“ፋክት” መፅሔት ላይ ቋሚ አምደኛ በመሆን በየሳምንቱ በወቅታዊ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የሚያተኩሩ ፅሁፎችን ወደ አንባቢ ሲያደርስ የነበረው ሙሉዓለም ገ/መድኅን አዲስ መጽሐፍ ለኅትመት አብቅቷል፡፡
የመፅሃፉ ርዕስ፡- የኢሕአዴግ ቁልቁለት
ደራሲ ፡- ሙሉዓለም ገ/መድህን
የገፅ ብዛት፡- 235
ዋጋ ለአገር ውስጥ፡- 52 ብር ለውጪ አገር፡- 20 ዶላር
አጠቃላይ ይዘት
መፅሃፉ በአራት ክፍሎች እና በአስራ አራት ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን፣ ክፍል አንድ ላይ “ቁልቁለቱን በኢሕአዴግ ጎዳና” በሚል አምስት ምዕራፎች ተካተዋል፡፡ በዚህ ክፍል ብሶት ወለደኝ የሚለው ህወሓት ተነሳሁለት የሚለውን የትግል ዓላማ እንዴት እየቀለበሰው እንደመጣ በዝርዝር ያስቃኛል፣ በመስመር መሀል ከጫካ ጀምሮ የህወሓት የፖለቲካ አሽከር ስለሆነው ኢህዴን/ብአዴን ፖለቲካዊ ክሽፈት ያነሳል፣ ለቁጥር ብቻ ስለሚፈልጉት የኢሕአዴግ ሴቶች የፖለቲካ መሪነት ተሳትፎ ከአህዛዊ መረጃዎች ጋር እያነፃፀረ የሴቶቹን የቁጥር ማሟያነት በማሳያዎች አስደግፎ ያብራራል፣ ስለ ተጨፈለቀው የዳኝነት ነፃነት ጥያቄ እና ፍሬን አልባ ስለሆነው የአገዛዙ የዴሞክራሲ ቁልቁልነት ይተነትናል ፣ የኢህአዴግ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ኢትዮጵያን እንዴት ወደ ሶስተኛው አብዮት እየገፋት እንደሆነ በአገሪቱ የፖለቲካ አደባባይ ላይ እየታዩ ያሉ “አብዮታዊ ሁኔታዎች”ን እያጣቀሰ በዝርዝር ያስቃኛል፡፡
የመፅሃፉ ክፍል ሁለት ደግሞ “በአዙሪት የታጅበው የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና የቁልቁለቱ ተፅዕኖ” በሚል የቀረበ ሲሆን፤ በዚህ ክፍል የተካተቱ ምዕራፎች የያዟቸው መልእክቶች የኢትዮጵያን ፖለቲካ ጥልፍልፋዊ ጉዞ ለማሳየት ተክሯል፡፡ በተለይም “የሦስት ትውልድ ተንከባላይ ዕዳ” በሚለው ምእራፍ ውስጥ ከነ ግርማሜ ንዋይ ትውልድ እስከ ያ ትውልድ ድረስ እንዲሁም ስለዚህኛው ትውልድ ተንከባላይ ዕዳ ማሳያዎችን በማንሳት በዝርዝር ለማብራራት ተሞክሯል፡፡
ክፍል ሶስት የአገሪቱን የሰሜን ምዕራብ ማህበረ-ፖለቲካዊ ሁነቶች የሚያስቃኝ ሲሆን፤ በአካባቢው እየታዩ ያሉ የብሔርተኝነትና የጎጠኝነት ስሜቶች፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ የአማራ ክልልና የትግራይ ክልል የአዋሳኝ ድንበር ወዝግብን በተመለከተ፣ በአካባቢው ስላለው ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና ስለ ቅማንት የማንነት ጥያቄና ውዝግቡ በዝርዝር ያስቃኛል፡፡
የመፅሃፉ የመጨረሻ ክፍል የሆነው ክፍል አራት “ቁልቁለቱን ለማቆም ትልቁ የቤት ስራችን” የሚል ሲሆን፤ በዚህ ክፍል አገሪቱ ካለፉት አራት አስርታት ወዲህ የተጓዘችበትን የማህበረ-ፖለቲካ ጉዞ በማስቃኘት መጪው ጊዜ እጅግ አስከፊ መሆኑን በማሳየት መአቱን ለመሻገር ተቀራርቦ መወያየቱና አቻቻይ የመፍትሔ ሀሳብ በማፍለቅ አገሪቱን በብሔራዊ እርቅ ማንፃት ምርጫ የሌለው መንገድ መሆኑን በስፋት ይተነትናል፡፡
ስርጭት
መፅሀፉን በአገር ቤት በዋናነት በአዲስ አበባ ብሔራዊ ቲያትር ጀርባ “አይናለም መፅሐፍት መደብር” እና ጃፋር መፅሃፍት መደብር ውስጥ በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ መፅሃፉ ለጊዜው በሰሜን አሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት ውስጥ ባሉ የኢትዮጵያን ሬስቶራንቶች እና የሐበሻ ሱፐር ማርኬቶች በ20 ዶላር የቀረበ ሲሆን፤ በቀጣይ ቋሚ የመሸጫና ማከፋፈያ ቦታ ለማመቻቸት ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡ በሌሎች የሰሜን አሜሪካ ግዛቶች፣ ካናዳ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ ደቡብ አፍሪካና መሰል አገራት መፅሐፉን ለመሸጥ የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የመፅሃፉን ዋና አከፋፋይ በስልክ ቁጥር 0918 19 19 43 በመደወል ማነጋገር ይቻላል፡፡
Getiye Diriba says
ለሚደርሰኝ መረጃ ሁሉ አመሠግናለሁ፡፡
amsayew says
10q