“የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች በድረ-መለስ ኢትዮጵያ፣ ርዕዩተ ዓለምና የትግል ግብና ዕቅድ ሁኔታዎች” በሚል ርዕስ አቶ ጋሻው ዓለሙ ጥሩ የመወያያ ሃሳብ አቅርበውልናል። ማለፊያና ብዙ የምስማማባቸውን ነጥቦች የያዘ በመሆኑ፤ ላመሰግንና ድጋፌን መስጠት እፈልጋለሁ። መቼም ብዕሬን ያነሣሁ ተስማምቻለሁ ለማለት ብቻ አይደለም። የተስማማሁባቸውን መደረቱም አንባቢን ማድከም ነው። የማቀርበው ለየት ያለ አቀራረብ ሊኖረው ይገባ ነበር ያልኳቸውን ላመላክት ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ በኔ በኩል ድክመት ሳይሆን ልዩነት ነው ያለው። በርግጥ በተለያዬ መልክና ቦታ ይኼ ጉዳይ በጽሑፉ ውስጥ ተጠቅሷል። ነገር ግን ማዕከላዊ ቦታ መያዝ የሚገባው ጉዳይ ተለጣፊ በመሆን ቀርቧል ባይ ነኝ።
እንዲህ ነው።
የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎችን አንድ ተግባር እንዲፈፅሙ እንፈልጋለን። ይኼም ተግባር የዘረኛውን አምባገነን የወያኔ ቡድን አስተዳደር አውርደው በቦታው ለሕዝብ ተጠሪ የሆነ መንግሥት እንዲያቋቁሙ ነው። ይህ ተግባር እንግዲህ፤ ተግባሩ ምን እንደሆነ፤ ለምን መፈፀም እንዳለበትና እንዴት መፈፀም እንዳለበት የተስማሙ አካላት እንዳሉና እንደተነሱ መቀበልን ግድ ይላል። ከዚህ በኋላ ሳይፈፅሙት ሲቀሩ፤ ድክመት አለ ብለን መናገር እንችላለን። አለበለዚያ ሌላ ጉዳይ አለ ማለት ነው። ለኔ ሌላው ጉዳይ ልዩነት ነው።
ልዩነት፤ በተግባሩ ላይ ልዩነት ካለ፤ ያልተፈፀመው በልዩነቱ ምክንያት እንጂ፤ በድክመት አይደለም።
ልዩነት – ሀ፤ ወያኔ፤ ለዘመናት በሀገራችን በገዥዎችና በሕዝቡ መካከል የነበረውን መሠረታዊ የፖለቲካ ቅራኔ አሽቀንጥሮ ጥሎ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ሕዝቡን በትውልድ ከፋፍሎ፣ አንዱን ጠላት አድርጎ በማስቀመጥ፤ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሂደት መሥርቷል። ከዚህም ተነስቶ አስተዳደሩን በክፍፍሉ መሠረት ጠንስሶ፤ አንዱን ተጠቃሚ ሌላውን የበይ ተመልካች አድርጓል። ይህ ደግሞ የሚከተሉንን ትውልዶች ለማያባራ አይቀሬ የርስ በርስ ትልቅልቅ አመቻችቷቸዋል።
ይኼን ሀቅ ለመቀልበስና ቀጣይ ትውልዶችን ከዚህ አይቀሬ መተላለቅ ለማዳን፤ ወያኔ ከነሥርዓቱ መወገድ አለበት። የሚያስወግደው ኃይል፤ ይኼን መሠረታዊ መነሻ በትግሉ ያዋኻደ መሆን ይገባዋል። ስንቱ ነው ከተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች መካከል ይኼን የተቀበለ? ስንቱስ ነው የማይቀበል? የሚቀበሉና የማይቀበሉ ካሉ፤ ታዲያ እንዴት እኒህ ተቃራኒዎች ባንድነት ሊቆሙ ይችላሉ?
ልዩነት – ለ፤ ወያኔ ተወግዶ የሚተካው የሕዝብ ተጠሪ መንግሥት፤ ወያኔን ከነሥርዓቱና ከነመመሪያው የሚያስወግድና የሕዝቡን ፈቃድ በማንኛውም ተግባር ጠያቂ መሆን አለበት። ይኼን የሚያደርግ ክፍል፤ በድርጅታዊ መርኀ ግብሩ ላሠፈረው አጀንዳ ሳይሆን፤ ሕዝቡ ለሚጠይቃቸው ጉዳዮች ተገዢ መሆን አለበት። ባሁኑ ሰዓት፤ ያሉት የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች በየአጀንዳዎቻቸው ተጠቅልለው በመሠረታዊ ሀገር አቀፍ ጉዳዮች ላይ ስምምነት መድረስ ያቃታቸው ናቸው። ታዲያ እንዴት እነኚህ ክፍሎች የሕዝብ ተጠሪ መንግሥት ሊያቋቁሙ ይችላሉ?
መወንጀል ብቻና እጅን መተጣጠቡ ከታጋይ ወገን ነኝ ከሚል አይጠበቅም። መንገድ ማሳየት ግዴታ አለብኝ። እስኪ እነኝህን የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች በሚከተሉት አምስት ጉዳዮች ላይ እያንዳንዳቸው መልስ ይስጡባቸው። እኒህ አምስት እሴቶች፤ ከግለሰብና ከድርጅት በላይ ሀገራዊ ናቸው። መልሳቸው አብረው መሥራት ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ይነግረናል። ልዩነት ከሌላቸው፤ ስህተቴን ተቀብዬ ልክ ልገባ ቃል እገባለሁ።
፩ኛ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብን አንድነት በተመለከተ፤ አንድ ሕዝብ ነን ወይንስ አይደለንም?
፪ኛ፤ ሀገራችንን በተመለከተ፤ ኢትዮጵያ፤ የቆዳ ስፋቷና ክልሏ ተጠብቆላት፤ አንድ ሀገር ናት ወይንስ አይደለችም?
፫ኛ፤ የዴሞክራሲያዊ መብትን በተመለከተ፤ እያንዳንዷ ኢትዮጵያዊት፤ የግለሰብ መብቷ ተከብሮላት፣ በየትኛውም የሀገሪቱ ክልል ሠርታ የመጠቀም፣ መኖሪያ የማበጀት፣ ሀብት የማፍራት፣ በኢትዮጵያዊነቷ (ከሃይማኖትና የዘር ትውልድ ባልተዛመደና ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ በማያገልል መንገድ) ከመሰል የአስተሳሰብ አንድነት ካላቸው ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች ጋር የፖለቲካ ተሳትፎዋን ማድረግ የምትችልበት እንድትሆን ነው ወይ ትግሉ?
፬ኛ፤ የሕግ የበላይነትን በተመለከተ፤ ከግለሰቦችና ድርጅቶች ውጪ፤ በሕገ ደንብና አሠራር ለመገዛትና ለመተማመን ነው ወይ የምንታገለው?
፭ኛ፤ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በተመለከተ፤ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ጠላት ዘረኛው አምባገነን የወያኔ አስተዳደር ነው። ይህ መንግሥት ሊታረም የማይፈልግና የማይችል ነው። ይህን መንግሥት መወገድ አለበት ወይስ የለበትም?
በሌላ በኩል፤ የተቃዋሚ ኃይሎች ልሂቃን ያቀረቡት፤ “አሁን ያለውን ሥርዓት ለመታገል፤ የአሁኑ ትውልድ ሀገራዊ ፍቅርም ሆነ ወኔ ያንሰዋል።” ማለታቸው በጣም አሳዝኖኛል። የተለመደ አባባል አለ። “በኛ ጊዜ ሁሉ ወርቅ ነበር። ያሁኖች ልጆችማ አይረቡም።” የሚለው። ይኼ ከትውልድ ትውልድ እንደቅርስ የሚተላለፍ ነበር፤ ነውም። እኒህ ልሂቃን የመከራከሪያ ሃሳባቸው መሠረተ ቢስና ቁንፅል፤ ባጠቃላይም ደካማ አስተሳሰብ ነው።
በመጀመሪያ ነገር፤ ትውልድ ሲባል የወቅቱን ጠቅላላ የሀገሪቱ ተወላጆች ያጠቃልላል። እናም የትናንቱ ትውልድ ሲሉ፤ መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ መላኩ ተፈራ፣ አሊ ሙሳ፣ ግርማ ከበደ፣ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ንግሥት አዳነ፣ ኃይሌ ፊዳ፣ መለስ ዜናዊና አረጋዊ በርሄን ባንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጥላሁን ግዛው፣ ሻምበል ሞገስ ወልደሚካኤል፣ ማርታ መብራቱ፣ ባቢሌ፣ ይካተቱበታል። እናም ገዳይም ተገዳይም፣ ተራማጅም አድሃሪም፤ ሁሉንም ያካተተ ነበር። እኔም የዚሁ ተጠቃሽ ትውልድ አባል ነኝ። መቼም ዘመኑን የመከለል እንጂ፤ መርጠን ይኼ ነው የዚያ ትውልድ የሚባለው ይኼኛውን አንፈልገውም የሚባልበት ትውልድ አመካከል አይፈቀድልንም። ታዲያ በምን መንገድ ነው የትናንቱ ትውልድ ከዛሬውና ከነገው ትውልድ የሚለየው?
ማንም ትውልድ የወቅቱን የኅብረተሰብ ሀቆች ተከትሎ፤ ወግኖ የወቅቱን መፍትሔ ከወንዝ ወዲያና ወዲህ በመሆን ይጋፈጣል። ለትውልዱ መፈራጃ የሚሆኑት፤ የወቅታቸው የኅብረተሰብ ክንውኖች እንጂ፤ በዘመናቸው ያልተከሰተ ኩነቶች አይደሉም። ትናንት ከወያኔ ጋር ተጋፍጣ ሕይወቷን የሰጠችው ሽብሬ ደሳለኝ ቁጥሯ ከነበላይ ዘለቀ ነው። ለምን ቢባል፤ በነበረችበት የታሪክ ወቅት፤ የኅብረተሰቡ ችግር የሆነውን ተጋፍጣ ሕይወቷን ሰጥታለችና። ታዲያ የሽብሬ ደሳለኝን ትውልድ ነው ወኔ የለውም የምንለው? በጣሊያን ጊዜ የታገሉት እነበላይ ዘለቀ፤ ታሪክ በወቅታቸው ያጋፈጣቸውን ግዴታ ፈፅመዋል። በዘመናቸው ባንዳዎች እንደነበሩ ሁሉ፤ ዛሬም ጫማ ላሾች አሉ። ሀቁ ግን፤ ወጣቱ ከማናቸውም ባላነሰ መልኩ እየታገለ፤ መሪ በማጣቱ ነው፤ ትግሉ በምንወደው ፍጥነት ወደፊት መሄድ ያልቻለው። ትግሉ እየተካሄደ ነው። የዛሬው ትውልድ ታሪካዊና ትውልዳዊ ተልዕኮውን እየተወጣ ነው። የጎደለው ተመክሮ ያላቸው አዛውንቱ መምራት ስላልቻልን ነው። ተጠያቂ ከተፈለገ፤ አሁንም ለማስመር ያህል፤ ተጠያቂው የአሁኑ ትውልድ ሳይሆን፤ አንድም ባለማውረስ፤ ሌላም የራስን ድርሻ ባለመወጣት አዛውንቶቹ ነን።
አንድ ሌላ ያልተቀበልኩት ነጥብ አለ። “መሠረታዊ የትግል ስልት ሊመራ የሚገባው በሰላማዊና ህጋዊ ማዕቀፍ ሊሆን ይገባዋል።” ይላል ጽሑፉ። የትኛውና የማን ህግ ተጠቅሶ ነው? በዝርዝርም የትግሉ ትጥቅን ማካተት አፍራሽነት ሠፍሯል። ትግል እኮ በጠላትነት ፈርጀውት በሚታገሉት ኃይልና ሊያቸንፉ በሚፈጉት ክፍሎች ጥንካሬ የሚተረጎም እንጂ በቀኖና ቋሚ የሆነ ቅፅ የሚከናወን አይደለም። እያንዳንዱ ትግል የራሱ የሆኑና ሁሉን አቀፍ የሆኑ ባህርይ አሉት። ሁሉን አቀፍ ባህሪዎቹ አጠቃላይ አቅጣጫውን ሲያመለክቱ፤ የራሱ የሆኑት ባህሪዎቹ ደግሞ፤ የራሱን የመፍትሔ መንገድ ይወስናሉ። ጠመንጃ ያነሳ ሁሉ አይወገዝም። ለወረራ፣ ለቅኝ ገዥዎች፣ ለፍፁም አምባገነኖች የሚደረጉ ትግሎች፤ የአመጻቸው መንገድ ግዴታ ትጥቅን ይላል። እንደኛ ባለው ሀገር የሚካሄዱ ትግሎች ችግራቸው፤ ትጥቅ ማንሳታቸው ሳይሆን፤ ትጥቁን ያነሳው ክፍል ምን ያህል ሕዝቡን ያቀፈና ብዙኀኑን ያካተተ መሆኑ ላይ ነው። አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ ማንም አንድ ድርጅት ትጥቅ ቢያነሳ፤ ጉልቻ መቀያየር መሆኑን እጋራለሁ። ነገር ግን፤ ብዙኀኑ ሀገራዊ የሆኑት ክፍሎች ተሰባስበው የሚመሩትን የትጥቅ ትግል፤ የማልኮንነው ነው።
ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ፤ “ስለዚህ የተቃዋሚዎች ውስጣዊ ድክመቶችና የገዥው ቡድን ሁለንተናዊ የበላይነት ጋር ተዳምሮ ተቃዋሚዎች በመርህ ላይ የተመሠረተ ያጋራ ትብብር መፍጠር እንዲችሉ አግዷቸዋል።” የሚለው ሠፍሯል። ለኔ ያገዳቸው ጉዳይ፤ ያላቸው አቋም የተለያየ መሆኑ ብቻ ነው። ወያኔን ለማውረድ የሚፈልጉት ለተለያየ ግብ ስለሆነ፤ በምንም መንገድ አንድ ላይ ሊሰባሰቡ አይችሉም። ባንድ ላይ ካልተሰባሰቡና ላንድ ዓላማ፤ ባንድ ካልቆሙ፤ የውጩ ኃይል ሳይሆን፤ የውስጣቸው ጉዳይ ብቻ ነው ተጠያቂ እላለሁ።
(ይህ ጽሁፍ አቶ ጋሻው ዓለሙ፡ “የተቃዋሚፖለቲካኃይሎችበድረ-መለስኢትዮጵያ፣ርዕዩተ ዓለምና የትግል ግብና ዕቅድ ሁኔታዎች” በሚል ለጻፉት መልስ ነው)
ታህሣሥ ፳፰ ቀን ፳፻፭ ዓመተ ምህረት
ሙስጠፋ says
እጥር ምጥን ያለ እና ወቅታዊዩን የአገራችን የተቃዋሚ ፓርቲዎች የትግል እንቅስቃሴ ድክመቶችን ከመፍትሄ ሃሳብ አቅጣጫ ምልከታ ጋር ያቀረበ በመሆኑ እጅግ ጠቃሚና ልንተገብረው የሚገባን ሃሳብ ነው እላላሁ። እንድህ አይነት የጋራ ርዕይ ይዘን በጋራ እስካልተንቀሳቀስን ድረስ ትርጉም ያለው የትግል ውጤት ለማምጣት አዳጋች እንደሚሆን ይሰማኛል።
በለው ! says
“የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች በድረ-መለስ ኢትዮጵያ፣ ርዕዩተ ዓለምና የትግል ግብና ዕቅድ ሁኔታዎች”
***ያለው ሥርዓት ከነበረው ፈላጭ ቆራጭ የወታደራዊ ሥርዓት የተሻለ ያመጣው ነገር የለም !ይበልጡን በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በክልል፣ በመከፋፈል ሕዝብ እርስ በዕርሱ ሲባላ ወዳጅ ዘመድ ታማኝ ጥቂት ጥቅመኞች እና ሀብታም ኢንቨስተሮች ሆነው ሥርዓቱ እንዲቀጥል ድሃውን ሕዝብ በአዕምሮውም በነፃነቱም በመብቱም በመሬቱ እንዳይጠቀም የተለየ የፖለቲካ አማራጭ እንዳይኖረው፡ የአደጉት ሀገሮች የደረሱበትን የቴክኖሎጂ ውጤት እንኳ ተጠቃሚ እንዳይሆን ታፍኖ እንዲኖር በኩላቸውን የጥፋት ድረሻ እያበረከቱ ይገኛሉ። ትንሽ ጉልበትና ጥሬ ገንዘብ ያለውም የድሃ ልጅ በመከራ ሊጠበስ ባሕር የተሻገረ… ያልቻለም የባሕር አዞ ዋጠው! የጫካ አውሬ በላው!የበረሃ ጨካኝ ወንበዴ የውስጥ ዕቃውን እያወጣ ሸጠው! ያሞራ ሲሳይ የሆነውና የተደፈሩ የተንገላቱ ዜጎቻችንን ቤቱ ይቁጠረው። ሀገር ፲፩ በመቶ አድጎ ከመካከለኛ ገቢ ካላቸው ተርታ ተሰልፈን ፎቶ እስክንነሳ አህያ ቀንድ ታወጣለች። ይህ ውሸታም ከሀዲና ሀገር በላ የወያኔ ቡድን ከራዕዩና ከነሥርዓቱ መወገድ አለበት!!። የሚያስወግደው ኃይል፤ ይኼን መሠረታዊ መነሻ በትግሉ ያዋኻደ መሆን ይገባዋል!!።
፪) ስንቱ ነው ከተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች መካከል ይኼን የተቀበለ? ስንቱስ ነው የማይቀበል? የሚቀበሉና የማይቀበሉ ካሉ፤ ታዲያ እንዴት እኒህ ተቃራኒዎች ባንድነት ሊቆሙ ይችላሉ?
**ለመሆኑ እውነተኛው ተቃዋሚው ማነው?? (፩) አንዳንዶች የምርጫ ሰሞን ሱፍ ልብስ እቤታቸው የሚላክላቸው አሉ።(፪) የምርጫ ምልክት ለመውሰድ ዘመድ አዝማድ ጠርተው ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት ወረፋ ይይዛሉ።(፫)በእየ ስብሰባ ቢሮው ሲውጡ ሲገቡ አንጀባ ያበዛሉ በወያኔ ቴሌቪዥን ይታያሉ ።(፬) ካለው ገዢ ፓርቲ በበለጠ የሀገሪቱን ዕድገት ያሟሙቋሉ። (፭)የመግለጫና የመገልጨጫ ልዩ ሰዓት ተይዞላቸው ስለዴሞክራሲና ልማት ጥናታዊ ፅሑፍ ያነባሉ’ (ያነብባሉ) (ያነበንባሉ) (፮)የጥያቄና መልሱን ሰዓት ለመግደል ወይም ሰዓቱን ለመሻማት ሲቀላምዱ ይውላሉ(፯)በጣም የሚገርምና የሚያስቀው “የፖለቲካ አቋም የለንም, አልቀረፅንም በህዝቡ ፍላጎት ለመምራት ሕዝብ ይምረጠን ይላሉ።(መኪና ቢኖረኝ መኪናው የሚሄድበትን ካልነገረኝ በጭራሽ አላንቀሳቅሰውም!) (፰)የተጀመረውን ዕቅድ ለማሳካት ተሰካክተን በመተባበር መሥራት ይበጃል የድጋፍ አቋማችንን ገልፀናል የሚሉም አሉ። አሁን አወሳሳቢው ግን አሳሳቢው ነገር ፍሬውን ከግርዱ የመለየቱ ሁኔታ አመኔታ የተጣለበት ተቃዋሚ ማነው? ምንስ ተቃውሞ ምን ያሻሽላል? የሕዝቦችን አንድነት የሀገር ሉዓላዊነት የሰንደቅን ክብር ይጠብቃል ወይስ ለራሱ ይከብራል ተወለደበትን ያካባቡ ባንዲራ ይዞ ይጯጯሃል/ ለመሆኑ በአንድ ሀገር ብዙ ሕዝብ መኖር የተለያየህ ነህ ብሎ ሲቀባጥሩ መኖር ትርፉ ምን ይሆን?” “ልዩነታችን ውበታችን “ያልተለያየ አያምርም ማለት ነው ።?’