
እንደ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አህዛዊ መረጃ በመዲናዋ ውስጥ 1671 የሚሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ መረጃው ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ኮሌጅ መሰናዶ ድረስ ያሉትን የግል ትምህርት ቤቶች የሚያጠቃልል ሲሆን ፤ ትምህርት ቢሮው በ2006 የትምህርት ዘመን መጨረሻ ወራት ላይ ባወጣው ሪፖርት መሰረት ፣ በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ) የሚሆኑ ተማሪዎች ይማራሉ፡፡ ትምህርት ቢሮው የ2007 የትምህርት ዘመን አጠቃላይ አህዛዊ መረጃ አጠናቅሮ በድረ ገፁ ይፋ ባያደርግም ቁጥሩ ካለፈው የትምህርት ዘመን ሊልቅ እንደሚችል ይገመታል፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም ከሚጠናቀቀው የሚሊንየሙ የልማት ግቦች አንዱ የሆነውን ትምህርት ሙሉ ለሙሉ ዕድሜቸው ለትምህርት ለደረሱ ህፃናት የማዳረስ ዕቅድ ያላት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሚሊንየሙን የልማት ግቦች በማሳካቱ ረገድ የግሉ ሴክተር እንደ አንድ የድጋፍ መሰረት የሚታይ ሲሆን ፤ መንግስት ከጥራት በመለስ ትምህርትን ለዜጎች ለማዳረስ እያደረገ ባለው ጥረት ውስጥ የግል ትምህርት ተቋማት ቀላል የማይባል ሚና አላቸው፡፡ ከዚህም ባለፈ የመንግስት የስራ ዘርፍ ሙሉ በሙሉ ቀርቶ በግማሽ መጠን ያህል እንኳ ማስተናገድ ያልቻለውን የስራ አጥ ቁጥር በመቀነሱ ረገድ የግል ትምህርት ቤቶች አጋዥ መሆናቸውን ተጨባጭ እውነት ነው፡፡
በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ የሚታየው የሥነ-ምግባር ጉድለት አሳሳቢ መሆኑን ሳንዘነጋ መንግስት ፍፁም ያልተሳካለትን የትምህርት ጥራት በአንፃሩ በማሳየት ረገድ የተሻለ ተሞክሮ እንዳላቸው በየትምህርት ዘመኑ የስምንተኛ ፣ የአስረኛ እና የአስራ ሁለተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናዎች ውጤት ትንተና ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በመንግስት ትምህርት ቤቶች እየታየ ካለው የትምህርት ጥራት ችግር አኳያ ከፍለው ማስተማር የሚችሉ በርካታ የሸገር ወላጆች ብቸኛ ምርጫቸው የግል ትምህርት ቤቶች ሁነዋል፡፡ ይሁንና ትምህርት ቤቶቹ በየትምህርት ዘመኑ በትምህርት አገልግሎት ክፍያ ላይ በሚያደርጉት ጭማሪ የተነሳ የወላጆች ምሬት ከፍ ብሎ መሰማት ጀምሯል፡፡
ይህንን ማህበራዊ ጉዳይ እንደ መነሻ ሀሳብ በመጠቀም ስለ ግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት አገልግሎት ክፍያ መጠን የወላጆች ምሬት ፣ የትምህርት ቢሮውን “አቋም” እና የግል ትምህርት ቤት ባለሀብቶች አለን የሚሉትን ቅሬታ በተመለከተ ያነጋገርኳቸውን የባለ ድርሻ አካላት ሀሳብ እንደ ግብአት በመጠቀም ይህ ፅሑፍ ተዘጋጅቷል ፡፡ በዚህ አጀንዳ የግል ትምህርት ቤት እየተባሉ የሚጠሩት የኮሚኒቲ ፣ የግለሰብ ፣ የማህበር ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉትን ያካተተ ሲሆን ፤ ለዚህ ፅሁፍ ግብአትነት ይረዳ ዘንድ የቃል መጠይቅ ቀርቦላቸው ምላሻቸውን ከሰጡ ወላጆች በስተቀር የትምህርት ባለሙያዎችና ባለሀብቶች ስማቸው እንዲጠቀስ ያለፈቃዱ በመሆኑ የስም ለውጥ ለማድረግ መንገዴን አየገለፅኩ ፣ ግለሰቦቹ ለሰጡኝ መረጃ ከልብ እያመሰገንኩ ከፍርሀት ቆፈናቸው የሚላቀቁበት ደግ ዘመን ይመጣ ዘንድ በመመኘት ወደ አጀንዳው ዝርዝር ጉዳይ እቀጥላለሁ፡፡
የግል ት/ቤቶችና ክፍያቸውን በጨረፍታ
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች እንደ አላቸው የሰው ሀይል መጠን፣ ጥራት፣ አደረጃጀት፣ ‹እየሰጠን ነው› ከሚሉት የትምህርት አገልግሎት ጋር በተያያዘ እንደየ ትምህርት እርከኑ በየወሩ ይሁን በሩብ ዓመት (ተርም) ደረጃ ከሚያስከፍሉት ክፍያ አኳያ በሦስት ደረጃ ከፍሎ ማየት ይቻል ይመስለኛል፡፡
በደረጃ አንድ የምናስቀምጣቸው የግል ትምህርት ቤቶች በአብዛኛው መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የአምባሳደርና የዲፕሎማት ልጆች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ልጆችን እንዲሁም የከፍተኛ ባለሀብት ልጆችን የሚያስተናግዱት እንደ ሊሴ ገ/ማርያም፣ ሳንፎርድ፣ አይ.ሲ.ኤስ (ICS)፣ ብርቲሽ ኢንተርናሽናል የመሳሰሉት ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ ትምህርት ቤቶች የኮሚኒዮቲ ቢሆኑም ቁጥራቸው የበዛ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እጅግ ደጎስ ባለ ክፍያ ያስተናግዳሉ፡፡ ለአብነት የ2007 የትምህርት ዘመን የነበረውን የትምህርት አገልግሎት ክፍያ እንደ ማሳያ ብንወስድ ፣ አንድ ወላጅ ልጁን በ“ሳንፎርድ” ትምህርት ቤት ለማስተማር ቢፈልግ ለአዲስ ተማሪ ለመመዝገቢያ ብቻ 50,000 (ሃምሳ ሺህ ብር) የኢትዮጵያ ብር (ሃምሳ ብር አላልኩም ደግመው ያንብቡት) መክፈል ከወላጅ እንደሚጠበቅ በትምህርት ቤቱ ድረ ገፅ የተለጠፈው መረጃ ያመለክታል፡፡ ሌሎች ተዛማጅ ወጪዎችን ሳይጨምር፣ አንዲት ጀማሪ የአፀደ ህፃናት (Nursery) ተማሪ የመመዝገቢያና አመታዊ የትምህርት ክፍያ 76,578 (ሰባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ሰባ ስምንት ብር) ሲሆን፤ አዲስ ገብ ለሆነ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ደግሞ 104,960 (አንድ መቶ አራት ሺህ ዘጠኝ መቶ ስልሳ ብር) ለአንድ አመት መክፈል ግድ ይላል፡፡
ወዳጄ! “እግዚኦ/የአላህ” እያሉ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ግድ የለም አይቸኩሉ ፤ ይሄ እኮ የትምህርት አገልግሎት ክፍያ ብቻ የሚከፈል ነው፡፡ በትምህርት ቤት ደረጃ የሚከበሩ ካርኒቫል፣ ፌስቲቫል እና ልዩ ልዩ ቀናት (color day, water day, crazy day, fun day…) እየተባሉ ለሚከበሩ ፕሮግራሞች የሚወጣውን ወጪ ብናሰላው ደግሞ የክፍያ መጠኑ ማሻቀቡ የታወቀ ነው፡፡ ርግጥ ሌላ ተአምር በአዲስ መስመር መመልከት እንችላለን፡፡
እ.ኤ.አ በ1964 ዓ.ም በአዲስ አበባ አሮጌው ኤርፖርት አካባቢ በአሜሪካውያን የተመሰረተው “ኢንተርናሽናል ኮሚኒቲ ት/ቤት (ICS)” ከ60 በላይ አገራት ዜግነት ያላቸው ተማሪዎችን ከቀደመ መደበኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ በአሜሪካ ስርዓተ ትምህርት የሚያስተምር ሲሆን፤ በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችም ይገኛሉ ፡፡ ትምህርት ቤቱ በ 2007 የትምህርት ዘመን 210 አዲስ ተማሪዎችን በመቀበል በአጠቃላይ የተማሪዎችን ብዛት 830 ለማድረስ አቅዶ እንደተንቀሳቀሰ፣ 128 ፕሮፌሽናል መምህራን እና 50 ረዳት መምህራን እንዳሉት፣ ከነዚህ ውስጥ 40 የሚሆኑት ረዳት መምህራን ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ የትምህርት ቤቱ ድረ ገፅ ያመለክታል፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች አማርኛ ቋንቋ “የአፍ መፍቻ ቋንቋ ወጌሻ (Mother tongue maintenance)” ተብለው በሚጠሩ መምህራን በሳምንት እንደ አንድ ጊዜ ለአንድ ሰዓት ያህል ተማሪዎች ፍቃደኛ ሲሆኑ ብቻ እንደሚማሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ትምህርት ቤቱ ለ2007 የትምህርት ዘመን ለአዲስ ተማሪዎች በየ ትምህርት እርከኑ በዶላር የሚያስከፍለዉን የትምህርት አገልግሎት ክፍያ በተመለከተ ሰንጠረዡን ይመልከቱ:-
የክፍል ደረጃ | የመመዝገቢያ ክፍያ | ተጨማሪ ቀረጥ(Capital levy) | አመታዊ የት/ት ክፍያ | አጠቃላይ ክፍያ |
ቅድመ መደበኛ | $ 500 | – | $ 8,500 | $ 8,500 |
1ኛ -5ኛ ክፍል | $ 500 | $ 5,000 | $ 19,165 | $ 24,665 |
6ኛ -8ኛ ክፍል | $ 500 | $ 5,000 | $ 21,735 | $ 27,235 |
9ኛ -10ኛ ክፍል | $ 500 | $ 5,000 | $ 22,365 | $ 27,865 |
11ኛ-12ኛ ክፍል | $ 500 | $ 5,000 | $ 22,705 | $ 28,205 |
- ለቅድመ መደበኛ ተማሪዎች የሚከፈለው የመመዝገቢያ ብር ከአመታዊ የት/ት ክፍያ ላይ ታሳቢ ይሆናል፡፡
ምንጭ፡- www.icsaddis.edu.et
ማስታወሻ፡- ትምህርት ቤቱ የሚያስከፍለው በዶላር እንደመሆኑ መጠን አጠቃላይ የትምህርት አገልግሎት ክፍያውን ከወቅቱ የምንዛሬ ተመን ጋር ማስላቱ የርሶዎ የቤት ስራ ይሁን፡፡
ለልጆች የደብተር መግዢያ ቀርቶ ለዕለት ጉርሱ ያጣና የነጣ ህዝብ በሚማርበት ከተማ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ለሆነ ልጁ በአመት ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ለትምህርት ቤት ክፍያ የሚያወጣ አባወራ መኖሩን ስናይ “ኧረ እንደምን ተራራቅን!?” ብለን ልንጠይቅ ግድ ይለናል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ከሚማሩ ተማሪዎች ውስጥ በየዕለቱ ጠኔ ጠንቶባቸው ተዝለፍልፈው የሚወድቁ ህፃናት በርከት ያሉ መሆናቸውን በተመለከተ ሸገር 102.1 ራዲዮ ልዩ የወሬ ፕሮግራም እንደሰራበት የሚታወስ ነው፡፡ ተወደደም ተጠላም የዝህች አገር ዜጎች የኑሮ ደረጃ ልዩነት በዚህን ያህል መጠን ተራርቋል፡፡ እዚህ ህፃናት በምግብ እጥረት የተነሳ በየመማሪያው ክፍላቸው ተዝለፍልፈው ይወድቃሉ ፤ እዚያ ማዶ ያለ ወላጅ ደግሞ ግማሽ ሚሊየን ብር (የአንድ ቀበሌ ሰራተኞች የግማሽ አመት የደመወዝ ክፍያ) የሚሻገር ወጪ ለልጁ የአንድ አመት የትምህርት ቤት ክፍያ ይከፍላል፡፡
የሆነው ሆኖ የአጀንዳው የትኩረት አቅጣጫ የግል ትምህርት ቤቶችን የክፍያ ሁኔታ በተመለከተ ነውና ትኩረታችን ወደዚያው እናድርግ፡፡ በነገራችን ላይ በነዚህ ትምህርት ቤቶች የትምህርት አገልግሎት ክፍያው በየትኛውም መጠን እየጨመረ ቢሄድ እንኳ ወላጆች ደንበኝነታቸውን የሚያቋርጡ አይነት አይደሉም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የምናስቀምጣቸው ትምህርት ቤቶች በአብዛኛው በኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶች በግልና በማህበር የተመሰረቱ ሲሆን ፤ ለአብነት ፡- እንደ ጊብሰን ፣ ኢትዮ ፓረንት ፣ አንድነት ኢንተርናሽናል ወዘተ የመሳሰሉ የግል ትምህርት ቤቶች ከትምህርት አገልግሎት ክፍያ አኳያ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቃለሉ ናቸው፡፡ በነዚህ ትምህርት ቤቶች ልጃቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች ኑሮውን በውጭ አገር ያደረገ ቤተሰብ ያላቸው ሆኖ ጠቀም ያለ ድጎማ የሚያገኙ፣ የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴ ያላቸው፣ በሚኒስተር ዴኤታና ከዛ በታች ባለው የመንግስት ሥልጣን ላይ የተቀመጡ፣ ወ.ዘ.