩን እጅግ ያስገረማቸው፤ ለሞተ ዘመድ የሚደረገው ኢትዮጵያዊው አሸኛኝት፤ ተማሪዎች ከመጡባቸው አገሮች አሸኛኝት ልዩ መሆኑ ብቻ አልነበረም። አብሮኝ ከነበረው ኢትዮጵያዊም የተለየ በመሆኑ ነበር። መምህሩ ተማሪዎች በጻፉት ላይ አጠቃላይ ሀሳብ ሲሰጡ፤ የኔን ለይተው በማቅረብ እንዳለ አነበቡት። ቀጠሉና “ሁለታችሁም የመጣችሁ ካንድ አገር ነው። ለምን ተለያያችሁ? ብለው ሁለታችንን ጠየቁን። ጓደኛየ “እናትና አባቴ ከመወለዴ በፊት ኦርቶዶክሶች ነበሩ። በኋላ ወደ ፕሮቴስታንትነት ተቀየሩ። በነሱ ስር ያደኩ ነኝ። እሱ ኦርቶዶክስ ነው። ኦርቶዶክሶች ወንጌል አያውቁም። ስለ ትንሳኤም ብዙ አያስተምሩም፤ ባህል ብቻ ነው የሚሰብኩት። እሱ ባህሉ አለቀው ብሎ፤ ያንኑ ባህልኑን ጻፈው እንጅ፤ የመጣነው ካንዲት ኢትዮጵያ ነው” ብሎ መለሰ።
ፕሮፌሰሩ ተበታትኖ የቀረበውን የተማሪዎችን ሀሳብ አስተካክለው ፈር ለማስያዝ፤ “አሁን ሲደረግ የተመለከታችሁት የእንግሊዞች እንጅ የኬንያውያን ባህል አይደለም” አሉ። ቀጠሉና፤ እንግሊዞች ወደ ምሥራቅ አፍሪቃ ከመምጣታቸው በፊት፤ በኬንያ የነበሩ ጎሳወች የተለየ የቀብር ስርአት ነበሯቸው። እንዲያውም ባንዳንድ ጎሳዎች ሰው ታሞ ከቤት ውስጥ እንዳለ ነፍሱ ከወጣች፤ እንደ መረገም የሚቆጠርና መቅሰፍት የሚያስከትል ተደርጎ ይታመን ነበር። የማይተርፍ ከመሰላቸው እግሩን በረዥም ገመድ ጫፍ አስረው፤ የገመዱን ጫፍ ከቤት አካባቢ ባለ ዛፍ ወይም ግንድ ላይ ቋጥረው፤ ከቤት ራቅ አድርገው ይጥሉታል። ጧት ጫፉን ሲጎትቱ ገመዱ ብቻ ተስቦ ካለመጣ የመርገም ምልክት ነው ብለው ያለቅሳሉ። በሽተኛውን አውሬ በልቶት ገመዱ ብቻውን ከመጣ እንደ በረከት ይቆጥሩታል። ደስ ይላቸዋል የሟቹ ከብቶች እየታረዱ ይበላሉ። ይጨፍራሉ። ቅኝ ገዝዎች በቅኝ ግዛት ዘመናቸው ካስተካከሏቸው ነገሮች አንዱ ይህ ነው” ብለው ነገሩን።
ቀጠሉና “እኛ እንግሊዞች ለኬንያውያን የሰጠናቸው ስርአትም ሆነ ያስተውናቸው የራሳቸው ስርአት፤ ሰውነትን የሚገልጽ አልነበረም። ከኢትዮጵያውያኖች ስርአት ጋራ ስናነጻጽረው፤ የኛም የኬንያዎቹም ከሰባዊነት ክብር እርቋል” ካሉ በኋላ “ኢትዮጵያውያን እራሳቸው የሰሯቸውንም ሆኑ፤ ከውጭ የተቀበሏቸውን ክስተቶች፤ ከራሳቸው ባህርይና ታሪክ ጋራ በማስተሳሰር ለክፉም ለደጉም ይጠቀሙባቸዋል” በመልካም ቀን በደስታ ያሳልፉታል። በክፉ ቀን ደግሞ የገጠማቸውን ችግርና እንቅፋት ያስወግዱበታል። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ የራሷን ታሪክ ጠብቃ የሄደች ብቸኛ አስደናቂ አገር ናት” ብለው ውይይቱን ዘጉት። ፕሮፌሰሩ እንዳሉት በኦርቶዶክሳዊት ነገረ መለኮት ጥናት፤ በዓላት የሚከበሩት ሃይማኖታውያን ይዘቶች ስላሏቸው ብቻ ሳይሆን፤ ለማህበራውያን ችግሮችም መፍቻወች በመሆናቸው ነው። ለዚህም ምሳሌ የምናደርገው የእምነታችንን መስራች ኢየሱስ ክርስቶስን ነው።
፪ኛ፦ደመራ ክርስቶስ ሰባዊ ችግርን ለማስወገድ የተጠቀመበት መለኮታዊ ዘዴ ነው።
ኢትዮጵያዊው ነገረ መለኮታችን፤ “ደመረ ሥጋሁ ምስለ መለኮቶ” ብሎ ይጀምራል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማህጸነ ማርያም በተጸነሰባት ቅጽበት መለኮቱን ከሥጋችን ጋራ በመደመር የማዳኑን ተግባር ጀመረ። ከዚያ በኋላ “እኛ አንድ እንደሆን እነርሱም አንድ ይሆኑ ዘንድ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። አንተ በኔ፤ እኔ ባንተ እንዳለሁ ሁሉም አንድ እንዲሆኑ እነርሱንም እንደ ወደደካቸው ዓለም ያውቅ ዘንድ አንድነታቸው ፍጹም ይሁን”(ዮሐ ፲፯፡ ፳_፳፫) እያለ ስለመለኮታዊና ሰባዊ ድመራ ተናገረ። ይህች ከዚህ በላይ የተጠቀሰችው የክርስቶስ ንግግር የገረ መለኮታችን፤ የእምነታችንና የባህላችን መግለጫ ብቻ ሳትሆን፤ ክርስቶስ“ዓለም ያውቅ ዘንድ አንድነታቸው ፍጹም ይሁን” እንዳለው፤ በዓለም ለምንታወቅበት ለኢትዮጵያዊነታችን መሠረት ናት።
ሰው ሁሉ የአዳም ዘር ከመሆኑ ባሻገር፤ የተዋህዶውን እምነትና ትምህርት፤ ወደ ኅብረ ትሥጉታችን ስናመጣው፤ “እስመ ሥጋሁ ለእግዚእነ ውእቱ ሥጋ ዘበአማን። ወ፩ዱ ውእቱ ምስለ ሥጋ ዚአነ። ወእግዝትነ ቅድስት ድንግል ማርያም እኀትነ ይእቲ፤ እስመ ኩልነ እምነ አዳም ንሕነ “(ሃ አ ም ፴፡ ፵፭) ማለትም “ያለ ወንድ ዘር በሥጋ የወለደችው እናቱ ድንግል ማርያም እንደኛ የአዳም ልጅ እኅታችን በመሆኗ የጌታችን ሰውነት በእርግጥ የኛ ሰውነት ነው” ክርስቶስ የለበሰው ሥጋ የሁሉም ነው። በክርስትና ይመንም አይመንም ይቀበለው አይቀበለው የግለ ሰቡ ፈቃድ ቢሆንም፤ የተሰቀለው ለደቂቀ አዳም ነው። ማንንም ሰባዊ ፍጡር በተዋህዶ ነገረ መለኮት ባለማመኑ ልንጠላው ልንጎዳውና ሰውነቱን ወንድምነቱን ልንክደው አንችልም። በሰውነታችን የተደመርን ነን። በኢትዮጵያ ምድር ያሉ ሁሉ ጎሳወች ሁሉም በሁሉ ላይ በሥጋቸውና በደማቸው ተቀላቅለዋል ተደምረዋል። ክርስቶስ ደመራን ለደቂቀ አዳም ችግር መፍቻ እንደተጠቀመበት፤ እኛም መደመራችንን ተገንዝበን የደመራውን በዓል የገጠመን ችግር ለመፍታት ልንጠቀምበት ይገባናል። ይህን የማይቀበል ጎሳ ወይም ግለ ሰብ ኢትዮጵያችንን አያውቃትም። ኢትዮጵያም አታውቀውም። የደመራውን በዓል ሊሳተፍ ይቅርና፤ ቅዱስ ጳውሎስ “ሲቃወምና ሲጻረር የነበረውን የዕዳ ጽህፈት ክርስቶስ ከነ ሕግጋቱ በመደምሰስ በመሰቀል ላይ ቸንክሮ ከመንገድ አስወገደው” እንዳለው፤ በራሱ ሞራል ውድቀትና ከሀዲነት ከደመራው መሰረታዊ ታሪክ ጋራ በመጋጨቱ፤ በደመራው መንፈስ ተቸንክሮ ከኢትዮጵያውያን መካከል መወገድ አለበት።
፫ኛ፦ እሌኒ ደመራን ለችግር መፍቻ ተጠቀመችበት።
እሌኒ በደመራው እሳትና ጢስ፤ መሰንቀሉን ከተከመረበት ትቢያ አመድና ድንጋይ ፈንቅላ በማውጣት ብቻ አልተወሰነችም። በሕይወቷና በምትወደው ትዳሯ ላይ፤ ተንኮለኞች፤ ሸፍጠኞችና ስግብግቦች በስውር የፈጸሙትን ተሰውሮ ይኖር የነበረውን ደባ ፈንቅላ አወጣች። ባልፈጸመችው ኃጢአት ወደ ባህር በመወርወር የሞት ፍርድ ከፈረደባት፤ እሱም ባላወቀው ነገር ከስሮ ከማይወጣው የችግር አዘቅት ላይ ወደቆ ይማቅቅ የነበረውን የምትወደውን ባሏን ከወደቀበት መከራና ስቃይ አወጣችበት። የባሏን ንብረት በሀሰት ወስዶ ባሽከር በሎሌ በገረድ ተዝናንቶና ተንደላቆ ይኖር የበረውን ሸፍጠኛ አዋረደችበት። ለተፈጠረው ችግር መሳሪያ ሆና ያገለገለችውም ሴት በሸፍጥ ባገኘችው ወርቅ ባሽከር በገረድ ተንደላቅ ከምትኖርበት የዓመጽ ኑሮ ተላቃ ንስሀ እንድትገባ አደረገቻት። ይህም ማለት፤ ቅድስት እሌኒ ፍትህንና ርትዕን ከተደበቁበት ፈንቅላ ለማውጣት ደመራውን ተጠቀመችበት። የዚህን ሙሉ ታሪክ በስፋት ለመረዳት ከፈለጉ፤ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “ባህረ ሀሳብ” በሚል ርእስ ከግእዙ ተርጉመው ካሳተሙት መጽሐፍ ከገጽ 57_62 ላይ ይመልከቱ።
፬ኛ፦ አባቶቻችን ከገጠማቸው ችግር ለመላቀቅ ደመራን ተጠቀሙበት
በአጼ ገላውዴዎስ ዘመን ለርዳት ከፖርቱጋል የመጡ አውሮፓውያን ከኢትዮጵያውያን ጋራ ተቀላቅለው መኖር ከጀመሩ በኋላ፤ ኢትዮጵያውያንን በንቀት እየተመለከቱ ከመኖራቸው ባሻገር፤ ወገኖቻቸውን እየጠሩ በመብዛት መስፋፋትና የቅኝ ግዛታቸው ለማድረግ ረዥም እቅድ ዘረጉ። ሊቃውንት አባቶቻችን ፖርቹጋሎችን ላንድና ለመጨረሻ ጊዜ እንዴትና በምን መንገድ ጠራርገው ለማስወገድ አሰቡ። ከሊቃውንቱ መካከል የብሉይና የሀዲስ ኪዳን ትርጓሜና የቅኔ መምህር የነበሩ ሊቅ፤ በመጽሐፈ መሳፍንት ምዕ ፱ ከቁጥር ፳ ላይ “ለትጻዕ እሳት እምቤተ አቤሜሌክ፥ ከመ ትብላእ አብያተ ሴኬም፡ ወትሜሎም:: ወለእመ አኮ እሳት ትጻእ እምቤተ ሴኬም ወትሜሎም ከመ ትብላዕ ቤተ አቤሜሌክ” የሚለውን ምንባብ ከችቦና ከደመራ እሳት ጋራ አገናዝበው ፖርቱጋሎች ከጫኑባቸው መካራ ሊላቀቁበት ወሰኑ። “እኛ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራችን የተደጋገመ ግፍ እየተፈጸመብን ነው:: ይህች ከኢትዮጵያውያን ቤት እየተጫረች የምትወጣ የዘንድሮው የመስቀል በዓል እሳት፥ በሸርና በሸፍጥ በእርዳታ ስም መጥተው የወረሩንን ፖርቹጋሎችን ትብላ፥ ለአገራችን ለነጻነታችን መታገላችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጥቶ ረድኤቱን ከነፈገንም፥ ለዘላለም በፖርቹጋሎች ሥር ተጠቅተን ከመኖርና ለልጆቻችንም የተገዥነትን ውርስ ከማውረስ ይሕች ከየቤታችን የጫርናት እሳት እኛኑ ትብላን” ብለው ቆርጠው ተነሱ:: ፖርቱጋሎች ከጫኑባቸው ውርደት ለመላቀቅ ደመራውን ተጠቀሙበት።
፭ኛ፦ የዲሲ ርእሰ አድባራት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንና፤ በዲሲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች፤ ኢትዮጵያንና ቤተ ክርስቲያናችንን የገጠሟቸውን ችግሮች ለመላቀቅ የሚያስችል አቅጣጫ በዘንድሮው ደመራ በዓል ላይ አንጸባረቁበት።
ሀ፦ በዲሲ ርእሰ አድባራት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የዚህ አመት የደመራው እሳት ከመቃጠሉ በፊት፤ የደብሩ መምህር የሆኑትን ሊቀ ማእምራን አማረ ካሣየ በመምህሮቻችን ጉባዔ ሲታተት የሰሙትን የደመራውን ተልእኮ፤ በችቦው፤ በደመራው፤ በእሳቱ፤ በፍሙ፤ በከሰሉና ባመዱ ምሳሌነት ባጭሩ አንጸባርቀው፤ አሁንም በዘመናችን፤ ወያኔዎች በገጠር በከተማ የሚኖረውን ህዝባችንን ከመንደሩ በማፈናቀል፤ አርሶ ቆፍሮ የሚተዳደርበትን የእርሻ ቦታ እየነጠቀ ለባእድ በመስጠት የሚፈጽሙትን ግፍና ጭካኔ ገልጸዋል። በህዝብ ላይ የሚደረገውን መከራ አትፈጽሙ ብለው በሚቃወሟቸው ወገኖች ላይም የሚነደውን የመከራ እሳት አጉልተው ለማሳየት ሞክረዋል።
የደመራውንና የችቦውን ስብስብ፦ ላንድነታችን፤ እሳቱን፤ ነበልባሉንና ፍሙን ካንድነታችን የሚፈልቀውን ሕዝባዊ ኃይል፤ ወያኔ ባነደደው የመከራ እሳት በመሰቃየት ላይ ያሉትን ዜጎች ደግሞ፡ በእሳት ነጥሮ እንደሚወጣ ወርቅ፤ በዘር፤ በጎሳና በጥቅም ከወያኔዎች ጋራ በመስማማት በህዝብ ላይ መከራ ለማድረስ ከወያኔዎች ጋራ የሚተባበረውን እንደ ደመራው ከሰል፤ አመድና ጢስ በነፋስ በኖ የሚጠፋ መሆኑን በመግለጽ ካድራጎታቸው እንዲመለሱ አስገንዝበዋል።
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰርገው የገቡ ቤተ ክርስቲያናችን በአብነት ጉባዔዋ የምታስተምራቸውን ነገረ መለኮት፤ ቀኖናና ታሪክ ያልተረዱ፤ መጽሐፋችን አዳዲስ ተክሎች የሚላቸው ሰዎች ጳጳስ ቆሞስ የሚል ስም በራሳቸው እየለጠፉ ጥቅምና ክብር ለመሰብሰብ በቤተ ክርስቲያናችን የተሰገሰጉትን፤ ዶክተር አረጋዊ በርሄ “የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር በ1979 አመተ ምህረት አስተሳሰብ ለዋጭ የፕሮፓጋንዳ መርሀ ግብር ለሚመለምላቸው ቀሳውስት ዘረጋ። የማሰልጠኑ ዓላማ ቤተ ክርስቲያኗን ከህዝብ ለይቶ በመምታት ስፋቷን ማጥበብና በትግሬአዊነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ስሜት በትግራይ ተወላጆች ጭንቅላት መክተት ነው። ቤተ ክርስቲያኗ ለረዥም ዘመናት በህዝቡ አዕምሮ ላይ ስትተቀርጸው የኖረችውን ብሄራዊ የኢትዮጵያነትን ስሜት ከትግራይ ህዝብ አዕምሮ ጠራርጎ በጠባቡ ትግሬአዊነት ስሜት በመተካት የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዘት እያጠበቡ ራሷን ቤተ ክርስቲያኒቱን መምታት ነው።” ብለው የለጹት ወያኔዎች የነደፉት እቅድ የወለዳቸው እንደሆኑ በመናገር ህዝቡ እነዚህን ከመሳሰሉ ሰዎች ራሱን እንዲጠብቅ አስጠንቀቀዋል።
ሊቀ ማእምራን፦ሊቃውንት አበው ተንትነው የሚናገሩትን የደመራውንና የችቦውን ይዘት ካስተላለፉ በኋላ፤ “እኛ አንድ እንደሆን እነርሱም አንድ ይሆኑ ዘንድ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ. . . አንተ በኔ እኔ ባንተ እንዳለሁ ሁሉም አንድ እንደሆኑና አንተም እንደወደድካቸው ዓለም ያውቅ ዘንድ አንድነታቸው ፍጹም ይሁን” (ዮሐ ፲፯፡ ፳_፳፫) በማለት ክርስቶስ በተናገረው መንፈስ፤ በደመራ ባንድነት ተያይዘን ምድራዊውን ህይወታችን እንድንፈጽምና፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮታዊና ትስብእታዊ ድመራ ያዘጋጀልንን ሰማያዊት መንግሥት ወርሰን፤ ከቅዱሳን ጋራ ለዘላለም ነግሰን እንኖር ዘንድ፤ የነቃ ህሊናና አስተዋይ ልቡና ያድለን በማለት የደመራውን ስርአት ደመደሙ።
ለ፦ በዲሲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች፤ ኢትዮጵያንና ቤተ ክርስቲያናችንን ከገጠሟቸው ችግሮች ለመላቀቅ የሚያስችል አቅጣጫ፤ በዘንድሮው ደመራ በዓል ላይ ተግባራዊ ክንውን አንጸባረቁበት።
