በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ አካባቢ በቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ስራ ተቋራጭነት በMH ኢንጅነሪንግ አማካሪነት እየተገነባ የሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተገነባ ይገኛል።
የስታዲየሙን የጣራ እና የማጠቃለያ ግንባታ የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢፊድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር እንዳሉት በሀገራችን የነበረው ብቸኛው ስታዲየም የአዲስ አበባ ስታዲየም እንደነበር ጠቁመው በአሁኑ ሰዓት በሁሉም የሀገራችን ክልሎች ከ12 በላይ ስታዲየሞች በመገንባት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።
እነዚህ ስታዲየሞች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ለስፖርት ሴክተር በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ የሚገኘው የአደይ አበባ ስታዲም ግንባታም በተያዘለት ጊዜ እና በፍጥነት እንዲሁም በተቀመጠው የግንባታ ጥራት መሠረት እንዲጠናቀቅ መንግስት ከፍተኛ ፍላጎት አለው ሲሉ ገልፀዋል።
ለዚህም ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ማኒጅንግ ዳይሬክተር ሚስተር ሚንግ ቾ በበኩላቸው ኩባንያቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመስራት ከፍተኛ ልምድ ያለው መሆኑን ጠቅሰው የዓለም አቀፍ ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ በመቋቋም ስታዲየሙን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የግንባታ ተቆጣጣሪ አማካሪ ድርጅት ባለቤት ዶ/ር ኢንጅነር መሰለ ህይሌ ስታዲሙ በአሁኑ ስዓት አለም የደረሰበትን ቴክኖሎጅ ያሟላ መሆኑን እና የኦሎምፒክ እና የአለም ዋንጫን ማስተናገድ በሚችል መልኩ ሆኖ በመገንባት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ግንባታውን በማስመልከት በሰጡት አስተያየት ሀገራችን በአሁኑ ስዓት የካፍ እና የፊፋን መስፈርት ያሟላ ኢንተናሽናል ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚያስችን ስታዲምየም እንደሌለ ጠቁመው፤ የአደይ አበባ ስታዲም የአለም ዋንጫ ፍፃሜን ማስተናገድ የሚያስችን ስታዲየም እየተገነባ መሆኑ ትልቅ ደስታን ፈጥሮልኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ፕሪዚዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ በሌሎች ሀገራት ያየነው ስታዲየም በሀገራችን እየተገነባ መሆኑ የሚያስደስት እና ለተሻለ ውጤት የሚያነሳሳ ነው ብላለች።
ብሔራዊ ስታዲየሙ ከ62 ሺ በላይ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን በሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ የመጫወቻ ሜዳውን ሳር ማልበስ፣ የመሮጫ ትራክ ማንጠፍ፣ የስታዲየሙን ጣሪያ ማልበስና ወንበር መግጠም፣ ሰው ሰራሽ ሀይቅ፣ የሄሊፕተር ማረፊያ፣ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራ፣ ሳውንድ ሲስተም፣ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች፣ የመለማመጃ ሜዳዎች እና ሌሎች የማጠቃለያ ስራዎች የሚያካትት ይሆናል።
የ2ኛው ምዕራፍ ግንባታ ለማካሄድ እና አጠቃላይ ስራውን ለመስራት 900 ቀናት ይፈጃል ተብሎ ይታሰባል።
ግንባታውን ለማከናወን ከ5.57 ቢሊዮን ብር በላይ ይፈጃል ተብሎ ይታሰባል።
ለመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ 2.47 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል።
በመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ከተካተቱት ውስጥ ከ30 በላይ የሚዲያ ክፍሎች፣ ጋዜጣዊ መግለጫ አዳራሾች፣ የክብር እንግዶች ማረፊያዎች፣ አሳንሰሮ፣ የተለያዩ ደረጃቸውን የጠበቁ ካፌዎች እና ሬስቶራንቶች፣ ከ1000 በላይ መፀደጃ ክፍሎች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ተጠናቀዋል።
ስታዲየሙን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ መንግስት ከ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይሆናል።
አጠቃላይ ፕሮጀክቱም 48.8 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ስታዲየሙ ብቻውን 95,000 ካሬ ሜትር ይሸፍናል። (ምንጭ፤ የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply