አቶ ዠ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ከተጫነባቸው በኋላ በUN ኢትዮጵያን ወክሎ የመቀመጥ ስልጣናቸው ቀረና ወደ ሌላ ሥልጣን ተሻገሩ። እድገት ወይም ውርደት (promotion ወይም demotion) ሳንል፣ ወደ ሌላ ሥልጣን ተሻገሩ እንላለን። አቶ ዠ የሃገሪቱ የዋና ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ሆነው ተሾሙ። እንግዲህ “ፕሬዚደንት” የሚለው ቃል እስካለ ድረስ፣ ሹመቱ፣ ማዕረጉ ትልቅ ነው ተብሎ እንዲታሰብ የአቶ ዠ መልካም ፈቃድ ነው እንላለን። የዋና ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ሆነው የተሾሙበት ጊዜ ደግሞ እንዳጋጣሚ ሆኑ የኦሎምፒክ ውድድር የተቃረበበት ጊዜ ነበር። ዠ አዲሱ ቢሮአቸው ሆነው አንድ ሃሳብ ብልጭ አለላቸው። ሃገራቸውን በኦሎምፒክ መወከል። የሃገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ በኦሎምፒክ መክፈቻ ላይ ተገኝቶ ማውለብለብ…። እንዴት ያለ ድንቅ ሃሳብ ሲሉ አሰቡ አቶ ዠ።
እንግዲህ መሰደብ፣ መዋረድ፣ መሰደድ፣ መደብደብ፣ መራብ… ወዘተርፈ… ባጨሩ ያለም ሁሉ መከራ ተሰብስበው የሃገሪቱ ህዝብ ላይ የወረዱበት ዘመን መሆኑ አይረሳም። የዚህ ሁሉ ምክንያት ደግሞ ያው “ዠ”ዎች ናቸው ተብሎ በሰፊው ይታመናል። ሙሰኝነት፣ ቅጥ ያጣ ስግብግብነት፣ ዘረኝነት፣ በሥልጣን ያለአግባብ መጠቀም… ወዘተርፈ (ላበ-ተርፈ ሊባል አይችልም። ዛሬ “ዠ”ዎች ወዛም እንጂ ላባም አይደሉምና) ያመጡት ጣጣ ነው።
ሰሞኑን የሃገሬው ህዝብ ያፈረበትና የተሰደበበት ሁኔታም በዚሁ ምክንያት ነው፣ የስግብግብነትና በሥልጣን ያለአግባብ መጠቀም ውጤት ናቸው። አባት ልጁን ከሌሎች፣ ችሎታ ካላቸው የማስቀደም – ዠ “ጉ” ን ከሌሎች፣ ችሎታው ካላቸው የማስቀደም ውጤት ናቸው። “ዋናተኛው” ጉን ማስቀደማቸው። “ዋናተኛው” ጉ ሃገሩን ወክሎ “ዋኝቶ” ህዝቡንና ሃገሩን አሳፍሯል። የሃገሬው አትሌቶች ህዝባቸውን በማኩራትና ሃገራቸውን በበጎ በማስጠራት ነበር የሚታወቁት። ጉ፣ የአቶ ዠ ልጅ ደግሞ በበኩሉ በአለም ታይቶ የማይታወቅ ቀርፋፋነትን በማሳየት ሃገሪቷን ዳግም አስጠራ። ዳግም አዋረዳት! ጋዜጦች ጻፉ፣ “ሃገሪቷ እኮ ባህር የላትም፣ መሬት ብቻ ነች።” ሲሉ። “ጉ የሚዋኝበት፣ የሚለማመድበት የለም እኮ” እንደማለት ከጀላቸው። ሰው ዋና የሚዋኘው ባህር ውስጥ ብቻ ነው? ሃይቆችና ወንዞች የሉም እንዴ?
