- በግፍ አስሮም ህክምና መንፈግ ለምን?
- ሀሳብን የደፈረው ጀግና …!
የወንድም ኡስታዝ አህመዲን ጀበልን በእስር ላይ ህክምና መነፈጉን ከተለያዩ ምንጮች ለማረጋገጥ ችያለሁ። በእስር ላይ ያሉ ወገኖችን በህገ መንግስትና በአለም አቀፍ ህግ የተደነገገ እየተጣሰባቸው ነው። በህግ ስር ባለው ኡስታዝ አህመዲንና በብዙ ታሳሪዎች መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈጸመባቸው ተደጋግሞ ተመልክተናል። ዛሬ አደባባይ በአህመዲን ያየነውም ይህንኑ ነው። በኡስታዝ አህመዲን ሰውነት ላይ የሚታየውን ጉዳትና መጎሳቆል ስመለከት የተሰማኝ ስሜት ደስ አይልም።
አሳሪው መንግስት ደጋግሞ “ኡስታዝ አህመዲንና ጓደኞቹ የታሰሩት በህግ ጥሰት ነው!” ቢልም የታሰረበት በመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴነቱ ብቻ እንደሆነ አምናሁ። ከታሰሩት በርካታ የመፍትሔ አፈላላጊዎች ኮሚቴ አባላት መካከል ኡስታዝ አህመዲንን ጨምሮ ጥቂቶች ተለይተው ሲቀሩ ዋና ዋና የተባሉት ተከሳሾች በነጻ ተፈትተዋል። ዛሬ ጎልማሳው ወንድም አህመዲን እንደቀሩት ወንድሞቹ እኩል ከወህኒ እንዲወጣ ባይፈቀድለት እንኳ ህክምና የማግኘት መብቱ ሊከበርለት ይገባል እላለሁ!
በእስር ላይ ሆኖ ህክምና አለማግኘት ቀርቶ ህክምና እያገኙ ኑሮን መግፋት እጅግ የከፋ መከራ ስለመሆኑ ከ4 ዓመት በፊት በወራት የሳውዲ ወህኒ ህይዎቴ አውቀዋለሁ። “ከአረብ ሀገራት በተሻለ መልኩ የሰብአዊ መብት ይዞታ ተከብሯል” በምትባለው ኢትዮጵያ ሀገራችን መሳሪያ ያላነሳ ታሳሪን ህክምና ነፍጎ ማሰቃየትን የመሰለ የከፋ ግፍ ሲፈጸም ደጋግመን ተመልክተናል። ይህ መራራ እውነት እጅግ በጣም ያሳዝናል! ልብን በሀዘን ይሰብራል! ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በአስቸኳይ ህክምና ይደረግለት ዘንድ የዜጋ ድምጼን አሰማለሁ!
ሀሳብን የደፈረውን ጀግና ፍቱት …!
ወንድም ኡስታዝ አህመዲን ጀበልን ሳስታውስ ብዙ ነገሩ ትዝ ይለኛል። ኡስታዝ አህመዲን ለቆመበት አላማ ጽኑ ነው። የህዝብ ከበሬታ ያሰጠው አስተምህሮት መሆኑንም ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልፈጀብኝም። ኡስታዝ አህመዲን በሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ተመርጦ በወቅቱ ለነበረው ሁከት መፍትሔ አመንጭ ከነበሩት መካከል አንዱ ነበር። ዳሩ ግን ለመፍትሔ የተወከሉት “ወንጀለኛ” ተብለው ዘብጥያ ሲወርዱ አህመዲን ክራሞቱ ወህኒ ሆነ። በእሱና በቀሩት ወንድሞች እስር አዘንን።
ኡስታዝ አህመዲን የሀገሬ ሰው ለማንሳትና በአደባባይ ለመሞገት ይፈራቸው የነበሩ የሙስሊም ጉዳዮችን በስራዎቹ እያነሳ የማይደፈር ሀሳብን የደፈረ በመሆኑ አደንቀዋለሁ። በጋዜጦችና በየአደባባዩ ሀሳብን ሲያቀርብና ሲሞግት፣ ከዚያም የታሪክ ድርሳናትን ፈታትሾ ለንበብ ሲያቀርብ ተመልክቻለሁ። አህመዲን የማህበረሰቡ ውስጥ ይንሸራሸር የነበረውን ሀሳብ በአደባባይ ማውጣቱና መነጋገሪያ ማድረጉን አደንቃለሁ!
የኡስታዝ አህመዲንን የጻፋቸውን መጻሕፍት ደጋግሜ ካነበብኳቸው ውስጥ ቀዳሚዎቹ ናቸው። “ስለ ሙስሊሙ ጉዳት ያገባኛል” ማለቱንና ሀሳቡን በነጻነት መግለጹን አከብርለታለሁ። በመጽሐፍቱ ያሰናዳቸውን ሀሳቦችና ምልከታዎቻ ጋር ግን ብዙም አልስማማም። በሀሳብ ልዩነት አምናለሁ፣ የሀሳብ ልዩነት አለን ማለት ሰብአዊ መብቱ ሲጣስ ዝም እላለሁ ማለት አይደለም።
ጎልማሳው ኡስታዝ አህመዲን የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል ሆኖ እያለ ሲጀመር መንግስት ሆደ ሰፊ በመሆን መፍትሔ አብሮ እንደመፈለግ ማሰሩ ምን ጠቀመ? በግፍ አስሮም ህክምና መንፈግስ ለምን? ብየ ደጋግሜ ራሴን ጠይቄያለሁ። አጥጋቢ መልስ ግን የለኝም። በህግና ስርአት እስር ላይ ያለን ፍርደኛ ህክምና ነፍጎ ማንገላታትና እንዲህ እንዳየነው ከሰው ተራ ማውጣት ግለሰብን ብቻ ሳይሆን ዜጋን መናቅ ማለት ነው። እናም የታሳሪውን ስቃይ ስሰማ ከተናቁት ዜጎች መካከል መሆኔ ተሰምቶኛል። ለኡስታዝ አህመዲን ጀበል ህክምና ከማድረግ በላይ በህዝብ ውክል በመውሰዱ ለወህኒ የተዳረገ ወጣት ነውና በአስቸኳይ ትፈቱት ዘንድ የዜጋ ድምጼን አሰማለሁ!
ፍትህ ለኡስታዝ አህመዲንና በግፍ ለሚሰቃዩት ታሳሪዎች!
ወዳጄ ኡስታዝ አህመዲን ሆይ ምህረቱን ይላክልህ! (ፎቶዎቹ ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኙ ናቸው)
እስኪ ቸር ያሰማን
ነቢዩ ሲራክ
ህዳር 7 ቀን 2010 ዓም
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply