ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በብዙ አፍሪካ አገሮች የሚታየው የአስተዳደር ብልሹነት፣ የህዝቦች ኑሮ መዘበራረቅና ዓላማ-ቢስ መሆን፣ እንዲያም ሲል በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ በሃይማኖትና በጎሳ አሳቦ ርስ በርሱ እንዲጠላላ ማድረግና፣ የመጨረሻ መጨረሻም ወደ ርስ በርስ መተላለቅ እንዲያመራ መንገዱን ማዘጋጀት፣ በተራ አነጋገር ከመልካም አስተዳደር እጦት፣ ከአምባገነናዊ አስተዳደር መስፈንና ከዲሞክራሲ አለመኖር ጋር ሲያያዝ ይታያል። አንዳንዶች እንዲያውም እንደዚህ ዐይነቱን ዓላማ-ቢስ የህብረተሰብ ጉዞ የአፍሪካ መሪዎች ወይም የጥቁር ህዝብ ችግር አድርገው የሚመለከቱ አሉ።
በእርግጥ ለአንድ አገር ስርዓት ባለው መልክ መተዳደርና፣ ህብረተሰቡም በዕቅድና በዓላማ እንዲመራ ከተፈለገ በዚያ የሰፈነው አገዛዝ ህብረተሰቡን በማደራጀት ረገድ የሚጫወተው ከፍተኛ ሚና አለ። ጥያቄው ግን አንድ ህብረተሰብ ዓላማ ባለው መልክ እንዳይደራጅና ቆንጆ ቆንጆ ስራዎችን እንዳይሰራ የሚያግዱት ነገሮች ምን ምን ናቸው? በስነ-ስርዓት እንዲደራጅስ ከተፈለገ መሪዎችም ሆነ ህብረተሰቡ መከተል የሚገባቸው ኖርሞች፣ ሞራልና ስነ-ምግባር አሉ ወይ? ምንስ ይመስላሉ ? ወይስ አንድ ህዝብ እየተዋከበና ርስ በርሱ እየተፋጠጠ መኖሩ ተፈጥሮአዊ ግዴታ ነው ወይ ? አንድ ህብረተሰብስ በምን መልክ ነው መታየት ያለበት? በሌላ አነጋገር፣ ለመብላትና ለመጠጣት ብቻ የሚኖርበት ? ወይስ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ስነ-ምግባራዊ፣ ጥበባዊና ኢኮኖሚዊ፣ እንዲሁም ሌሎችም ነገሮች ተደራጅተው ህብረተሰቡ እንደሰውነታችን በብዙ ነርቮች ተሳስሮ፣ ልክ እንደደም ዝውውር ሳያቋርጥ፣ በተለይም ኢኮኖሚው አንድኛው መስክ ከሌላው ጋር በመያያዝ ውስጠ-ኃይሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና እየተጠናከረ የሚጓዝበት መድረክ ነው ወይ ? የሚሉትን ጥያቄዎች ጠጋ ብሎ መመልከትና መመርመር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በተለይም በአሁኑ ዘመን የግሎባል ካፒታሊዝም አይሎ መውጣትና፣ የብዙ ህብረተሰቦችን ህይወት ወሳኝ ብቻ ሳይሆን ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲያመሩ ማስገደድና ማዘበራረቅ፣ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ፈራቸውን እየሳቱና በቀላሉ የማይመለሱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት ይቻላል።
ከዚህ ስንነሳ በፍጹም ልናልፈው የማንችለው ጥያቄ ከፊታችን ተደቅኖ ይገኛል።ይኸውም ብዙ የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች ከሞላ ጎደል ስርዓት ባለው መልክ ተደራጅተው ሲጓዙና፣ የብዙ ሚሊያርድን ህዝቦች ዕድል ወሳኝ መሆን ሲችሉ፣ እንደኛ ያለውንስ ህዝብ ስነ-ስርዓት ያለው አደረጃጀት ለምን ተሳነው? ስነ-ስርዓትስ ባለው መልክ ለመደራጀት እንዳንችል የሚጎድሉን ነገሮች ምንድናቸው? ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊ፣ ህብረተሰብአዊ ? ወይስ የፖለቲካ ፍልስፍና እጦትና መሪዎች የሚመሩበት አንዳች ፍልስፍና አለመኖር ?
ለአንድ ህብረተሰብ በስነ-ስርዓት መደራጀትን አስመልክቶ ከጥንት የግሪክ ስልጣኔ ጀምሮም ሆነ ከዚያ በፊት ህግና ስርዓት አስፈላጊ መሆናቸውን በብዙ ምርምር የተደረሰበትና በኢምፔሪካል ደረጃም የተረጋገጠ ነው። ይሁንና በተለይም ፍልስፍናን ከፖለቲካ ጋር ማያያዝና፣ አንድም ህብረተሰብ ሚዛናዊ በሆነ መልክና በስነ-ስርዓት የማደራጀትን አስፈላጊነት በከፍተኛ ደረጃ ውይይት የተካሄደበት ከግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል። ከዚያ በኋላ የተነሱና ብዙም ምርምር የተካሄደባቸው የፖለቲካ ፍልስፍናዎች፣ ህብረተሰብን በአንድ ስርዓት ባለው መልክ ማደራጀት፣ በግሪኩ የተለያዩ ፍልስፍናዎች ላይ ተመርኩዞ ነው ማለት ይቻላል። እዚህ ላይ ሌላው የሚነሳው ጥያቄ፣ የተለያዩ የግሪክ ፈላስፋዎች አትኩሯቸውን ለምን በፍልስፍና ላይ፣ በተለይም በፖለቲካ ፍልስፍና ላይ አደረጉ ? የሚለው ከባድ ጥያቄ ነው። እንደሚታወቀው የሰው ልጅ እንደማንኛውም ተንቀሳቃሽ ፍጡር ለህይወቱ ምግብ፣ ውሀ፣ መጠለያና መከላከያ ቢያስፈልገውም፣ ከሌላው ፍጥረት ጋር ሲወዳደር የማሰብ ኃይልና ራሱንም በማደራጀት ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚሽጋገር የታወቀ ነው። ይሁንና የማሰብ ኃይሉን እንዳያዳብር፣ አዳዲስ መሳሪዎችን በመፍጠር ከዝቅተኛ ህብረተሰብ ወደ ከፍተኛ እንዳይሸጋገር፣ ከቁም ነገር ስራ ይልቅ በሆነ ባልሆነው ነገር በመያዝ ወይም በጦርነት በመጠመድ ዝብርቅርቅ ኑሮ እንዲኖርና፣ በዚያው እንዲገፋበት የሚያደርጉትና፣ ይህ ዐይነቱም ኑሮ እንደ ባህልና እንደ ልማድ የሚወሰድበት ሁኔታ አለ። ይህንን ሁኔታ ጠጋ ብለው የተመራመሩት የግሪክ ፈላስፎች የሰው ልጅ ከእንስሳ የተለየ ከሆነና፣ ራሱንም ማደራጀትና በሰላም መኖር የሚችል ከሆነ ለምንድን ነው ወደ ጦርነት የሚያመራው? ለምንድን ነው የተዘበራረቀ ኑሮ የሚኖረው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ነበረባቸው።
ሶክራተስና ፕላቶ ብቅ ከማለታቸው በፊት በስድስተኛው ክፍለ-ዘመንና ከዚያ በፊት የግሪክ ህዝብ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኝ ነበር። የርስ በርስ መተላለቅ፣ መጠን የሌለው ብዝበዛና ድህነት፣ የተፈጥሮ አደጋዎች መደጋገምና ሌሎችም የግሪክን ህዝቦች ኑሮ ያመሰቃቀሉና፣ ዕረፍትና ሰላም አንሰጥም ያሉ ሁኔታዎች የህዝቡ ዕጣዎች ነበሩ። እነዚህን የመሳሰሉ የኑሮን ትርጉም ያሳጡ ሁኔታዎች በነ ሆሜርና በሄሲዮድም ሆነ በግሪክ ህዝብ ዕምነት የአምላኮች ድርጊት እንደነበርና፣ ባስፈለጋቸው ጊዜ ህዝቡን ለመቅጣት ሲሉ የሚልኩት ውርጅብኝ እንደነበርና፣ ህዝቡም ካለ አምላኮች ፈቃድ በራሱ አነሳሽነት ምንም ሊያደረገው የሚችለው ነገር እንደሌለና የነሱንም ትዕዛዝ መጠበቅ እንደነበረበት የታመነበት ጉዳይ ነበር። ይህንን አስተሳሰብ ከሶክራተስና ከፕላቶ በፊት የነበሩ የመጀመሪያዎቹ የተፈጥሮ ፈላስፎች ትክክል እንዳልሆነና፣ በተፈጥሮ ውስጥ ይከሰቱ የነበሩ አደጋዎች፣ለምሳሌ እንደ ብልጭታና የመሬት መንቀጥቀጥም ሆነ ሌላ ነገሮች የአምላኮች ተልዕኮዎች ሳይሆኑ የተፈጥሮ ህግጋት እንደሆኑና፣ ማንኛውም ነገር ካለምክንያት እንደማይከሰት አመለከቱ። ይህ የመጀመሪያው የተፈጥሮ ፍልስፍናና፣ በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን በታላቁ የግሪክ መሪ በሶሎን ተግባራዊ የሆኑት የመጀመሪያው የፖለቲካ ሪፎርሞች በግሪክ ህዝብ አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሉ። ከፍተኛ የባህል ለውጥ የታየበትና ልዩ ልዩ የፍልስፍና አስተሳሰቦችና የሂሳብ ምርምሮችና ሳይንሳዊ አስተሳሰብም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው በተለይም የግሪክን ምሁር ጭንቅላት መያዝ የጀመሩትና ዕውነተኛ ዕድገት መታየት የተጀመረበት። በፒታኩስና በሶሎን የአገዛዝ ዘመን የግሪክ ህዝብ ከጦርነት ተላቆና በአጉል ጀግንነት ላይ የተመሰረተን ዝናን ጥሎ ራሱን በማግኘት ዕውነተኛ የሲቪክ አገዛዝን የተቀዳጀበት ዘመን ነበር። የማቴሪያል ደስተኛነት ብቻ ሳይሆን የመንፈስንንም ነጻነትና ደስተኛነት በመቀዳጀት የመፍጠር ችሎታውን ያዳበረበት ዘመን ነበር። ከፒታኩስና ከሶሎን አገዛዝ በፊት የግሪክ ህዝብ ዕድል በጦርነት የተጠመደና ይህንን እንደሙያው አድርጎ በመያዝ የሚዝናናበት ዘመነ ነበር። ይሁንና ግን ስልጣኔው እየገፋ ሲሄድና የስልጣን ሽግግር ሲመጣና የኃይል አሰላልፍ ሲቀየር፣ የፖለቲካ ፍልስፍናና አደረጃጀት እነሶሎን በቀደዱት መልክ ሊጓዝ አልቻለም። በተለይም የስልጣንን ምንነት ከራሳቸው ዝናና ጥቅም አንፃር መተርጎምና ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩ የግሪክ መሪዎች የፖለቲካውን አቅጣጫ ይቀይራሉ።ህብረተሰባዊ ስምምነትን የሚያጠነክር ሳይሆን ውዝግብነትን አፍላቂ እንዲሆን ይደረጋል። በዚህ ላይ የኦሊጋርኪዎችን አመለካከት የሚያስተጋቡና ይህም ትክክል ነው ብለው የሚያስተምሩ ፈላስፋዎች፣ ሶፊስቶች ተብለው የሚጠሩ፣ የፖለቲካውን መድረክ እየተቆጣጠሩና ብዙ ወጣቶችንም ማሳሳት ይጀምራሉ። በተለይም የአቴን ግዛት አይሎ መውጣትና ከሌሎች ደሴቶች ጋር ሲወዳደር በስልጣኔ ቀድሞ መሄድ የግሪኩን የመጀመሪያውን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እየደመሰሰው መጣ።
የተለያዩ የግሪክ ግዛቶች፣ በአንድ በኩል በራሳቸው ውስጥ በሚደረግ ሽኩቻ የተወጠሩ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የፐርሺያ አገዛዝ አቴንና ሌሎችንም ግዛቶች በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ተደጋጋሚ ጦርነት ይከፍታል። ይሁንና በፐሪክለስ የሚመራው የአቴን ግዛት ሌሎችንም በማስተባበር ከፐርሺያ የተከፈተበትን ጦርነት መክቶ ይመልሳል። አቴን በአሽናፊነት ስትወጣ የጥጋብ ጥጋብ ይሰማታል። ቀደም ብሎ የተደረሰበትን የእኩልነት ስምምነት በማፍረስ በሌሎች የግሪክ ግዛቶች ላይ ወረራ ታደርጋልች። እምቢ ያሏትን ግዛቶች ሁሉ በመውረርና በተለይም ወንድ ወንዱን በመጨረስ ሴቶችንና ህፃናትን ገባር ታደርጋቸዋለች። ድርጊቱ እጅግ አሰቃቂ ነበር። የግሪክን ህዝብ ትርምስ ውስጥ የከተተ ነበር። ይሁንና ይህ የአቴን ጥጋብና ግፍ በስፓርታ ግዛትና አመራር ሊከሽፍና ሊገታ ቻለ። በዚህ ድርጊቱ ፐሪክለስ አቴን ለሌሎች ግዛቶች በስልጣኔዋ ምሳሌ ትሆናለች ብሎ እንዳለተመጻደቀ ሁሉ፣ በተግባር ያሳየው ግን በኃይሉ በመመካት ወረራንና ጭፍጨፋን ነበር ያረጋገጠው።
እነ ሶክራተስና ፕላቶ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻና በአራተኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ ብቅ ሲሉ ይህንን የወንድማማቾችን ርስ በርስ መተላለቅና ህዝቡን ሰላም ማሳጣትና ኑሮም ትርጉም እንዳይኖረው ማድረግ የተረጎሙት ከተሳሳተ ፍልስፍና ጋር የተያያዘ ስልጣን መሆኑን በማመልከትና፣ በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ የሚሳበብ ሳይሆን፣ ጠቅላላውን የፖለቲካ አወቃቀርና አገዛዙ የሚመራበትን ፍልስፍና በመመርመር ነበር። በሶክራተስ ዕምነትና አመለካከት፣ በጊዜው ፐሪክለስ ታላቅ መሪ ቢሆንም በሱ ዘመን አቴን ወደ ኢምፔርያሊስትነት የተለወጠችና፣ የአገዛዙም ዋና ፍልስፋና ዝናን በማስቀደም ኃይልንና ስግብግብነትን(Power and Greed) ዋና ፍልስፍናው አድርጎ የተነሳ አገዛዝ መሆኑን በማመልከት ነበር። በመሆኑም ይላል ሶክራተስ፣ በፐሪክለስ ዘመን ወጣቱ ሰነፍ፣ ለፍላፊና አጭበርባሪ የሆነበት ዘመንና፣ አሳሳች አስተሳሰብ በማበብ በተለይም የወጣቱን ጭንቅላት በመያዝ ወደ ማይሆን አቅጣጫ እንዲያመራ የተደረገበት ዘመን ነበር። ባህላዊ ኖሮሞችና መከባበር የጠፋበት፣ ሽማግሌ የማይከበርበትና፣ ህዝቡም አንድ ይዞ የሚጓዘው ዕምነት አልነበረውም። አስተሳሰቡ ሁሉ የተዛበራረቀበት ነበር።
በጊዜው የነበረው ትግል ይህንን አቅጣጫ የሌለውን ጉዞና በስልጣን መባለግ አስመልክቶ በሶክራተስና በፕላቶ በአንድ ወገን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሶፊስቶች መሀከል የጦፈ ትግል ይካሄድ ነበር ። ሶፊስቶች የእነ ፐሪክለስን ስልጣንና ፍልስፍናን ሲደግፉ፣ የአመለካከታቸው የፍልስፍና መሰረት በጊዜው የነበረውን ሁኔታ መቀበልና ይህም ትክክል መሆንኑ ማስተማር ነበር። ሶፊስቶች በአነሳሳቸው ተራማጅ ቢሆኑም፣ ፍልስፍናቸው በቀጥታ በሚታይ ነገር ላይ ተመርኩዞ ትንተና መስጠትና በጣፈጠ ግን ደግሞ በተሳሳተ አቀራረብና አነጋገር የሰውን ልብ መሳብ ነበር። ስለዚህም በሶፊስቶች ዕምነት ስልጣን ላይ ያለው የገዢ መደብ የሚያወጣውን ህግ አምኖ መቀበልና፣ ከዚህ ሌላ አማራጭ ነገር እንደሌለ ሲከራከሩና ለማሳመን ሲጥሩ፣ እነሶክራተስና ፕላቶ ደግሞ፣ በሶክራተስ በመመሰል ይሉት የነበረው የጠቅላላውን የፖለቲካ አወቃቀር ለመገንዘብ ከነበረው ሁኔታ አልፎ(Trnascedental) መሄድና መመርመር እንደሚያስፈልግ ያመለክቱ ነበር። በሌላ አነጋገር፣ ሶፊስቶች ኃይልንና ለስልጣን መስገብገብን ትክክል ነው ብለው ሲሰብኩ፣ እነሶክራተስና ፕላቶ ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱ ጉዞ እጅግ አደገኛ እንደሆነና፣ የመጨረሻ መጨረሻም አንድ ህብረተሰብ ሊወጣ የማይችልበት ማጥ ውስጥ የሚከተው ነው ብለው በጥብቅ ያሳስቡ ነበር። ካሊክለስ የሚባለው ሌላው የሶፊስቶች መሪ ደግሞ የነሶክራተሰን በአርቆ አስተዋይነትና በሚዛናዊነት ላይ የተመረኮዘ የፖለቲካ ፍልስፍና ሞኞች ብቻ ናቸው የሚከተሉት ብሎ በመስበክና በማንቋሸሽ፣ ፖለቲካ በስምምነት ላይ ሳይሆን በአሽናፍና በተሽናፊነት ላይ የተመረኮዘና፣ የመጨረሻ መጨረሻም ኃይል ያለው ብቻ ነው ሊገዛ የሚችለው በማለት ሽንጡን ገትሮ ይከራከር ነበር። በተጨማሪም በሶፊስቶች ዕምነት አንድ ሁሉንም ሊያሰተባብርና ሁሉም ሰው ለቀበለው የሚችለው ዕውነት ነገር የለም። ሁሉም ሰው አንድን ነገር እንደፈለገው ሊተረጉምና ሊረዳ ይችላል። ፕርታጎራስ የሚባለው የሶፊቶች ሌላው መሪ ማንም ሰው የራሱ የዕውነት መለኪያ(Man is the Measure of Everything) አለው በማለት አንድ ሁሉንም ሊያሰተባብርና ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባው ዕውነት የለም በማለት የሶፊስቶችን የተሙለጨለጨ አመለካከት ያስተጋባ ነበር።
በሶክራተስና በፕላቶ የፍልስፍና ዕምነት ግን ማንም ሰው ዓላማና ተግባር ሲኖረው፣ በመጀመሪያ ከትክክለኛ ዕውነት ጋር ነው የሚፈጠረው። ይሁናን ግን በዚህች ዓለም ላይ ሲወረወር እንደየህብረተሰቡ ሁኔታ ከተፈጠረበት ዕውነት ጋር እየራቀ ይሄዳል። በአንድ ወቅት ነገሮች ርስ በራሳቸው እንደተያያዙና የተወሳሰቡ መሆናቸውን ይገነዘብ የነበረው ጭንቅላት፣ የተያያዙ ነገሮችን እየበጣጠሰ መመልከት ይጀምራል። ነገሮች ሁሉ ብዥ ይሉበታል። ዕውነትንና ውሽትን ለመለየት፣ እንዲሁም ደግሞ ለአንድ ችግር መነሻ የሆነውን ምክንያት ለመረዳት ችግር ውስጥ ይወድቃል። በሶክራተስም ሆነ በፕላቶ ዕምነት ወደ ጥንቱ ሁኔታ ለመመለስ ማንኛውም ሰው ዕውነትን ለመፍለግ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ አለበት። እየመላለሰ ራሱን መጠየቅ አለበት። በቀላሉ በሚታዩ ነገሮች ላይ መማረክና እነሱን ትክክል ናቸው ብሎ መቀበል የለበትም። በሶክራተስም ሆነ በፕላቶ ዕምነት የሰው ልጅ ሁሉ ጠላት ከመንፈስ ተነጥሎ የሚታየው አካል ነው። ሰዎች ራሳቸውን ለማጎልመስ ሲሉ በሆነው ባልሆነው ነገር ይታለላሉ። እየገፉ ሲሄዱ ስግብግብነትንና አብጦ መገኘትን፣ ሌላውን ሰው ደግሞ ማንቋሸሽና መናቅን እንደ ዋና የኑሮ ፍልስፍናቸው አድርገው ይመለከታሉ። ይህ ዐይነቱ አመለካከትና ከቆንጆ ስራ እየራቁ መሄድና በራስ ዓለም ውስጥ መኖርና መሽከርከር ለጦርነትና ለአንድ ህብረተሰብ መመሰቃቀል ምክንያት ነው ይላሉ።
በሶክራተስም ሆነ በፕላቶ ዕምነት የሰው ልጅ ሁሉ ችግር የማሰብ ኃይል ችግር ወይም የዕውቀት ችግር ነው። ዕውነተኛ ዕውቀት በሶክራተስም ሆነ በፕላቶ ዕምነት ትምህርት ቤት የምንማረው ወይም ሸምድደን እንደ ዳዊት የምንደግመው አይደለም። በሁለቱም ዕምነት ሆነ ኋላ ብቅ ላሉት የአውሮፓ ፈላስፋዎችና ተመራማሪዎች፣ ዕውነተኛ ዕውቀት ማለት ራሳችንን እንድናውቅ የሚያደርገንና፣ ወደ ውስጥ ራሳችንን ለመመልከት እንድንችል የሚያደርገን፣ የበለጠ ራሳችንን እንድንጠይቅ የሚያስችለን፣ የተፈጥሮን ህግጋት ጠለቅ ብለን እንድንረዳ የሚያስችለንና፣ በጥንቃቄም በተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን ነገሮች በማውጣትና ቅርጻቸውን በመለወጥ እንድንጠቀምባቸው የሚያግዘን፣ ህብረተሰብን በስነ-ስርዓትና መልክ ባለው ሁኔታ እንድናደራጅ የሚረዳን፣ ከሰውነታችን ፍላጎት ይልቅ የመንፈስን የበላይነት በማረጋገጥ በመንፈስ ኃይል በመመራት ከሌላው ተመሳሳይ ሰው ጋር ተሳስቦ መኖር መቻል፣ በፍጹም የራስን ጥቅም በማስቀደም ዓላማ አለመመራት…ወዘተ. ናቸው። ለተንኮልና ለምቀኝነት ተገዢ አለመሆንና ወደ ብጥብጥ አለማምራትና፣ ህብረተሰብአዊ ምስቅልቅልነት እንዲፈጠር ሁኔታዎችን አለማዘጋጀት፣ የማንኛውም የሰው ልጅ ፍጡር ጥረት አርቆ በማሰብ ኃይል በመመራት ወደ እግዚአብሄር ለመጠጋት መጣር ነው። በፕላቶ ዕምነት ሌላው ለአንድ ህብረተሰብ ምስቅልቅል ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ወይም ለጦርነት ምክንያት የሚሆኑ ከሰብአዊነትና ከወንድማማችነት ይልቅ የብሄረ-ሰብ/ጎሳነት(Ethnic Solidarity) ምልክት የሆኑ ቅስቀሳዎች ቦታ ከተሰጣቸው ነው። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ለሚከሰት ችግር ዋናው ምክንያት የተለያዩ ብሄረሰቦች በመኖራቸው ወይም አንደኛው ብሄረሰብ በሌላው ላይ ጫና ስለሚያደርግ ሳይሆን፣ በስልጣን ላይ ያሉ ኃይሎች ራሳቸው በሚፈጥሩት ልዩነትና ስልጣን ላይ ለመቆየትና ህዝቡን አደንቁረው ለዘለዓለም ለመግዛት እንዲችሉ የብሄረሰብን ጥያቄ እንደ ፖለቲካ መሳሪያ አድርገው ሳይንሳዊውንና የስልጣኔውን ፈለግ ያሳስታሉ። ስለዚህም ለአንድ ህብረተሰብ ችግር ዋናው መፍትሄ እያንዳንዱ ግለሰብ ከሌላው የማይበልጥ መሆኑን ሲረዳና፣ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የተለያዩ ብሄረሰቦች መኖር የታሪካዊ ግዴታ እንጂ እንደክፋት መታየት የሌለባቸው መሆኑን ሲገነዘብ ነው። በተጨማሪም ተፈጥሮ ውስጥ የተለያዩ ነገሮች፣ ለምሳሌ የተለያዩ አበባዎች፣ የተለያዩ ዛፎችና የተለያዩ ከብቶች መኖር የተፈጥሮን ውበት እንደሚያመለክቱና የተፈጥሮም ግዴታ የሆኑትን ያህል ሁሉ፣ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥም የተለያዩ ብሄረሰቦች፣ ጥቁርና ቀይ መልክ ያለው ሰው፣ ረዥምና አጭር ሰው… ወዘተ. መኖር እንደ ውበት መታየት ያለባቸው ነገሮች ናቸው። ስለዚህም በአንድ ህብረተስብ ውስጥ የሚከሰቱ ብጥብጦች የተፈጥሮን ውስብስብነትና ውበት ለመረዳት ካለመቻልና ጠለቅ ብሎ ለማየት ካለመፈለግ የተነሳ ወይም በተሳሳተ ዕውቀት በመመራት አንድን ህብረተሰብ ለመግዛት መቻኮል ነው። ለዚሁ ሁሉ መፍትሄው ይላል ፕላቶ፣ ማንኛውም ግለሰብ አርቆ አሳቢነትን በማስቀደም በመፈቃቀር ላይ የተመሰረተ ህብረተሰብ ለመግንባት መጣር ነው። ማንኛውም ግለሰብ ይህንን የዩኒቨርስ ህግ ሲረዳና ስምምነትንና ስርዓትን(Harmony and Order) በጭንቅላቱ ውስጥ ሲቀርጽ በምድር ላይ ዕውነተኛውን ገነት ይመሰርታል።
ወደድንም ጠላንም ከብዙ ሺህ ዐመታት ጀምሮ በዓለም ላይ የተከሰቱ የርስ በርስ መተላለቆች፣ በአገሮች መሀከል የተካሄዱ ጦርነቶች፣ ረሀብና የወረርሽኝ በሽታዎች፣ በዘመነ-ሳይንስ እሰካዛሬም ድረስ ዘልቆ ብዙ የሶስተኛውን ዓለም አገሮች የሚያምሰውና የአንድ አገር ህዝብ እየተሰደደ እንዲኖር የሚያደርግና፣ ጊዜ ያመጣላቸው ኃይሎች ድንበር እየጣሱ የሌላውን አገር የሚወሩ፣ እነ ሶክራተስ ከፈለሰፉት የሰብአዊነት(Rational Humanism) ይልቅ ሳይንሳዊ አርቆ-አሳቢነትን( Scientific Rationalism) በማስቀደምና በበላይነት በመመካት ነው። ለምሳሌ ሜስትሮቪክ „The Barbarian Temperament“ በሚለው እጅግ ግሩም መጽሀፉ የሚያረጋግጠው፣ በሃያኛውና በሃያአንደኛው ክፍለ ዘመን የምዕራቡ ዓለም በሳይንስና በቴኮኖሎጂ ቢራቀቀም፣ እንዲሁም ደግሞ የሊበራል ዲሞክራሲን አስፍኛለሁ ቢልም የተወሳሰቡ የጦር መሳሪያዎች፣ የኬሚካልና የባዮሎጂ መርዞች በመስራት በሚያስፈልገው ጊዜ ጠላቴ ነው በሚለው ላይ እንደሚበትንና ብዙ ሺህ ህዝቦችን መጨረስ እንደሚችል ነው። ይህ ዐይነቱ ዕልቂት በፋሺዝም ዘመን በጉልህ የታየና የተረጋገጠ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ሁኔታ እንደገና ሊከሰት የሚችልበትም ሁኔታ አለ። በኢራቅ ህዝብ ላይ የደረሰው ግፍ፣ በየቀኑ በአፍጋኒስታንና በፓኪስታን ህዝብ ላይ የሚደርሰው፣ ከሁለት ዐመት በፊት ደግሞ አንድን አምባገነን ገዢ አዳክማለሁ ብሎ በዚያውም አሳቦ በሊቢያ ህዝብ ላይ ይወርድ የነበረው የቦንብ ውርጅብኝ የምዕራቡን ዕውነተኛ ገጽታ የሚያሳየን ነው። በተጨማሪም በእንደዚህ ዐይነቱ ቅጥ ያጣ የቦምብ ውርጅብኝ እነዚህ አገሮች እንደገና በእግራቸው ሊቆሙ ወደማይችሉብት ሁኔታ ወስጥ እየተጣሉ ነው። በጣም ከተዳከሙና ሃምሳና ስድሳ ዐመት የሰሯቸው ስራዎች፣ የገነቧቸው ከተማዎችና የመሰረቷቸው ህብረተሰቦች ከፈራረሱና ከተመሰቃቀሉ በኋላ እንደገና መልሶ ለመገንባት እጅግ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። ሰለጠንኩ የሚለውን የምዕራቡን ዓለም ተንኮል የማይረዱ የሶስተኛው ዓለም መንግስታትና አንዳንድ ነፃ አውጭ ነኝ የሚሉ ድርጅቶች የማያስፈልግ እሳት እየጫሩ መጨረሻ ላይ ማቆም የማይቻል እሳት እየሆነ በመምጣት ላይ ነው። ታላቁ ሺለር እንደሚለን፣ የሰው ልጅ ከአርስቲቶለስ ጀምሮ ዲሞክራሲ የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ ሰምቷል፤ ሆኖም ግን በመሰረቱ ከአረመኔ ባህርዩ አልተላቀቀም። ፍሪድርሽ ሺለር፣ „ታሪክ ማለት ምን ማለት ነው፣ ለምንስ ዓላማ የዓለምን ታሪክ ማጥናት አለብን“ በሚለው እጅግ ግሩም ስራው የሰውን ልጅ እጅግ አስቸጋሪ ጉዞ ከመረመርና የግሪክን ስልጣኔና የአውሮፓን የህብረተሰብ ታሪክ ካጠና በኋላ የደረሰበት ድምዳሜ፣ የሰው ልጅ ህብረተሰብአዊ ባህርይ እንዲኖረውና ታሪክን እንዲሰራ ከፈለገ የግዴታ ውጣ ውረድን ማሳለፍና ከፍተኛ የጭንቅላት ስራ መስራት እንዳለበት በጥብቅ ያሳስባል። ሺለር ይህንን ችግር ለመወጣት የሰው ልጅ ልቡን ከአእምሮው ጋር ማገናኘት እንዳለበት ያስተምረናል። ሺለር እንደዚህ ዐይነቱ ድምደማ ላይ የደረሰው በአስራስባተኛው ክፍለ-ዘመን በአውሮፓ ምድር በፕሮቲስታንና በካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎች የተለኮሰውንና ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ዕልቂት ምክንያት የሆነውን ሰላሳ ዐመት የፈጀውን ጦርነት በሰፊው ከመረመረና የመሪዎችን የተሳሳተ ፖለቲካ በጥልቀት ካጠና በኋላ ነው። በአስራአራተኛው ክፍለ-ዘመንም በጣሊያን ሰፍኖ የነበረው ሁኔታ፣ ህዝቡ እርስ በርሱ አለመተማመን፣ መተረማምስ፣ በሳይንስ ላይ የተመሰረተ አንድ ወጥ ቋንቋ አለመኖር፣ በዲያሌክት ቋንቋ መብዛት አለመግባባትና ለስልጣኔ በአንድነት አለመነሳት፣ በዘመኑ በአሪስቶክራቲክ መሪዎች መባለግና በካቶሊክ ሃይማኖት ጭፍነነት ሰፊውን ህዝብ ማደንቆርና የተፈጥሮን ህግ ተረድቶ ችግሩን እንዳይወጣ ማድረግ፣ በተስቦ በሽታ እንዲያልቅ ማድረግ አንድ ህዝብ በጨለማ አስተሳሰብ ወይም በጭፍን ርዕዮተ-ዓለም የተመራ እንደሆን ብቻ ነው። የዳንቴ የአምላኮች ኮሜዲ ትልቁ የሌትሬቸር ስራ የሚያስተምረን፣ አንድን ህዝብ ከጨለማ ጉዞ ወደ ብርሃን ለማውጣትና የስልጣኔውን ቁልፍ ለማስያዝ የህብረተሰብን ችግር በጥልቀት መረዳት ያስፈልጋል። አንድ ህዝብ ጭንቅላቱ ዕውነተኛ የዕውቀት ብርሃን እንዲፈናጠቅበትና የራሱን ዕድል ራሱ ወሳኝ መሆኑን እንዲያውቅ ማድረግ ያስፈልጋል። ሬናሳንስ የሚባለው የግሪኩን ዕውቀት እንደገና ማግኘት የተጀመረው እነዳንቴ በቀደዱት የብርሃን መንገድ አማካይነት ነው።
እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ እያንዳንዱ ግለሰብ በተለይም አገርን አስተዳድራለሁ የሚል እንዴት አድርጎ ስምምነትንና ስርዓትን በጭንቅላቱ ውስጥ ሊቀርጽ ይችላል? እንዴትስ ቆንጆ አስተሳሰብ ከጭንቅላቱ ጋር በማዋሃድ የራሱን ጥቅም ሳያስቀድምና ከአለአድልዎ፣ እንዲሁም የርዕዮተ-ዓለም ሰለባ ሳይሆን አገር ማስተዳደር ይችላል? እንዴትስ ለስልጣኔና ለቆንጆ ስራዎች ታጥቆ ይነሳል? የሚሉትን ጥያቄዎች በዝርዝር እንመልከት።
በብዙዎቻችን ዕምነት ትምህርት ቤት የተማረና ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ኢኮኖሚክስም ሆነ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት አጠናቆ በማስትሬት ወይም በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቀ አገር ማስተዳደርና፣ አገርን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በማድረግና ሚዛናዊ ዕድገት በማምጣት በስልጣኔ እንድትታወቅና ህዝቦቿም በደስታና በስምምነት እንዲኖሩ ሊያደርግ የሚችል ይመስለን ይሆናል። የሶክራተስን፣ የፕላቶንና፣ እንዲሁም በኋላ የተነሱትን ታላላቅ ሃይማኖትን ከፍልስፍና ጋር በማጣመር በአውሮፓ ምድር ስልጣኔ እንደገና እንዲያንሰራራ ያደረጉትን የታላላቅ ቀሳውስት ስራዎች ስንመለከት፣ እንዲሁም ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን በኋላ ብቅ ብቅ ያሉትን ሳይንቲስቶችንና ለሰው ልጅ ያስተላለፉትን ዕውቀት ስንመረምር፣ በግጥምና በቲያትር እንዲሁም በፍልስፍና የፖለቲካ ተዋንያንን አእምሮ ለመቀረጽ የታገሉትን እንደ ሺለር፣ ላይብኒዝና ካንት እንዲሁም ጎተን ስራዎች ስንመለከት እኛ ትምህርት ቤት ገብተን የተማርነው ትምህርት ላይ ከጠቀስኳቸው አዋቂዎች፣ ካፈለቋቸው ዕውቀት ጋር በፍጹም አይጣጣሙም። ከነዚህ ታላላቅ የፍልስፍና ምሁራንና ሳይንቲስት ጽሁፎች መገንዘብ የምንችለው የቱን ያህል የሰው ልጅ አእምሮ ውስጥ ገብተው መመርመር እንደቻሉና ካለ አእምሮ ምንም ነገር መደረግ እንደማይችል የደረሱብት የምርምር ውጤት።
