መነሻ፤ ወርሃ የካቲት ለነፃነትና ለባንዲራ ከወራሪዎች ጋር ተናንቀው ኢትዮጵያን በነፃነት ያቆምዋትን ሠማዕታት አብናቶቻችንን (አባት እናቶቻችንን) የምንዘክርበትና ስለባንዲራና ስለኢትዮጵያ ቃል ኪዳናችንንም የምናድስበት ወር ነው። እነሆ ደግሞ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን ካነቀው ሀገር በቀል ዘረኛ ወራሪ የህወሃት አገዛዝ ነፃነቷንና ክብሯን ለመመለስ በሚደረገው የህልውና ትንቅንቅ በህወሃት ወህኒ ቤቶች ወደር አልባ ናዚስታዊ ግፍና ሰቆቃ የተፈፀመባቸውን የነፃነት ታጋዮች ለማስፈታት ይህ ወጣት ትውልድ /ቄሮ ወፋኖ/ ባልተቋረጠው ሠላማዊ ትግል በትንግርተኛው ወርሃ የካቲት እንደ አብናቶቹ ታሪክ ሰርቷል፤ ህወሃትን በግማሽ አንበርክኮ ናሙናውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝንም አሰናብቷል። እነሆም ናዚስት ህወሃት በህዝባዊ እምቢተኝነት ማንቁርቱን ታንቆ ያለ ውዴታው ተገዶ በየወህኒው የዘጋባቸው ሠላማዊ የነፃነት ታጋዮች ከህዝብ ጋር ተቀላቅለዋል። ከግፈኞች ወህኒ ቤቶች ለተፈታችሁ የነፃነት ጀግኖቻችንና ቤተሰቦች እንኳን ደስ አላችሁ! ክብርና ምሥጋና ለህዝብና ለዚህ ትንታግ ወጣት ትውልድ ይሁንና በፀናው ትግሉ በኢትዮጵያ ሠማይ የሰፈነው የጨለማው ዘመን ይገፈፋል!! የህወሃት አምባገነንነት ይሰበራል!! ቁማርተኛው ህወሃት በአንድ እጁ እስረኞች ሲፈታ በሌላ እጁ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፅፎ ደንግጓል። በያዝነው ወርሃ የካቲት በሀገር በቀል ኮሎኒያሊስት የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት /ህወሃት/ የታወጀው ሶስተኛው ዙር የአፈናና የኢሰብዓዊነት መሳሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም እንደ ቀዳሚው ሁሉ ይከሽፋል። የጣሊያን ፋሽስት ኮሎኒያሊስትን ቀንበር የሰበረው የአብናቶቻችን ትውልድ የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ እኛም ከህወሃትና ህወሃታውያን ጋር ለምናደርገው ተጋድሎ ዋቢያችን ነውና…
ሁለተኛው የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ/ም አዲስ አበባ ላይ “ክተት ሠራዊት” ተብሎ በይፋ ታወጀ። እነሆም ከ1928 ዓ/ም እስከ 1933 ዓ/ም ለአምስት ዓመታት በአባቶቻችንና እናቶቻችን ተጋድሎ በተካሄደ የአንገዛም ባይነት የነፃነትና የሉዐላዊነት ከፍተኛ መሥዋዕትነት በድል ተጠናቋል። ፋሽስት ኢጣሊያ የ1888 ዓ/ምን የአድዋ ጦርነት መራር ሽንፈት ለመበቀል ለ40 (አርባ) ዓመት ስትደራጅና ስትዘጋጅ ቆይታ በዕብሪት በከፈተችው በዚህ የበቀል ጦርነት ካሰለፈችው ግዙፍ ዘመናዊ ሠራዊትና መሳሪያ በተጨማሪ በዓለም መንግሥታት ማህበር የታገደውን የመርዝ ጋዝ ቦንብ በኢትዮጵያውያን ላይ ተጠቅማለች።
