ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በኖርዌይ፣ ኦስሎ የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ካስተላለፉት መልዕክት የተወሰዱ አንኳር ነጥቦች፤
• የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ለሰጠኝ እውቅና አመሰግናለሁ
• ለኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሰላም ቁርጠኝነት ወሳኝ ነበር
• ይህንን ሽልማት የምቀበለው የአፍሪካ እና የዓለም ህዝቦችን ወክዬ ነው፤ በኢትዮጵያውያን እንዲሁም በኤርትራውያን እና በኢሳያስ አፈወርቂም ስም ነው
• እዚህ የደረስኩት በብዙ ጦርነት ውስጥ አልፌ በዕድል ነው፤ ይህን ሳያዩ ያለፉ ብዙ ናቸው፤ ከ20 ዓመታት በፊት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የሬድዮ ኦፕሬተር ነበርኩ
• የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በርካታ ቀውሶችን አስከትሏል፤ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ተፈናቅለዋል፤ የንብረት መውደምም አጋጥሟል
• ሁለቱ ሀገራት ለሁለት አሥርት ዓመታት ጦርነትም ሰላምም በሌለበት የውጥረት ሁኔታ ውስጥ ቆይተዋል፤ በዚህም በርካታ ሰራዊት በሁለቱ አገራት ድንበር መሽጎ ቤተሰቦች ሳይገናኙ ቆይተዋል
• ከ18 ወራት በፊት ወደ ሥልጣን ስመጣ ለዚህ እልባት መስጠት በጣም አስፈላጊ ሆኖ አገኘሁት
• ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ተገናኝተን ሁለቱ አገራት ጠላቶች እንዳልሆኑ ይልቁንም የጋራ ጠላታችን ድህነት እንደሆነ ተስማምተን ለአገራቱ እና ለቀጠናው ብልፅግና መስራት ጀመርን፤ እናም አሁን በሁለቱ ሀገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሰፍኗል
• ሰላም የመኖር መንገድ፣ ጦርነት የሞት መሠረት ነው የሚል እምነት አለኝ፤ ሰላም በቤተሰብ፣ በጎረቤት፣ በመንደሮች፣ በከተማዎች፣ በሕዝቦች መካከል ያስፈልጋል፤ በዜጎቻችን ልብ ውስጥ ሰላም፣ ፍቅር እና እርቅ ልንዘራ ይገባል
• የኔ የሰላም ራዕይ በመደመር ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ ነው፤ መደመር አገር በቀል ሀሳብና የጋራ ብልጽግና ላይ ያተኮረ ፍልስፍና ነው
• የመደመር ጽንሰ ሀሳብ እንደ ዘር ውስጤ የበቀለው በኦሮሚያ ክልል በምትገኝ የትውልድ መንደሬ በሻሻ ውስጥ ነው
• የመደመር ፍልስፍና ብዝሃነታችን የኢትዮጵያችን ውበት ነው፤ እኔ የወንድሜ እና የእህቴ ጠባቂ ነኝ፤ “አንተ በሰላም እንድታድር ጎረቤትህ በሰላም ይደር” የሚል እሳቤን የያዘ ነው
• በመደመር ጽንሰ ሀሳብ ውስጥ እኛና እነሱ የሚባል ነገር የለም
• ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆማችን ለዓመታት ነፃ አገር ሆነን ቆይተናል
• የአፍሪካ ቀንድ የአሸባሪዎች ቀጠና እንዲሆን አንፈልግም፣ የሰላም ቀጠና እንጂ
• ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰላም ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይጠበቅበታል
• የፖለቲካ እስረኞችን ፈትተናል፤ ለዓመታት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲካሄድባቸው የነበሩ እስር ቤቶችን ዘግተናል፤ ለዴሞክራሲ ግንባታ መንገድ ጠርገናል፤ በቅርቡ ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ እናካሂዳለን
• ለሁሉም ዜጎቿ እኩል ፍትሕ እና እኩል መብት የምትሰጥ ሀገርን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንገነባ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ጥሪ አቀርባለሁ
© EBC
Leave a Reply