የማንኛውም ልጅ አእምሮ/መንፈስ እንደየሁኔታው ጥሩም ሆነ መጥፎ ሆኖ ሊገነባ ይችላል። በጥሩ ዕውቀት ሊገነባ ወይም ደግሞ በተበላሸና ገለብ ገለብ ባለ ትምህርት በመበከል ለተዛባና ለምስቅልቅል ሁኔታ መንገድን እንደሚያመቻች መገንዘብ እንችላለን። ለዚህም ነው እነ ሶክራተስም ሆነ ከሁለት ሺህ ዐመት በኋላ ደግሞ እነ ሺለር ለአእምሮ/መንፈስ ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ትግል ያደረጉት። ስለሆነም ማንኛውም ሰው ከህጻንነቱ ጀምሮ ከጥሩ ዕውቀት ጋር ማደግ ካልቻለ፣ አስተሳሰቡ ቀና ሆኖ ካልተቀረጸ፣ በተለይም አድልዎ የበዛበት፣ ከቆንጆ ስራ ይልቅ ቆሻሻና የተዝረከረከ አሰራር እንደባህል ተደርጎ በሚወሰድበት ህብረተሰብ ውስጥ ተወልዶ ያደገ ህጻን ትምህርት ቤት ከገባ በኋላ ደግሞ በጥሩ ዕውቀት ተኮትኩቶ ካላደገ ስራው ሁሉ ተንኮልና ጥፋት ይሆናል። ጥሩ ትምህርት ከፍተኛ ሚና ቢኖረውም ለአንድ ልጅ አስተሳሰብ ዕድገት ቤተሰብና አካባቢም ከፈተኛ ሚናን እንደሚጫወቱ የተረጋገጠ ነው። እንደሚባለው ማንኛውም ሰው የቤተሰቡና የአካባቢው ግልባጭ ነው። መንፈሱ ተረብሾ ያደገ፣ ከመጀመሪያውኑ በተንኮል ጭንቅላቱ የተወጠረ፣ እየሸመደደ በጣም ጥሩ ውጤት ቢያመጣም ይህ ማለት ስልጣኔ ገብቶታል ማለት አይደለም፤ ለስልጣኔና ለእኩልነት ሽንጡን ገትሮ ይታገላል ማለት አይደለም። የዕውነት ጠበቃ ይሆናል ማለት አይደለም። ስለሆነም አንድ ሰው በዚህ ወይም በዚያኛው ርዕዮተ-ዓለም እመራለሁ ቢልም ይህ ማለት ቀናና ጥሩ ሰው፣ እንዲሁም ከተንኮል የጸዳ ነው ማለት አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ርዕዮተ-ዓለም ሽፋን እንጂ የአንድን ሰው ምንነት መግልጫ አይደለም። አንድ ሰው ማርክሲስት ነኝ ወይም ሊበራል ነኝ ወይም ደግሞ ይህንኛውን ወይም ያኛውን የፖለቲካ ዕምነትና ሃይማኖት እከተላለሁ ቢልም እነዚህ ሽፋኖች ድብቅ ዓላማውን የሚገልጹ ወይም ማንነቱን የሚያሳዩ አይደሉም። ወይም አንድ ሰው ሊበራል ነኝ ስላለ የተቀደሰ ዓላማ፣ ማርክሲስት ነኝ የሚለው ደግሞ የሰይጣን ዓላማ አላቸው ማለት አይደለም። እነዚህ ዐይነቱ ግለሰቦች በተናጠልም ሆነ በፓርቲ ደረጃ ተደራጀተው ለዚህ ወይም ለዚያኛው ርዕዮተ-ዓለም እንታገላለን ቢሉም የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ተግባራዊ ለማድረግ የሚታገሉባቸው መሳሪያዎች እንጂ በራሳቸው ዕውነተኛ ስልጣኔ አጎናጻፊ አይደሉም። እንዲያውም የዕውነተኛውን የስልጣኔ መንገድ የሚያደናቅፉና ወደ ሌላ ውዝግብ ውስጥ የሚከቱን ናቸው። ዛሬ በንጹህ የካፒታሊዝም ሊበራል ስርዓት ውስጥ እያለን እንኳ ዓለም ወደ ሰላም እያመራች አይደለችም፤ እንደምናየው የዓለም ህዝብም ብልጽግናን እያየ አይደለም። ጦርነትና ድህነት በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ የሀብት ዘረፋን ማከማቸት የሰው ልጅ እጣ ሆኗል ማለት ይቻላል።
ከዚህ አጭር ትንተናና በመነሳት ከአስራ ሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአሽናፊነት የወጣውን የካፒታሊዝምን ፕሮጀክት ወደ ኋላ በመተው በብዙ የአውሮፓና የአፍሪካ አገሮች በስልጣኔ ልዩነት ሊመጣ የቻለው የላይኛውን አጠር ያለ ሀተታ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባን እንደሆን ብቻ ነው። ከእስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን አንስቶ ካፒታሊዝም የበላይነት እየተቀዳጀ ሲመጣ ደግሞ የስልጣኔው ፕሮጀክት እየተደመሰሰና የዓለም አቀፍ ህብረተሰብ፣ በተለይም የአፍሪካ ሁኔታ እየተበላሽና እየተዘበራረቀ ይመጣል። የካፒታሊዝም ተልዕኮ ስልጣኔ መሆኑ ቀርቶ በጉልበት ላይና በስግብግብነት እንዲሁም በማጭበርበር ላይ በመመርኮዝ ብዙ የሶስተኛውን ዓለም አገሮች መቀመቅ ውስጥ ይከታቸዋል። ህብረተሰቦች በጤናማ መሰረት ላይ እንዲገነቡ ከማድረግ ይልቅ መንግስታትን በልዩ መሳሪያ በማስታጠቅና በማማከር ወደ መፋለሚያ መድረክ ይቀይራቸዋል። በተለይም ከሁለተኛው ዓለም መፈጸሚያ በኋላ ሙሉ በሙሉ በአሽናፊነት የወጣው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ተልዕኮው ህብረተሰቦችን ማዘበራረቅና በህብረተሰቦች ውስጥ ግጭት እንዲፈጠር ሁኔታውን ማመቻቸት ሆነ ተግባሩ። ለዚህ ደግሞ የትምህርት መስኩ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል። የአንድን ሰው አእምሮ ስትቆጣጠረውና በገንዘብ ስትገዛው የህብረተሰቡንም አቅጣጫ ታዛንፋለህ። የስልጣኔውን መንገድ ሁሉ ታጨልማለህ። አብዛኛው ህዝብ የማሰብ ኃይሉ ሲዳከም በቀላሉ ወደ ባርነት ትለውጠዋለህ። የዓለም ገበያና የዓለም ንግድ እንዲሁም ለዚህ እንዲያመች ተብሎ የረቀቀው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ዋናው ዓላማቸው የብዙ አፍሪካ ህዝቦችን ዕድል በዚህ ዐይነት የካፒታሊስት ሎጂክ ውስጥ እንዲሽከረከሩ በማድረግ ለዝንተዓለም ባርያ አድርጎ ማስቀረት ነው። ለምሳሌ ለትምህርት ቤትና ለዩኒቨርሲቲ ተብሎ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተዘጋጀውን የኤኮኖሚክስ መማሪያ መጽሀፎች ለተመለከተ፣ እንደዚህ ዐይነቱ ተቀባይነት ያገኘ(Conventionalism or normative positivism) የመማሪያ መጽሀፍ በራሱ አርቀን እንዳናስብና የዕውነተኛን ስልጣኔን ትርጉም እንዳንረዳ ሊያደርገን በቅቷል። ዕድገትንና ስልጣኔን ከህብረተሰብ አወቃቀርና ከታሪክ አንፃር እንዲሁም የተለያዩ አገሮችን ልምድ መሰረት አድርጎ እንደመነሻና እንደመማሪያ ከመወሰድ ይልቅ፣ ርዕዮተ-ዓለምንና የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍል ጥቅሞችን የሚያንፀባርቅ ትምህርት በመማር የታሪክ ወንጀል ተሰራ፤ እየተሰራም ነው። የሳይንስና የቴክኖሎጂን ዕድገት ስንመለከት ግን ንፁህ የምርምርና የጭንቅላት ውጤት መሆናቸውን መገንዘብ እንችላለን። ኢኮኖሚክስ ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ከፊዚክስ፣ ከኬሚስትሪና ከባዮሎጂ ጋር ሲያያዝ ብቻ ነው። ይህንን መሰረተ-ሃሳብ ያላካተተ የኢኮኖሚክስ ትምህርት የመጨረሻ መጨረሻ አገሮችን መቀመቅ ውስጥ ነው የሚከታቸው። ለምሳሌ በኢኮኖሚክስ ታሪክ ውስጥ መርካንትሊዝም፣ ፊዚዮክራሲ፣ በእነ አዳም ስሚዝና ፔቲ ኢንዲሁም ሪካርዶ የሚወከለው ክላሲካል ኢኮኖሚክስ፣ ይህንን እያረመ ወይም እያስተካከለ የወጣው የማርክሲስት ኢኮኖሚክስ፣ ከዚያ በኋላ ማርክሲዝምን በመቃወም የወጣው የማርጂናሊስት ወይም የኒዎ-ክላሲክል፣ ዛሬ ደግሞ ኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ተብሎ የሚታወቀው፣ በእነ ሹምፔተር የሚወከለው ኢቮሉሺናሪ ኢኮኖሚክስ፣ በቬብለን ቶርስታይን የሚወከለው የኢንስቲቱሽን ኢኮኖሚክስ፣ ብዙ የምዕራብ አውሮፓ ኢኮኖሚዎች የተገነቡበት፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ፊዚካል ኢኮኖሚክስ እየተባለ የሚታወቅ በጣም ጠቃሚ ዕውቀት፣ እነዚህ ሁሉ የኢኮኖሚክስ ዘርፎች ናቸው። ተማሪው ይህንን ሁሉ እንዳያውቅና፣ በተለይም ምዕራብ አውሮፓ የአደገበትን ምስጢር እንዳይገነዘብ በሃያኛው ክፍል-ዘመን በእነሳሙኤልሰንና በሌሎች የተደረሱት እንደ መማሪያና ሌላ አማራጭ የሌለ ይመስል፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠር የአፍሪካ ምሁራን ሊሳሳቱና ለየአገራቸው ድህነት እንደ ዋና ምክንያት ሊሆን ችሏል። ኒዎ-ሊበራሎች የበላይነትን በመቀዳጀት ከዩኒቨርሲቲ አልፈው ኢንስቲቱሽኖችን ሁሉ በመቆጣጠር አብዛኛው ተማሪ ዐይኑን እንዳይከፍትና የዕውነተኛ ዕድገትንና ስልጣኔ ትርጉም እንዳይረዳ ሆኗል። ለዚህም ነው ሶክራተስ፣ ፕላቶና የእነሱን ፈለግ ይዘው የተነሱ ምሁራን ተቀባይነት ያገኘን ዕውቀት መሳይ ነገር አጥብቀው የታገሉት። ምክንያቱም ተቀባይነት ያገኘ ነገር ሁሉ ካለንበት ቦታ ርቀን እንዳንሄድ ያደርገናል። በማሰብ ኃይልና በኮመን ሴንስ ልንፈታ የምንችላቸውን ችግሮች እንዳንፈታ መንገዱን ሁሉ ይዘጋብናልና።
ወደ አገራችንና ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ችግር ስንመጣና ሁኔታውን ለመረዳት ስንጥር የግዴታ የላይኛውን ትንተና ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት አለብን። የኛንም ሆነ የሌሎች አፍሪካ አገሮችን የተወሳሰበ ችግር ስንመረምር አውሮፓውያን እስከ አስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የተጓዙበትን የምሁር ውይይትና ምርምር እንደልምድና ትምህርት አድርገው ሊወስዱ አልቻሉም። ይህ ችግር ከምን የመነጨ ነው? አንደኛ የብዙ አፍሪካ አገሮች ህብረተሰብ አወቃቀር ከብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ጋር ሲነፃፀር ይለያል። ብዙ የአፍሪካ ህብረተሰቦች ከሌላው ዓለም ጋር የነበራቸው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ግኑኝነት እጅግ የላላ ነበር። ለምሳሌ የግሪክ ስልጣኔ በአረቦችና በአይሁዲዎች አማካይነት ከግሪክ ቋንቋ ወደ ላቲን እየተተረጎመ ወደ አውሮፓ ሲገባና ሲስፋፋ፣ ብዙ አፍሪካ አገሮች ይህ ዕድል አላጋጠማቸውም። ሁለተኛ፣ የብዙ ምዕራብ አውሮፓ የሀብረተሰብ አወቃቀር በሩቅ ንግድ አማካይነት ሲሸረሸርና ውስጠ-ኃይል በማግኘት ወደ ተሻለ የህብረተሰብ አወቃቃር ሲሸጋገር፣ አብዛኛዎቹ አፍሪካ አገሮች ይህ ዐይነቱ ዕድል አላጋጠማቸውም። በአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን በባሪያ ንግድና በአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ በቅኝ አገዛዝ አማካይነት ህብረተሰብአዊ አወቃቀራቸው ይበላሻል። በማበብ ላይ የነበረው የስራ ክፍፍል ይኮላሻል። አብዛኛዎቹ አፍሪካ አገሮች ለምዕራብ አውሮፓ ጥሬ-ሀብት አቅራቢ ብቻ እንዲሆኑ ይፈረድባቸዋል። ለዚህም የየመንግስታቱ አወቃቀር ወደ ውስጥ ዕድገትንና ስልጣኔን እንዳያመጣ ሆኖ ይዘጋጃል። ከቅኝ አገዛዝ መላቀቅ በኋላ በዓለም አቀፍ ላይ አዲስ የተፈጠረው የኃይል አሰላለፍ የአፍሪካን ዕድገት የሚጻረር ይሆናል። በአውሮፓው ምድር ፍጻሜ ያገኘው ጦርነት ወደ አፍሪካና ወደ ሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ይሸጋገራል። አውሮፓውያን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ሲበለጽጉ አፍሪካ በጦርነት መድማት አለባት፤ ህዝቦቿም የሰከነና የሰለጠነ ኑሮ መኖር የለባቸውም፤ መዋከብና መበዝበዝ ዕጣቸው መሆን አለብት። ለዚህ ደግሞ ፍልስፍና አልባ የሆኑ መሪዎች እንደ አሻንጉሊት በየቦታው ተቀመጠዋል። በተዋቀራላቸው የስለላ መሳሪያ፣ በሰለጠነላቸው ወታደርና የፖሊስ ሰራዊት አማካይነት ማንኛውንም ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ማፈንና ብልጽግና እንዳይመጣ ማድረግ አለባቸው። በአገራችንና በሌሎች አፍሪካ አገሮች የተቋቋሙት የወታደር ተቋሞች፣ የስለላ መዋቅሮችና የፖሊስ ሰራዊት በመሰረቱ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረውን ኃይል አሰላለፍ የሚያንፀባርቁና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘረጋውን የአገዛዝ ሰንሰለት አጋዦችና ታዛዦች እንጂ ከየህብረተሰቦቻቸው ፍላጎት ከታች ወደ ላይ ቀስ በቀስ እየተደራጁና ሲቪክ የሆነ ባህርይ እንዲኖራቸው ሆነው የሰለጠኑ አይደሉም። በዚህም ምክንያት በብዙ የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያንም ጨምሮ የሲቪልና የወታደሩ ቢሮክራቶች እጅግ አረመኔና ህብረተስብአቸውን ለውጭ ኃይል አሳልፈው እንዲሰጡ የተዘጋጁ ነው የሚመስሉት።
በዘመነ-ግሎባላይዜሽን ሁኔታው ምስቅልቅልና ለብዙ ምሁራንና የፖለቲካ ተዋናዮች ግልጽ ያልሆነ ሁኔታ የተፈጠረበት ዘመነ ነው። ዛሬ በብዙ የአፍሪካ አገሮች አምባገነንነት ሰፍኗል፤ ዲሞክራሲ የለም እየተባለ የሚለፈፈውና የሚወደሰው ይህንን ውስብስቡን የዓለም ሁኔታ ለመመርመር ካለመቻል የተነሳ ነው። የብዙ የአፍሪካ አገሮች ችግር ፕላቶ እንደሚለን ዕውነትን ከውሸት ለመለየት የሚያስችል ዕውቀት ለመስፋፋት አለመቻሉና፣ ዕውነተኛ ሁለ-ገብ የሆነ ምሁራዊ እንቅስቃሴ አለመኖሩ ነው። ሰፋ ያለ የዳበረ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በሌለበት አገር የውጭ ኃይሎች ከውስጡ ኃይል ጋር በማበር የጨለማውን ዘመን ያራዝማሉ። የጭቆና መሳሪያዎች እየላኩና እያስታጠቁ የጸጥታ ኃይል በሚሉት አማካይነት አንድ ህብረተሰብ ተዋክቦ እንዲኖር ያደርጋሉ። ህብረተሰቦች ታሪክ የሚሰራባቸው፣ ህዝብ ተራጋግቶ እንዲኖር ነገሮች በስነስራዓት ከሚዘጋጅባቸው ይልቅ ወደጦርነት አውድማ መቀየር አለባቸው። ዕውነተኛ ህብረተስብአዊ ሀብትን በማይፈጥር በተራ ሽቀጣ ሸቀጥ አማካይነት ህብረተሰብን ማዋከቡ በከፍተኛ ፍጥነት መካሄድ አለበት። እንደ አገራችን ባሉት ደግሞ ከሌሎች ነገሮች ጋር ተደምሮ የኮሞዲቲ ገበያ የሚባል በማቋቋም ሰፊው ገበሬ አመለካከቱን ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲያዞር በማድረግ ለዓለም ገበያ የቡናና የሰሊጥ ምርት አቅራቢ፣ ለውስጥ ጌቶች ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆን ተደርጓል። በዶክተር ኤልኒ ገብረመድህን የተቋቋመውና በሷ ይመራ የነበረው የኮሞዲቲ ገበያ ዋና ዓላማው ኢትዮጵያ ውስጥ የተስተካከለ ዕድገትና ዕውነተኛ ስልጣኔ እንዳይመጣ ማድረግ ነው። ይህ በግሎባልይዜሽን ዘመን ንቃተ-ህሊናቸው የደከሙ ህብረተሰቦችን እየፈለጉ፣ በኒዎ-ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም የሰለጠኑ እንደዚህ ዓይነት ተውረግራጊዎችን እየፈለጉና እያሰለጠኑ በአንድ በኩል ህብረተሰቦች ርካሽና የቆሻሻ ፍጆታ ዕቃ መጣያ ሆነዋል፤ በሌላ ወገን ደግሞ አብዛኛው ህዝብ ብዙ ቀናትና ወራት የለፋበትን የቡናም ሆነ የሰሊጥ ምርት በርካሽ ዋጋ እንዲሸጥ በመገደድ ወደ ባርነት እንዲለወጥ ተደርጓል። እንደዚህች ያለች አገራችንን በግሎባላይዜሽን መዳፍ ስር ወድቃ እንድትታሽ የምታደርግና ለህዝባችን የበለጠ ደሀ መሆን ተጠያቂ ከሆኑት አንዷ፣ በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ድህረ-ገጽ አዘጋጆችና ግለሰቦች ስትወደስና የዐመቱ ምርጥ ሰው እስከመባል ካለማወቅ ዝናን ለማግኘት በቅታለች። ብዙዎቹ ሳያውቁት የድህነት ፍልፈላው አጋዥ ሆነዋል። አንድ ሰሞን ናዝሬት ድህረ-ገጽ አንድ ጽሁፍ አቅርባ ወደ አራት መቶ የሚሆን ደብዳቤ ተጽፎላታል። አባዛኛው የሚያሞግሳት ነበር። በዚህ መልክ ባለፈው ሃያ ዓመት በህብረተሰብአችን ውስጥ አዲስ ድህነትን ፈልፋይና የአገራችንን አቅጣጫና ዕድገቷን ያጣመመ እጅግ አደገኛ የህብረተሰብ ክፍል ብቅ ሊል ችሏል። ይህ የህብረተሰብ ክፍል በዓለም አቀፍ ደረጃ በተዋቀረው የፊናንስ መረብ ውስጥ በመከተት በካፒታሊስት አገሮች የሚካሂደውን የሀብት ክምችት(Capital Accumulation) አጋዥ ሆኗል። ወደ ውስጥ ደግሞ የህብረተሰቡን ሀብት በመምጠጥና የተንደላቀቀ ኑሮ በመኖር ለከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ምክንያት ሆኗል። በራሱ ዓለም ውስጥ የሚኖር፣ ዐይን ያወጣና ህብረተሰቡም ወደ ጥፋት እያመራ ማየት የማይችልና፣ ማየት ባይችል እንኳ ደንታ የሌለው የህብረተሰብ ክፍል ነው። ፍልስፍና አልባ የሆነና ህብረተስብአዊ ኖርሞችን መከተል የማይችል፣ ወይም ህብረተሰቡ በተወሰነ ኖርሞች ላይ እንዲተዳደር ማድረግ የማይችል ከሰፊው ኢትዮጵያ ህዝብ ተነጥሎ የሚኖር፣ የራሱ መዝናኛ ቦታና ልዩ የመገበያያ ቦታ(Shoping Center) ያለው ነው። በዚህ መልክ ብቻ ነው የዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም ብዙ የሶስተኛውን ዓለም አገሮች የሚቆጣጠረውና ለመቆጣጠር የሚችለው።
ዛሬ በአገራችን ምድር የሰፈነውን ፍልስፍና አልባ ፖለቲካና ህዝብን ማዋከብ ከዚህ ቀላል ሁኔታ በመነሳት ነው መመርመር መቻል ያለብን። በቀላል የሊበራል ዲሞክራሲና የነፃ ገበያ ፎርሙላ የህብረተሰብአችንን የተወሳሰበ ችግር ለመገንዘብ አንችልም። የአገዛዙ ችግር የፖለቲካ ፍልስፍና አልባነት ችግር ነው ስል ምን ማለቴ ነው? በመጀመሪያ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር አለ። ይኸውም ወያኔ/ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ውስጥ የፈለቀና የፊዩዳሊዝምና እጅግ የተዘበራረቀው ካፒታሊዝም፣ አባዛኛውን በአርባዎቹ መጨረሻና በሃምሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ከአዋቂነትና ከብልህነት፣ ከጥበብና ከቆንጆ ቆንጆ ስራዎች ይልቅ ተንኮለኛ፣ ዳተኛና አራዳ እንዲሁም አገር ከፋፋይ አድርጎ ያወጣቸው ውጤቶች ናቸው። ከሰማይ የመጡ ወይም ከሌላ አገር የመጡ አይደሉም። ምናልባት የዛሬዎቹ አቶ መለስ ከመሞታቸው በፊት ይመሯወቸው የነበሩ ግለሰቦችና አሁንም በስልጣን ላይ ያሉት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ሲነፃፀሩ ልዩ የሚያደርጋቸው በተወለዱበት አካባቢ ካፒታሊዝም ከአዲስ አበባና ከአንዳንድ ክፍለ-ሀገሮች ጋር ሲወዳደር ሰርጎ ባለመግባቱ ትንሽም ቢሆን የኮስሞፐለቲካን ባህርይ ሊያድርባቸው ባለመቻሉ ብቻ ነው። በአስተሳሰባቸው አንድ ወጥና ድርቅ ማለት፣ በምንም ዐይነት ለሰው ልጅ አለማሰብ፣ ወይም ህብረተሰብአዊ ፍቅር አለመኖር፣ አሁንም ቢሆን ጦርነትንና ድንፋታን ማስቀደም፣ ሶክራተስና ፓላቶ እንዳሉት ከህዝባዊ ስነ-ምግባርነት(Civic Virtue) ይልቅ፣ ህብረተሰቡን ማመሰቃቀል፣ ታዳጊው ትውልድ ኃላፊነት እንዳይኖረው ማድረግና ቀማኛ እንዲሆን ሁኔታውን ማመቻቸት፣ ከፋፋይነትና ለውጭ ኃይሎች ሰጥ ለጥ ብሎ መገዛትና፣ ይህንን እንደትልቅ ፈሊጥ አድርጎ መያዝ፣ ይህ ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ሲወዳደሩ ልዩ ሊያስመስላቸው ይችል ይሆናል፤ ነውም። በአንዳንድ ነገሮች ከቀደመው የኃይለስላሴና የደርግ አገዛዝ ቢሮክራቶች የሚመመሳሰሉበት ሁኔታ ደግሞም አለ። ይኸውም ብሄራዊ ባህርይ ማጣት፣ በተለይም ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሰጥ ለጥ ብሎ ማጎብደድ፣ ወይም አሜሪካንን እንደ አምላክ ማየትና አገርን መካድና የአገርን ምስጢር አሳልፎ መስጠት፣ ሰፊውን ህዝብ መናቅና ተንኮሎኝነት፣ በዚህ የሚመሳሰሉ ናቸው። ይህንን በጭንቅላታችን ውስጥ ስንቋጥር ነው የነገሮችን ሂደት መገንዘብ የምንችለው። ዝም ብሎ ግን አገዛዙ ለኢትዮጵያ አጀንዳ የለውም፤ ማርክሲስት ነው፤ የአልባንያውን ዐይነት ሶሻሊዝም ነው የሚያካሂደው፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ነው የሚያራምደው፤ ህገ-መንግስቱ ስታሊንስታዊ ነው፤ የሚሉት አነጋገሮች በዕውነቱ አይ የህብረተሰብእችንን ስርዓትና የህሊና አወቃቀር እንዲሁም ደግሞ የታሪክን ሂደት ለመረዳት ካለመፈለግ ወይም ህብረተሰብአዊ አወቃቀሮች በሰው ልጅ አስተሳሰብ ላይ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ ባለመገንዘብ የሚሰነዘሩ ታሪክን ሊያሰሩ የሚችሉ ከትንተና ዘዴዎች በመነሳት አይደለም የአገዛዙን ምንነት ለመረዳት ጥረት የሚደረገው። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ተንታኝ ከራሱ ስሜት በመነሳት እንጂ አንዳች ፍልስፍናንና ስልትን(Methodology) በመከተል አይደለም ለመተንተን የሚሞክረው። እንደዚህ ዐይነቱ በአንዳች ፍልስፍናና ስልት ላይ ያለተደገፈ አቀራርብ ደግሞ የችግሩን ዋና ምንጭ እንዳንረዳ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ፍቱንና ህብረተሰብአችንን ሊያረጋጋና ወደስልጣኔ ሊያመራው የሚያስችል መፍትሄ እንዳንሰጥ ያደርገናል። ለመጻፍ ተብሎ የሚጻፍ፣ ወይም ደግሞ ቁጭትን ለመወጣት ተብሎ የሚጻፍ ነገር የለም። በብዙዎች የሚቀርበው ሁኔታዎችን በደንብ ያላገናዘበ አቀራረብና የፖለቲካ ስሌት በፍልስፍና፣ በሳይኮሎጂና በህሊና ሳይንስ የሚደገፍ አይደለም። የአንድን ቡድን ወይም ግለሰብ ድርጊት ልንገነዘብ የምንችለው ከላይ የተቀመጡትን መሰረተ-ሃሳቦች ከቁጥር ውስጥ ያስገባን እንደሆን ብቻ ነው።
የሁለቱ ቀደም ብለው የነበሩትን አገዛዞች ትተን የዛሬው የወያኔ/የኢህአዴግ አገዛዝ የፖለቲካ ስልጣንን ሲጨብጥ ሜዳው ክፍት ነበረለት። ማንም የሚቋቋመው ሲያጣ ፍቅርና ሰላምን ከማስቀደም ይልቅ እንደልቤ መፈንጫ አገኘሁ በማለት ህብረተሰቡን ማዋከብ የፖለቲካው ዘዬ አድርጎ ተያያዘው። የህበረተሰቡን ሀብት በመንጠቅና ጥቂቶችንም በማባለግ እያበጠ መምጣት ጀመረ። ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ዕርዳታ ሲፈስለት እኔነኝ ብቸኛው ኃይል በማለት በግሎባላይዜሽን ጉያ ስር በመውደቅና በመታሸት የህብረተሰቡን ችግር ውስብስብ አደረገ። አቶ መለስ ከመሞታቸው በፊትና ስልጣን ላይ 20 ዐመታት ያህል በቆዩበት ዘመን፣ ልክ ሶክራተስ ፐሪክለስን እንደወነጀለው፣ ሰነፍ፣ ለፍላፊ፣ አጭበርባሪ፣ አገር ሻጭና ከሃዲ፣ በዝሙት ዓለም ውስጥ የሚዋኝ፣ ዕውነትን ከመፈለግ ይልቅ ለውሸት ጠበቃ የቆመ ትውልድ፣ በግልጽ የሚታዩ ነገሮችን የሚክድና፣ ተቀባይ ሲያጣ ደግሞ ጠበንጃ የሚሰነዝር ትውልድ ለማፍራት በቅተዋል። ይሁንና ግን አቶ መለስ ከፕሪክለስ ጋር ሊወዳደሩ የሚችሉ መሪ አልነበሩም።ፐሪክለስ በሌሎች የግሪክ ግዛቶች ላይ የአቴንን የበላይነት ለማስፈን የታገለና በአቴን ስልጣኔ የሚኮራ ነበር። በአቶ መለስ ይመራ የነበረው የወያኔ አገዛዝ ግን „ከአሜሪካን ጋር እየተመካከርን ነው የምንሰራው“ በማለት የበታችነቱን የሚያረጋግጥና ለስልጣኔ ጠንቅ የሆነ አገዛዝ ነበር፤ ነውም። የዓለም የገንዘብ ድርጅትንና የዓለም ባንክን የኒዎ-ሊበራል አንጀት አጥብቅ የሞኔተሪ ፖሊሲ በመከተልና በዚህ በመዝናናት ድህነትን የፈለፈለ ነው። የዚህ ሁሉ ምንጭ በስልጣን መታወርና ማንአለብኝ ብሎ እየተመጻደቁ መኖር ነው። በዚህ ዐይነት በውሸት ላይ በተመሰረተ አገዛዝ ግን ደግሞ ነገ እንደዱቄት የሚበንና ህብረተሰቡን ለሌላ ችግር አጋፍጦ በሚሄድ አገዛዝ አማካይነት ህዝባችን ሞራሉ እንዲዳሽቅ ሆኗል። ዕውነተኛ ፍቅር ከልቡ ተደምስሶ ጠፍቷል። ደስታ ምን እንደሆነ እንዳያውቅ ተደርጓል። በሀዘን ዓለም ውስጥ እንዲኖር ተፈርዶበታል። ግራ የገባው፣ ለምን እንደሚኖርና ወዴት እንደሚጓዝ የሚያውቅ አይደለም። ለማኝ እንዲሆን ተደርጓል። በራሱ ላይ ዕምነት እንዲያጣ ሆኗል። ተፈጥሮአዊ ነፃነቱን ተገፏል። ወጣት ልጆቹን ለውጭ ከበርቴዎች ካለ ዕድሜያቸው ለጋሽ እንዲሆን ተደርጓል። ብሄራዊ ነፃነታችን ተገፏል። በአንድ በኩል አሽረሽ ምችው፣ በሌላው ወገን ደግሞ ተስፋ መቁረጥና መዘናጋት የህብረተሰብአችን ልዩ ባህርይ ሆነዋል።
ከዚህ የተወሳሰበና አገርን ለማውደም ከተቃረበ ችግር እንዴት እንወጣለን ? የሚለው ነው ዋናው ጥያቄያችንና መመለስ ያለብን ተግባር። በተራ የነፃ ገበያና የሊበራል ዲሞክራሲ ፎርሙላ ወይስ አስቸጋሪ በሆነው ግን ደግሞ ፍቱን በሆነው በሬናሳንስ ፍልስፍና አማካይነት ነው የተወሳሰበውን የህብረተስብአችንን ችግር ልንፈታ የምንችለው። በእኔ ዕምነት ተራ የሊበራል ዲሞክራሲና የነፃ ገበያ ፎርሙላዎች ለኛ ብቻ ሳይሆኑ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ችግር በፍጹም መፍትሄ ሊሆኑ አይችልም። መፍትሄው የመንፈስን የበላይነት የሚያስቀድመውን የሬናሳንስን የሁለ-ገብ የህብረተሰብን ችግር መፍቻ ስልት የተከተለን እንደሆን ብቻ ነው። እኛ ብቻ ሳንሆን ዛሬ የተቀረው የዓለም ህዝብ የሚመኘው የመንፈስን የበላይነት የሚያስቀድምና የኑሮን ትርጉም እንድንረዳ የሚያደርገንን መንገድ ነው። ከየት እንደመጣን፣ በዚህ ዓለም ላይ ለምን እንደምንኖርና፣ ምንስ ማድረግ እንዳለብንና ወዴትስ እንደምናመራ የተገነዘብን እንደሆን ብቻ ተቀራራቢ መፍትሄ መስጠት የምንችለው። ለዚህ ሁሉ መፍትሄውም የፒታጎራስን፣ የሶክራተስንና የፕላቶንን ወንድማዊ ወይም የእህትማማች ፍቅር እንደመመሪያ አድርገን የወሰድን እንደሆን ብቻ ነው። ይህ ፍቅር ግን በዕውቀት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ምሁራዊ ፍቅር ማለት ነው። ዕውነትን ለመፈለግ የሚረዳንና ሶፊስታዊውን የመሙለጭለጭ መንገድ አሽቀንጥረን የሚያስጥለን መሆን አለበት። በሃሳብ እንድንገናኝ የሚያደርገንና፣ ራሳችንን አውቀንና ለውጠን ህብረተሰብአችንን ከገባበት ማጥ ውስጥ እንዲወጣ የሚያስችለው ፍልስፍናና መመሪያ መሆን አለበት።
ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
fekadubekele@gmx.de
Nyala says
Dr. Fekadu, this is Messianic! This certainly illuminates how contemporary Ethiopians should have sailed to reach our destination. What lies around us as proximate stuff is pretty insignificant compared to what lies within us.