ኢትዮጵያ በፋሽስት ጣሊያን ወራሪ ሠራዊት መጠነ ሰፊ የሆነ ውድመትና ጥፋት ተፈፅሞባታል። ኢትዮጵያን የወጓት ባህር የብስ እና ህዋ አቋርጠው የመጡት የቤኒቶ ሙሶሎኒ ወራሪዎች ፋሽስቶች ብቻ አልነበሩም። ለፋሽስቶች አድረውና በጥቅምና በሥልጣን አብደው የራሳቸውን አካል ወንድምና እህቶቻቸውን በጨፈጨፉና ሀገራቸውን በካዱም ሹምበሾች /ባንዶች/ ጭምርም እንጂ።
በሁለተኛው ዙር የፋሽስት ጣሊያን የበቀልና የጥፋት ጦርነት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ ተሰውተዋል። ለምሳሌም በግራዚያኒ ላይ በተጣለ የቦንብ ጥቃት ሳቢያ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ/ም (ፌብሩዋሪ 19 1937) አዲስ አበባ ውስጥ ለሶስት ማዕልትና ሌሊት በዘለቀው የፋሽስቶች ጭፍጨፋ ሰላሳ ሺህ ኢትዮጵያውያን (እናቶች ህፃናት አዛውንቶች እርጉዞች) ከነነፍሳቸው በእሳት ጋይተዋል፤ በመትረየስ ረግፈዋል፤ በአካፋና በቆንጨራ አልቀዋል።
በግራዚያኒ የመግደል ሙከራ ላይ ተባባሪ ናችሁ ተብለው በደብረ ሊባኖስ ገዳም የሚኖሩ ሶስት መቶ ሃያ (320) መነኮሳት ያለ አንዳች ርህራሄ እንዳለ በመትረየስ ተረሽነዋል። እንደዚሁም ከዝቋላና ከዜና ማርቆስ ገዳማት ከአንድ ሺህ የማያንሱ መነኮሳትንና መነኮሳስትን ረሽነዋል። በፋሽስት ጣሊያን የበቀል ወረራ ከሁለት ሺህ አብያተ ክርስትያናትና ከአምሰት መቶ ሃያ ሺህ በላይ መኖሪያዎች ወድመዋል። ከሰባት ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን በሶማሊያና በኤርትራ እስር ቤቶች ወስደው አጉረዋል። በተለይ የተማሩና ህዝብን የሚያስተባብሩ አርበኞችና መሪዎች የተባሉትን በሙሉ መንጥረው አብዛኛውን ወደ ጣሊያን እስር ቤቶች አግዘዋል። እኒህና ተዛማጅ ጥፋቶች በተለያዩ ሀገራዊና የውጪ የታሪክ ፀሀፈት (ጣሊያናውያን ፀሀፍቶችንም ጨምሮ) በፅሁፍ የታያዙ መረጃዎች ያሉዋቸው ሰቆቃዎችና ውድመቶች ናቸው። የአርበኛው ራስ አበበ አረጋይ ሠራዊት አባላት በሆኑትና በዓመፀኛ ዋሻ በተጠለሉት ኢትዮጵያውያን ላይ የወረደውን መዐት ግን ብዙዎች ተገቢውን ያህል የዘከሩት አይመስልም። እናም እነሆ የዓመፀኛ ዋሻ ታሪክ ….
ዓመፀኛ ዋሻ በመንዝ ጌራ ምድር አውራጃ ልዩ ስሙ ዘረት በሚባል ስፍራ ይገኛል። ወደ ዓመፀኛ ዋሻ የሚደረገው ጉዞም ብርቱ ጥንቃቄን ይጠይቃል። እልም ያለው ገደል አስፈሪ ከመሆኑም በላይ መንገዱም ጠመዝማዛና ረዥም በመሆኑ ከገደሉ አፋፍ እስከ መግቢያው ጫፍ ያለውን አጭር ርቀት ለመሸፈን ከግማሽ ሰአት በላይ ይፈጃል።
የወንጪትን ወንዝ ከስሩ አጋድሞ ግርማ ሞገስን ተላብሶና በኩራት ደረቱን ገልብጦ የሚታየው ዓመፀኛ ዋሻ የታሪክ እማኝነቱን ለመናገር የፈለገ ይመስል፤ በስፋት አፉን ከፍቶ ሲያዩት አንዳች ስሜት መላ ሰውነትን ይወርራል። የደቡብ ወሎን ተረተር በስተቀኝ አድርጎ በዙሪያውና ባሻገር በሚታዩት ጎጆዎች ተከቦ የሚገኘው ዓመፀኛ ዋሻ ተፈጥሯዊ አቀማመጡና ዙሪያ ገባው አንዳች ምትሃታዊ መስህብም አለው።