ተ የመሳሰለ ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ለዚህ ፅሑፍ ግብአትነት ሲባል በተደረገ ቅኝት ለማጣራት ተሞክሯል፡፡ በነዚህም ትምህርት ቤቶች ውስጥ የነባርና አዲስ ተማሪዎች የመመዝገቢያ ክፍያ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ በአማካይ ከ 1,200-4,500 ብር የሚደርስ ክፍያ የሚጠየቅ ሲሆን ፤ የመደበኛ ትምህርት ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት (Tutor) እና ሌሎች ተዛማጅ ወጪዎችን ጨምሮ በየወሩ አለያም በሩብ አመት ደረጃ የሚከፈለው ክፍያ ወደ ዓመታዊ ክፍያ ሲቀየር ለአንድ ተማሪ በነፍስ ወከፍ ከ32,000-58,000 ብር ድረስ መክፈል ግድ ይላል፡፡
በነገራችን ላይ ከክፍያ መጠን አኳያ በሁለተኛ ደረጃ ባስቀመጥናቸው የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚከፍል ክፍያ በአንደኛ ደረጃ እንደ ተቀመጡት ትምህርት ቤቶች የክፍል ደረጃው እየጨመረ በሄደ ቁጥር የክፍያው መጠንም በዚያው ልክ የሚያድግ በመሆኑ በነዚህ ትምህርት ቤቶ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ያለው ወላጅ በአማካይ ክፍያው ጣራ (58,000 ብር) የሚከፍል ይሆናል፡፡ በዚህን ያህል የክፍያ መጠን ሁለትና ከዚያ በላይ ልጆች ያሏቸው ወላጆች የክፍያ ዳገቱን እንዴት ሊወጡት እንደሚችሉ ማሰብ በራሱ እንቆቅልሽ ይመስላል፡፡ ይሁንና ደንበኝነታቸውን በነዚህ ትምህርት ቤቶች ያደረጉ ወላጆች የልጆች የትምህርት አገልግሎት ክፍያ እየጨመረባቸው ቢሄድና ክፍያውን መቋቋም የማይችሉበት የኑሮ ደረጃ ላይ ቢደርሱ እንኳ ከቀደመው ትምህርት ቤት አነስ ያለ ክፍያ የሚያስከፍሉ ትምህርት ቤቶችን በመፈለግ የልጆቻቸውን ትምህርት በግል ትምህርት ቤት ውስጥ የማስቀጠል አቅም አላቸው፡፡
ከትምህርት አገልግሎት ክፍያ አኳያ በሦስተኛ ደረጃ በምናስቀምጣቸው የግል ትምህርት ቤቶ ውስጥ ልጆቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች በአብዛኛው በንዑስ ከበርቴው መደብ የሚጠቃለሉ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በነዚህኞችም ትምህርት ቤቶች የነባርና አዲስ ተማሪዎች የመመዝገቢያ ክፍያ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ ከ400-1,000 ብር የሚደርስ ክፍያ እንደሚከፈል፣ የመደበኛ ትምህርት አገልግሎት ክፍያ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት ክፍያና መሰል ተዛማጅ የትምህርት ወጪዎችን ጨምሮ በአንድ የትምህርት ዘመን ከ9,700-28,660 ብር የሚደርስ ወጪ እንደሚያወጡ ከወላጆ ያገኘሁት መረጃ ያመለክታል፡፡ የትምህርት አገልግሎት ክፍያ ጭማሪን ባለመቋቋም ከፍተኛ ምሬት እያሰሙ ያሉ ወላጆች በሦስተኛው ምደብ ይጠቃለላሉ፡፡ በዚህ አጀንዳ የወላጆ አስተያየት እየተባለ የተገለፀውም የነዚህኞቹ ድምፅ መሆኑ ልቡ ይባል፡፡
የወላጆች ምሬት …
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መስሪያ ቤት ከዓመት በፊት በሰራው ጥናት፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ 56 በመቶ የሚሆኑት በየዓመቱ በአማካይ ከ20-25 በመቶ በሚሆን መጠን የትምህርት አገልግሎት ክፍያ እንደሚጨምሩ ያመለክታል፡፡ ይህን ተከትሎ ቁጥራቸው የበዛ የሸገር ወላጆች “የቀጣይ ዓመት የልጆቼን የትምህርት ቤት ክፍያ እንዴት ልወጣው ነው?” የሚለውን ክቡድ ማህበራዊ ጥያቄ ከወርሃዊ የገቢ መጠናቸው ጋር እያነፃፀሩ ክረምቱን በምሬት መግፋት ተለምዷዊ የኑሮ ዘይቤ አድርገውታል፡፡ የዘንድሮው ከራሞትም ከአለት ከጣጠረው የኑሮ ውድነት ጋር ተጋምዶ የልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ ተራራን የመግፋት ያህል የከበዳቸው ወላጆች ተበራክተዋል፡፡ በዚህ መሰል አታካች የኑሮ ሂደት ውስጥ በየትምህርት ዘመኑ መጀመሪያ ላይ በረከት ያሉ የግል ትምህርት ቤቶች “አስገዳጅ” በሚሏቸው ምክንያቶች (የትምህርት ቁሳቁስ መወደድ ፣ ለመምህራን ደመወዝ ጭማሪ ፣ የቤት ኪራይ መጨመር) የተለመደውን የትምህርት ቤት ክፍያ በመጨመራቸው የሸገር ወላጆች ችግር “በእንቅርት ላይ . . .” ሆኖባቸዋል፡፡
ወ/ሮ ሀዳስ ሙሉ ይህን በመሰለው ኢኮኖሚያዊ ፈተና ላይ ወድቀዋል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ባለቤታቸውን በመኪና አደጋ ያጡት እኒህ ወ/ሮ፣ በአንድ የግል ባንክ በሂሳብ መርማሪነት ተቀጥረው በሚያገኙት ደመወዝ ከሟች ባለቤታቸው ያፈሯቸውን ሁለት ልጆች የማስተዳደሩ ኃላፊነት በትከሻቸው ላይ ወድቋል፡፡ “ለልጆቼ ጥየው የማልፈው ጥሪት የሌለኝ ሰው በመሆኔ፣ ዕውቀትን አውርሻቸው ልለፍ በሚል ከጓደኞቼ በታች እየኖርኩኝ ልጆቼን በግል ትምህርት ቤት ለማስተማር ተገድጃለሁ” የሚሉት ወ/ሮ ሀዳስ “መስከረም ወር በመጣ ቁጥር ድህነቴ ይበልጥ ይሰማኛል” ሲሉ በምሬት ይናገራሉ፡፡
ጎልማሳው አቶ አለማየሁ ጫቦ በመኪና ድለላ ሥራ የተሰማሩ ሲሆን ፤ ከድለላ ስራቸውና በመኖሪያ ቤታቸው ግቢ ሰርተው ከሚያከራዩቸው አራት ክፍል ቤቶች በሚያገኙት ገንዘብ ባለቤታቸውን ጨምሮ አራት ልጆቻቸውን የማስተዳደር ኃላፊነት የራሳቸው ነው፡፡ “አንደኛው ልጄ የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሲሆን፤ ቀሪ ሶስቱ ልጆቼ ደግሞ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ናቸው” የሚሉት አባወራ፡፡ “በመንግስት ትምህርት ቤቶች የትምህርት አሰጣጥ ስለማለተማመን፣ ልጆቼን ከግል ትምህርት ቤት ውጪ ማስተማር አይታየኝም፡፡ የዋጋቸው ነገር ደግሞ ፈታኝ ሆነ” ይላሉ አቶ አለማየሁ፡፡ መፍትሄ ብለው ያቀረቡት ነገር “ልጆቼ የሚማሩበት ትምህርት ቤት በየአመቱ ክፍያ በጨመረ ቁጥር እኔም የቤት ተከራዮቼ ላይ ለመጨመር ተገድጃለሁ” ሲሉ ችግራቸውን ለማቃለል የተጠቀሙበትን መንገድ ይናገራሉ፡፡
የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መ/ሩ አቶ ተፈራ የአንድ ልጅ አባት ሲሆን፣ ባለቤቱ የግል ስራዋን አቋርጣ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን በመማር ላይ ትገኛለች፡፡
“የቤት ኪራይ፣ የአስቤዛ ወጪና የልጆችን የትምህርት አገልግሎት ክፍያ መክፈል በእኔ ላይ የወደቀ ኃላፊነት ሆኗል” ይላል መ/ር ተፈራ፡፡ “ባለቤቴ ቀደም ብላ በቆጠበቻት ብር የድህረ ምረቃ ትምህርቷን እየተከታተለች ያለ ቢሆንም፣ ብቻየን የማልወጣው ወጪ ለመጋፈጥ ተገድጃለሁ” የሚለው የዩኒቨርስቲ መ/ሩ፣ “ልጃችን ከሚማርበት የግል ትምህርት ቤት ከማስወጣት ላልተወሰነ ጊዜ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ቁጠባችን ለማቋረጥ ከባለቤቴ ጋር በጋራ ወስነናል” ሲል በምሬት ይናገራል፡፡
ለዚህ አጀንዳ ግብአትነት ሲባል በአቅራቢያየ የሚኖሩትን ወላጆች ምሬት ከላይ በተመለከተው መልኩ ለመዘገብ ሞክሬአለሁ፡፡ ግና፣ ስንቱ የሸገር ወላጅ በየጓዳው እየተብሰከሰከ እንዳለ ቤት ይቁጠረው፡፡
በዚህ ዘመን ጥሪት ለልጅ ማሻገር የማይታሰብ ሆኗልና የብዙሃኑ ወላጅ ምርጫ ልጆች የተሻለ እውቀት የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ብቸኛው መንገድ እንዲሆን ግድ በሏል፡፡ ችግሩ ይህኛው መንገድ ከባድ የኢኮኖሚ ተግዳሮት ገጥሞታልና የወላጆች ምሬት ገንግኗል፡፡
ትምህርት ቢሮው ምን ይላል?