የቀለም መለያየት ለአበባ ውበት ይሆናል, ለሰው ልዩነት አምላክ ሲፈጥር በአምሳሉ እንጂ በፖለቲካ አመለካከቱ ወይም በዘር በቋንቋ አልነበርምና መምድር በተናቸውን ሁሉ እኩል ብዙና ተባዙ መሬትንም ሙሏት ፍሬዋንም ተጠቀሙበት አለ።”በዚያኛው ዘመን ቤተ ሠሪ ይበዛል የሚኖርበት ግን አይኖርም ሲልም ተዛብቷል…እንደዲያስፖራው(ፈላሹ) ኢንቨስተር መሆኑ ነው ፵ በ፷ የቤት እንሥራ ጥየቃ!!ለመሆኑ ያ አፈር ገፊ፣ ተሸካሚ፣ ድንጋይ ፈላጭ፣ዘበኛው፤ወታደሩ፣አነስተኛና ትቃቅን ታቃፊዎች ፲ በ ፺ ይፈቀድላቸዋልን እኩል ማስተዳደር ማለት ያ ነው። ታዲያ ይህ ሁሉ አጅብ ያለው መንግስት እያለ የትኛው ተቃዋሚ ነው አንድ ሆኖ ሆ !ብሎ ሕዝብ አስተባብሮ ለውጥ እንዲያመጣ የሚፈቀድለት ? በሞኖፖል ተይዟል!!!
፩) አንድ ሕዝብ ነን ወይንስ አይደለንም?
*አንድ ህዝብ ማለት ምን ማለት ነው? የተለያየ ቋንቋ የምንናገር(ስታንቋርር ብትውል የማትሰማና የማትስማማ) አለባበሳችን(እደዛሬው ካኒቴራ ጡት ማያዣ ባርኔጣ አድረጎ ምግብ መብላት ሳይጀመር) አመጋገባችን(ሁላችንም በእጃችን ትኩስና የሚያቃጥል መብላታችን)ከአልጫው ሚሊኒየም በፊት… የሠርግም(የሺህ ጋብቻ በጅምላ ) ይሁን የሀዘን (ለጠቅላይ ሚ/ሩ መሞት ትርዒት)እንደታየው ሁሉ የነበረውን እያጠፍን በአዲስ እያጠፋፋን መቀጠላችን “አዲሲቷ ኢትዮጵያ ተብሎ “ካልተመፃደቅን በቀር ሠፊና ድንቅ ሆነ ተወራራሽ ባህል አብረን የሠራነው ታሪክ ያለንአ ንድ ህዝብ ነበርን። አሁን ያሰጋል? ?
፪) አንድ ሀገር ናት ወይንስ አይደለችም?
*ኢትዮጵያ አንድ ሀገር ናት !ብዙ ህዘቦች የሚኖሩባት…ለአገዛዝ እንዲያመች የተከለለ ተናጋሪ ከብት አደርጎ እራስን በራስ ማስተዳደር (ማሠር)።ሀገሪቱ በፌዴራሊዝም ሥርዓት ስትመሠረት ቋንቋን ወይም ብሄርን ምክንያት ማድረግ አልነበረበትም።አራት ነጥብ፡፤አትራፊው ገዢው መንግስትና ሥርዓቱ ለዘመናት የፌዴራል መንግስቱ ከትውልድ ትውልድ ተተካኪ አንባገነናዊ ሥርዓትን እነደያዙ ይቀጥላሉ . ..ክልሎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት የሚሰጣቸውን ድራጎት እየበሉ እያለቀሱ ይኖራሉ ሙያ ያላቸውም አባይ ካድሬዎችም ከአውራው መንግስት ‘ክላስተር ቦንብ ‘ይጠመድላቸዋል!!።
፫) የአስተሳሰብ አንድነት ካላቸው ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች ጋር የፖለቲካ ተሳትፎዋን ማድረግ የምትችልበት እንድትሆን ነው ወይ ትግሉ?