ተፈጥሮ የራሷ በሆነ ምትሃታዊ ዘዴ ያዘጋጀችው ይህ አስደናቂ ዋሻ ሰፊ ከመሆኑም ሌላ በሁለት ታላላቅ ክፍሎች የተከፈለ ነው። የዓመፀኛ ዋሻ መግቢያም ሆነ መውጫ አንድ ነው። ጥቂት ሜትሮችን ወደ ውስጥ ከዘለቁ በሁዋላ ጥቅጥቅ ካለ ጨለማ በስተቀር የሚታይ ነገር የለም። እናም የዓመፀኛ ዋሻን ውስጠ ታሪክ ለመቃኘት ሀያል የሆነ ባትሪ መያዝ ግድ ነው።
ይሁን እንጂ ወደ ውስጥ በዘለቁ ቁጥር ደግሞ ሰፊው ዋሻ ብርሃን ውጦ ስለሚያስቀርና መመለሻም ስለሚቸግር በየጥቂት ሜትር ርቀት ላይ የመንገዱን አቅጣጫ የሚጠቁሙ ሻማዎች እየለኮሱ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። አለበለዚያ መውጫ ፍለጋ ሲዳክሩ መዋል ነው። ዓመፀኛ ዋሻ በቀላሉ ተገብቶ በቀላሉ የሚወጣበት አይደለም።
ማንኛውም ሰው በቁም መራመድ የሚችልበትን የዋሻውን ክፍል እየዘለቁ ወደፊት በገፉ ቁጥር ከማስጎንበስ አልፎ በደረት እስከ መሳብ ግድ የሚል የዋሻው ክፍል ይከተላል። በመጨረሻ ከምትገኘው አንዲት የአንገት ማስገቢያ ከምታክል በር አልፎ መሄድ ግን የማይሞከር ነው።
እንደ አረጋዊው አርበኛ አቶ ደመቀ ጩፋ አባባል ከዚህ ጠባብ መግቢያ አልፎ ራሱን የቻለ ሌላ ሰፊ ሆድ ያለው የዋሻው ክፍል አለ። በዚያም ውስጥ የበርካታ አረጋውያን፤ ህፃናትና….አርበኞች አስከሬን ይገኛል።
በሰፊው ዓመፀኛ ዋሻ አንደኛው ክፍል ውስጥ ለታሪክ የተቀመጡ አያሌ የአርበኞች አፅሞች ይገኛሉ። ዋሻው ተቆፍረው በተቀበሩ የእህል ድብኝቶች የተሞላ ነው። ሰፌድ፤ እንቅብ፤ ሳጠራ፤ የሸክላ እቃዎች ስብርባሪ…..በብዛት ይታያሉ።
ዋሻው ውስጥ ከሚገኙ ቋጥኝ መሰል ድንጋዮች የተሰሩ ወፍጮዎችና መጆች እናት አርበኞችና ከፋሽስት ኢሰብዐዊ ጭፍጨፋ ሸሽተው በዋሻው የተጠለሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ይጠቀሙበት እንደነበር የሚጠቁም የታሪክ ማስረጃ ነው።
ከእድሜ ብዛት ወደ ትቢያነት የተቀየሩና በመቀየር ላይ ያሉ ጨርቃ ጨርቆች በዚሁ ዓመፀኛ ዋሻ መጀመሪያ ክፍል ውስጥ ይገኛሉ። አለፎ አለፎም ለአይን የደበዘዙ ፅሁፎች በግርግዳዎች ላይ ይታያሉ።
የዋሻው ሌላ ክፍል ተፈጥሯዊ በሆነ የቋጥኝ ግርግዳ የተሰራ ሲሆን በዚህ ቦታ ሰፊ የሆነ የውሃ ኩሬ ይገኛል። ይህ የውሃ ኩሬ ነበር በዋሻው ተጠልለው ለነበሩት አርበኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች ነፍስ አድን ወዳጅ ሆኖ የቆየው።
በ1982 ዓ/ም (ዋሻውን በጎበኘሁበት ወቅት) የ76 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋና የጦር ቁስለኛ የነበሩት አርበኛው አቶ ደመቀ ጩፋ በአመፀኛ ዋሻ ስለተፈፀመው አሰቃቂ እልቂት እንደሚከተለው አጫውተውኛል፤
በሰሜን ሸዋ አካባቢ ማለትም በመንዝ፤ በይፋትና በመርሃ ቤቴ ይገኙ የነበሩ አርበኞች የፋሽስት ጣሊያንን ጦር መፈናፈኛ አሳጥተውት በየደረሰበት የጥይት ራት አደረጉት። ጣልያኖች በመንዝ ምድር ላይ የተለያዩ የጦር ካምፖችን መስርተው ነበር። ይሁን እንጂ አርበኛው ለፋሽስት ቦንብና መትረየስ ሳይንበረከክ ስለተፋለማቸው ሃይላቸውን አጠናክረው ይህንን የአርበኞች ትግል በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል በስፋት ተንቀሳቀሱ።
የጣሊያን አውሮፕላኖች ቦንብ እንደ ዝናም አወረዱ። መትረየሶቻቸው ላንቃዎቻቸውን ከፈቱ። ህፃናት፤ አረጋውያንና ሴቶች ተረሸኑ። ይህ የጣሊያን አረመኔያዊ ድርጊት ሲከፋ በደጃዝማች ተሾመ ሸንቁጤ የሚመራው የአርበኞች ጦር ቅዳሜ መጋቢት 24 ቀን 1931 ዓ/ም በብዙ መቶ የሚቆጠሩ አረጋውያን፤ ህፃናትና ሴቶችን ይዞ ወደ አመፀኛ ዋሻ ገባ። ህፃናትና አረጋውያን ታዝለው፤ ነፍሰ ጡሮች ተደግፈው የዓመፀኛ ዋሻን ገደል ወረዱ። አርበኞችና ጉልበት ያላቸው ወጣቶች እህል፤ እንጨት፤ የማብሰያ እቃዎችንና የመሳሰሉትን በማጋዝ በዓመፀኛ ዋሻ አከማቹ። እናም ኑሮ በዓመፀኛ ዋሻ ሆነ።
ይሁንና ማን አለብኝ ባዩ የፋሽስት ጦር ዱካ እየተከታተለ ቦንቡን ማዝነም ቀጠለ። የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችም ማህፀኗን ተገን አድርገው፤ ዋሻ ቁጥቋጦውን ተከልለው ፍልሚያቸውን አጧጧፉት። በዓመፀኛ ዋሻ የተጠለሉትም ለአርበኛው ስንቅ በማዘጋጀት፤ ውሃ በማቀበልና በአስፈላጊው ሁሉ አርበኛውን እየረዱ ከጎኑ ተሰለፉ።
“የእናት ሆድ ዥንጉርጉር” እንዲሉ ሆኖ ለነፃነቷ፤ ለክብሯ፤ ለአንድነቷና ለሉዐላዊነቷ ከሚታገሉት አርበኞች ጎን ሀገራቸውን ለፋሽስት አሳልፈው የሸጡ፤ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ፤ ኢትዮጵያዊነታቸውን የካዱ ሹምባሾች /ከሀዲዎች/ ተፈጠሩ።
በየፈፋውና በየሸለቆው የሀገሩን ባንዲራ እያውለበለበ የሚዋጋውን አርበኛ ሠራዊት በሀይል ማንበርከክ ያቃተው የፋሽስት ሠራዊት እኒህን ባንዳዎች (ሹምባሾች) እየመለመለ ማሰለፍ ጀመረ። እናም በመንዝ ገደላ ገደል የመሸገውን አርበኛ ለማጥፋት ፋሽስቶች በባንዳዎች መሪነት ወደ ዓመፀኛ ዋሻ ተንቀሳቀሱ።
የአርበኞቻችንን ቁርጠኝነትና የዓመፀኛ ዋሻን ገደል የፈሩት ፋሽስቶች በባንዶቹ ጠቋሚነትና መሪነት ከበባቸውን አጠናቅቀው በተለያዩ አቅጣጫዎች መድፎቻቸውንና መትረየሶቻቸውን አነጣጥረው ደገኑ።
ሚያዚያ 12 ቀን 1931 ዓ/ም ነበር ጣሊያኖች ከዓመፀኛ ዋሻ ገደል አናት ላይ ቆመው በሹምባሽ (ባንዳ) ሃይለ ማርያም ገብሬ አማካኝነት በድምፅ ማጉያ “ሃያሉ የጣልያን መንግሥት ምህረት አድርጓልና በገደላ ገደሉ የመሸጋችሁ በዓመፀኛ ዋሻ የተከማቻችሁ ሁሉ እጃችሁን ስጡ” ሲሉ የለፈፉት።
አርበኛው ግን ለፋሽስት ጣልያን ጥሪ ምላሽ ጣቱን ከታጠቀው መሳሪያ ቃታ ላይ አሳረፈ። በብዙ መቶ የሚቆጠረው ህዝብም የአርበኛው ደጀን ሆኖ ተሰለፈ። እናም ለነፃነት የሚተኮሰው ጥይት በዓመፀኛ ዋሻ አስተጋባ። ፋሽስቶች ባለ በሌለ ሃይላቸው ተረባረቡ። መድፎቻቸው አጓሩ፤ መትረየሶቻቸውም የጥይት ዶፍ አወረዱ። የመርዝ ጭስ (የመርዝ ጋዝ) ዓመፀኛ ዋሻ ላይ ደጋግመው ጣሉ።
(ከላይ የሚታየው ፎቶ Effects of mustard gas on a patient picked up by a Norwegian Red Cross ambulance.)
