
በወያኔ ዘመን በህወሃት ቀንበር
ያሳለፍነው ህይወት የጠጣነው አረር
እንዴት እንደሆነ እንዴት እንደነበር
ጠበቃ ከማቆም እማኝ ከመደርደር
ይኸው የኛ ፎቶ ታሪኩን ይናገር።
*የተከበርክ አንባቢ ሆይ! ቀጣዮቹን ፎቶዎች በፅሞና እና በማስተዋል ተመልከታቸው፤ መልዕክቶቹንም ረጋ ብለህ ወደ
ነፍስህም ቀርበህ አንብብ። ምናልባት ለመፍትሄውም ሆነ ለችግሩ አንተ ትቀርብ ይሆናልና።

በጎንደር ከተማ የሚታየው ዘግናኝ የቁልቁለት ‘እድገት’። በህወሃት በይፋ ጠላትነት ተፈርጆ የቁም ስቅሉን እያየ በሚገኘው የአማራ ህዝብ ላይ ሆን ተብሎ በመካሄድ ላይ ያለው የኢኮኖሚ ተዐቅቦ ያስከተለው መከራና ድህነት እጅግ ዘግናኝ ሲሆን በቅርቡ በወጣ ጥናታዊ ዘገባም የአማራ ህፃናት ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ (በርግጠኝነትም በሌሎች ክልሎች በዚህ ስፋትና መልክ ያልተከሰተ) ያለ ዕድሜያቸው እየቀነጨሩ በመሆኑ ክልሉ ሰፊ የሆነውን የነገውን የሥራና የአስተዳደር ተረካቢ የሆነውን ወጣት ሀይል የማጣት እድሉ ከፍተኛ እንደሆን ተጠቁሟል። ጎንደርና ባህር ዳር ሲጨልም መቀሌና አክሱም በብርሃን ያንፀባርቃሉ። በአማራው ክልል ባለፈው የህወሃት ሩብ ምዕተ ዓመት አገዛዝ የጤና ጣቢያዎች ሆስፒታሎች መንገዶች ት/ቤቶች የመብራትና የውሃ መስመሮች ሆን ተብለው እንዳይገነቡ የነበሩትም እንዲወላልቁና እንዲፈራርሱ የተደረገበት የክፉ ሰዎች በቀለኝነት በህዝብ ሰቆቃና ህይወት መጠነ ሰፊ ጥፋት ያደረሰና እያደረሰም ያለ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ዘር የማጥፋት ተልዕኮ ውጤት ነው።
በአማራው ክልል በሩብ ምዕተ ዓመት የተገነቡት ከባድ ኢንዱስትሪዎችም ሆኑ መጠነኛ ስንት ናቸው? የአማራው ክልል ካለው የቆዳ ስፋትና በውስጡም ከሚኖረው ህዝብ ብዛት አንፃር በትግራይ ክልል የተገነቡት ከባድ ኢንዱስትሪዎችና መጠነኞችስ ስንት ናቸው? ንፅፅሩስ ተገቢና ፍትሃዊ አይሆንምን? ብአዴን ይህንን አያውቅም? ብአዴን እመራዋለሁ የሚለው ህዝብ ፍትሃዊ ባልሆነ ብቻ ሳይሆን ጭፍን በቀለኛ በሆነው ህወሃት ቀጥተኛ ብቀላ ሲፈፀምበት መሬቱን ሲገፈፍ ንብረቱን ሲቀማ የመኖር ህልውናው በየአቅጣጫው በእሾህ ተከቦ ሲደማ፤ በትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር የአጥፍቶ ጠፊ ሰላዮችና በተባባሪዎቹ የዘር ድርጅቶችና አስፈፃሚ ታጣቂዎች በመላው ሀገሪቱ ደሙ ደመ ከልብ ሲሆንና ‘የድረሱልኝ’ ጣዕር ሲያሰማ እንዴት ሆኖ ነው ብአዴን ከአማራው አብራክ የወጣ ነው ማለት የሚቻለው? ብአዴን ሆይ! ሁለት ሞት የለምና አንዱንና ሰማዕታዊውን ሞት መርጠህ ለህዝብህና ሰው ስለመሆን ስትል ዘር አጥፊውን ህወሃት ተጋፍጠህ ብትሞት እንኳን ሞትክ አይባልምና አደባባይ ወጥተህ ህዝብህን ምራ! ወይም ለሀገራቸው ኢትዮጵያና ለሚወክሉትም ህዝባቸው ለመሞት ለተነሱ ትንታጎች የአማራ ውልድ ወጣት የኢትዮጵያ ልጆች አስረክብ!! ብአዴን ሆይ ስማ፤ ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ በተመሳሳይ ጊዜ መውጣት አይቻልም። ወይ የህወሃት ናዚስቶችን ወይ ህዝብህን ሀገርህን ኢትዮጵያንና ፍትህን ምረጥ፤ ይኸው ነው!

ባለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት በትግራይ ክልል የተካሄደው ልማትና ያስከተለው ለውጥ በመላ የኢትዮጵያ ግዛቶች ተካሂዷል ከተባለው ልማት ግንባታና እድገት በእጥፍ ድርብ የሚበልጥ ነው። ዘመናዊ የህዝብ ማመላለሻ አውሮፕላኖች የካርጎና የጦር ጄቶች ማሳረፊያ ጣቢያዎች እጅግ የተራቀቁ ሆስፒታሎችና በአቅርቦት የተደራጁ አያሌ ጤና ጣቢያዎች መንገዶች የተሟላ የመብራት አገልግሎት ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች የንፁህ ውሃ መስመሮች የተደራጁና የተሟሉ ትምህርት ቤቶች ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች እና ወዘተርፈዎች ሁሉ ከተከዜ በታች ባለው ግብር ከፋይ የኢትዮጵያ ህዝብና በሀገሪቱ አንጡራ ሀብት ኪሳራ በአንዲት ክፍለሀገር ላይ ተገንብተውና በመገንባትም ላይ የሚገኙ ሲሆን ይህ ሁሉ አደሏዊነትና ግፍ የሚፈፀመው ደግሞ ‘ትግራይ እስክትለማ ሌላው ይድማ” በሚለው የዘረኛው ህወሃት በቀለኛ መርህና በተባባሪዎቹ የሥልጣን አጎብዳጅነትና አሽከርነት ነው። ከተከዜ በታች የሚኖረው ኢትዮጵያዊና አዲስ ትውልድ አፍ መፍቻው ‘መብራት የለም፤ ውሃ የለም፤ ስኳር የለም፤ ሥራ የለም…’ ሲሆን በትግራይ ክልል በሚኖሩ ትግራውያን እኒህ አፍ መፍቻና የእለት ተእለት መግባቢያ ቃላት አይታወቁም። ወደ ሶስት አሥርታት እየተጠጋ የሚገኘው የህወሃት ፌዴራሊዝም ውጤት የኢፌዲሪ እኩልነት። ድንቄም እኩልነት!
መስፍን ማሞ ተሰማ
(ቀሪዎቹን ፎቶዎችና ታሪካቸውን ለማንበብ እዚሀ ላይ ይጫኑ)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply