ባለሥልጣኖቻችን ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን በጣም የናቋቸው ይመስላል፤ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀውን ሁሉ ያውቃሉ፤ የኢትዮጵያን ቴሌቪዥን ያያሉ፤ የኢትዮጵያን ራድዮ ይሰማሉ፤ ባሎቻቸውና አባቶቻቸው የዛሬ ሳምንት የተናገሩትን ረስተው፣ ወይም ክደው፣ ወይም ዋሽተው ተቃራኒውን ሲናገሩ መሸማቀቃቸው አይቀርም፤ እንዲህ ያለው የንግግር መገለባበጥ የእምነት መገለባበጥን፣ የማሰብ ችግርን፣ የመንፈስ ልልነትን ያሳያል፤ ታዲያ ሚስቶችና ልጆች እየተሸማቀቁ አካላቸውም ነፍሳቸውም ሲያልቅ ለባለሥልጣኖቹ አይታወቃቸውም? ወይስ የቤተሰብ አባሎች ጠባይ እየሆነ ሽታዬ ሽታዬ እየተባባሉ ነው?
አንዳንዶች ባለሥልጣኖች ወንበሩ ላይ የወጡት እግዚአብሔርን ሳይይዙ ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ እግዚአብሔርን ይዘው ወንበሩ ላይ ይወጡና እግዚአብሔርን ከተቆናጠጡ በኋላ እግዚአብሔርን ከውስጣቸው የሚያስወጡት ይመስላል፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ብዙ አናውቅምና ለሱ እንተውለት፡፡
ግን እኛም ሰዎቹ ባለሥልጣኖቻችን እውነተኞች ቢሆኑ፣ በትክክል ቢያስቡና የመንፈስ ልዕልና ቢኖራቸው እንኮራባቸው ነበር፤ አርአያም ይሆኑን ነበር፤ ልጆቻቸውም ከልጆቻችን ጋር ተግባብተው ያድጉ ነበር፤ ባለሥልጣኖቻችን ለቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የመንፈስ ልዕልና አርአያ እንዲሆኑልን ኃላፊነት አለባቸው፤ ተደጋግሞ እንዳየነው በየዘመኑ የተሰየሙልን ባለሥልጣኖቻችን የኃላፊነት ግዴታ የሚጎድላቸው ናቸው፤ ለአምላካቸው የኃላፊነት ግዴታ አይታይባቸውም፤ ለቤተሰቦቻቸው የመንፈሳዊ ኃላፊነት ግዴታ አላደረባቸውም፤ ለአገራቸውና ለወገናቸው ደኅንነትና ብልጽግና ኃላፊነት አይሰማቸውም፤ የሥልጣን ወንበሩ የሚፈለገው ለሁለት ዓላማዎች ብቻ ነው፤ ለጉልበትና ለሀብት ብቻ!
በእኔ ዕድሜ ሥልጣንና የኃላፊነት ስሜት ሲጋጩና ነፍስን ሲገነጥሉ “በቃኝ!” ብለው የመንፈስ ልዕልናቸውን መርጠው ሥልጣናቸውን ያስረከቡት ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ኃብተ ወልድ ናቸው፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ ፊት ቀርበው፣ የማይደፈረውን ደፍረው፣ አሻፈረኝ! የማይባለውን አሻፈረኝ! ብለው ሥልጣን የሌለበትን የአገር ኃላፊነት በአጼ ኃይለ ሥላሴ እግር ስር አስቀምጠው ራሳቸውን ነጻ አወጡ! ትልቅ ድፍረት ነው፤ እንኳን በአገር ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትርን የሚያህል ሹመትና በትንሹ በአውራጃ አስተዳደሪ ደረጃም ቢሆን የጃንሆይን ትእዛዝ አልቀበልም ማለት ዋጋ ያስከፍላል፤ (እኔ በትንሹ ከፍያለሁ!)
ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ለአገራቸው ብዙ የደከሙ ሰው ናቸው፤ በታወቀው በፈረንሳዩ ሶርቦን ዩኒቨርሲቲ ተኮትኩተው ያደጉና በኢጣልያ ወረራ ጊዜ በአውሮፓ እየተዘዋወሩ ለኢትዮጵያ ነጻነት የታገሉ ሰው ናቸው፤ ከጦርነቱም በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተባበሩት መንግሥታት የአውሮፓውያን (የነጮች)ኃይል አክሊሉ በልበ-ሙሉነት ከምዕራባውያን ኃይሎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በክርክር ሲተናነቁ ነበር፤ የምዕራባውያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጸሐፌ ትእዛዝን በጥቁርነታቸው ሊንቁ ሲቃጡ በአእምሮና በመንፈስ ልዕልናቸው እያሳፈሩ ልካቸውን አሳይተዋቸዋል፤ ነጮቹ በግዳቸው እንዲያከብሯቸው አደረጉ፤ እኝህ ሰው ናቸው በባህል ተጽእኖና በይሉኝታ ሥልጣን የሌለበትን ኃላፊነት ተቀብለውና ተሸክመው ለብዙ ዓመታት በጨዋ ደንብ የታገሉት፤ በመጨረሻም በቃኝ! አብዮታዊ እርምጃ ወሰዱና ለአጼ ኃይለ ሥላሴ ገበጣ መጫወቻ አልሆንም ሲሉ የኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ አቅጣጫን ያዘ፡፡
የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትር ከመጽሐፍ ቅዱስ ካልተማረ ከጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ሊማር ይችላል፤ በመማርም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአደጋ ሊያድን ይችል ይሆናል፤ አንድ ሰው ታሪክን ለመሥራት ይችላል፤ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ወኔውን ይስጠው!
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ጥቅምት 2009
(ምንጭ: Mesfin Wolde-Mariam Blog)
ፕ/ር መስፍን ስለ ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ከጻፉት ጋር በተያያዘ የዛሬ 4 ዓመት September 21, 2012 አካባቢ “ኃይለማርያም ደሳለኝ – እንደ ዳንኤል፤ እንደ አክሊሉ ወይስ እንደ መለስ?” በሚል ርዕስ ባወጣነው ርዕሰ አንቀጽ ላይ ስለ ጸሐፌ ትእዛዝ የሰጠነው ተጨማሪ መረጃ ስላለ ከፕሮፍ ጽሁፍ ጋር ክዚህ በታች አትመነዋል፡፡ “አንድ ጥፋት ሰው ላይ ከሚደርስ ብዙ ጊዜ ራሴን ብጎዳ እመርጣለሁ … እስካሁን ድረስ ጎድተኸኛል ብሎ የተናገረኝ ሰው የለም” ያለው ኃይለማርያም አሁን ስለራሱ ምን ይል ይሆን?
ኃይለማርያም ደሳለኝ – እንደ ዳንኤል፤ እንደ አክሊሉ ወይስ እንደ መለስ?
(ርዕስ አንቀጽ)
አገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ አስር የሚሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አስተዳድረዋታል፡፡ ከእነዚህ መካከል በተለየ ሁኔታ ከሚወሱት አንዱ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ናቸው፡፡
በጣልያን ወረራ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ በአውሮጳ ያደረጉት ተጋድሎ እጅግ ከፍተኛ ለመሆኑ በተለያዩ ቦታዎች ሲጠቀስ የሚሰማ ነው፡፡ አርበኞቻችን በአገር ውስጥ የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍሉ አክሊሉ ሃብተወልድ በአውሮጳ የከፈሉት መስዋዕትነትና ኢትዮጵያን ለማዳን የሠሩት ሥራ ተጽፎ የማያልቅ ታሪካቸው ነው፡፡ ያላንዳች ማጋነን የዲፕሎማሲውን ሥራ ያለመታከት ከግብ ያደረሱት አክሊሉ ነበሩ፡፡
በተለይ “የአክሊሉ ማስታወሻ” በተባለው የራሳቸው ታሪክ በከፊል የተወሳበት መጽሐፍ ላይ የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆር እና የፈረንሣዩ ጠ/ሚ/ር ላቫል ከኢትዮጵያ ክፍላተሃገራት አብዛኛው የሆነው ሐረር፣ ሲዳሞና ባሌን ጨምሮ ለጣሊያን እንዲሰጥ የተቀረው ጎጃም፣ ጎንደርና ትግራይ ለኢትዮጵያ እንዲሆን በምስጢር ያዘጋጁትን “የሆር-ላቫል” ስምምነት ሰነድ አክሊሉ በለንደን በጋዜጣ ላይ ይፋ እንዲወጣ በማስደረግና በእንግሊዝ ፓርላማ ውስጥ ከፍተኛ ሙግት በማስነሳት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆር እያለቀሰ ይቅርታ የጠየቀበትና ሰነዱም ውድቅ የተደረገበት ውሳኔ ጠ/ሚ/ር አክሊሉ ለአገራችን ከሰሩት ስፍር ቁጥር ከሌለው ውለታ አንዱ ነው፡፡
ከድል በኋላም አክሊሉ በውጭ ጉዳይ ቀጥሎም በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገራቸውን ባገለገሉባቸው ዓመታት ሁሉ ከሚጠቀሰት መካከል የኤርትራን ጉዳይ በተመለከተ በዲፕሎማሲው መድረክ ላይ ጣሊያን በከፈተችው ጦርነት ተባባሪ በመሆን ያስቸግሩ ለነበሩት የላቲን አሜሪካ አገሮች አክሊሉ የሰጡት ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ነበር፡፡ በመንግሥታቱ ማኅበር ፊት እንዲህ ነበር ያሉት፡-
“በዚህ አጋጣሚ ለባልደረቦቼ የላቲን አሜሪካ አገሮች ተወካዮች፣ በተለይም ለአርጀንቲናው ልዑክ እጅግ በጣም ከባድ ፋይዳ ስላለው ጉዳይ የማስተላልፈው መልዕክት አለኝ። ዛሬ አገሬ ከግብጽ እና ከላይቤሪያ ጋር ሆና እናንተ ከጣልያን ጋር በማደም የአፍሪቃን ሕዝቦች ለመጨቆን የምትጫወቱትን ሚና በጥንቃቄ እየተመለከትን ነው። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግን እዚህ ያለነው ሦስት አፍሪቃውያን አገሮች በአስር እጥፍ በዝተን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ተገቢ መቀመጫችንን እንይዛለን። ያን ጊዜ እኛ እንደናንተ ሳይሆን፣ ለዓለም ሰላም ድጋፍ እና ፍትሐዊ ፍርድ ድምጻችንን እንደምናሰማ ጥርጣሬ የለኝም።”
እንዳሉትም በርካታ የአፍሪካ አገራት በያኔው የመንግሥታት ማኅበር ውስጥ አባል በመሆን የኃይሉ ሚዛን ላይ ተጽዕኖ ማድረግ ጀመሩ፡፡
ከዘመነ አክሊሉ ወደእኛ ዘመን በፍጥነት ስንመጣ የምናገኘው ህወሓት/ኢህአዴግንና መለስን ነው፡፡ ባሳለፍናቸው 21ዓመታት መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ ስፋቱም ሆነ ጥልቀቱ ይህ ነው ተብሎ ሊዘረዘር የሚችል አይመስለንም፡፡ እርሳቸው ግን የቆፈሩትን ጉድጓድ ጥልቀቱንም ሆነ ስፋቱ ሳይናገሩ እንዴት እንደሚደፈን ለባልደረቦቻቸውም ሳያሳውቁ አልፈዋል፡፡ ዛሬ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጠቅላይ ሚኒስትር ወንበር ላይ እንዲቀመጡ ተሰይመዋል፡፡ አቀማመጣቸው እንዴት ይሆን?
አቶ ኃይለማርያም “ምዕራፍ” ለተሰኘ መጽሔት “ሕዝብን እና አገርን በመልካም አስተዳደር የማገልገል” የጸጋ ስጦታ እንደተሰጣቸው በተናገሩት ቃለምልልስ ላይ የሚጸጸቱበትን ውሳኔ አስተላልፈው እንደሚያውቁ ለተጠየቁት ምላሽ “አንድ ጥፋት ሰው ላይ ከሚደርስ ብዙ ጊዜ ራሴን ብጎዳ እመርጣለሁ … እስካሁን ድረስ ጎድተኸኛል ብሎ የተናገረኝ ሰው የለም” በማለት ነበር የመለሱት፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስም የባቢሎን ጠ/ሚ/ር እንደነበረው “ዳንኤል መሆን መልካም እንደሆነ” ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ ባደረጓቸው ንግግሮች ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ የመለስን ራዕይ፣ ዓላማ፣ ሃሳብ … የጋራ አመራር … የሥራ መለያቸው እንደሆነ ነግረውናል፡፡
ዳንኤል በባቢሎን በሥልጣን በነበረበት ጊዜ “ስለኃጢአታችንና (በደላችን) የሩሳሌም (እስራኤል) እና ሕዝብህ በዙሪያችን ላሉት ሁሉ መሰደቢያ ሆነዋል … ፊትህን አብራልን” በማለት ነበር በቅኝ ግዛት ሥር ስለወደቀችው አገሩ ነጻነት የማለደው፡፡
አክሊሉ ኢትዮጵያን ባገለገሉባቸው ዓመታት ከተናገሯቸው በርካታ ንግግሮች መካከል ተጠቃሽ የሆነው “የደረሰው ይድረስ ደካማ ሆኜ መታየት አልፈልግም፡፡የሀገሬን ጥቅምና መብት የሚነካ መስሎ ከታየኝ መናገሬን አልተውም” የሚለው አንዱ ነው፡፡ ይህም ከቃል አልፎ በሥራቸው ተተርጉሞ ህያው ሆኖ ይኖራል፡፡
መለስ ላለፉት 21ዓመታት ሲነግሩን የነበሩትን “ስድብ ተኮር” ቃላት መድገም ባያስፈልግም “የአዝማሪ” ያሉትን የኢትዮጵያን ታሪክ እርሳቸውም በህይወታቸው “የሚሊኒየም፣ …” እያሉ ሲያዜሙት መስማት አሁን ማስታወሻችን ነው፡፡
ኃይለማሪያምስ? እንደ አክሊሉ፣ እንደ መለስ ወይስ እንደ ዳንኤል ይሆኑ? የእኛ ምክር መጀመሪያ እንደራሳቸው እንዲሆኑ፤ ቀጥሎም እንደፖለቲከኛ እንደ አክሊሉ እንደ ሃይማኖተኛ ደግሞ እንደ ዳንኤል እንዲሆኑ ነው፡፡ እርሳቸው ግን እንዴት እንደሚሆኑት ዛሬ ጀምረውታል፡፡ ሕዝብ ማስተዋል፤ ታሪክም መመዝገብ ጀምሯል፡፡
ጌታቸው፡ወልደሥላሴ says
ድሮስ፡ከባንዳ፡ልጅና፡ከባንዳየልጅ፡ልጅ፡ምን፡ይጠበቃል?
Kifle says
ኃይለማርያም የፖለቲካ ሰው ናቸው። ለዚህም በመጀመሪያ፣ ሰንደቅ መጽሔት ካቀረበላቸው ጥያቄ መሓል ለአንዱ የሰጡትን መልስ እንመልከት።
ጥያቄ፦ ለምሳሌ አቶ መለስ አማኝ ወይም ክርስቲያን አልነበሩምና እሳቸው እግዚአብሄር ጋይድ ሆኖ [መርቶአቸው] አያውቅም ማለት ይቻላል?
ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም፦ “እሳቸው ክርስቲያን አልነበሩም ማለት አይቻልም። የእምነታቸው ጉዳይ የግል ስለሆነ እሱን ከፈጣሪና ከእሳቸው ጋር ያለውን ግንኙነት ደጅ ብናደርግ ይሻላል፤ በግሌ ግን እንደማምነው እሳቸው ፈሪሐ እግዚአብሄር ነበሩ በዚያ ላይ ቅን መሪ ስለነበሩና የኃይማኖት ነጻነት ካለገደብ በመፍቀዳቸው የብዙ መቶ ሺ ቅዱሳን ፀሎት ደግሞ ስለደገፋቸው በሞገስ ሊመሩ ችለዋል” ብለዋል። የኃይለማርያም ምላሽ ድርብ አሉታዊ እንደሆነ እናስተውል፤ መለስ ክርስቲያን ስለ መነበራቸው እርግጠኛ አይመስሉም። በአንጻሩ፣ መለስ በሕይወት እያሉ በእግዚአብሔር ያምኑ እንደሆነ በእንግሊዝ ጋዜጠኛ ተጠይቀው እንደማያምኑ፣ ለእንዲህ ዐይነቱ ስፍራ እንደሌላቸው ተናግረዋል። http://ethiopianchurch.org/en/editorial2/205-%E1%8B%AD%E1%8B%B5%E1%88%A8%E1%88%B5-%E1%88%88%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB%E1%8B%8D%E1%8B%AB%E1%8A%95.html
Tesfa says
ትላንት ሌላ ዛሬ ሌላ – ያለፉት ባለአባቶችም ሆኑ መሳፍንቶች በዘርና በጎሳ ወግነው አያውቁም። የውጭም ሆነ የውስጥ ጠላት ሲመጣባቸው የተጋፈጡት በጋራ ዘርና ሃይማኖት ሳይለያቸው ነበር። ሻብያ በአስመራ፤ ወያኔ በአዲስ አበባ የሃገር መሪዎች ከሆኑ በህዋላ ግን ሰልፋችን ሁሉ በዘር ዙሪያ ነው። የወያኔው አለቃ አቶ መለስ ዜናዊ የዛሬውን አሻንጉሊት ጠ/ሚ ስፍራቸውን እንዲወስድ ገና አፈር ሳይመለስባቸው መንገዱን ያመቻቹላቸው በመለስ ጭንቅላት አስበው በሳንባው መተንፈሳቸውን ካመነ በህዋላ ነው። አቶ ሃ/ማሪያም ሃገርን የማዳን ከራስ የመነጨ ሃሳብ ማቅረብም መፈጸምም አይችሉም።
የወያኔ ውሾች ከበዋቸዋል። ደ/ጽዮን፤ የመቀሌው አባይ ወልድ (በነገራችን ላይ በጎንደር ግርግር ያስነሳው በአባይ ወልድ ትእዛዝ ከመቀሌ የተላከ አፋኝ ቡድን ነው)፤ ሳሞራ እና ሌሎችም የቀን ጅቦች ሰውን በመግደል፡ በማሰር፤ በመሰወር በሥልጣን ላይ እንደሚኖሩ ያምናሉ። አልቅጥ ዘርፈው፤ ገድለው፤ አጭበርብረው በባህር ማዶና በሃገር ቤት ያካበቱት ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ሃብት አይናቸውን ከሥልጣናቸው ጋር በማበር ደፍኖታል። ማየትም መስማትም አይችሉም። ዛሬ በሃገሪቱ የትምህርት ተቋማት አማራው እንዳይማር (ከሰሞኑ 4 በመቀሌ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነብሩ የጎንደር ተወላጆች ተገለዋል) መንገድን ማጣበብ፤ በየሥፍራው በአስማሯቸው የስለላ መረብ መጥለፍና ለሞት መዳረግ፤ ማስፈራራት፤ አልፎ ተርፎም ስውርና ይፋ የሆነ ደባ በዘመድ አዝማድ ላይ መጫር ከወያኔ የክፋት ጥልቅ ባህር ትንሹ ነው።
ጠ/ሚ ሃ/ማሪያም የወያኔ የሥራ አስፈጻሚ በራሱ ማሰብ የማይፈቀድለት፡ በቁም እሥር ላይ የሚገኝ አሳዛኝ ፍጡር ነው። ስለሆነም ጠ/ሚ ሃይለማሪያም ሃገራችንን ከገባችበት የዘር አዘቅት የማውጣት ሥልጣኑም ሆነ እይታው የለውም። ደግሞስ ዛሬ መድረክ ላይ ስለወንጌል እየለፈለፉ መስቀል ይዘው አይደል ሃገር በእሳት ስትጠበስ ዝም የሚሉት። እምነት ያለቁርጠኝነት ዋጋቢስነት ነው።
tesfai habte says
የኢትዮጵያ መሪዎች እንድ ስጋ የያው ጅብ በስልጣን ከመቆራቆስ፡ በዘር ከፋፍሎ መግዛት፡ (ትግሬ፡ ኦሮሞ፡ ኣማራ—) እየተባለ ለዘመናት የዘለቀ፡ እስከ ጦርነት መድረሱ እና፡ (ጋላም ጭምር) የሚል ህገ-መንግስት እንዳልነበረ ቡሉ፡ በኢትዮጵያ የተፈጠረ ሽግር ሕሳቡ ወደ ኤርትራ መጠጋጋት በዛራፊዎች የተለመደ ነው። ዶላር ለማግኘት ከኣመሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን ሃያላን ሃገሮች ብተላላኪ ግንባር ተሰልፎው የዚህ የአፍሪቃ ቀንድ ህውከት፡ ውግያ፡ ግድያ፡ መዝመት፡ ሰውን መፈናቀሉ፡ ጎሳዎች፡ ዘረኞች ሽግር ብቻ እንጂ አንድም ያመጡት ፋይዳ የለም። መሬትዎ እንቺ ህዝብዋ ኣስፈልገንም የሚለው ሃይለስላሴ፡ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ልናጠፋቸው ተነስተናል ያለ ደርግ መንጉስቱ፡ ደም በጠርሙዝ ሞልቶ በኣዲስ አበባ በተሰለፈው ህዝብና ዓይን ላይ መሪዎች በተሰበሰቡበት፡ ወደ መሬት ሲወረውር የኤርትራውያን ደም፡ የዓይናቸውን ቀለም ያልማረን ማባረር ያለ ወያኔው መለስ፡ ምን ማለት ነው? ሰላም ነበር ማለት ነው? በኤርትራ መሬት ሰው እየተገደለ ያለ አዲስ አበባ ሰላም ሰፍኖ፡ የኤርትራውያን ደም ሲከሰከስ የት ተኝቶ ነበር። ተስፋ ኣንተ በሰላም ተኝተህ ትሆን ነበር፡ ይህ ደግሞ ከአመሪካ ላኪዎች የተማርከው የአሸባሪ ድርጊት ነው። የኤርትራ ህዝብ ግን በተጋደሎ ነበር። ዛሬ ተነስተህ የአባቶች ቃልን በማስታወስ እየጠቀስክ ሻብያ (ህዝብ) ማለት መግለጽህ የሚሰማ ሰሚ የለም። አመሪካም ቢሆን የራሱን ጉዳይ (የኣፍጋኒስታን፡ ሶማል፡ ዒራቅ፡ ሊብያ፡ ሶርያ፡ ኢትዮጵያ፡ ዩክሬን—–ሽግር በሽግር ተከቧዋል) ሽግር በዝቶት በኢትዮጵያ ሰው ሲጨፈጨፍ ሲሞት እያየ እንዳላየ እየተወላገደ ላይ ነው ያለው። አንድ ነገር አለ ”የኤርትራ ህዝብ ወደ ጫካ እየሄደ እኛ ስልጣኑን እየተረክብን ነው።” ዘረኛ እና ጉጠኛ እናገር እንዳለነበረ የመሳፍንት እና የዘር ቁንጨች አሁን ምን ሊነግሩ ነው? ዛሬ ኤርትራ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሌለች ሃገር ናት። በስራ፡ በእድገት እና በሰላም ወደ የምትፈልገው አቅጣጫ እየተጋዘች ናት። እኔ ጦርነት እስከ መቃብር የሚል ሰው ካለ ግን ”ዛሬ እንደ ድሮ ኣይደለም።” እኔ ውግያ ናፋቂ ነኝ የሚል ሰው ከተገኘ የሚመጣው ሽግሩ ራሱ ነው የሚሸከመው። ክብደቱ እንደገና ኣለመኖር ሊሆን ይችላል!–ሙሴ በተሰጠው የፈጣሪ በትረ ስልጣን፡ በኤርትራ ቀይ ባሕር ላይ ለፈርኦኖች እንዳጠፋውና፡ ፎርኦኖች እንደገና በስልጣን ኣልኖሩም፡፡ ዛሬም በሰይጣናው (666) የናንተ እና ISIS ላኪ በኣመሪካ በትረ ስልጣኑ ኣለመኖሩ መረዳት ኣለበት!