ሊቀ ማእምራን አማረ፤ በመንፈሳዊ፤ በብሄራዊና በታሪካዊ ግንዛቤ ላይ መስርተው ስለ ደመራው ከሰጡት ትምህርት ጋራ በተገናዘበ መንፈስ፤ በዋሸንግተን አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አክትቭስቶች በሚቀጥለው ቀን በወሰዱት ርምጃ፤ የኢትዮጵያዊነትን ሁለንተና የሚጻረረውን መንፈስ ነቃቅለው ጥለዋል።
“ኢትዮጵያውያን እራሳቸው የሰሯቸውንም ሆኑ፤ ከውጭ የተቀበሏቸውን ክስተቶች፤ ከራሳቸው ባህልና ታሪክ ጋራ በማስተሳሰር ለክፉም ለደጉም ይጠቀሙባቸዋል፤ በመልካም ቀን በደስታ ያሳልፉታል። በክፉ ቀን ደግሞ የገጠማቸውን ችግርና እንቅፋት ያስወግዱበታል። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ የራሷን ታሪክ ጠብቃ የሄደች ብቸኛ አስደናቂ አገር ናት” ብለው የውጭ ታዛቢዎች የሚነገሩትን፤ ጥቂት ወገኖቻችን በዲሲ ዋሽንግተን ኢምባሲ ግቢ በሰሩት አሁንም ህያው እንደሆነ አረጋግጠዋል።
አባቶቻችን ሊቃውንት “እየተደጋገሙ የሚከበሩትን በዓላት ስርወ ነገራቸውን ሳንረሳ፤ ቀልባችንንና ትኩረታችንን በግርግሩ በመብሉና በመጠጡ ሳናሰርቅ፤ ህሊናችንንም በሸፍጠኞች ስብከትና ሽር ጉድ ሳናስረግጥ የምናከብራቸው ከሆነ፤ ለክብራችንና ለልዕልናችን ዘብ ከመቆም አንዘናጋም” እንዳሉት፦ቀልባቸውንና ትኩረታቸው በወያኔዎች ግርግር ያላዘናጉ የዲሲ ነዋሪዎች ጥቂት ኢትዮጵያውያን፤ የወያኔን አራዊታዊ ባህርይና፤በአራዊታዊ ባህርይውም ኢትዮጵያውያን በመጨፍጨፍ ላይ እንዳለ ለዓለምና በመሸፋፈን ላይ ላሉት ለፕሬዝዳንት ኦባማ አርጋግጠው አሳዩበት።
የእግዚአብሔር ረድኤትም እነዚህን ንጹሀን ዜጎች የሚከተሉትን ዘዴዎች እንዲጠቀሙ መራቸው።
፩ኛ፦ ወደ ኢምባሲው ግቢ እንዲሄዱ አሳሰባቸው።
፪ኛ፦ “በሰለጠነው አገር እያለህም በሰው ላይ ትተኩሳለህ? እያሉ በኢትዮጵያ ምድር ያለው መንግሥት ከህገ አራዊት አለመላቀቁን እንዲናገሩ አደረጋቸው።
፫ኛ፦ የነፍሰ ገዳዮች ወኪል፤ አቶ ሰሎሞን የሚተኩሰው ጥይት ሳይበትናቸው፤ ይልቁንም በሚተኮሰው ጥይት መሞታቸውን ረስተው፤ “ተኩስ ተኩስ ተኩስ” እያሉ፤ በንጹኋ ባንዲራቸው ራሳቸውን ጋርደው ወደፊት እንዲገሰገሱ አደረጋቸው። ወያኔዎች በተመሳሳይ ጭካኔ እየተኮሱ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ መጨፍጨፋቸውን፤ አቶ ሰሎሞን ለዓለምና ለፕሬዝደንት ኦባማ በገሀድ በተግባር እንዲያረጋግጥ አስደረጋቸው።
፬ኛ፦ ኢትዮጵያን ለማፍረሱና ህዝቡን በጎሳ ከፋፍሎ ለመለያየቱ ምልክት አድርጎ ወያኔ የሰቀላትን ባንዲራ እንዲያወርዷት አደረጋቸው።