“ዋናተኛው” ጉ እጅግ ወደኋላ ከመቅረቱ የተነሳ ከቴሌቪዢን ካሜራ እይታ ውጪ ነበር። ሌሎቹ ዋኝተው ጨርሰው ኮፍያቸውንና መነጽራቸውን አውልቀው ሰውነታቸውን ለማደራረቅና ልብሳቸውን ለመቀየር ሲዘጋጁ “ጉማሬው” ዋናተኛ ጉ ውሃ ውስጥ ይጎማለላል። አንዳንዶች ”ምናልባት ነዳጅ እየፈለገ ይሆናል” ሲሉ አላገጡ። አንዳንዶች ደግሞ “አሳነባሪው” ጉ ብለው አንሾካሾኩ (tweet አደረጉ)። “አሳ ነባሪ እኮ በጣም ይዋኛል። ውቅያኖስ ያቋርጣል” ሲሉ ሌሎች ተከራከሩ። በመጨረሻ “ጉማሬው” በሚለው ቅጽል ተስማሙ።
“ጉማሬው” ዋናተኛ የሃገሪቱ ምርጥ ዋናተኛ አይደለም ሲል አንድ አንድ ታዋቂ ጋዜጣ ደግሞ እንዲህ ሲል ዘገበ፣ “ጭምጭምታ ከሁነኛ ምንጮች እንደሰማነው ጉ የሃገሩ ምርጥ ዋናተኛ አይደለም። በተለየ ችሮታ ነው እንዲወዳደር የተደረገው፣ አባቱ አቶ ዠ የሃገሪቱ የዋና ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ናቸው።” ይለናል። አቶ ዠ ከልጃቸው ከ ጉ ጎን ሆነው የሃገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው የታዩበትን ፎቶ ጋዜጣው ጎልጉሎ አውጥቶ ለጥፎታል።
ከውድድሩ በኋላ“ጉማሬው” ዋናተኛ ቃለ መጠይቅ ተደርጎለት ሲመልስ፣ “በኦሎምፕክ ስወዳደር የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው። ባገኘሁት ውጤት በጣም ተደስቻለሁ። በኦሎምፒክ መሳተፍ በጣም ትልቅ ክብር ነው። ስለዚህም ደስተኛ ነኝ። እኔ ሃገር ሁሉም ይሮጣል፣ ይሮጣል…እኔ ግን እንደነሱ መሮጥ አልፈለግኩም፣ በዋና ነው ሃገሬን መወከል የፈለግኩት” አለ። ጋዜጠኛው፣ “ምናልባት ብትሮጥ ኖሮ ቦርጭህ ስለሚረግፍ፣ በዋና ከዚህ የተሻለ ውጤት ልታገኝ ትችል እንደነበር ትገምታለህ” ሲል አከታትሎ ጠየቀው። ጉ አልመለሰም። አንገቱን አቀርቅሮ የዋና መነጽሩን ማሻሸት ያዘ።
የሃገሬው ህዝብ፣ “ይሄ ነገር እንዴት ነው?” ሲል ማሰላሰል ያዘ።
“የመጀመሪያዬ” የሚለው ቃል የሃገሪቱን ህዝብ አበሳጨ። “የመጀመሪያዬ”? ”ይሄ ሰው፣ ጉ ዠ ሃገራችንን ደጋግሞ ሊያሰድብ ይፈልጋል እንዴ?” ሲል የሃገሬው ህዝብ በቁጨት ጸጉሩን ነጨ። ህዝቡ “የሃገሩ ምርጥ ዋናተኛ ሳይሆን ይህ ዕድል ለሱ የተሰጠው በምን ምክንያት ነው? ሌሎች፣ ከሱ የተሻሉ ስንት አመት ሙሉ ለዚህ ዕድል፣ ለዚች ቀን፣ ለኦሎምፒክ ሲሉ ሲዘጋጁ የከረሙ እያሉ እሱ በምን ምክንያት፣ ያለችሎታው ለኦሎምፒክ በቃ? እስከመቼ ነው እንዲህ በቅጥ ያጣ ስግብግብነት፣ በዘረኝነት፣ በሥልጣን ያለአግባብ በመጠቀም በሚመጣ ውርደት ተሸማቀን የምንኖረው?” ሲል የሃገሬው ህዝብ ተቆጣ።
“ከሱ የላቀ ችሎታ ያላቸው እያሉ እሱ እንዴት ይህንን፣ ሃገራችንና እኛን እንዲወክል ተደረገ? በምንሥ ምክንያት ነው? የዚህ ሁሉ ፈላጭ ቆራጭ፣ የዋና ፌዴሬሺኑ ፕሬዚደንት፣ አቶ ዠ ተጠያቂ ይሆናሉንስ?” ሲል ህዝቡ እንደዝናብ አጉረመረመ፣ ከዚያም እንደነጎድጓድ አስጎመጎመ፣ አስጎምጉሞም አልቀረ። እንደ በልግ ዝናብ ድንገት መውረድ ጀመረ፣ እንደ ሃምሌ ወንዝ ጎዳናውን ሞላው፣ በቁጣ ሞገድ ጎዳናውን እንደ ማዕበል አናወጠ።
“መዋራድ በቃን! መሰደብ በቃን!”
“ክብራችንን ያዋረደው ዠ ተጠያቂ ይሁን!”
“ቅጥ ያጣ ስግብግብነት፣ ዘረኝነት፣ በሥልጣን ያለአግባብ መጠቀም አሁኑኑ ይቁም !”
አቶ ዠ ደግሞ ቢሮአቸው ሆነው በመስኮት ማዕበሉን ይመለከቱ ጀመር። የማዕበሉ ሞገድ እቢሮአቸው ገብቶ ጠራርጎ እንዳይወስዳቸው ሰጉ።
ከህዝቡ፣
“ሥራና ሃላፊነት በችሎታ እንጂ በችሮታ መሆኑ ዛሬውኑ ይቁም!” የሚሉ ቃላት እንደነጎድጓድ ያስጎመጉሙ፣ እንደ መብረቅ ያብለጨልጩ ጀመር።
በዚያ ብልጭታ ህዝቡ ተስፋ ማየት ጀመረ። የእኩልነት ተሰፋ፣ የማደግ ተስፋ፣ የመኖር ተስፋ፣ በችሎታ እንጂ በችሮታ ያለመኖርን ተስፋ…
Leave a Reply