ትምህርት ቢሮው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በግል ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ ወላጆችና አሳዳሪዎች በየጊዜው በትምህርት አገልግሎት ክፍያ ላይ በሚደረግባቸው ጭማሪና በሌሎች አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ዙሪያ የሰማቸው ምሬቶች እንደ መግፍኤ ሆኖት፣ በ2006 የትምህርት ዘመን መጨረሻ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረኮችን ለማዘጋጀት ሞክሯል፡፡ ወይይቱን ተከትሎ ትምህርት ቢሮው “በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ያስወሰንኩት” ነው ያለውን ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡
በጊዜው የተወሰነው ውሳኔ “የግል ትምህርት ቤቶች ለመማር ቀጥተኛና አግባብነት የሌላቸውን የክፍያ ጥያቄዎች በተመለከተ በቀጣይ ዘላቂ መፍትሔ እስከሚገኝ ድረስ ተግባራዊ እንዳይሆኑ” የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ለሁሉም የግል ትምህርት ቤቶች ስርኩራል በሆነ መልኩ ቢተላለፍም፣ ትህምህርት ቤቶቹ በአዲሱ የክፍያ መጠናቸው ተማሪዎችን ከመመዝገብና ከማስተማር ያገዳቸው አንዳች ነገር አለንበረም፡፡ በ2006 የትምህርት ዘመን የክረምት ወራት ስርኩራል ተላልፎ በነበረው ደብዳቤ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ካሉት 1671 የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለ2007 የትምህርት ዘመን ያልተገባ የትምህርት አገልግሎት ክፍያ ጠይቀዋል ያላቸውን 1000 (60%) ትምህርት ቤቶች የጠየቁትን የትምህርት አገልግሎት ክፍያ ዳግም እንዲከልሱ አስጠንቅቆ የነበረ ቢሆንም የትምህርት ቢሮውን ማስጠንቀቂያ “አገሪቱ የነፃ ገበያ ፖሊስ መርህ የመትከል መሆኑን የዘነጋ” የሚለው መከራከሪያ ከባለሀብቶቹ አንደበት ተደምጧል፡፡
ያሻቸውን የዋጋ መጠን ያህል እየጨመሩ ወላጆችን ምሬት ላይ ከመጣል የሚያግዳቸው ያጡት ባለሃብቶች ከትምህርት ቢሮ እስከ ሸማቾችና ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ድረስ ያሉ አካላትን ውሳኔ እንዴት ማሳጠፍ እንዳለባቸው ያውቃሉና የወላጆች ምሬት ሰሚ አልባ ሆኗል፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮም ሆነ የሸማቾችና ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ከትምህርት አገልግሎት ክፍያ ጋር በተያያዘ ከግል ትምህርት ቤት ባለሀብቶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት የዘገየ መሆኑን የሚያምኑት የትምህርት ባለሙያው አቶ ዮሐንስ “ትምህርት ቢሮው የያዘው አማራጭ ‹ይህን መምሪያ የማትቀበል ከሆነ የትምህርት ተቋምህን አንዘጋዋለን› የሚል ማንገራገሪያ አዘል መመሪያ መስጠት መጀመሩ፤ ከባለ ሀብቶቹ ጋር ተወያይቶ ለመተማመን እንቅፋት ሆኖበታል” ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ እኚህ ባለሙያ አክለውም “ከትምህርት ክፍያ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ቀጥተኛ ያልሆነና ያልተገባ ክፍያ ጠይቀዋል በሚል የተለዩ ትምህርት ቤቶች እርምጃ ይወስድባቸዋል ከተባለ በኋላ ነገሩ የውሃ ሽታ ሆኖ ሲቀር ማየት ተለምዷሚ አሰራር ሆኗል” ይላሉ፡፡ ሌላኛው የትምህርት ባለሙያ የሆኑት አቶ ወንድማገኝ “የግል ትምህርት ቤቶች ማህበራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ዘንግተውታል፡፡ ትምህርትን በመሰለ ዘርፍ ትርፍን ብቻ ማስላት ይከብዳል ለትውልዱ ማሰብ ዜግነታዊ ግዴታ ነው” ሲሉ ጣታቸውን ወደ ግል ባለሀብቱ ይቀስራሉ፡፡
ትምህርት ቢሮው “በግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት አገልግሎት ክፍያ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን ለማስተካከል ከሸማቾችና ጥበቃ ባለስልጣን መሥሪያ ቤት ጋር በመቀናጀት እየሰራሁ ነው” ቢልም እስካሁን ድረስ የታየ ለውጥ የለም፡፡ የወላጆች ምሬትም ከአመት አመት እየጨመረ ሲሄድ እያየን ነው፡፡ ትምህርት ቢሮው የግል ትምህርት ቤቶችን በተመለከተ የሚያስተላልፈው መልዕክት፣ የሚያወርደው መመሪያ በቅጡ ተፈፃሚ ሲሆን አይታይም፡፡ በተሸላ የትምህርት አደረጃጀት እና ብቁ የሰው ኃይል ታጅበው የሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ሳንዘነጋ በአንድ የበጋ ወቅት ጠጅ ቤት አልያም ፔንስዮን የነበረ ግቢ በሌላኛው የበጋ ወራት ትምህርት ቤት ሆኖ በምናይበት ከተማ፣ ለግል ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የማስተማር ፍቃድ እና የፍቃድ አድሳት ሁኔታ በምን መንገድ ተፈጻሚ እየሆነ እንዳለ ጥቁምታ ይሰጠናል፡፡ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች መጠነኛ እድሳት ተደርጎላቸው፣ ሳሎኑ መማሪያ ክፍል፣ ኪችኑ ስቶር፣ መኝታ ክፍሉ ቢሮ እንዲሆን እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ከወቅቱ የኑሮ ውድነት አኳያ ጣራ የነካ ገንዘብ መጠየቅ ከዜግነት በታች እንደ ማሰብ ቢተረጎምም፣ የጉዳዩ ፈፃሚዎችም ሆኑ አስፈጻሚዎች መንገዱ ተመችቷቸዋል፡፡ ለወላጆች ግን ይበልጡን ቆርቁሯቸዋል፡፡