፭ኛ፦ ኢትዮጵያውያንን ከሚወክለው ከኢማባሲያችን ቅጽር የጥፋት ምልክት የሆነችውን ባንዲራ ከነቀሉ በኋላ፤ ወያኔን በሚወክለው አምባሳደርና ለተሰበሰቡት ወኪሎች “ባንዳዎች ናችሁ” በማለት በግልጽ እየነገሩ፤ አባቶቻችን ለነጻነታቸው ምልክት በማድረግ ለዘመናት ሲጠቀሙባት የነበረችውን ሰንደቅ አላማ፤ እንዲተክሏት አደረጋቸው።
፮ኛ፦ አምባሳደሩን በደመራው እሳት ተለብልቦ እንደከሰለው እንጨት ከሰል አደረጉት። ሰሎሞን ወይኒን ከአሜሪካ እንደ ደመራው ጢስ በኖ እንዲጠፋ አደረጉበት።
፯ኛ፦ የመላ ኢትዮጵያውያንን ቀልብና ትኩረት በተለምዶ ሽር ጉድ ከሚደረገው አከባበር ለይተው፤ በተግባር ማክበር መቻሉን እንዲያሳዩ አደረጋቸው። በዋሸንግተን ዲሲ ዙሪያ ያሉትን የመገናኛ ኃይሎችን ሁሉ እንዲነጋገሩበት በማድረግ የዘንድሮውን የደመራ በዓል በመሰረታዊው ታሪኩ እንዲያከብሩት አደረጋቸው።
ይህ ሁሉ ቅንብር ካንዲት መንደር ተጠራርተው መጥተው ኢትዮጵያን ሲያመሷት የነበሩትን አቶ መለሰንን እና አቡነ ጳውሎስን ባንድ ሳምንት ሁለቱንም የጠራ አምላክ ካከናወነው ጥበብ እጅግ የተመሳሰለ መለኮታዊ ጥበብ ነው። በነዚህ ንጹሐን ጥቂት ዜጎች የተከናወነውን ረቂቅ ክንውን፤ በክህደት በድንቁርናና በሸፍጥ ከታወረው ከወያኔና ከተከታዮች በቀር፤ የሰው ጥበብ ያልቀመረው፤ የእግዚአብሔር ጥበብ ያጠናቀረው እንደሆነ የሚጠራጠር ማነው?
በኢትዮጵያና በውጭ ተበትነን የምንኖረው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በደመራው በዓል ያደረግነውን ሽር ጉድ። ዘመንን ከዘመን፤ ክስተትን ከክስተት፤ ታሪክን ከታሪክና አዲሱን ትውልድ ካለፈው ከትውልድ ጋር በሚያያይዝ፤ አገናዝበንና ደምረን እንዳባቶችን የሰሩልንን መንገድ እንድንከተል የዲሲ ነዋሪዎች ወገኖቻችን እንዳደረጉት ብንጠቀምበት፤ እነኳን ወያኔን፤ የውጭ ኃይላትን ለመቋቋም የሚያቅተን ነገር አለመኖሩን አሳዩበት፤ በተረፈ “ከህገ አረሚ ወጥታችሁ ከህገ ኦሪት ለመድረስ ጣሩ” የምትለውን አዋጅ የምታንጸባርቀውን፤ ከፊታችን በመምጣት ላይ ያለችውን የጥምቀት በዓል፤ እነዚህ ንጹሀን ዜጎች ያሳዩንን መንገድ በመድገም ችግራችን ለዓለም የምናሳይበትና ለመስወገጃም እንድንጠቀምበት እግዚአብሔር ጥበቡን ይግለጽልን።
ይቆየን::
ለሌሎች ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ጦማሮች የሚከተለዉን ድረ-ገጽ ይመልከቱ::
nigatuasteraye@gmail.com
መስከረም ፳፻፯ ዓ.ም.
Leave a Reply