መርዛማው ጭስ (ጋዝ) በዋሻው ውስጥ የነበሩትን በርካታ ሴቶች፤ ህፃናትና አረጋውያን አይናቸውን ይለበልብና ያቃጥላቸው፤ ሰውነታቸውንም ያጉረበርበው ገባ። ጭሱ እያደናበራቸው ከዋሻው የወጡት ሁሉ በፋሽስቶች መትረየስ ረገፉ። በዋሻው ውስጥ የቆዩትም አይኖቻቸውን በሽንታቸው በመታጠብና በሽንኩርት በማሸት ማስታገስ ሞከሩ። መፍትሄ ግን አልሆነም።
የጠላት ሃይል በማየሉና ቁልፍ የሆኑ መሹለኪያዎች በሹምባሾች መሪነት በፋሽስቶች ስለተያዙ በርካታ አርበኞች እየተታኮሱ ወደቁ። በመጨረሻም ደጃዝማች ሸንቁጤና ጥቂት አርበኞች የፋሽስቶችን ከበባ ሰብረው ሲያመልጡ በብዙ መቶ የሚቆጠሩት በዓመፀኛ ዋሻ የተጠለሉ ኢትዮጵያውያን ተማረኩ።
ፋሽስቶችም የተማረከውን ህዝብ እንደ ከብት በመገድ አስረው ከዓመፀኛ ዋሻ ገደል አፋፍ ላይ ካቆሙት በሁዋላ ያለ ርህራሄ ርሸናቸውን ተያያዙት። ወንድ፤ ሴት፤ ህፃን፤ ሽማግሌ ሳይመርጡ በሙሉ ፈጁዋቸው። …. ይሁን እንጂ ለአንዲት ኢትዮጵያ ነፃነትና ለባንዲራዋ ክብር ይዋደቅ የነበረውን አርበኛ ፋሽስቶችና ሹምባሾች ከቶም ሊያንበረክኩት አልቻሉም። ይልቁንም እንደ ዐድዋው ገድል ሁሉ ዳግም የሀፍረት ማቅ አከናንቧቸው ነፃነቱን በትግሉ ተቀዳጀ እንጂ! በማለት የዓመፀኛ ዋሻን ታሪክ አውግተውኛል፤ አዛውንቱ አርበኛ አቶ ደመቀ ጩፋ።
ዓመፀኛ ዋሻን በዚህ ወቅት (1982 ዓ/ም) ለተመለከተ በዚህ ታሪካዊ ስፍራ የሚገኘው የአርበኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች አፅም ተበታትኖ፤ ድብኝቱ፤ ሰፌዱ፤ የሸክላ እቃዎቹ ተመሰቃቅለውና ወደ ትቢያነት እየተቀየሩ፤ ዋሻው እንደ ተራ ዋሻ ሲታይ ያሳዝናል፤ ልብን ይሰብራል።
በአመፀኛ ዋሻ ያለቁት ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ክደው ለጠላት ባደሩ የእናት ጡት ነካሽ ሹምባሾች /ባንዳዎች/ ምክንያት መሆኑን ተከታታይ ትውልድ ልብ ሊለው ተገቢ ነው።
በመጨረሻም ከታሪካዊው ዓመፀኛ ዋሻ ጉብኝት በሁዋላ ዙሪያ ገባውን በደከሙት አይኖቻቸው እየማተሩ ይህንን ታሪክ ያወጉኝ አባት አርበኛ አቶ ደመቀ ጩፋ፤ ለዚህች ብርቅ ሀገራችን የሚበጃት አንድነቷና የዳር ድንበሯ ሉዐላዊነት ተከብሮ መኖር እንጂ መገነጣጠልና መከፋፈል እንዳልሆነ ይህ ትውልድ አበክሮ እንዲያጤን ለአንዲት ኢትዮጵያ በወደቁት ሠማዕታት አጥንት እማጠናለሁ፤ ብለዋል የነገይቷን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ አሻግረው የሚያዩ ይመስል ከዓመፀኛ ዋሻ አድማስ ማዶ አይኖቻቸውን ተክለው።
ማስታወሻ፤ {በመንዝና ግሼ አውራጃ መሃል ሜዳ ከተማ በመምህርነት በቆየሁባቸው ሶስት ዓመታት (ከ1980 – 1982 ዓ/ም) በራስ አነሳሽነት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር እየተዘዋወርኩ ከጎበኘሁዋቸውና ካጠናቀርኳቸው ታሪካዊ ስፍራዎች መካከል፤ ደንጨት ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያንና በስሩ የሚገኘው አስደናቂ ታላቅ የዋሻ አዳራሽ፤ ዐፅመ ቅዱሳን ዋሻ እና በዚህ ፅሁፍ ያቀረብኩት ዓመፀኛ ዋሻ ይገኛሉ። የእኒህ ታሪካዊና አመራማሪ ስፍራዎችን ታሪክ አንድም ለትውልድ ለማሳወቅ ሁለትም በዚያን ወቅት ያለ እንክብካቤ ደብዛቸው በመጥፋት ላይ የነበሩትን የታሪክና የመሥዋዕትነት ዋሻዎች ደራሽና ተንከባካቢ እንዲኖራቸው ለሚመለከታቸው አካላት ለማሳወቅ በማሰብ ፅሁፎቹን በ1982 ዓ/ም በተከታታይ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ የባህል አምድ ላይ በማቅረብ ለንባብ በቅተዋል። ከላይ የሚታየው የመታሰቢያ ሀውልት ምስል በዚያን ወቅት /በ1982 ዓ/ም/ ፀሀፊው ጉብኝትና ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ አልነበረም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ጥናታዊ ፅሁፎች ስለ ዓመፀኛ ዋሻ ዕልቂት አደባባይ የበቁ ሲሆን እንደ ፅሁፎቹ መረጃ ፋሽስቶች በዓመፀኛ ዋሻ በመርዝ ጋዝና በመትረየስ የፈጁዋቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሁለት ሺህ አምስት መቶ በላይ መሆኑን ይናገራሉ።}
መድረሻ፤ ኢትዮጵያ በቀዳሚው ትውልድ ተከታታይ መሥዋዕትነት በደምና በአጥንት ካስማና ማገርነት የቆመች ሀገር ናት። በዘመናት የታሪክና የትውልድ ቅብብሎሽ ብዙ እጅግ በጣም ብዙ ሀገራዊ መሥዋዕትነትን ድፍን ቀዳሚው የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍሎላት ነው ያስረከቡን። ይህቺን ክቡርና ታላቅ ሀገር ነፃነቷንና አንድነቷን መጠበቅና ለሚተካን ትውልድ በክብር የማስተላለፍ ሸክም በዚህ ትውልድ ትከሻ ላይ ወድቋል። ይህ ትውልድም ከቀደሙት ትውልዶች ሁሉ የተጋፈጠው ሃላፊነት እጅግ የገዘፈና እጅግም የተወሳሰበ ነው። ‘ረቂቅ’ ጠላት ‘ከረቂቅ’ ዓለማና ግብ ጋር ሀይልና ሥልጣንን ይዟልና።
በዚህ ዘመን የሚገኘው የኢትዮጵያ ጠላት ጣልያኖች የተዉለትን የመከፋፈል ዘር አርቅቆና አራቅቆ በተለየ ቀለምና አርማ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ በግዙፍ ድርጅታዊ ፤ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሀይልም ጭምር የዘመተባት የሹምባሾች የልጅ ልጆች በሆኑት ህወሃትና/ህወሃታውያን ወኪልነት ነው። የጣሊያን ፋሽስት ምሁራን ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍሎና ህዝቡን እርስ በርስ አናክሶ ወራሪው ግን ‘ገላጋይ ማዕከላዊ መንግሥት’ ሆኖ ለመግዛት ለኮሎኒያሊስት ጣሊያን የነደፉትን ዓላማ ህወሃት እንዳለ ገልብጦ ደደቢት ገባ።
እነሆ ከደደቢት በረሃ የጣሊያንን ንድፍ አንግቦና ለዚሁም ግብዐት ተማምሎ የተነሳው ሀገር በቀል ኮሎኒያሊስት ህወሃት አዲስ አበባ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት በጠመንጃ ከገባ ወዲህ ፋሽስታዊ ዓላማውን በናዚስት አፈፃፀም ከተከዜ መለስ ያለገደብና ስስት እየተገበረ ይገኛል። በኢትዮጵያዊነቱ መደራደር የማይፈልገው የኢትዮጵያ ትውልድ ሸክሙና ሃላፊነቱ ከዘመናት ሁሉ የከበደና የገዘፈ መሆኑም ጠላቶቹ ሀገር በቀል ‘ዘረኛ ኮሎኒያሊስቶች’ በመሆናቸውና ግብራቸውም ናዚስታዊ በመሆኑ ነው።
ከህወሃት እርኩስ ሀይልና የጥፋት ዘመቻ ኢትዮጵያን መታደግ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ትውልዳዊና ዜግነታዊም ሀላፊነትና ግዴታም ጭምር ነው። እንደ ሀገርና ህዝብ የመቀጠል የህልውና ጥያቄ ነው የዚህ ወጣት ትውልድ ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ። የህወሃት መነሻና መድረሻ የትግራይ ሪፑብሊክን መመስረት ብቻ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሀገርና ኢትዮጵያዊነት እንደ ዜግነት መገለጫ ለህወሃትና ህወሃታውያን ቁማር ከሆነ እነሆ ሶስተኛው አስርታት ሊጠቃለል ቀርቧል። ኢትዮጵያ ለህወሃት የግቡ መሰላል እንጂ ግቡ አይደለችም። መሰላሉን በማንኛውም ሰዐት አሽቀንጥሮ ለመጣል ዝግጁ ነው። ህወሃት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ይታደግ ዘንድ አይችልም!!!
ሀገራዊ መግባባትንና ሀገራዊ ሠላምን ለማምጣት እስከ አሁን የታለፈባቸው የታሪክ መልካም አጋጣሚዎች ሁሉ በህወሃት እንደ መቅሰፍት በመታየታቸው ምክንያት በሀይል ተጨፍልቀዋል። ህወሃትን ማስታመም ሳይሆን ህወሃትን ማስወገድ ብቸኛው አማራጭ ከሆነ ሰንብቷል። ለዚህም ነው ትንታጉ ወጣት ትውልድ (ቄሮ ወፋኖ) ከወልቃይት ባህርዳር ወልዲያ ከቆቦ (ሰሜን) እስከ ኮንሶ ዲላና ቦረና (ደቡብ) ከጨለንቆ ጨርጨር ድሬደዋ (ምሥራቅ) እስከ ቡኖ በደሌ ጮራና ዴጋ (ምዕራብ) ከሻሸመኔ አምቦ ቢሾፍቱ (እስከ መሃል) ድረስ “የህወሃት የበላይነት ይብቃ! ወያኔ በቃን! ነፃነታችንን እንፈልጋለን የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ!” እያለ ከናዚስት ጦር አጋዚ ጋር በባዶ እጁ ተጋፍጦ የሚሞተው። ኢትዮጵያ በህወሃት ናዚስታዊ አገዛዝ ካዘመመችበት አስከፊ ውድቀት በዚህ ትንታግ ወጣት ትውልድ (ቄሮ ወፋኖ) መራራ ትግል ትነሳለች! ዳግም በግርማ ሞገስም ትቆማለች! ይህ ስለመሆኑም አንዳች አንጠራጠርም!!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!
መስፍን ማሞ ተሰማ፤ የካቲት 2010 ዓ/ም (ፌብሩዋሪ 2018)
ሲድኒ አውስትራሊያ mmtessema@gmail.com
ፎቶ፤ ከጉግል ፈልግ ምስሎች
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Yalew says
I apperciate you