ትምህርት ቢሮው በየትምህርት ዘመኑ ማገባደጃ የክረምቱ ወራት ወላጆች የሚያሰሙትን ቅሬታ ለማርገብ ‹ያልተገባ የትምህርት አገልግሎት ክፍያ በሚጠይቁ ትምህርት ቤቶች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን› የሚል ምላሽ መስጠት የቢሮው የሰርክ ምላሽ ሆኖል ፤ ርግጥ ነው አገሪቱ የነፃ ገበያ ሥርዓት የምትከተል ሀገር ነች፡፡ ይሁንና የፍየል ጉሮኖ በመስሉ የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ ተማሪዎችን ለሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች ፍቃድ እንደ ቀበሌ መታወቂያ ከማደል የትምህርት ቤቶች መመዘኛ ስታንዳርድ እና የክፍያ መጠኑ በትይዩ የሚሄድበትን አቻቻይ የአሰራር ስልት መቀየስ የነፃ ገበያ ሥርዓቱን እምብዛም የሚያምሰው አይመስልም፡፡ ርግጥ ይሄኛው አማራጭ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ አይደለም፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በመንግስት ትምህርት ቤቶች ያለውን የትምህርት አሰጣጥ ጥራትን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን ማድረጉ አቻ የሌለው የመፍትሄ ሀሳብ ቢሆንም የመንግስት ትምህርት ቤቶች የገዢው መደብ የፖለቲካ ክንፍ ሆነዋልና ጥራት የማይታሰብ ሆኗል፡፡
የግል ትምህርት ቤቶች ቅሬታ
ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት በየ ዓመቱ እየጨመረ የሚመጣውን የህብረተሰቡን እድገትና የትምህርት ፍላጎት በመንግስት አቅም ብቻ ለማዳረስ አቅምን የሚጠይቅ በመሆኑ የግል ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ መግባታቸው ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም “መንግስት ተገቢውን ድጋፍ አላደረገልንም” የሚሉት አቶ ሚናሴ “በትምህርት ዘርፍ ከተሰማራሁ አስራ ሁለተኛ ዓመቴ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ የግለሰብ ቤት ተከራይቼ፣ ከባንክ በወሰድኩት ብድር እድሳትና የማስፋፊያ ግንባታ በመስራት ስራዬን እየሰራሁ ብገኝም በ22,000 ብር የተከራየሁት ግቢ ዛሬ ላይ በወር 110,000 ብር እየከፈልኩበት እገኛለሁ” ሲሉ ከመሬት አቅርቦት ጋር ተያይዞ ያላቸውን ቅሬታ ያሰማሉ፡፡
የአቶ ሚናሴን ሀሳብ የሚጋሩት ወ/ሮ ትሁት “የግለሰብ ቤት ተከራይቼ የማስፋፊያ ግንባታዎችን የሰራሁ እንደ መሆኔ አከራዬ በየትኛው መጠን ክፍያ ቢጨምሩብኝ እንኳ ግቢውን ከመልቀቅ ይልቅ መደራደርን እመርጣለሁ” የሚሉት ወ/ሮዋ በአከራያቸው የሚጨመርባቸውን የክፍያ መጠን የትምህርት አገልግሎት በሚሰጣቸው ተማሪዎች ላይ “መጠነኛ” የሚሉትን ክፍያ በመጨመር እንደሚያካክሱት ይናገራሉ፡፡ “በትምህርት ቤቱ የሚሰጠው ትምህርት ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የተሻለ ዕውቀት ያላቸው ትጉህ መምህራንን እና የትምህርት አስተዳደሮችን መቅጠር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተሻለ ክፍያ መክፈል ይጠበቅብናል፡፡ ይህን ክፍያ የማገኘው ደግሞ ከደንበኞቼ ነው” የሚሉት ባለሀብቱ አቶ መስፍን፣ የትምህርት አገልግሎት ክፍያ አስገዳጅ በሆኑ ምክንያቶች እንጂ እንዲሁ በዋዛ የሚጨመር አለመሆኑን ይከራከራሉ፡፡
አስር ወር ከተማሪ የምንሰበስበውን የትምህርት አገልግሎት ክፍያ ለአስራ ሁለት ወራት የሰራተኛ ደመወዝ፣ የተጋነነ የቤት ክራይ፣ የትምህርት ቁሳቁስ፣ የህንፃ እድሳት ወ.ዘ.ተ ለማድረግ ልዩ ልዩ ወጪዎችን ማውጣት ይጠበቅብናል የሚሉት የግል ትምህርት ቤት ባለሀብቶች፣ “መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ሳያደርግልን ቢወቅሰን ትርፉ ቅሬታን መፍጠር ነው” የሚለው አስተያየት የጋራ ደምፃቸው ነው፡፡ “በስመ የግል ትምህርት ቤት፣ ደረጃቸውን ባልጠበቁ መማሪያ ክፍሎችና ምቹ የትምህርት ሁኔታና አካባቢ ባልተፈጠረበት ሁኔታ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶችን በመለየት አስተማሪነት ያል እርምጃ መውሰድ የትምህርት ቢሮው ኃላፊነት ቢሆንም ይህ ሲሆን አላየንም” የሚሉት አቶ ሚናሴ፣ ሁሉንም የግል ትምህርት ቤቶች በአንድ ላይ ጠቅልሎ መተቸት የመፍትሔ መንገድ እንዳልሆነ የግል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
መፍትሔው ምንድር ነው?!
መንግስት ለረዥም ዓመታት “ትምህርትን ማስፋፋት” በሚል በሄደበት መንገድ ጥራቱን እንደ ደፈጠጠው ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ በአናቱም ከላይ እንደተመለከተው የመንግስት ትምህርት ቤቶች የገዢው መደብ የፖለቲካ ክንፍ ሆነዋል፡፡ ይህን እውነት ለመረዳት የማይሰንፉት የሸገር ወላጆች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ልጆቻቸውን ከግል ትምህርት ቤቶች ለማስተማር ተገደዋል፡፡ ቁጥራቸው የበዛ ወላጆች በችግር ውስጥ ሆነው እንኳ ልጆቻቸውን ከግል ትምህርት ቤት ለማስወጣት ድፍረት አጥተዋል፡፡ “የመንግስት ትምህርት ቤቶች ከትምህርት ጥራት አተገባበር አኳያ እምነት የሚጣልባቸው ቢሆን ኖሮ፣ እኔና መሰል ወላጆች ለዚህ ሁሉ ችግር ባልተዳረግን ነበር” የሚለው የኮተቤ ዩኒቨርስቲ መ/ሩ ተፈራ “መንግስት ለወላጆች ምሬት ምላሽ መስጠት ከፈለገ በስሩ ያሉ ትምህርት ቤቶች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት የሚሰጥባቸው እንደሆኑ ማድረግ ይጠበቅበታል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ “በመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት ችግር ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ማስተካከል” የሚለው የመፍትሔ ሀሳብ ተመራጭ ቢሆንም “የትምህርት ጥራትን እውን ለማድረግ የአካዳሚክ ነፃነት ያስፈልጋል” የሚሉ አስተያየቶች ተያይዘው ይነሳሉ፡፡ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ርዕስ መምህር ሆኖ ለመስራት በትምህርት ዕቅድ አዘገጃጀትና አመራር (EDPM) መመረቅ ሳይሆን የሚያስፈልገው ለስርዓቱ አደግዳጊ ሆኖ መገኘት በቂ ነው፡፡
የትምህርት ቤት አስተዳደሮች የሚገመገሙትም በትምህርት ቤታቸው ውስጥ እንዲፈጠር ባደረጉት የትምህርት ጥራት ደረጃ ሳይሆን የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ካምፕ እንዲቀላቀሉ ባደረጋቸው የመምህራን ብዛት ልክ ነው፡፡ ይህ እየሆነ ባለበት ሁኔታ የአካዳሚክ ነፃነት ይፈጠራል ብሎ መጠበቅ ወደ ህልመኝነት ያስጠጋል፡፡
አብዛኛው የግል ትምህርት ቤት ባለሀብቶች “መንግስት የመሬት ጥያቄያችን ቢመልስልን፣ ለትምህርት ግብአቶች የታክስ ማሻሻያ ቢደረግልን፣ … ለትምህርት አገልግት ክፍያ የምንጠይቀውን ገንዘብ መቀነስ በቻልን ነበር” ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ባለሀብቶች የሚያነሱት የመሬት ጥያቄ ከአዲስ አበባ ከተማ የቆዳ ስፋት ውስንነትና መንግስት መሬት ላይ ካለው ግትር አቋም አኳያ ጥያቄቸው በስርዓቱ መቃብር ላይ ካልነ በስተቀር ምላሽ የሚያገኝ አይመስልም፡፡ እስከዛው ግን የአንዳንድ የሸገር ወላጆች ምሬት እንዲሁ ይቀጥላል … (ፎቶ: Addis Fortune)
ሙሉአለም ገ.መድህን
የዚህ ዘገባ አቅራቢ “የኢህአዴግ ቁልቁለት” መጽሃፍ ደራሲ ናቸው:: ይህንን ዘገባ የላኩት ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ነወ::
Leave a Reply