*ማን ሰው አለሽና መንገድ ላይ ታፏጪያለሽ”አሉ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች? በዚህ ሥርዓት ወያኔ/ኢህአዴግ ብቻ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦችን የፈጠረ “ብቸኛው የሀገሪቱ ተቆርቋሪዎች ሙሉ ሰው ያሉበት ቡድን! “ሆኖ አሳቢ፣ ፈፃሚ፣ አስመራጭ፣ መራጭ፣ አሸናፊ፣ ሆኖ በአንደኛ ዜግነት የተፈጠረ አድረጎ የሚያስተምሩ ፐሮፌሰር፣ ዶ/ር፣ ዳንኪረኛ፣መሐንዲስ፣ እያሉ ሁለተኛ ዜግነታቸውን ያረጋገጡ/የተረገጡ ሊሂቃንም በጣም በጣት ከሚቆጠሩት በቀር! የታሪክ ተወቃሾችም ተከሳሾችም ናቸው።
፫-፩) የብሔሮችን ከአንድ ክልል ወደአንድ ክልል ተዘዋውሮ መሥራት ሀብት ማፈራት ዶሞክራሲ መብት? ?
* ‘የተፈጥሮ መብት ሕግጋት’ እና ‘የዶማ-ክራሲ መብት’ ባይምታታብን ጥሩ ነው። ለመሆኑ ሕዝብን ለምን ማጠር መከለል አስፈለገ? መጀመሪያ ተዘዋውሮ ለመሥራት ገንዘብ ያስፈልጋል።ገንዘብ ያለው ወታደራዊ መዋቅሩ፣ የፓርቲ አባላት፣ ካድሬ፣የፓርቲው ጠባቂዎች ሹማምንት እና ባለሥልጣናትና ቤተሰቦች እጅ ነው።ትግሬ ደቡብ ክልል መሬት ቤት አለው ሁመራና አላማጣ የትግራይ ክልል ነው።የእንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የአምስት ዓመት ዕቅድ ውረስ የተፃፈላት ከተማ ናት። ስለዚህ ዋናው የትግል አጋር የሚሆነው በጥቅም ተይዟል።ያም ማለት ሁሉም የትግራይ ሕዝብ ደልቶታል ሁሉም የትግራይ ሕዝብ የጥቅም ተካፋይ ሆኖ ተመችቶታል ማለት ግን በፍጹም አደለም!!። ለልጆቹ ንፁህ ውሃ፣ ለእግሩ ጫማ፣ ለወገቡ ፍራሽ የሌለው ፣በእየገበያው ዝንብ የሚወረው ድሃም አለ!። የደቡብ ተወላጅ ‘የኢፈርት’ ኩባንያ ባለቤት ሆኖ ትግራይ ላይ ፋብሪካ ከሰራ አውነትም ይህ ሕገ መንግስት አብዷል።አንዳንዴም ‘መዘዋወር’ እና ‘መንቀሳቀስ’ ሲጠናበር ይታያል!!ንብረት ‘ማፍራት’ እና አሰፈላጊ ሆኖ ከተገነኘ ‘ማፍረስ’ የሚልም አለው።
፬) በሕገ ደንብና አሠራር ለመገዛትና ለመተማመን ነው ወይ የምንታገለው?
**ያው ሰማንያ ሚሊየንን ሕዝብ ወክለው ፳፱ ግለሰቦች የተሳተፉበት የሕገመንግስት ፅሑፍ ሲደረስ የውጭ ሀገር ታዛቢዎች ከፍተኛውን ቁጥር ይዘዋል አሁን ችግሩ ‘የፃፉት ለእነሱ የሠራላቸውን አንቀፅ እንጂ የእኛን ቤት በእኛ አቅም እንዴት እንደምንገነባው ዕድሉን አላገኘንም!እንዴትስ ህዝባችሁን ይመቸዋል አላሉም!።ሕዝብ ህገ መንግስት አተረጓጎምም የህግ አተገባበር ችግር አለ ሲል መልሱ ሂዱና ለነጭ ክሰሱን የፃፉት እራሳቸው ናቸው ሆነ ጨዋታው። አሃ…ለዚህም ነው የእንግሊዘኛው እና የአማርኛው አተረጓጎም የተጣረሰው… ቀጥሎም ኢህአዴግ ህገ መንግስቱን አልጣስኩም አከበርኩ ሲል ተቃዋሚው ኢህአዴግ ጣሰው!… ጨፈለቀው!…ደፈጠጠው!…ሲሉ ይሰማል ለመሆኑ ትክክለኛው ማነው?ወያኔ? ተቃዋሚ? ሕገመንግስቱ?
፭) ይህ መንግሥት ሊታረም የማይፈልግና የማይችል ነው። ይህን መንግሥት መወገድ አለበት ወይስ የለበትም?
**”ሕገ መንግስቱ ከተናካ እነጠፋፋለን”ይላል ወያኔ ለመሆኑ ‘ክላስትር ቦንብ ‘ነው? ” የኃይለመልስ በአልጀዚራ….ፉገራ እና ጥገራ “constitution = precondition + constitution is constitution you can’t change constitution evrey body under and below ? In way he say it (dominatede or controlled by WHO? Hierarahy?
Therefore (art.104-105) IS WHAT ??
*በመሠረቱ አብዛኛው አንቀፅ የተወሰደው ከፍትሀ ነገስቱና ከቀድሞው ደርግ ህገመንግስት የቃላት እና (የማሽሞንሞኛ እና ማንቆለጳጰሺያ) የፈረጅ ዓረፍተ ነገርና ቃላት “እንደድሃ ጎመን ወጥ ውስጥሥጋ ጣል ጣል ተደርጎ የተሠራ” አይነት ነው…የተበሻቀጠውም ድብቅ አጀንዳውም እዚያው ላይ ነው። ስለዚህም ቢያንስ ከመቶ ያላነሱ መመሪያ፣ ደንብ እና አዋጆች እንዲሁም በጦር መሳሪያ በበቂ ታማኝ የጦር መኮንኖች እና ወታደር እያንዳንዱ አንቀፅ ባይደገፍ ኖሮ ኢህአዴግና ሕገ መንግስቱ ገና ድሮ አንገቷን አሸዋ ውስጥ የደበቀች ቂጧን ለጅብ ያጋለጠች ‘ሰጎን’ ሆኖ ነበር በለው! ። ለጠቅላለ የሀገር ሰላም፣ የአብሮ መኖር፣ መደጋገፍና አብሮ የመበልፀግ ህገመንግስቱ ጠቅላላ ባይጣልም በሀገር በቀል ምሁራን የሚታረሙ መጥፎ ፅሁፎች አሉት እንግዲህ “የቤቴ መቃጥል ለትኋኑ መጥፋት በጀኝ” እንዳንል እንጂ ሥርዓቱ ቶሎ ሀገራዊ እርቅና እርማትን ካልወሰደ መወገድ አለበት!!የኢትዮጵያ ሕዝብ አንቀፅ ፴፱ አደለም መንግስቱ ኃይለማርያምም ሀገር ለቀው! ጠ/ሚኒስትር ለገሠ(መለሰ) ተጠቅልለው!ተጠባበቂው ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደስአለኝ በጠ/ሚኒስትርነት ማዕረግ ከቤተ መንግስት ውጭ ሲንከራተቱ ሕዝቡ እራሱን በሰላም፣ በጨዋነት፣በትዕግስት የዕለት ኑሮውን የመራ ኩሩ ህዝብ ነው። ያ ማለት ግን ፈሪና የተነጣጠለ ሕዝብ አለመሆኑን እንወቅ! ! ተናግራችሁ እንድንናገር መብት ስለሰጣችሁን እናመሰግናለን በለው! ከሀገረ ካናዳ በቸር ግጠመን