አቶ አሰፋ ጫቦ ከአርባ ዓመታት በላይ ከዘለለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ጎልተው የታዩ ሰው ነበሩ። እንዲሁም ሊጽፏቸው የፈለጓቸውን ነገሮች የራሳቸው በሆነ የአፃፃፍ ስልት የሚያቀርቡ፣ ስለነበሩ በዚሁ ሥራቸው በብዙዎች ዘንድ ሞገስና ውዳሴ አትርፈዋል። በቅርቡም የትዝታ ፈለግ የሚባል መጽሐፍ አሳትመው ሕዝብ እንዲያነበው አድርገዋል።
የዚህ ጽሁፍ ዓላማ በአቶ አሰፋ የፖለቲካ ሕይወት ወይም ስነጽሁፋቸውን ለመቃኘት ሳይሆን የአሟታቸውን ሁኔታ በተመለከተ ቬሮኒካ መላኩ ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ ተመርኩዞ የተነሳ ነው።
ቬሮኒካ መላኩ በጽሑፋቸው አቶ አሰፋ ከመሞታቸው በፊት በነበሩ ቀናት ውስጥ በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኙ እንደነበር በመገልጽ ለቦርከና ድረገጽ ባለቤት ወደ ደረሰው መልዕክት ይንደረደራሉ። በመልዕክቱም ግሪጎሪ ማኬንዚ የተባሉ ሰው አቶ አሰፋን እንደሚያውቁ ሁለቱም ዓለም በቃኝ እስር ቤት አብረው ታስረው እንደነበርና ጓደኛሞችም እንደነበሩ የአቶ አሰፋን ኢሜይል እንደሚፈልጉ ጭምር ገልጸው ከአውስትራሊያ አሜሪካ በሚመጡ ጊዜ ሊያገኟቸው እንደሚፈልጉ ይጽፋሉ። የቦርከና ድረገጽ አዘጋጅም ይሄንንኑ መልዕክት ለአቶ አሰፋ ይልካሉ። አቶ አሰፋም ማኬንዚን እንደሚያውቁትና ሊያገናኙትም እንደሚፈልጉ ገልጸው መልስ ይሰጣሉ። ከዛ በኋላ ግሪጎሪ ማኬንዚ እና አቶ አሰፋ በተጀመረው መስመር ተጉዘው ይገናኛሉ። በዳላስ ከተማ በሚገኝም አንድ የጣሊያን ሬስቶራንት አብረው ራት ይበላሉ። ለሦስት ሰዓት ያህል ሲጨዋወቱ ካመሹም በኋላ ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ ይዘው ይለያያሉ።
አቶ አሰፋ ከራት በፊት የተነሱት በሚመስለው ፎቶ ላይ ጥሩ ሁኔታና ጤንነት ይታይባቸው ነበር ያሉት ቬሮኒካ፤ በማግስቱ ጠዋት ግን ሆስፒታል እንደገቡ፣ የምግብ መመረዝ ሕመም እንዳጋጠማቸው እና ይሄንኑ ለግሪጎሪ ማኬንዚም እንደጻፉ፤ ከዛ በኋላ ግን አቶ አሰፋ ከሆስፒታል ሕይወታቸው አልፎ እንደወጡ፤ አብሮ ራት የበላው እንግዳ ግን ምንም እንዳልሆነ በመግለጽ የአቶ አሰፋ ሕልፈተ ሕይወት ድረስ ያለውን ጉዳይ በዚህ ይቋጫሉ።
ከዚህ አያይዘው ለአቶ አሰፋ ሞት ምክንያት ይሆናሉ የሚሏቸውን ነገሮች ያነሳሉ። የአገር ውስጥና የውጪ አገር የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ሽኩቻ እንደነበራቸው፣ የድርጅቶቹንም እኩይ ባህሪና ሴራ አጋልጠው እንደጻፉ፣ ወደፊትም እንደሚጽፉ፤ ቅራኔያቸው ከነሱ ብቻ ሳይሆን ከእጀ ረዥሙ ከሲ.አይ.ኤ.ም (CIA) ጋር እንደነበርና እሱንም ከማጋለጥ ወደ ኋላ እንዳላሉ። በዚህም ምክንያት የፖለቲካ ድርጅቶቹ ወደፊትም ሕዝብ የማያውቀው ጉዳያችንን ያወጣብናል ብለው እንደሚፈሯቸው CIAም ትንሽም ሆነ ትልቅ ጠላት ንቆ እንደማይተው ገልጸው፤ የገዳይና የተገዳይ ድራማ የሚመስል ነገር በአቶ አሰፋ ሞት እንደሚታይ ጥርጣሬያቸውን አስፍረዋል።
ጸሐፊዋ ተቆርቆሪነታቸውን ገልጸው ይህንንን መጻፋቸው ባያስወቅሳቸውም፤ ከዛ በኋላ ግን እሳቸውም ሆኑ ቤተሰብና ወዳጅ፣ አንባቢም ሆነ ሰሚ፣ ወቃሽም ሆነ ተወቃሽ አንዳቸውም ጉዳዩን ሳያነሱት ወራቶች መቆጠር ጀመሩ። ቬሮኒካ ሄንን ለመጻፍ ብቻ ሲሉ የጻፉ ስላልሆነ ከዛ በኋላ የተሰማ ወይም የተደረሰበት ነገር ካለ ቢጽፉልን መልካም ነበር። ጥርጣሬን ብቻ ጥለው ሲጠፉ ግን፤ ጥርጣሬአቸው ሌላ ጥርጣሬና ጥያቄዎች ሊያስከትል በቃ።
ለመሆኑ ቬሮኒካ ከራት በፊት ይመስላል ያሉትን የአቶ አሰፋን ፎቶ የት አዩ? አቶ አሰፋ ለግሪጎሪ ማኬንዚም የጻፉት ደብዳቤ መኖሩን በምን አወቁ? ጽሑፉንስ ያየው ማነው? እንግዳውስ ጤና መሆኑ የታወቀው እንዴት ነው? ሌላው በጥርጣሬ ውስጥ የወደቁት የፖለቲካ ድርጅቶችን ቤሮኒካ ያነሱትን ለመጠየቅ አልሻም። አፍም ብዕርም ያላቸው በመሆኑ እሱን ለነሱ ትቼ የምጠይቀውን ተጨማሪ ጥያቄ ላንሳ።
የአቶ አሰፋ ቤተሰብ ስለአሟሟታቸው የሚያውቀም ምንድነው? ሐኪምስ በምን ምክንያት እንደሞቱ ያረጋገጠበት መረጃ ምን ይላል? በርግጠኝነት የተነገርው የምግብ መመረዝስ ከምን ተነሳ? ራት ከበሉት ምግብ ከሆነ የበሉበትን የኢጣሊያን ሬስቶራንትን ስለዚሁ ጉዳይ የጠየቀ የለም ወይ? አብሮ ራት የበላው እንግዳስ ስለጉዳዩ ምን ተናገረ? እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉን ጥያቄዎች ዓይን አፍጠው የተቀመጡ በመሆናቸው ቬሮኒካም ሆኑ ሌሎች ጉዳዩ ያገባናል የምትሉ ካላችሁ መልስ ስጡ። ተገድለውም ከሆነ “ተገደሉ”፤ የግዜሩን ሞት ሞተውም ከሆነ “ሞቱ” በሉን። አንባቢን ከጥርጣሬ ውስጥ ስለከተታችሁት የአቶ አሰፋ ሞት ጉዳይ ምን ደረሰ ማለቱ አይቀርም።
ቸር ይግጠመን!
ወለላዬ ከስዊድን ለጎልጉል ልከውት የታተመ።
Al says
Veronica is TPLF planted cyber task force creating confusion, spreading hate and weaken the vibrant diaspora. Open your eyes people.